በአዲስ አበባ በመንግሥት ሠራተኞች ደምወዝ ጭማሪ ምክነያት ኑሮ ተወደደ
በአዲስ መልክ የተሻሻለው የሠራተኞች የሥራ መደብ ምዘና ደረጃዎች ምደባ ሠራተኛው የዜጎችን ፍላጎት በሚያሟላ ስነ ልቦና መንቀሳቀስ እንደሚያስችል ተነግሮለታል::
የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየስ ውሳኔው የመንግሥት ሠራተኞች በልማዳዊ መንገድ ለረጅም ዘመናት በተደጋጋሚ ሲሰሯቸው የነበሩትን ስራዎች በተገቢው መንገድ በመመዘን በዘመናዊ አግባብ ስራ እና ሰራተኛን የሚያገናኝ ነው ብለዋል::
የመንግስት ቢሮክራሲ የሲቪል ሰርቪሽ ማሻሻያ በሚል በተቀረጹ የ ማስተካከያ ሥራዎች ሲመራ መቆየቱን የተናገሩት ኮሚሽነሩ ውሳኔው በኢትዮጵያ እየታየ ካለው ዙሪያ መለስ ለውጦች ጋር በማጣመር ሥራ እና ሠራተኛን በአግባቡ በማገናኘት ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ የመስጠትን ሂደት ያሳልጣል ይላሉ::
መዳረሻውን የደሞዝ ስኬል ሽግግርን አድርጎ የተጠናቀቀው ይህ ፕሮጀክት የደሞዝ ጭማሪ ለማድረግ ወይንም ማስተካካያ የመስራት አለማ እንደሌለው እና ሠራተኛው የደሞዝ ልዩነትን ባልተመዘኑ ስራዎችን ለመፈለግ ከመስሪያ ቤት መስሪያ ቤት ወይንም ከዘርፍ ዘርፍ የሚያደረገውን ፍሰት የሚያስቀር እንደሆነም አስረድተዋል::
ሠራተኛው የተመደበበት ቦታ እና የሥራ ባህሉ በአደገበት ቦታ ላይ የበለጠ እየዘመነ የዜጎችን ፍላጎት በሚያሟላ ስነ ልቦና መንቀሳቀስ የሚያስችል እንደሆነም ሰምተናል:: የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው የእቸኳይ ጊዜ ስብሰባ የሲቪል ሰርቪስ ባቀረባቸው የሰራተኞች የስራ መደብ ምዘና ደረጃዎች ምደባ እና ተያያዝ ጉዳዮች ላይ አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማድረግ ከሃምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆኑ ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም::
ይህ በእንዲህ እንዳለ የመንግሥት ሠራተኞች የደምወዝ ማሻሻያን ተከትሎ በአዲስ አበባ የሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶች በፍጥነት ጭማሪ አሳይተዋል:: ሰበብ ፈላጊዎቹ ነጋዴዎች ለወትሮው በፆም መገባደጃ የሚቀንሰውን የአትክልት እና ፍራፍሬ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አድርገዋል::
በርካታ የቤት አከራዮችም ከቀጣይ ወር ጀምሮ የዋጋ ጭማሪ አንዳደረጉ በመግለፅ ተከራዮች ካልተስማማቸው አማራጭ እንዲፈልጉ በማሳሰብ ላይ ናቸው:: የመንግሥት ሠራተኞች ደምወዝ በጨመረ ቁጥር ብዙኃኑ ሕብረተሰብ የስግብግብ ነጋዴዎች ሲሳይ መሆኑ ብዙኃኑን ሕዝብ እያበሳጨ ነው::
መንግሥት የነጋዴዎችን ሕገ ወጥ ብዝበዛ መቆጣጠር በሚችልበት ቁመና ላይ ሣይሆን ያደረገው ጭማሪ ለፍቶ አዳሪውን የመኖር ሕልውናውን ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል::
አዲስ አበባ ላይ በአሁኑ ሰዓት አንድ ኪሎ ሽንኩርት ከ22 እስከ 25 ብር እየተሸጠ ነው:: ድንች ኪሎው ሰላሳ ብር ሲገባ አንድ ኪሎ ምስር 90 ብር በመሸጥ ላይ እንደሆነ ተዘዋውረን ተመልክተናል::
ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ የ2019 የዓለም የቱሪዝም ሽልማት አሸናፊ ሆኑ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የ2019 የዓለም የቱሪዝም ሽልማት አሸናፊ ሆኑ:: የለውጡ ፊታውራሪ በሀገሪቱ ቱሪዝም ዘርፍ ባበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የ2019 “የዓለም የቱሪዝም ሽልማት አሸናፊ “እንደሆኑ በኢትዮጵያ የሚገኘው የብሪታንያ ኤምበሲ ገልጿል::
ወደ ሥልጣን ከወጡበት ማግስት አንስቶ በሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ የሠሩትን የሚታይ ዕውነታ ተንተርሶ ለተለያዮ ሽልማቶች መታጨታቸው አይዘነጋም:: ዶክተር ዐቢይ ይህንን ሽልማት ከሦስት ወር በኋላ በህዳር ላይ በለንደን ከተማ በሚካሄደው የዓለም የቱሪዝም ሽልማት ስነ ስርዓት ላይ ይቀበላሉ::የዓለም የቱሪዝም ፎረም ፕሬዚዳንት ቡሉት ማግቺ ባሳለፍነው ወር መጨረሻ ከምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ጋር ተገናኝተው ሲወያዮ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2020 የሚካሄደውን የዓለም የቱሪዝም ፎረም በአዲስ አበባ ከተማ ለማዘጋጀት ፍላጎት እንዳለ ገልፀው ነበር::
