የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 13 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 13 ቀን 2011 ዓ.ም

ኢሕአዴግ ውሕደት ያደርጋል የሚለውን ድራማ ሕወሓት አይቀበልም ሲሉ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ

ስልጣን ላይ ያለው ኢህአዴግ ተዋህዶ አንድ ወጥ ሃገራዊ ፓርቲ ይሆናል እየተባለ የሚነገረውን ሕወሓት ፈጽሞ እንደማይቀበለው የሕወሓትና የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ አስታወቁ።

ፓርቲው አጋር ድርጅቶችን ጨምሮ በመዋሃድ “የኢትዮጵያ የብልጽግና ፓርቲ” ይሆናል እየተባለ የሚነገረውን ጉዳይ በተመለከተ የግንባሩ መስራችና እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የድርጅቱ ቁንጮ ሆኖ የቆየው ሕወሓት ያሉት ችግሮች መፍትሄ ሳያገኙ እንደማይቀበለውም ይፋ አድርገዋል።

“እንደዚህ ዓይነት ለስልጣን ተብሎ የሚፈጠር  ውህደትን ሕወሓት ፈጽሞ አይቀበለውም። ሕወሓት እንደ መርህ የሚከተለው ግለሰቦች ስልጣን ላይ እንዴት ይቆዩ የሚል ሳይሆን፤ አንድን ድርጅት፣ ድርጅት የሚያደርገው ሃሳብን ነው” ያሉት አወዛጋቢው የወያኔ ሹመኛ ጉዳዮን በተመለከተ ይፋዊ መግለጫ መውጣቱን እንደማያውቁና ይሁን እንጂ እንዲህ አይነት ሩጫ በመካሄድ ላይ እንደሆነ መረዳታቸውን ጠቁመዋል::

ባለፈው ግንባሩ  ባካሄደው ስብሰባ ወቅት ውህድ ፓርቲ የመፍጠር ጉዳይ ተነስቶ እንደነበር ፣ የተባለው ውሁድ ፓርቲ ስለተባለ ብቻ መፈጠር የለበትም ተብሎ፤ የዓላማ አንድነት በአባል ፓርቲዎች መካከል ተፈጥሯል ወይ የሚል ጥያቄ በሕወሓት በኩል ተነስቶ ነበርም ብለዋል::

“በየእለቱ እርስ በርስ እየተናቆሩ የሚውሉት አባል ፓርቲዎችን ይዘን የሃገር ችግርን በመረዳትም ሆነ ችግርን ለመፍታት በምንከተለው መንገድ ጭምር እርስ በእርሱ በሚጋጩበት ሁኔታ፣ ውሁድ ፓርቲ ለመመስረት መሯሯጥ፤ የጥቂት ግለሰቦች የስልጣን ጥማት ለማርካት ካልሆነ በስተቀር የሃገሪቷን ችግር የሚፈታ ሃገራዊ ፓርቲ ይፈጠራል ብሎ ሕወሓት አያምንም” የሚሉት አቶ ጌታቸው ረዳ ፤ በአባል ፓርቲዎች መካከል ያለው የእርስ በእርስ መጠራጠርና የዓላማ አንድነት መጥፋት የሚወገድበት መንገድ መፈለግ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ እና ግንባሩ በስብሰባው ለዚህ ችግር መፍትሄ እንዲፈለግ ተስማምቶ እንደነበረም ለማስታወስ ሞክረዋል::

ነገር ግን ከዚያ በኋላ ችግሮች ከመባባሳቸው ባለፈ የተሻሻለ ነገር የለም ፤ የነበረው ውስጣዊ ልዩነት አሁን የበለጠ ሰፍቶ ካልሆነ በስተቀር መፍትሄ አላገኘም የሚል ተራ ምክንያት ያቀረቡት የሕወሓት ዳግም የበላይነት ናፋቂ  “ከዚህ ውጪ ካልተዋሃድን ወይም ስያሜ ካልቀየርን በቀጣዩ ምርጫ አናሸንፍም በሚል ርካሽ ስልጣን ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ አካሄድን ሕወሓት ድሮም አይቀበለውም አሁንም የሚቀበለው አይሆንም” ብለዋል::

