የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ነሐሴ 10 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ነሐሴ 10 ቀን 2011 ዓ.ም

ጠ/ሚ/ሩ መርቀው የከፈቱት ረጲ የሀይል ማመንጫ ችግር ላይ ነው

የቆሻሻ አያያዝ ችግር እና የዘመናዊ ተሽኸርካሪ እጥረት የረጲ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ዋነኛ ችግሮች መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አስታወቀ:: የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል በረጲ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ሓላፊዎች፣  የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች እና ከክፍለ ከተሞች የተውጣጡ አባላትን ያካተተ ጉብኝት በዛሬው ዕለት አካሂደዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ከሚያዚያ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ የገባው የረጲ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ እስካሳለፍነው ሃምሌ ወር ድረስ 54 ሺህ 770 ሜጋዋት ኤልክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ከ162 ሺህ ቶን በላይ ቆሻሻ ተጠቅሟል::

ቆሻሻን ከተለያዮ ማህበራት በመግዛት የሚጠቀመው ረጲ ሀይል ማመንጫ ከቆሻሻው ጋር ብረት ጭቃ እና እንጨት ወደ ማመንጫው ስለሚገቡ በምርት ሂደቱ ላይ እንቅፋት እየበዛበት ነው ተብሏል:: በተከታታይ ቆሻሻ ያለመቅረቡ ሌላው ችግር ሲሆን በመዲናዋ የከባድ ተሽከርካሪዎች ላይ የወጣው የእንቅስቃሴ ገደብ እንዱ ሌላኛው ችግር ነው ተብሏል:: ሀያ አራት ሰዓት የሚሰራው ሃይል ማመንጫ ለዚሁ ተግባር የሚጠቀማቸው ዘመናዊ ተሽከርካሪዎች ሁለት ብቻ ናቸው::

ኦሮሚያ፣  ደቡብ፣  ትግራይ እና አማራ በመሬት አጠቃቀም ችግር አለባቸው ተባለ 

ክልሎች የገጠር መሬት ይዞታ ለማስተላለፍ የተቀመጠውን የህግ መንግስት ድንጋጌ በጣሰ መልኩ ተግባራዊ እያደረጉ እንደሆነ ተነገረ::

በጉዳዩ ላይ ሰፊ ጥናት ያካሄደዉ የህግ መንግስት አጣሪ ጉባኤ በኦሮሚያ፣ አማራ፤ ትግራይ እና ደቡብ ክልሎች የገጠር መሬት ይዞታ ህጎች ላይ  ችግሮቹን በብዛት አግኝቷል:: በዳሰሳ ጥናቱ ከኪራይ፣ ስጦታና ውርስ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ህጎችን ተግባራዊ ማድረጋቸው የፍርድ ቤቶች እና የህገ መንግስት የማጣራት ስራ ላይ ጫና እንዲፈጠር አስገድደዋል።

የፌዴራል መንግስት የመሬት አጠቃቀም አስተዳደርን በተመለከተ ህግ የማውጣት ስልጣን እንዳለውና የክልል መንግስታት ደግሞ የፌዴራል መንግስት ባወጣው ህግ መሰረት የገጠር መሬትን ያስተዳድራል።  የገጠር መሬትን አርሶ እና አርብቶ አደሮች በነፃ የማግኝት የመጠቀም መብትንም ያጎናጽፋል። በዚህም መሠረት አርሶ አደሮች በመሬት የመጠቀምና በይዞታ ላይ በጉልበታቸው እና በገንዘባቸው ያፈሩትን ሃብት የመሸጥና የማውረስ መብት አላቸው።

ማከራየት፣ ማውረስ፣ በስጦታ የመስጠት፣ ከሌሎች ይዞታ ጋር የመቀያየርና መብትንም ያጎናጽፋል። በህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ጽህፈት ቤት የህገ መንግስት አስተምህሮ ቡድን ተጠሪ አቶ ያደታ ግዛው ባቀረቡት የዳሰሳ ጥናት፥ በክልሎች ወጥቶ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የገጠር መሬት ይዞታ አጠቃቀም አዋጆች ህገ መንግስቱን ያልተከተሉና አርሶ አደሩን ለአደጋ ያጋለጡ ጭምር እንደሆኑ አስተውቀዋል::

