አወዛጋቢው አዲሱ የምርጫ ሕግ ዛሬ በፓርላማው ፀደቀ
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው እለት አስቸኳይ ስብሰባው የሕግ ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበለትን የኢትዮጵያ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅን አፅድቋል:: ቋሚ ኮሚቴው አዋጁን ባቀረበበት ወቅት የአዋጁ ስያሜን ጨምሮ በአዋጁ 149 በሚሆኑ አንቀጾች ላይ ማሻሻያም አድርጓል:: የአዋጁ ስያሜም የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ በሚል መስተካሉ ተነግሯል::
በአዲሱ አዋጅ በፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ፣ በምርጫ ተወዳዳሪዎች እንቅስቃሴ፣ በምርጫ ወቅት መከናወን ባለባቸው ህጋዊ እንቅስቃሴዎች፣ በህግ አፈጻጸም፣ በመገናኛ ብዙሀን አጠቃቀምና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ማሻሻያዎች ተደርጓል። በአዋጅ ማሻሻያ ላይ ወንድ እና ሴት ተወዳዳሪዎች እኩል ድምጽ ቢያገኙ ሴት ተወዳዳሪዋ እንደምታሸንፍ አስቀምጦ የነበረ ቢሆንም፥ ምክር ቤቱ ሀሳቡ ከፆታ እኩልነት ጋር የሚፃረር በመሆኑ ውድቅ ተደርጓል::
በማሻሻያ አዋጁ አዋጁን ለማስፈጸም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደንብ ሊያወጣ እንደሚችልና መመሪያውን የሚያወጣው ደግሞ ምርጫ ቦርድ እንደሆነ አመልክቷል።
በፀደቀው አዋጅ በዋናነት የምርጫ ስርአት፣ የምርጫ አፈፃጸም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመሰራረትና አስተዳደር፣ የምርጫ ስነ ምግባር፣ በምርጫ ሂደት የሚነሱ ክርክሮች የሚዳኙበትንና የሚፈቱበትን የአሰራር ስርኣት የያዘ ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቀናጁበት፣ እንደ አዲስ የሚዋኸዱበትን ዝርዝር የያዘ እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ያሳተፈ ነው ተብሏል።
አንድ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት ቢያንስ 10 ሺህ እንዲሁም አንድ የክልል ፓርቲ ለመመስረት ደግሞ ቢያንስ 4 ሺህ አባላት እንደሚያስፈልጉ ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ከፀደቀው አዲስ አዋጅ መረዳት ችለናል።
አፋን ኦሮሞ ትምህርት ለድርድር እንደማይቀርብ አቶ ሽመልስ አብዲሳ አሳወቁ
በያዝነው ሣምንት መጀመሪያ ይፋ የሆነውን የትምህርት ፍኖተ ካርታን አስመልክቶ የኦሮሞ ልሂቃን እና ፖለቲከኞች የተለያዮ አስተያየቶችን እየሰጡ ነው:: የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የአፋን ኦሮሞ ትምህርት ለድርድር የማይቀርብና ለቋንቋው እድገት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናግረዋል::
የኢትዮጵያን ስርዓተ ትምህርት አስመልክቶ በትምህርት ሚኒስቴር የተሰጠው መግለጫ፤ የአፋን ኦሮሞን ተጨባጭ ሁኔታ የማይገልጽ እንደሆነ እና የክልሉ መንግስት በቋንቋ ጉዳይ ላይ የማያወላዳ አቋም እንዳለው ህዝቡ ሊረዳ እንደሚገባም ይፋ አድርገዋል::