በመላኩ ፈንታ የሚመራው “የአማራ ባንክ ” የአክሲዮን ሽያጬን ዛሬ በይፋ ጀመረ
ብዙ ሲነገርለት የቆየው እና በምስረታ ሂደት ላይ ያለው የአማራ ባንክ አክሲዮን ማህበር የአክሲዮን ሽያጬን በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል።
አማራ ባንክ ዛሬ በሸራተን ሆቴል ባካሄደው ስብሰባ እስካሁን በተከናወኑ ተግባራት፣ ውሳኔ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችና እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ በስፋት መክሯል::
የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የቦርድ ሊቀመንበሩ አቶ መላኩ ፈንታ የባንኩ መመስረት በሀገር እና በክልል ያለውን የልማት ፍላጎት ከማሟላት አኳያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል:: ከዚህ ባለፈም የሚመሰረተው ባንክ ኢንቨስትመንት እና የውጭ ምንዛሪ ተቀማጭ እንዲኖርና ዳያስፖራውንም ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም ጠቁመዋል::
በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ የአደረጃጀት ኮሚቴው የአማራ ባንክ አክሲዮን ማህበር የሥነ ምግባር ደንብ ይፋ ሆኗል። በዚህ መሰረትም የአንድ አክሲዮን መሸጫ ዋጋ አንድ ሺህ ብር መሆኑ ተገልጿል። አንድ ሰው መግዛት የሚችለው ዝቅተኛ የዕጣ ብዛት 10 ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ 100 ሺህ እንደሆነም ተነግሯል።
የደቡብ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ሥራ መጀመሩን ሞፈሪያት ካሚል ተናገሩ
የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ወይዘሮ ሞፈሪያት ካሚል በደቡብ ክልል በተለያዩ ግጭቶች የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ስራ እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል::ተፈናቃዮችን በፈቃደኝነት ላይ በመመስረት ወደ መደበኛ ኑሯቸው የመመለስ ስራ እየተሰራ ነው ተብሏል::
የሰላም ሚኒስቴሯ ተፈናቃዮቹን ወደ መኖሪያቸውከመመለስ በተጨማሪ በዘላቂነት ለማቋቋም መኖሪያ ቤቶችን የመገንባትና የፋብሪካ ውጤቶችን የማቅረብ ጎን ለጎን እየተከናወነ እንደሆነ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል::
ማህበረሰባዊ ድጋፎች እንደተጠበቁ ሆነው ቁሳቁሶችን የማሟላትና ወደተሟላ የራሳቸው የስራ እንቅስቃሴ እስከሚገቡ የፌዴራል የዕለት ደራሽ እርዳታ እየተደረገ ይደረጋል ያሉት የደኢህዴን ሊቀ መንበር ጊዜው የግብርና ወቅት እንደመሆኑ እንዳያልፍ የእርሻ መሳሪያና የግብዓት አቅርቦት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመተባበር ድጋፍ ለማድረግ መታሰቡንም ጠቁመዋል::
ትምህርታቸውን ያቋረጡ የተፈናቃይ ቤተሰብ ልጆች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ዝግጅት መደረጉንም ለመወቅ ተችሏል።
የሱዳን ተቃዋሚዎችና ወታደራዊ ሃይሉ ስልጣን ለመጋራት ተስማሙ
የሱዳን ተቃዋሚዎችና ወታደራዊ ሃይል ስልጣን መጋራት የሚያስችላቸውን የመጨረሻ ስምምነት ተፈራረሙተቃዋሚዎችና ወታደራዊ ሃይል በመሰረቱት የሽግግር መንግስት ዙሪያ የመጨረሻ የስምምነት ስነ ስርዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የተለያዮ ሀገራት መሪዎች በታደሙበት ተከናውኗል::
በተፈረመው መግባባት የሱዳን ተቃዋሚዎች እናወታደራዊ ሃይል ስልጣን ይጋራሉ:: ስምምነቱ በሀገሪቱ ለበርካታ ወራቶች የቆየውን ያለመረጋጋት እና ህዝባዊ ተቃውሞ መቋጫ ያበጅለታል ተብሎ ተስፋ ተደርጎበታል::
ዛሬ በተፈጸመው ስምምነት መሰረት የሉዓላዊ ምክር ቤት የሚቋቋም ሲሆን ምክር ቤቱ ስድስት የሲቪል እና አምስት ወታዳዊ አመራሮችን በአባልነት እንዲያካትት ተደርጓል::
ይህ በልዮ ሁኔታ የሚቋቋመው ሉዓላዊ ምክር ቤት ኹለቱ ወገኖች በየሶስት ዓመት እየተፈራረቁ የሚመሩት ሲሆን በዚህ መሰረት ለቀጣይ ሶስት ዓመታት የነፃነትና የለውጥ ሀይል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ይሾማል::ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዚህ የመጨረሻ የስምምነት ስነ ስርዓት ለመሳተፍ በዛሬው ዕለት ሱዳን ካርቱም ይገኛሉ።