ዶ/ር አብይ መከሰስም ሆነ መወቀስ ካለበት በወጣት ህሊና ግጥም ሳይሆን ህብዝን ሲያሸብሩ፣ የእርስ በርስ ግጭቶችን ሲቀሰቅሱ እና የመንግስት አካላት ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩ እንቅፋት የሆኑት እነ ጃዋር መሃመድን እና ግብረ አበሮቹን በሕግ ተጠያቂ ባለማድረጉ ነው። እነዚህ ሰዎች ጥላቻን በአደባባይ ሲሰብኩ፣ እነሱ በቀሰቀሱት ሁከት የሰው ህይወት ሲጠፋና ንብረት ሲወድም እያዩ ከልክ ባለፈ ትዕግስት ሲያስታምሙ በመቆየታቸው ሊጠየቁ ይገባል። በተቃራኒው ሃሳባቸውን በጨዋ ደንብ በማንጸባረቃቸው ብቻ በባለአደራ አባላት እና አመራር ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ፤ ከዛም አልፎ እንደ ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩን አይነት ሰላም ሰባኪዎችን በማሰራቸው ሊጠየቁ ይገባል።
ህሊና በግጥሟ ውስጥ ያንጸባረቀችውን ሃሳብ መቃወምም ሆነ መንቀፍ፣ መተቸት ይቻላል። ግጥም እና እረቂቅ ሚስጥር የያዙ ስዕሎች ሁሌም ለብዙ እይታዎች እና ትርጉሞች ክፍት ናቸው። ገጣሚውም ሆነ ሰዓሊው ባላሰቡት መልኩ ሁሉ አንባቢና ተመልካች ሊተረጉማቸው ይችላል። የእነዚህ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች ውበትም ይሄው ነው። ከዛ አልፎ ግን ገጣሚዋን ማንቋሸሽ፣ የጥላቻ ስሜት ማንጸባረቅ፣ ስድብ እና ዛቻው ግን ህሊና ቢስ ከሆነ ሰው የሚጠበቅ አስነዋሪ ተግባር ነው።
ይች ልጅ በግጥሟ ውስጥ ማንንም ሰው ወይም ቡድን ወይም ማህበረሰብ በስም ጠርታ አላመሰገነችም፣ አላንጓጠጠችም፣ አላወገዘችም። በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ሊንጸባረቁ የሚችሉ የሰዎች እና የቡድኖች ባሀሪያትን ግን ቁልጭ አድርጋ አስቀምጣለች። መጥፎ የሚባሉ እሳቤዎችን አውግዛለች፤ ጥሩውን አወድሳለች። እራሳችንን የቱጋ እንደቆምን መፈለግ የኛ ድርሻ ነው። መጋ፣ ዘረኛ፣ ጎጠኛ፣ ጠባብ ነኝ ያለ በመንጋ ተርታ፤ መልካም አሳቢ፣ አገር ወዳድ፣ ወገን አፍቃሪ እና ሁሉን አቃፊ፣ የራሱን ብሔር ከሌሎች የማያስበልጥ ወይም የማያሳንስ እና በእኩልነት መንፈስ የታነጸ ሰው ነኝ ያለ በመልካሞች ተርታ እራሱን ያሰልፍ። እዳው ለራስ እንጂ ወደ ገጣሚዋ የሚሔድበት ምንም አግባብ የለም። የልጅቷን ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ለማፈን የሚደረገው ጥረት ግን ውጉዝ ከማሪዎስ ሊባል ይገባዋል። የህሊና አይነት ሃሳባቸውን በድፍረት፣ በአማረ ቋንቋ እና ልዩ ጥበብ መግለጽ የሚችሉ ባለህሊና ወጣቶችን ያበርክትልን።
አቶ ግርማ ጉተማ ልጅቷም ሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕግ ይከሰሳሉ የሚል ነገር ጠቅሰዋል። ይቺ የሳምንቱ አስቂኝ ንግግር ተደርጋ ትወሰድ። የማን ስም ጠፋ ተብሎ ይሆን ክስ የሚመሰረተው? እርሶ እኳ አንድን ማህበረሰብ እና የአንድ እምነት ተከታት በተደጋጋሚ ጊዜ በስም እየጠሩ ሲሳደቡ፣ ሲያንቋሽሹ፣ እርምጃ እንዲወሰድበት ሲቀሰቅሱ በሕግ የጠየቀዎት የለም። ዶ/ር አብይ እርሶን፣ ጃዋርን እና መሰል ጥላቻን እና አመጽ ቀስቃሽ ንግግሮችን የምታደርጉትን ሰዎች ሳይከሱ ህሊና ትከሰስ ማለት ህሊና ቢስ መሆን ብቻ ነው የሚጠይቀው።