ከዚህ በፊት በግንባሩ ስብሰባዎች ላይ እንደተወያዩት አባል ፓርቲዎቹን የሚለያዩዋቸውን ጉዳዮች በማጥበብ በሃሳብ ወደ አንድ የሚያመጣችውን መንገድ መፈለግ አስፈላጊ አይደለም ያሉት ጌታቸው ረዳ “አሁን እኔ የተናገርኩት ግን ሕወሓት ውህደትን የሚረዳበትን አግባብ ነው ፤ሕወሓት በዘፈቀደ ለስልጣን ማርኪያ ተብሎ በግለሰቦች የሚደረግን ማናቸውንም ድራማ አይቀበልም” በማለት ለቢቢሲ አስታውቀዋል::

ባሳለፍነው ዓመት 1229 ሰዎች በኢትዮጵያ ተገድለዋል ተባለ

የዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው መፈናቀል፣ ሰደትና ግጭት ከመቼውም ጊዜ በላይ ስር በሰደደባት ኢትዮጵያ ፤ ባለፈው 2011 ዓ.ም፣ በመላ የአገሪቱ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች 1.229 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል::

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በፌስ ቡክ ገጹ ይፋ እንዳደረገው ፣ ለበርካታ ሰዎች ሞት መንስዔ ሆነዋል ፣ በግጭቶቹ ተሳትፈዋል የተባሉ 1.323 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመስርቶ 645 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየታየ ነው ብሏል::  667 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች ደግሞ ገናእንዳልተያዙ ፤ የ10 ተጠርጣሪዎች ክስም በምህረት መነሳቱን በኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተደራጁ ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ፍቃዱ ፀጋ አስታውቀዋል::

በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በግጭቶች 1,393 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ሲደርስ በ19 ሰዎች ላይም የግድያ ሙከራ ተደርጓል:: አሁንም በሀገሪቱ ያለው ዜጎችን የማፈናቀል እና በየቦታው በሚነሱ ግጭቶች ሰዎችን የመግደሉ እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ካለመዋሉ ጋር ተያይዞ በዚህ ዓመት የሟቾች ቁጥር ሊቀንስ እንደማይችል በርካቶች በመናገር ላይ ናቸው::

ባለፈው ዓመት 2,290,490,159.(ሁለት ቢሊየን ሁለት መቶ ዘጠና ሚሊየን አራት መቶ ዘጠና ሺ አንድ መቶ ሃምሳ ዘጠኝ ብር ገደማ) የሚገመት የዜጎች ንብረት በተነሱ ግጭቶች አማካይነት ወድሟል::1,200437(አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺ አራት መቶ ሰላሳ ሰባት) ዜጎች ከመኖሪያ ቤታቸውና ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውን ከዐቃቤ ሕግ መረዳት ችለናል::

የመስቀል ደመራ ከፖለቲካ መልዕክቶች የፀዳ እንዲሆን ማህበረ ቅዱሳን ቅስቀሳ ጀመረ

የፊታችን አርብ የሚከናወነው የደመራ በዓል ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ እየተራገበ ከሚገኘው የፖለቲካ አጀንዳ ውጭ በሆነ መልኩ እንዲከበር ማህበረ ቅዱሳን እና አብያተ ክርስቲያናት ከፍተኛ ቅስቀሳ በማካሄድ ላይ ናቸው::

በተለይም የመስከረም አራቱ ሰልፍ መራዘም እና በሌሎች ክልሎች ሕዝበ ክርስቲያኑ በተከታታይ ሳምንታት ሰልፍ መውጣቱ ያበሳጨው የአዲስ አበባ ነዋሪ በአጋጣማው ተቃውሞውን ሊያሰማ ይችላል የሚል ስጋት በመንግሥት በኩል መኖሩን ሰምተናል::

