የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም

ቅዱስ ሲኖዶስ በ30 ቀናት ውስጥ ምላሽ ካልሠጠ ዕርምጃ እንደሚወስዱ ቀሲስ በላይ አሳወቁ

የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ፅህፈት ቤት በክልል ደረጃ እንዲዋቀር የቀረበው ጥያቄ ምላሽ ቅዱስ ሲኖዶሱ በ30 ቀናት ውስጥ እንዲያሳውቃቸው፤ይህ ተግባራዊ ካልሆነ ግን አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስዱ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ፅህፈት ቤት አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቀሲስ በላይ መኮንን አስታውቀዋል።

በዛሬው ዕለት ነሐሴ 26፣2011ዓ.ም በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ኮሚቴው ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ ያወጣ ሲሆን፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ የክልላዊ ፅህፈት ቤቱን ጥያቄ የሚቀበለው ከሆነ የሰው ኃይል አመዳደቡም ሆነ አፈፃፀሙ ይህ አደራጅ ኮሚቴና ጠቅላይ ቤተ ክህነት በጋራ የሚወስኑት እንደሚሆን ተገልጿል::

በተጠየቀው መሰረት አስቸኳይ ምላሽ የማያገኝ ከሆነ የምዕመኑን ጥያቄ ለመመለስ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ኮሚቴው አስጠንቅቋል። እርምጃው ምን እንደሆነ በዚህ ወቅት ግልፅ ባያደርጉም ከዚህ ቀደም እንደተናገሩት በራሳቸው ክልላዊ ቤተ ክህነት ፅህፈት ቤት እናቋቁማለን ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ቀሲስ በላይ በዚህ ወቅት እንደገለፁት የዚህ ጉባኤ እምነቱ አንድ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ አንድ ፓትርያርክና አንዲት ቤተ ክርስቲያን መሆኑን አምነው የቤተ ክርስቲያኗን ሌላ ህግ ማውጣት እንደማያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ክልላዊ ቤተ ክህነት ፅህፈት ቤት የማቋቋም ጥያቄ የቤተ ክርስቲያኗ የዶግማና የቀኖና ትውፊት ለውጥ ሳይኖር አስተዳደራዊ ችግሮችን ለመፍታት መዋቅር የማበጀት ጥያቄ መሆኑንም ገልፀዋል።

ጥያቄው አዲስ እንዳልሆነና ታሪካዊ ዳራ ያለው መሆኑን ተናግረው ቤተክርስቲያኗ በአፄ ኃይለ ስላሴ አገዛዝም ወቅት በጠቅላይ ግዛት በአውራጃና በወረዳ ደረጃ የመንግሥት አደረጃጀት ተከትላ ትሰራ እንደነበርና እንዲሁም በደርግ ወቅትም ይህ አሰራር እንደቀጠለ ገልፀዋል።

በኢህአዴግ አገዛዝም ወቅት የፌደራል አደረጃጀቱን ተከትሎ ገረ ስብከቶች መቋማቸውንና በክልል ደረጃ ፅህፈት ቤት ማጣቷ ላለው ማህበረሰብ ተደራሽነት ሳይኖረው እንደቀረ ተናግረዋል። ቀሲስ በላይ አክለውም ቤተ ክርስቲያኗ በልዩ ልዩ ቋንቋና ለተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች ለመደረስ መዋቅር ለመዘርጋት እና ከአስተዳደራዊ ችግሮችም ጋር በተያያዘ የተደራሽነቷ መጠን መቀነሱን ፤የቤተ ክርስቲያኗ ምዕመናን መኮብለላቸውን፣ አብያተ ክርስቲያናት በከፍተኛ ቁጥር የቀነሰ ሲሆን ይህም በከፍተኛ የሚስተዋልበት የኦሮሚያ ክልል አንዱ መሆኑን አስረድተዋል።

የኦሮምኛ ቋንቋ በክልሉም ሆነ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል ቢነገርም ቤተ ክርስቲያኗ ያሏት ጥቂት ዲያቆናት፣ አገልጋዮች መምህራን ብቻ በመኖራቸው እነዚህም ለአዲሱ ትውልድን ያማከለ ቋንቋ የሚናገሩ ባለመሆኑ ክልላዊ መዋቅሩ መፍትሄ ሊያበጅለት ይችላል  ያሉት ቀሲስ በላይ ይህ ችግር ሁሉንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞችን የሚመለከት መሆኑንም

