ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች በወታደራዊ ትብብር ዙሪያ መከሩ
ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ወታደራዊ ትብብራቸውን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸው ተነገረ።
የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ጀነራል አደም መሀመድ ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ሌተናል ጀነራል ሀማድ መሃመድ ታኒ አል ራቱኒ ናቸው በወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሀገራቱን ወክለው የተደራደሩት።
ባለስልጣኑ በውይይታቸው ላይ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ወታደራዊ ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የሚያረጋግጡ ዜናዎች ተሰምተዋል።
የጦር ኢታማዦር ሹሙ ሌተናል ጀነራል ሀማድ መሃመድ ታኒ አል ራቱኒ የተመራ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ወታደራዊ ልኡክ በኢትዮጵያ ጉብኝት በማድረግ ላይ ሲሆኑ፤ የጉብኝቱ ዋነኛ ዓላማ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ወታደራዊ ትብብር በምን ደረጃ ላይ አንደሚገኝ ለመገምገም፣ እንዱሁም በጋራ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ ውይይቶችን ለማድረግ ታስቦ ነው እንደሆነ ታውቋል።
የኦሮሚያ ካቢኔ አዲስ የኢንቨስትመንት መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያን አፀደቀ
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ካቢኔ ትናንትና ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የኢንቨስትመንት መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያን ማጽደቁን አስታውቋል።
ኢንቨስትመንት የክልሉን ልማት እንዲያግዝና እና የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ እንዲያደርግ እንዲሁም ኢንቨስትመንት በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ እና ወደ ክልሉ ለመሳብ ሕገ ደንቡን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ተብሏል።
በኢንቨስትመንት ምክንያት ከእርሻ መሬታቸው ለሚነሱ አርሶ አደሮች ካሳ ከፍሎ ከቦታቸው ይዞታቸውን ከማስለቀቅ በዘለለ በኢንቨስትመንቱ ውስጥም የአክሲዮን ድርሻ ኖሯቸው ተጠቃሚ እንዲሆን ሁኔታዎችን የሚያመቻች ሕገ ደንብ በአዲስ መልክ ከመዘጋጀቱ ባሻገር፤ ግንባር ቀደም የሆኑ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች እንዲሁም ከጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ የሚሸጋገሩ ማህበራትን ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ታምኖበታል።
በክልሉ የሚካሄዱ የኢንቨስትመንት ስራዎች የስራ እድሎችን በመፍጠር የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ውስጥ ደርሻውን እንዲወጣ ከማድረግ ባሻገር፤ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ለመስጠት የነበረውን የተጓተተ አሰራር ለማሻሻል እና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችል የመተዳደሪያ ደንቡ ማሻሻል ማስፈለጉ ተነግሯል። እነዚህን ነጥቦች መሠረት ባደረገ መልኩ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ካቢኔ የክልሉ የኢንቨስትመንት መተዳደሪያ ደንብ ረቂቅ ማሻሻያ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ መተዳደሪያ ደንቡን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
የጃፓን መንግሥት በ500 ሚሊዮን ብር ለባህርዳር ንጹሕ ውሃ ሊያቀርብ ነው
በ500 ሚሊየን ብር ወጪየሚገነባው የባህር ዳር ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ዛሬ በይፋተጀምሯል። የግንባታውን ሙሉ ወጪ የሚሸፍነውም የጃፓን መንግሥት መሆኑ ታውቋል።
በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የጃፓን አለም ዓቀፍ የልማት ትብብር ሓላፊዎችና ተባባሪዎች ተገኝተዋል። የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ በባህር ዳር ከተማ አባይ ማዶ አካባቢ የሚገነባ ሲሆንየግንባታ ሂደቱም በሁለት ዓመት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የንጹህ ውሃ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በቀን 30 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የማመንጨት አቅም ያለው መሆኑን የገለጹትየክልሉ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ቢሮ ምክትል ሓላፊ አቶ ይመር ሀብቴ ይህም የአባይ ማዶ እና አካባቢውን ማህበረሰብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፍልጎት መቶ በመቶ ሊመልስ ይችላል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ የባህር ዳር ከተማን ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፍላጎት ከነበረበት 65 በመቶ ወደ 80 በመቶ ከፍ ያደርገዋል ያሉት እኚህ ከፍተኛ የክልሉ ሓላፊ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ግንባታም ከጃፓን በመጡ አማካሪዎችና ተቋራጮች እንደሚከናወን አረጋግጠዋል።
አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ ከፈረንሳይ መንግስት የክብር ሽልማት ተበረከተለት
የኢትዮጵያን ሙዚቃ በዓለም አቀፍ መድረክ በማስተዋወቅ ረገድ የሀገር ባለውለታ የሆኑት አንጋፋው አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ ከፈረንሳይ መንግስት የክብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል:: አርቲስቱ በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ጉብኝት እያደረጉ ካሉት የሀገሪቱ የባህል ሚኒስቴር እጅ ዛሬ ተቀብለዋል።
የክብር ሽልማቱን ለሙላቱ አስታጥቄ ያበረከቱት የፈረንሳይ የባህል ሚኒስትር ፍራንክ ሬስተር ፤ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት በዓለም አቀፍ የዘርፉ እይታ ውስጥ የሚገቡት በጣት የሚቆጠሩ አርቲስቶች እንደሆኑ፣ ከእነዚህም መካከል አንዱ አንጋፋው የኢትዮ ጃዝ ሙዚቀኛ አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ መሆናቸውን ጠቁመው ከፈረንሳይ መንግስት ለአርቲስቱ የቀረበላቸውን አድናቆትና ክብር ገልጸዋል።