ባለፈው እሁድ የኢሬቻ ሩጫ በአዲስ አበባ መካሄዱ እና በቀጣይ ሳምንት የኢሬቻን በዓል ከ150 ዓመት በኋላ ፊንፊኔ ላይ እናከብራለን የሚለው የኬኛ ፖለቲካ መጀመሩ በቅሬታ ውስጥ ያለውን የአዲስ አበባ ወጣት ለአመፅ ሊያነሳሳው ይችላል የሚል ስጋት በከተማዋ አስተዳደር በኩል እንዳለ ይነገራል::

ወትሮም ቢሆን በመንፈሳዊ ክብረ በዓሎች ላይ ከቤተ ክርስቲያን ስርዓት ውጪ ሆኖ የማያውቀው አዲስ አበቤ አንዳንድ ብሔርተኛ ፖለቲከኞች አጋጣሚውን ለሌላ ዓላማ እንዳይጠቀሙበት ከወዲሁ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ማህበረ ቅዱሳኖች ከየአድባራቱ ጋር በመሆን ምዕመናኑን የማነቃቃት ሥራ በማከናወን ላይ ናቸው::

በዕለቱ በዓሉን ለማክበር ወደ መስቀል አደባባይ የሚሄደው ምዕመን በዝማሬና በምስጋና ከመጓዝ ውጪ ምንም ዓይነት መፈክሮችን እንዳይዝና እንዳይጠቀም ጥሪ ያቀረቡት ማኅበበረ ቅዱሳኖች ምዕመኑ ራሱንም ቤተክርስቲያኒቱንም ከተሳሳተ ዓላማ የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበትም ተናግረዋል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ የደመራ በዓል በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሰራታቸውን የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል::

የደመራ በዓል ኢትዮጵያ በዓለም የቅርስ መዝገብ ካስመዘገበቻቸው ቅርሶች ውስጥ አንዱ ነው። በዓሉ በዩኔስኮ ከመመዝገቡ በተጨማሪም መስህብ በመሆን እና ጎብኚዎችን በመሳብ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑም ይነገራል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም በዓሉ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ባማረ እና በተሳካ ሁኔታ እንዲከበር የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን፥ የሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ታሪኩ ነጋሽ ተናግረዋል። ከሚደረጉት ዝግጅቶች መካከል ከሀይማኖት መሪዎች እና ከሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ከፌደራል እስከ ታች ካሉ የስራ ሓላፊዎች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ይገኙበታል።

በዓሉ አንድነትን በማጠናከር እና ሀዝብን በማቀራረብ ረገድ ያለውን ፋይዳ በሚመለከትም ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው ይሆናል።በተለይም ወጣቱ በበዓሉ አከባበር መቀራረብን እና መተሳሰብን እንዲማር የማድረግ ስራዎች እንደሚሰሩም ነው አቶ ታሪኩ የተናገሩት።

እንደ ሚኒስቴሩ መረጃ በበጀት አመቱ ከአንድ ሚሊየን በላይ የውጭ ሃገር ጎብኚዎችን ለመሳብ እና በዚህም 5 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል። የሚኒስቴሩ መረጃ እንደሚያሳየው በፈረንጆቹ በ2017 ላይ 432 ሺህ 687 ጎብኚዎች በዓሉን ሲታደሙ፥ በ2018 ደግሞ 384 ሺህ 615 ጎብኚዎች የመስቀል ደመራ በዓልን ተንተርሰው ሃገር ውስጥ ገብተዋል። በዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓልም ካለፉት አመታት የተሻለ የኚብኝዎች ቁጥር ይመዘገባል ተብሎም ይጠበቃል::