የኦሮሚያ ክልል ም/ፕሬዝዳንት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትን የማስተዳደር፣ የትምህርት ስርዓትን ማዘጋጀት፣ የስምንተኛ ክፍል ፈተና ማዘጋጀትና አርሞ ውጤት መወሰን ለክልል የተሰጠ ስልጣን እንደሆነ አስታውሰው በዚህ ላይ ጫና የሚያሳድር ማንም ሊኖር እንደማይገባ እና እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ በአፋን ኦሮሞ የሚሰጥ ትምህርት እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።
የአፋን ኦሮሞ ቋንቋን ለማሳደግ ከዚህ በፊት በቋንቋው ትምህርት በማይሰጥባቸው አካባቢዎች ጭምር መማሪያ እንዲሆን የክልሉ መንግሥት እየሰራ በመሆኑ ሁሉም ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ በተጨማሪም በኦሮሚያ ውስጥ ከክልሉ ስርዓተ ትምህርት ውጪ የሚያስተምሩ የግል ትምህርት ቤቶች ላይም በተያዘው ዓመት የዕርምት ዕርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
ሕገ መንግሥቱ ከተሻሻለ አገራዊ ብጥብጥ እንደሚነሳ የህወሃቱ አቶ ጌታቸው ረዳ አሳሰቡ
ከመንበረ ሥልጣኑ የተገፋውና መቀመጫውን ከ4 ኪሎ ቤተ መንግሥት መቀሌ ለማድረግ የተገደደው የአፈንጋጬ የህወሀት ቡድን ጉዳይ አስፈፃሚ የሆኑት ጌታቸው ረዳ ሕገ መንግሥቱ አማራን ስለማይወክል ይጣል የሚለው ዕሳቤ የተሳሳተ ነው ሲሉ ገለጹ። እንዲህ ዓይነት ጥያቄ የሚያቀርቡት ከ28 ዓመት በኋላ ያደጉ ፖለቲከኞች ናቸው ሲሉ ተሣልቀዋል:: ሕገ መንግሥቱ ችግር እንዳለበት በማመን ለማሻሻል እንደሚሞከር ዶ/ር ዐቢይ ከዚህ ቀደም መናገራቸው አይዘነጋም።
ያለ ሕዝብ ተሳትፎ ወያኔ እና አሽከሮቹ ያፀደቁትን ከማሞካሸት ባሻገር ፍፁም አድርገው ያቀረቡት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ “በነገራችን ላይ ይህ ህገ መንግስት ነው አማራ መኖሩን ለመጀመሪያ ጊዜ አምኖ የተቀበለው፣ ከዛ በፊት አማራ የሚባል ነበር እንዴ? እኔ ግን በእጃችን ያለው የመጫወቻ ሕግ እሱ ነውና እሱን ይዘን ብንጫወት ይሻላል ባይ ነኝ ” ሲሉ ተናግረዋል::
“ኢትዮጵያም፣ በኢትዮጵያ ያሉ ማንነቶችም በጋራና በእኩልነት መቀጠል አለባቸው። ብሄሮችን የማትቀበል ኢትዮጵያ በአዋጅ ሳይሆን በሁኔታዎች ተገድዳ መፍረስ ትችላለች” በማለት በችግር የታጠረውን ሕገ መንግሥት ይቀየር ከተባለ ሕወሓት እና ጀሌዎቹ አገር ለማበጣበጥ ዝግጁ መሆኑን የጠቆመ አስተያየት አሰምተዋል።
“ኢትዮጵያ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ 40 ጊዜ ስሟ ተንስቷልና ቅድስት ነች፤ ምትሃት ነች የሚሉ አሉ። ሶርያ ከ150 ጊዜ በላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሳለች፤ ያ ግን አሁን ካለችበት ሁኔታ አላዳናትም። ፕራክቲካል መሆን አለብን።” ያሉት ኹከት ናፋቂው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ፤ ታላቂቷ ኢትዮጵያ ማንም አይነካትም በማለት ሃገር ማዳን አይቻልም ሲሉ የእሳቸውን እና የአለቆቻቸውን አቋም በተዘዋዋሪ አሳይተዋል።