በክልሉ ቤተ ክህነት ፅህፈት ቤት እንዲቋቋም በተደጋጋሚ ለቀድሞው ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስና ለቅዱስ ሲኖዶሱ የቀረበ ሲሆን አስፈላጊነቱ ቢታመንም ምላሽ እንዳላገኘ፣ በአቡነ ማትያስ የፓትርያርክነት ዘመንም የክልሉ አባገዳዎችና ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ምእመናን ለቅዱስ ሲኖዶሱ በ2010 ዓ.ም ጥያቄው ቢቀርብም እሰስካሁን ምላሽ እንዳልተገኘ በጋዜጣዊ መግለጫው ተነግሯል::

የአሸንድዬ መዝጊያ በሚሊኒየም አዳራሽ ሲከበር፤ ተቃውሞ የገጠማቸው ታከለ ኡማ ዛሬም ተገኙ

የአሸንዳ በዓል የማጠቃለያ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ በሚሊኒየም አዳራሽ በደመቀ ስነ ስርዓት ተከበረ::

የኢትዮጵያ ልጃገረዶች ጨዋታ በሚል ስያሜ በአገር ባህል ቅርስነት በዮኔስኮ ለማስመዝገብ የታቀደው የአሸንዳ በዓል በሁሉም ኢትዮጵያዊያን መዲና አዲስ አበባ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች መቋጫው በድምቀት ተከብሯል::

ዛሬ  በሚሊኒየም አዳራሽ የበዓሉ ማሳረጊያ ሲከናወን ከቀናት በፊት አሸንዳን ሊያከብሩ በሚሊኒየም አዳራሽ በተገኙ በብዙ ሺኅ ሕዝብ ከፍተኛ ተቃውሞ ፤ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማና አፈጉባኤ ኬሪያ ኢብራሂምን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል መንግሥቱና የከተማው መስተዳድር ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሓላፊዎች ተገኝተዋል:: የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ የትግራይ ክልል ተወላጆችና የአሸንዳ ልጃገረዶች በሚሊኒየም አዳራሽ በመገኘት ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ በዓሉን ሲያደምቁ ተመልክተናል::

“አሸንዳ የሰላም፣ አንድነትና ልማት ተምሳሌት” በሚል መሪ ቃል ከነሐሴ 16 ጀምሮ በትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ሲከበር መቆየቱ አይዘነጋም::

በትግራይ ክልል በነሐሴ ወር የሚከበሩ የአሸንዳ፣ ማሪያ እና ዓይኒ-ዋሪ በዓላት፥ የክልሉን ባህል፣ ትውፊትና የቱሪዝም መስህቦች በማስተዋወቅ ረገድ የላቀ ሚና የሚጫወቱ በዓላት በመሆናቸው ፤ በዚህም መሠረት አሸንዳ እና ማሪያ ከነሃሴ 16 ቀን ጀምሮ እየተከበሩ የሚገኙ ሲሆን፥ ዓይኒ-ዋሪ ደግሞ ነሃሴ 24 ቀን 2011 ዓ.ም በአክሱም ከተማ እና አካባቢው የልጃ ገረዶች ተከብሯል::

12 ከተሞች ብርሃን ለሁሉም መርሀ ግብር ከ3 ወር በኋላ የኤሌከትሪክ አገልግሎት ያገኛሉ

አዲስ በተነደፈው በብርሀን ለሁሉም መርሀ ግብር በ12 ከተሞች እየተከናወነ የሚገኘው የአነስተኛ ሀይል ሙከራ ማመንጨ ስራ ከ3 ወር በኋላ እንደሚጠናቀቅ የውሃ መስኖ እና ኢነርጅ ሚኒስቴር ገለጸ::

የኤሌክትሪክ ሃይል ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች የብርሃን ለሁሉም መርሃ ግብር ዙሪያ የውሃ መስኖ እና ኢነርጅ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሽ በቀለ ለፋና  እንደገለጹት ከሆነ፤ በ12 ከተሞች በዚህ መርሃ ግብር የተጀመረው ከዋናው የኤሌክትሪክ ቋት ውጭ ከታዳሽ ሀይል የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ያለው ስራ ውጤታማ የሚባል እና እስከ 3 ወር ባለው ጊዜ ይጠናቀቃል:: መርሃ ግብሩ ሲጠናቀቅ ወደ 68 ሺህ ያህል ሰዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል::