በሌላ መልኩ በኪራይ፣ በስጦታ፣ በውርስ የመጠቀም መብትን በማስተላለፍ መልኩ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይና ደቡብ ክልሎች ያወጧቸው ህጎች በፌዴራል መንግስት የገጠር መሬት ይዞታ ማስተላለፍ ጋር ግልፅ የሆነ ተቃርኖ አላቸው ተብሏል:

አርሶ አደሩ በመሬት ላይ የመጠቀም መብቱን ለማከራየት ኦሮሚያ ከ2 እስከ 20 ዓመት ሲፈቅድ ትግራይ ክልል ከ3 ዓመት እስከ 20 ዓመት የሚፈቀድበት አሠራር መኖሩ በአብነት ቀርቧል::

በተመሳሳይም በውርስ ስጦታ የማስተላለፍ ሂደቱ በአራቱ ክልሎች የተለያዩ ከመሆናቸው ባሻገር ከህገ መንግስቱ ጋር ይጣረሳሉ:: ለህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ህገ መንግስታዊ ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ተብሎ ከ2008 እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ ከተከፈቱ 2 ሺህ 200 መዝገቦች ውስጥ 500የሚሆኑት  ከገጠር መሬት ጋር የተያያዙ ናቸው።

የፌዴራሉ የገጠር ይዞታ አስተዳደር አዋጅ ጥቅል መሆኑና ለክልሎች ብዙ ዕድል በመፍጠሩ ክልሎችም ከህገ መንግስቱ ከሚሰጣቸው ስልጣን ውጪ ህጎችን በማውጣት ተግባራዊ ማድረጋቸው ለችግሩ መንገድ ጠራጊ ሆነዋል።  በክልሎች ከገጠር መሬት ማስተላለፍ ጋር የወጡ ህጎች  በስጦታ፣ ኪራይና ውርስ በፌዴራል መንግስት ህጉ ከሚደነግገው ውጪ እያሰፉ መሄድ፣ አርሶ አደሮች እስከ 30 ዓመት በሚደረስ የይዞታ ኪራይ ከመሬታቸው የመፈናቀል አደጋ እንዲገጥማቸው እያደረገ መሆኑ የችግሩን ስፋት አመላክቷል።

በርካታ አቤቱታዎች ወደ ፍርድ ቤት እና ህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ እንዲመጡ አድርጓል የሚሉት ደግሞ የህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ሰብሳቢና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መአዛ አሸናፊ ናቸው:: “ይህም ዜጎች ተመሳሳይ ባልሆነ ህግ መዳኘትን ከማስከተሉ ሌላ ዳኞችም የተለያዩ ህጎችን ዋቢ እንዲያደርጉ በማድረግ ተጽዕኖ ያሳድራልም” ብለዋል።

በተጠቀሱት ክልሎች በገጠር መሬት ይዞታ አጠቃቃም ላይ ያለው ልዩነት ወደ ፍርድ ቤት ከመጡ በኋላ የሚዳኙበትን ስነ ሰርዓት መለየታቸው ችግሩን አጉልቶታል:: መሬት በባህሪው የተለየ በመሆኑ ወጥነት ያለው ፍትህ ለመሰጠትም ከመሬት ጋር እውቀት ያላቸው ዳኞች የሚኖሩት ራሱን የቻለ የዳኝነት ስራ እንደሚያስፍልግም ዳኞች ሀሳብ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የዋጋ ማሻሻያ አደረገ

በአዲስ አበባ ከተማ  የባቡር አገልግሎት ተጠቃሚዎች የዋጋ ቅናሽ እንደተደረገላቸው ለማወቅ ተችሏል:: በሁሉም የከተማዋ አቅጣጫዎች ለሚደረግ አንድ ጉዞ ታሪፍ 4 ብር እንዲሆን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ውሳኔ ማሳለፉን ሰምተናል:

አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ሦስት አመት ሊሞላው ጥቂት ወራት የቀሩት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ለተለያዩ ርቀቶች የተለያዮ የዋጋ ታሪፎችን ሲያስከፍል እንደቆየ ይታወቃል:: ከዚህ በፊት በነበረው የኮርፖሬሽኑ አሠራር ተሳፋሪዎች ለአጭር ርቀት 2 ብር፣ ለመካከለኛ ርቀት 4 ብር እንዲሁም ለረጅም ርቀት 6 ብር ታሪፍ የክፍያ ስርዓት እንተዲፈጽሙ ያስገድድ ነበር::