ሚድያው ምንድ ነው እያለ ያለው? በጂኦግራፊ የተመሰረተ ፌደራሊዝም አይደለም እንዴ እየተሰበከ ያለው? በማለት የጠየቁት አቶ ጌታቸው ረዳ አሁን ባለው ሕገመንግሥት በአዲስ አበባ የሚኖሩ አሮሞዎች በቋንቋቸው መጠቀም ካልቻሉ ህመማቸውንም ሆነ ቋንቋቸውንም ተሸክመው ለመኖር ይገደዳዳሉ ሲሉ ለአመፅ የሚያነሳሳ መርዛቸውን ረጭተዋል።
ጌታቸው ረዳ የአማራና የኦሮሞ ማህበረሰብን እሳት እና ጭድ በማለት ህዝብን ከህዝብ በማነሳሳት ያደረጉት ሙከራ እንደነበር አይዘነጋም።
የ4 ቢሊዮን ችግኝ መርሀ ግብር ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁን ብሄራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ገለጸ
በያዝነው ዓመት የክረምቱ መርሀ ግብር የተያዘው የአረንጓዴ አሻራ ፕሮጀክት፤ የ4 ቢሊየን የችግኝ መርሃ ግብር ሙሉ ለሙሉ መሳካቱን በሀገር አቀፍ ደረጃ የችግኝ መርሃ ግብሩ አስተባባሪ ብሄራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ገለጸ:: የችግኝ ተከላ ማሳረጊያ መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት በጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ተካሂዷል::
የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ የ4 ቢሊየን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የተተከሉ የችግኝ አይነቶች እና ብዛት የማጣራት ሥራ እንደሚካሄድ ገልጾ፤ በክረምቱ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ 60 በመቶ የሚሆኑት ለጥምር ግብርና የሚያገለግሉ ሲሆን 40 በመቶዎቹ ደግሞ ለደን የሚሆኑ ችግኞች መሆናቸው ተሠምቷል:: በቀጣይነትም ችግኞችን የመንከባከብ ሥራ በተቀናጀ ሁኔታ ይከናወናል ተብሏል::
ዛሬ የ 4 ቢሊዮን ችግኝ ተከላው መጠናቀቁ በይፋ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ብሄራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን በቤተ መንግሥት ችግኝ ተክለዋል። ኢትዮጵያውያን ከዚህ በመቀጠል ለችግኞች እንክብካቤ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
መንግሥት የአራት ቢሊዮን ችግኝ ተከላው መጠናቀቁን ይግለፅ እንጂ በርካታ ኢትዮጵያውያን በቀጥሩ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ አላቸው:: 70 ሚሊዮን ችግኝ መተከሉን በተገቢው መንገድ አረጋግጦ አገሪቱን በዓለም የክብር መዝገብ ላይ ማጻፍ ያልቻለ መንግሥት 4 ቢሊዮን ችግኝ መትከሉን በምን መንገድ አረጋገጠ? ሲሉ በመጠየቅ ላይ ናቸው።
በአዋሽ ወንዝ መሙላት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች በሄሊኮፕተር የታገዘ ድጋፍ እየደረሠ ነው
በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞን ኢሉ ወረዳ በአዋሽ ወንዝ መሙላት ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ተገለጸ::
ሞልቶ በተጥለቀለቀው የአዋሽ ወንዝ ጎርፍ ተከበው ወገኖች መከላከያ ሰራዊት ከኢፌዴሪ አየር ሀይል ጋር በመተባበርበሄሊኮፕተር በመታገዝ የተለያዩ ድጋፎቸን አቅርበዋል።