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እስካሁን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ያልሆኑ ሌሎች 25 ከተሞች ደግሞ ሥራቸውን ለማስጀመር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ሓላፊዋ በ5 ዓመት ውስጥ በኢትዮጵያ የመብራት ሀይል ተደራሽ ያልሆነባቸውን ቦታዎች ተደራሽ በማድረግ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የመብራት ሀይል ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችለው መርሀ ግብር ይፋ ከተደረገ እና ሥራ ከጀመረ 2 አመት እንደሞላውም ገልጸዋል::

በቀሪጣዮቹ 3 አመታት አሁን በሥራ ላይ ያሉትን እና ለወደፊቱ የታቀዱትን ለማከናወን በትኩረት የሚሠራ ሲሆን፤ብርሀን ለሁሉም መርሀ ግብር ተግባራዊነት ከ 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪን እንደሚጠይቅ እና መስመር ተዘርግቶባቸው መብራት ያላገኙ አካባቢዎችንም በ2012 አመት በፍጥነት መብራት እንዲያገኙ ማድረግም ሌላኛው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ እንደሆነም ተነግሯል።

ኢትዮጵያና እስራኤል በሳይበር ደህንነት ላይ በጋራ ሊሠሩ ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ጽህፈት ቤት የክብር አቀባበል ተደረገላቸው።

በእስራኤል ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ እየሩሳሌም በሚገኘው ጽህፈት ቤታቸው ልዮ ግብዣ እንዳካሄዱላቸው እየወጡ ያሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በፕሮግራሙ ላይ ሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በአገራቱ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኢትዮጵያ እና የእስራኤል ግንኙነት ዘመናትን የተሻገረ እንደሆነ ጠቁመው ፤ ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ የማጠናከር ፍላጎት ያላት ከመሆኑን እና ለዚህም በጤና፣ ቱሪዝም፣ አይሲቲ ፣ በግብርና እና በሌሎች ዘርፎች አብራ የመስራት ፍላጎት ያላት መሆኑን ገልጸዋል።

የእስራኤል ባለሃብቶችና የንግድ ሰዎችም በኢትዮጵያ በቴሌኮም፣ በአቬሽን እንዱስትሪ፣ በሃይልና ኢነርጂ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸው እንዲያፈሱ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በእስራኤል የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያ (ቤተ እስራኤላውያን) በሁለቱ ሀገራት መካከል እንደ ድልድይ ሆነው ለግንኙነቱ መጠናከር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ እምነት እንዳላቸውም  ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላይ የደረሰውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር የእሳት አደጋ ባለሙያዎችን በመላክ ላደረገቸው አስተፅኦም  እስራኤልን  አመስግነዋል::

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው እስራኤል በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በቴክኖሎጂ እና በጸጥታ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በቅንጀት የምትሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ሁለቱ አገራት ታሪካዊ ግንኙነታ ያለቸው መሆኑን ያስታወሱት ኔታኒያሁ፥ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እያካሄደቸው ያለውን የለውጥ ሂደት በእጅጉ ይደነቃል ብለዋል::

በመጨረሻም የሁለቱ አገራት አምባሰደሮች ባለ አምስት ነጥብ የጋራ መግባቢያ ተፈራርመዋል። በዚህ መሰረትም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ ትብብር በሀገራቱ ሀግና መመሪያ መሰረት በጋራ የበለጠ ለማጎልበት እና በግብርና ፣ በውሃ ፣ በመስኖ ልማት ፣ በጤና እና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተፈረሙ ስምምነቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ትብብራቸውን ይበልጥ አጠናክሮ ለመቀጠል ፊርማቸውን አኑረዋል::

ኢትዮጵያ እና እስራኤልለቱ የሳይበር ደህንነት፣ ቴሌኮሙኒኬሽን እና የጠፈር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂን ጨምሮ በሌሎች የትብብር መስኮች ላይ ተጨማሪ ስምምነቶች ለመፈራርም የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለመመርመር  ከስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን፤ የተፈረሙ ስምምነቶችን ተፈፃሚነት ለመቆጣጠር እና በአፈፃፀም ወቅት ሊከሰቱ ለሚችሉ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት እንደአስፈላጊነቱ ተጨማሪ ስልቶችን ለመቀየስ  ከወዲሁ መግባባትን ፈጥረዋል::

በዛሬው ዕለት በናዚ የተጨፈጨፉ አይሁዳዊያን ማስታወሻ ሃውልትን የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሬቬን ሪቭሊን ጋርም ተገናኝተዋል::

LEAVE A REPLY