የቀላል ባቡር ተጠቃሚዎች ከነሐሴ 12 ቀን 2011 ዓም ጀምሮ በሁሉም ርቀት ለሚደረግ አንድ ጉዞ 4 ብር የትኬት ታሪፍ ብቻ ተግባራዊ ለማድረግ እንደወሰነ ኮርፖሬሽኑ ዛሬ ባወጣው  መግለጫ ላይ በግልፅ አስቀምጧል:: አዲሱ የታሪፍ ማሻሻያ ምቹ የቁጥጥር ስርዓት ለመዘርጋት፣ ከትኬት ህትመት ጋር የተያያዙ ወጪዎችን ለመቀነስ፣ የትኬት ስርዓቱን ዘመናዊ ከማድረግ በተጨማሪ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ተብሎ ተገምቷል::

ቀደም ሲል የነበረውን የተዘበራረቀ አሠራር ወጥ በሆነ ታሪፍ ስርዓት ለመዘርጋት ይቻል ዘንድ ኮርፖሬሽኑ ያካሄደውን ጥናት መሰረት በማድረግ እና ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን ጋር ምክክር እንዳደረገም ታውቋል:: የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በየቀኑ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት በሚሰጠው አገልግሎት በየቀኑ እስከ 120 ሺህ መንገደኞችን ያመላልሳል:: በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ከ29 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን በማሳፈር ከ3 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስገባቱን ከደረሰን ዜና መረዳት ችለናል።

ገዱ አንዳርጋቸው ካምፓላ ላይ እየመከሩ መሆናቸው ተሰማ

3ኛው የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ዛሬ በኡጋንዳ ከምፓላ እየተካሄደ ነው:: በኹለቱ ሃገሮች የጋራ ጉባኤ ላይ ለመካፈል ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በትናትናው ዕለት ካምፓላ ደርሰዋል።

ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ በፖለቲካ፣ በደህንነት፣ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት በአውሮፓዊያኑ ሃምሌ 22 ቀን 2011 ተፈራርመው ወደ ሥራ እንደገቡ ይታወሳል:: በዚህ መሠረት የመጀመሪያው የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን በኡጋንዳ ካምፓላ፤ ሁለተኛው በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ተካሂደዋል:: የአሁኑ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ደግሞ በኡጋንዳ አስተናጋጅነት በካምፓላ ለ3ኛ ጊዜ የሚካሄድ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ  ኹለቱ ሀገራት አባል በሆኑባቸው ዓለም አቀፍ እና ክልላዊ መድረኮች በመቀራረብ እና ተመሳሳይ አቋም በማራመድ በመሥራት ላይ ናቸው:: በተለየ መልኩ የተመሰረተው የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን የትብብር ማዕቀፍ ሁለቱ ሀገራት ተቀራርበው እና አዳዲስ የትብብር መስኮችን ለይተው በጋራ እንዲሰሩ ያገዘ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ የወጣው መግለጫ ያስረዳል።

ካምፓላ የገባው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሚመራው ልኡክ ከኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ጋር ተወያይቷል። በውይይቱ ፕሬዚዳንት ሙሴቪኒ ኢትዮጵያና ኡጋንዳ ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት በማስታወስ ይህ ግንኙነት ይበልጥ ሊጠናከር በሚችልበት ሁኔታ ላይ ጠንክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ሲያሳስቡ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያና ኡጋንዳ የኢጋድ አባል ሀገር እንደመሆናቸው የቀጠናውን ሰላም ለማስጠበቅ በጋራ ምክክር የሚሰሩ መሆናቸውን በመጥቀስ በሰላም ማስከበር ስራም የሚያደርጉት ትብብር ውጤታማና ለአብነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም አቶ ገዱ እና የልዑካን ቡድናቸው ከኡጋንዳ ከፍተኛ ሚኒስትሮች ጋር በተለያየ ጉዳይ እየመከሩ ናቸው።