ትናንት ከተደረገው ዕርዳታ በተጨማሪ ማክሰኞ ዕለትም በጎርፍ የተከበቡ ዜጎችን ለማውጣት የሚረዱ 2 ጀልባዎችን ጨምሮ 132 ካርቶን ወተት እና 132 ካርቶን ብስኩቶች፤እንዲሁም የአልጋ አጎበርና የተለያዩ መድሃኒቶች ለተጎጂዎቹ መሰጠቱ ይታወሳል።
ወደ ስፍራው ያቀኑ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሓላፊዎች የአዋሽ ወንዝ በመሙላት በህዝቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በስፍራው ተገኝቶ ከመጎብኘት ባሻገር ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል። የአዋሽ ወንዝ መሙላት በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ሸዋ ዞን ኢሉ ወረዳ ባስከተለው የጎርፍ መጥለቅለቅ በርካታ ዜጎችን ጉዳት የደረሰ ሲሆን፥ የተዘሩ የተለያዩ ሰብሎችንም ከጥቅም ውጪ ማድረጉ አይዘነጋም።
በአሁኑ ሰዓት የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ከ1 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት ያጥለቀለቀ ሲሆን፥ ከ8 ሺህ በላይ ሰዎችም በዚሁ ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠዋል። ከዚህ በተጨማሪ በ1 ሺህ 800 ሄክታር ላይ የተዘሩ የተለያዩ ሰብሎችን ከጥቅም ውጪ ማድረጉም ታውቋል።
ከየመን እና ሶማሌላንድ የመጣው የአንበጣ መንጋ አምስት ክልሎችን ወረረ
ከየመን እና ሶማሌላንድ እድገቱን የጨረሰ አንበጣ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት አምስት ክልሎች ውስጥ እንደተገኘ ታወቀ::ይህ የአንበጣ መንጋ በራሱ ጉዳት ባያደርስም እንቁላል ጥሎ በእንቁላሉ አማካኝነት ግን ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ተነግሯል::
በግብርና ሚኒስቴር የዕጽዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዎስ ሰላቶ እድገቱን የጨረሰ አንበጣ ብዙም እንደማይመገብ ጠቁመው ፣ አዝዕርትን ያለ ዕረፍት በመመገብ ጉዳት ስለሚያደርስ እንቁላሉ እንዳይፈጠር ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ግን አልሸሸጉም። በአሁኑ ወቅት በሶማሌ፣ በኦሮሚያ ምስራቅና ምዕራብ ሃረርጌ፣ በአፋር፣ ድሬዳዋና ሰሜን ምስራቅ አማራ አንበጣው የደረሰ በመሆኑ ጥፋቱን ለመታደግ ከወዲሁ ሥራ ተጀምሯል::
አንበጣው በተንቀሳቀሰባቸው የተወሰኑት አካባቢዎችም ቅድመ መከላከል ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል። ቦታውን በትክክል መለየትና የሚረጩት ኬሚካሎች ጉዳት ስለሚያደርሱ ነዋሪው ከብቶቹንና ልጆቹን እንዲጠብቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል። ርጭቱን ለሚያከናውኑ ሰዎችም በተመሳሳይ ስልጠናዎች በመሰጠት ላይ ናቸው::