ሕገወጥ መሣሪያ የጫነው መኪና በሌሊት ባዶውን መጓዙ እንዳጠራጠረው ሲራጅ አብደላ ገለጸ

በአፋር ክልል ዞን አንድ፣ ኤሊዳአር ወረዳ ማንዳ ቀበሌ በፖሊስነት ሙያ ላይ ተሰማርቶ  የሚገኘው ዋና ሳጅን ሲራጅ አብደላ፤ የሥራ አካባቢው ድንበር በመሆኑ ሕገወጥ የመሣሪያ ዝውውሮችና ኮንትሮባንዶች የሚበዙበት ፈታኝ ቦታ እንደሆነ ለቢቢሲ ገለጸ::

መስከረም 8 ቀን 2012 ዓ.ም ከምሽቱ አምስት ሰዓት ገደማ አንድ ተሽከርካሪ ባዶውን ለማለፍ ሲሞክር የተመለከተው ሲራጅ በወቅቱ በሥራ ላይ እሱን ጨምሮ አራት የፖሊስ አባላት የነበሩ ቢሆንም ወደ መንገዱ ያመራው ግን እርሱ ብቻ ነበር።

መንገድ በመዝጋት ተሽከርካሪው እንዲቆም ትዕዛዝ በሰጠው መሠረት አሽከርካሪው መኪናውን አቆመ። ምንም የጫነው ነገር አልነበረም። ጋቢና ውስጥ ግን ሹፌሩ፣ ረዳቱና ሌላ ባለቤት እንደሆኑ የተነገረው አንድ ሰው መቀመጣቸውበዚህ ሌሊት ምንም ጭነት ሳይዝ ምን ያስጉዛቸዋል? የሚል ጥርጣሬ ሊያሳድርበት ችሏል::

“ቦታው ግንባር በመሆኑ ከመከላከያ መኪና በስተቀር ሌሎች መኪናዎች እምብዛም አያልፉም” ሲል በዋናነት ወደ ጥርጣሬ የከተተውን ምክንያት የገለጸው ምስጉኑ ፖሊስ ከዚህ ባሻገር ቀደም ብሎ ከሕብረተሰቡ ጥቆማ ደርሶት ስለነበር ተሽከርካሪውን የእጅ ባትሪ አብርቶ መፈተሽ ሲጀምር ጥርጣሬው እውነት ሆኖም ከተሽከርካሪው ጎማ በላይ የታሰረ ጆንያ ያያል። “ይህ ምንድን ነው?” ብሎ ሲጠይቅ ግለሰቦቹ “እኛ የምናውቀው ነገር የለም” የሚል መልስ ቢሰጡትም፤ በፍተሻው 29 ክላሽንኮቭ የጦር መሣሪያ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲያመሩ ትዕዛዝ መስጠቱን ገልጿል::

 ሁኔታው ያስደነገጣቸው ግለሰቦች ግን አንድ መሣሪያና አርባ ሺህ ብር በመስጠት መደራደር ጀመሩ። ፖሊስነት ከተቀጠረ ሁለት ዓመት ያልሞላው ብልሁ ሲራጅ አርባ ሺህ ብሩን በመያዝ ከእነመሣሪያቸው በቁጥጥር ሥር ሊያውላቸው ችሏል።

“አርባ ሺህ ብር እና አንድ መሳሪያ ከአገር ደህንነት አይበልጥም” ያለው ቆፍጣና ፖሊስ ከዚህ ቀደም በነበረው አጭር የሥራ ልምድ እንዲህ ዓይነት ጉዳይ አጋጥሞት እንደማያውቅም አረጋግጧል::

“ወደፊትም እንደዚህ ዓይነት ሕገ ወጥ ተግባር ብናይ ማለፍ እንደሌለብን በሥልጠናችን ወቅት አስቀድመን ቃል የገባንበት ጉዳይ ነው” ሲል የሙያ ግዴታው ፣ ሓላፊነቱን ፣የሕዝብንና የአገር ደህንነትን ማስጠበቅ እንደሆነምያስረዳል። የክልሉ መንግሥትም ለፖሊስ አባሉ የ50 ሺህ ብር ሽልማት እና የዋና ሳጅን ማዕረግ አበርክቶለታል::