የኤድስ በሽተኛው ከሆስፒታል በኃይል እየተጎተተ እንዲወጣ መደረጉ አለምአቀፍ ውዝግብ አስነሳ 

ኤች.አይ.ቪ በደሙ ውስጥ ያለበት አንድ ግለሰብን ሀይል በተቀላቀለበት ሁኔታ በግድ ከሆስፒታል እንዲወጣ  መደረጉን የሚያሳየው ምስል ከተለቀቀ በኋላ በግብፅ ከፍተኛ ቁጣ እና ተቃውሞ መቀስቀሱን ቢቢሲ ዘግቧል:: ከግብፃውያን በተጨማሪ የተለያዮ የሰብአዊ መብት ተቋማት ድርጊቱን መኮነናቸውን ተከትሎ የግብጽ ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ ምርመራ ጀምረናል ብለዋል።

ከግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘውና ጋርቢያ ተብሎ በሚጠራ የግብጽ ሰሜናዊ ክልል ውስጥ ባለ “ካፍር ኤል ዛያት” በተሰኘ ሆስፒታል ውስጥ ነው ይህን መሰሉ አሳፋሪ ድርጊት የተፈጸመው:: ህመምተኛው መሬት ላይ በኃይል እየተጎተተ እንዲወጣ ሲደረግ የሚያሳየው ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት መሠራጨቱን ተከትሎ የግብፅ መንግሥት ባለሥልጣናት ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ወድቀዋል::

የግብጽ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፤ ድርጊቱን የፈጸሙት የሆስፒታሉ ሠራተኞች ለህመምተኛው ተገቢ አገልግሎት ባለመስጠት ተጠያቂ እንደሚሆኑ ይፋዊ መግለጫ በመስጠት በመጥፎ ጎኑ ስሟ በዓለም አደባባይ እየጠለሸ ያለውን ሀገራቸውን ለመታደግ ሞክረዋል።

ሆስፒታሉ የሚሰሩ አንድ ከፍተኛ ሓላፊ የኤድስ ህመምተኛ የሆነው ግለሰብ ወደ ሆስፒታሉ ሲመጣ አደንዛዥ ዕፅ ተጠቅሞ ነበር ሲሉ ሰንካላ ምክንያት በማቅረብ በስራቸው ላሉት የሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች ጥብቅና ቆመዋል።

በትራምፕ ግፊት ሁለቱ  ሙስሊም የኮንግረስ አባላት ወደ እስራኤል እንዳይገቡ ታገዱ

የእስራኤል ኮንግረስ አባላት የሆኑት ራሺድ ተሊብ እና ኢልሃን ኦማርን የተሰኙ ኹለት ሴቶች ወደ እስራኤል እንዳይገቡ እግድ የተጣለባቸው መሆኑ ታወቀ።

የእስራኤል ባለስልጣናት እንዲህ ዓይነቱን እግድ ኹለቱ የኮንግረስ አባላት ላይ ለማስተላለፍ የወሰኑት ቀደም ሲል እስራኤል የፍልስጤማውያንን ጥያቄ የምታስተናግድበትን አግባብ አስመልክቶ በተደጋጋሚ በመተቸታቸው እንደሆነ ተነግሯል።

አወዛጋቢው እና ቢልየነሩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የእስራኤል መንግሥት በእነዚህ ሙስሊም የኮንግረስ አባላት ላይ እንዲህ ዓይነቱን ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ከፍተኛ ጫና ሲያሳድሩ እንደነበር አይዘነጋም።  ትራምፕ ራሺድ ተሊብ እና ኢልሃን ኦማርን ጨምሮ ከሌሎች ኹለት የኮንግረስ አባላት ጋር የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተው ነበር።

እነዚህ ሙስሊም የኮንግረስ አባላት ከፊታችን እሁድ ጀምሮ በእስራኤል እና በፍልስጤም ግዛቶች ጉብኝት ለማድረግ ፕሮግራም ተይዞላቸው ነበር። የእስራኤል ውሳኔ ይፋ ከመደረጉ በፊት ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ የኮንግረስ አባላቱ እስራኤልን እንዲጎበኙ የሚፈቀድ ከሆነ “ትልቅ ድክመትን ያሳያል። ራሺድ ተሊብ እና ኢልሃን ኦማር እስራኤልን እና አይሁድን ይጠላሉ ” ሲሉ መፃፋቸው ተውቋል።

LEAVE A REPLY