አሁንም ከየመንና ሶማሌላንድ ሊመጣ የሚችል የአንበጣ መንጋ ሊኖር እንደሚችል አለም አቀፍ ትንበያ መኖሩን መሠረት አድርገው የተናገሩት ዳይሬክተሩ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ የመርጫ መሳሪያዎችን ወደ አካባቢዎቹ የማንቀሳቀሱ ሥራ ተጀምሯል ብለዋል:: አንበጣው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው እርጥበትና አረንጓዴ ዕጽዋትን ለማግኘት የነፋስን አቅጣጫ በመከተል ነው። የአንበጣ እንቁላል ምቹ የአየር ሁኔታ ከገጠመው እስከ አስር ቀን እርጥበት ካለ ደግሞ እስከ 17 ቀን የሚቆይ ሲሆን አልፎ አልፎ እስከ 60 ቀን የሚቆይበትም ጊዜ አለ። በመሆኑም እስከ 50 ቀን ድረስ ክንፍ ስለማያወጣ በዚህ ጊዜ ውስጥ መከላከል እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
ዮሐንስ ቧ ያለው የወሎን አማራነት የሚጠራጠሩ ወፍ ዘራሾች ነው አሉ
የወሎን አማራነት ዘንግተው ፣ የራሳቸውን ማንነት ለመጫን ለሚፈልጉ ህልመኞችና ወፍ ዘራሽ ፈላስፎች ጆሮ ሳንሰጥ የአማራን እና የኢትዮጵያን አንድነት አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል ሲሉ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ተናገሩ::
በላስታ ላሊበላ የአሸንድዬ በዓል ሲከበር በክብር እንግድነት የታደሙት የአዴፓ ም/ሊቀመንበር እና የአዴፓ ማዕከላዊ ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው “የአማራን አንድነት እናጠናክር። አንደንዶች የወሎን የአማራ ማዕከልነት ዘንግተው ሌላ ማንነት ሊሰጡት የሚሞክሩ ህልመኞችና ወፍ ዘራሽ ፈላስፎች ተነስተውዋል። ይህም በእኛ ላይ የሚያሴሩ አካላት አሁንም ተደራጅተው እንዳሉ የሚያሳይ ቢሆንም ግን መቼም አይሳካላቸውም።” ብለዋል::
ወሎ የፍቅርና የመቻቻል ምድር ስለሆነ ማንም መጥቶ በፍቅር ኖሯል ወደፊትም ይኖራል ያሉት የአዴፓ ሓላፊ የትኛውም የአማራ ክፍልየኢትዮጵያውያን ሁሉ ቤት ስለሆነለአማራ አንድነትና ጥንካሬ በሠራን ቁጥር ለኢትዮጵያም እንደሠራን ይቆጠራል በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል::
“አባቶቻችን ቅኝ ገዥዎችን አሸንፈው ነፃ ባያደርጉን ኖሮ ዛሬ የምናከብረውም ሆነ የምንገፋፋበት ባህልና ትውፊት ባልኖረን ነበር። ይከበርልን ምንለው ቋንቋም ሆነ በዓል፣ አሸንዳም ሆነ እሬቻ ወይም ጨምባላላ ተጠብቆ የቆየን በአባቶቻችን ጀግንነት ነው” ሲሉ የተደመጡት አቶ ዮሐንስ ቧ ያለው ትውልዱ ከአያት ቅድመ አያቱ የተረከበውን ባሕላዊ ቅርስ መጠበቅ እንዳለበት ተናግረዋል።
ኳታር በ18 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በአዲስ አበባ የኩላሊት ህክምና ሆስፒታል ልትገነባ ነው
የኳታር መንግሥት በአዲስ አበባ ሁለ ገብ ግልጋሎት የሚሠጥ የኩላሊት ሆስፒታል ሊገነባ እንደሆነ ተሠማ:: የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር ተበጀ በርሄ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን ከኳታር ልማት ፈንድ የፕሮጀክት ሓላፊዎች ጋር ማዕከሉ ስለሚቋቋም ሁኔታም መክሯል::
የኹለቱ አገራት መሪዎች ቀደም ሲል ባደረጉት ስምምነት መሰረት የኳታር መንግስት በአዲስ አበባ የኩላሊት ሕክምና ሆስፒታል ለመገንባት የገባውን ቃል በአፋጣኝ ወደ ተግባር ለማሸጋገር በሚያስችሉ ዝርዝር ጉዳዮች ዙሪያ ላይ ተነጋግረው ፕሮጀክቱን በፍጥነት ሥራ ለማስጀመር ስምምነት ላይ ደርሠዋል ተብሏል:: የሆስፒታል ግንባታ ሂደቱ ሁለት ምዕራፎች የሚኖሩት ሲሆን፥ የመጀመሪያው ምዕራፍ የህንፃ ግንባታውንና የባለሙያዎች ስልጠናን ያካትታል:: ዕቅዱን ዕውን ለማድረግም የኳታር ልማት ፈንድ 18 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር መድቧል::
የልዑክ ቡድኑ ከኳታር ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ከተለያዩ የጤና ተቋማት ሓላፊዎች ጋር በዘርፉ ትብብር ለማድረግ እንዲቻል የጎንዮሽ ውይይቶችን ማካሄዱን የገለጸው በኳታር የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ በተጨማሪም በዕድሳት ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ከፍተኛ ቡድኑ እንደጎበኘ እና በኤምባሲ በሚገኘው የኮሚዩኒቲ መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችንም እንዳነጋገረ ይፋ አድርጓል።
ህዋ ላይ በታሪክ የመጀመሪያው ወንጀል መሠራቱን ናሳ ገለጸ
በህዋ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ወንጀል መፈፀሙ ተነገረ:: ጠፈርተኛዋ አን ማክሌን ነች በታሪክ የመጀመሪያ ነው የተባለውን ወንጀል የፈጸመችው። ከምድር ብዙ ርቀት ተጉዛ ህዋ ላይ የምትገኘው አን፤ በጠፈር ምርምር ታሪክ ህዋ ላይ ሳለች ወንጀል የሠራች የመጀመሪያዋ ግለሰብ መሆኗን ያረጋገጠው ደግሞ ናሳ ነው::
አን ከፍቅር ጓደኛዋ ጋር ከተቃቃረች ቆየት ያለ ቢሆንም ህዋ ላይ መሆኗ ታዲያ የቀድሞ ወዳጇን የባንክ አካውንት ፈትሻለች:: ጠፈርተኛዋ የቀድሞ ወዳጇን የባንክ አካውንት መፈተሿን ብታምንም፤ “ምንም አላጠፋሁም” ስትል መከራከሯን ኒውዮርክ ታይምስ አስነብቧል።
ኹለቱ ጥንዶች የሚያስብላቸውን ጋብቻ አን እና ስመር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2014 ቢመሰርቱም በ2018 ተለያይተዋል። የቀድሞ ወዳጇ ስምር ዎርደን ጉዳዩን ለንግድ ኮሚሽን ሪፖርት ካደረገ በኋላ፤ ጠፈርተኛዋ ወደ መሬት እንድትመለስ ተደርጓል::
የስመርን የባንክ አካውንት የፈተሸችው አብረው ሳሉ በጋራ ያሳድጉት የነበረውን የስምር ልጅ የሚያስተዳድርበት በቂ ገንዘብ እንዳለው ለማወቅ እንደሆነ ጠፈርተኛዋ ብትገልፅም ናሳ ግን ጉዳዩን ከኹለቱም ግለሰቦች እያጣራ እንደሚገኝ ለኒውዮርክ ታይምስ አስታውቋል::
እኤአ በ2013 ላይ አን ታላቁን ናሳን ከመቀላቀሏ በፊት ለ800 ሰዓታት የጦር አውሮፕላን ወደ ኢራቅ አብርራለች። ናሳ ሙሉ በሙሉ ሴቶች ያሳተፈ የህዋ ጉዞ ለማድረግ ባቀደበት ወቅት ከተካተቱ ጠፈርተኞች አንዷ ብትሆንም በወቅቱ ናሳ “ለጠፈርተኞቹ የሚሆን ልብስ አላዘጋጀሁም” በማለቱ ጉዞው መሰረዙ አይዘነጋም::
የህዋ ማዕከሉ ባለቤቶች አሜሪካ፣ ሩስያ፣ አውሮፓ፣ ጃፓን እና ካናዳ ናቸው። አንድ ሰው ወንጀል ቢፈጽም የሚጠየቀው በአገሩ ሕግ ነው። አንድ አገር ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠረውን ግለሰብ በሌላ አገር ሕግ ለመዳኘት ከወሰነች፤ ግለሰቡ ወደ ምድር እንዲመለስ ከተደረገ በኋላ ለፍርድ ይቀርባል። ከዚህ ቀደም ህዋ ላይ ወንጀል ተሠርቶ ስለማያውቅ የህዋ ሕግ ተግባራዊ የሚሆንበት እድል አልነበረም። ምናልባትም ቱሪስቶች ህዋን መጎብኘት ሲጀምሩ ሕጉ ሊተገበር ይችላል ተብሎ ይጠበቃል::