40 ሺህ ብር ሊሰጡት ነበር እምቢ ብሎ ነው ብለን ለክልሉ ፕሬዚደንት ስንነግራቸው፤ ከእነርሱ የበለጠ ነው የምንሸልመው ብለው ነው 50 ሺህ ብር የሸለሙት ሲሉ የክልሉ ፕሬዚዳንት በወቅቱ የተሰማቸውን ኩራት ኮሚሽነሩ ገልጸዋል:: እርሳቸው እንደሚሉት መሣሪያው በቁጥጥር ሥር የዋለበት ቡሬ ግንባር፤ ድንበር በመሆኑ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የኮንትሮባንድ ንግድና ሕገ ወጥ የመሣሪያ ዝውውር ያጋጥማል።

በዚህም ምክንያት የፖሊስ አባላቶቻቸው ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርጉ ግንዛቤ መስጠት ዝንፍ የማይሉበት ተግባራቸው ነው። በመሆኑም ሲራጅ ከሕብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሠረት በገንዘብ ሳይደለል ሕገወጥ የመሣሪያ አዘዋዋሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ማዋል ችሏል ይላሉ።ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የፖሊስ አባሉ ለሕግ የበላይነት ላበረከተው አስተዋፅኦ የእውቅና የምስክር ወረቀት እና ሜዳሊያ አበርክተውለታል።የፌደራል ፖሊስም የምስክር ወረቀትና ሞባይል ስልክ ሸልሞታል።

“የተሽከርካሪውን ሹፌር ባነጋገርኩበት ወቅት፤ ‘መኪናው ባዶ በመሆኑ ጠለቅ ያለ ፍተሻ አይደረግብንም’ በማለት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሲሰጣቸው እንደቆሙ ነግሮኛል” ሲሉ የማምለጥ ሙከራ እንዳላደረጉ ለቢቢሲ የገለጹት ኮሚሽነሩወዲያው ጥበቃ ላይ የነበሩ ሌሎች ፖሊሶችና የአካባቢው ማኅበረሰብ ትብብር እንዳደረጉለት አረጋግጠዋል::

ሕገወጥ መሣሪያ በማዘዋወር የተጠረጠሩት ግለሰቦች እና ተሽከርካሪው በአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በእስር ላይ ሆነው ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝም ኮሚሽነሩ አስረድተዋል። ከአንድ ወር በፊት፤ አንድ ተሽከርካሪ በዚያው ክልል ‘ሰርዶ’ የተባለ ኬላ ጥሶ በማለፍ ሎግያ መግቢያ ላይ የጦር መሣሪያና በርካታ ጥይቶችን እንደጫነ መያዙን አስታውሰዋል።

ምንም እንኳን እስካሁን ጉቦ በመቀበል ተጠርጥረው የተያዙ የፖሊስ አባላት ባይኖሩም፤ ሕገ ወጦች የፀጥታ አባላትን በተለያየ መንገድ በማማለል የማይሰሩት ሥራ ስለሌለ ሙስና ይኖራል ብለው ያስባሉ- ኮሚሽነሩ።

ስብሰባ ላይ በመናገራቸው ሹፌሮችን ያባረረው አንበሳ፤ 100 አውቶቢሶች ጨመረ

100 ተጨማሪ አዳዲስ አንበሳ የከተማ አውቶቢሶች ወደ ዛሬ መስከረም 14 ቀን ወደ ሥራ የገቡ መሆናቸው ታውቋል::

ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ፤ የከተማ አውቶቢሶቹ በአሁን ወቅት በአዲስ አበባ ያለውን የትራንስፖርት እጥረት ለማቃለል አስተዋፆኦ ይኖራቸዋል ተብሏል::

በከተማዋ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ የብዙሃን ትራንስፖርት አንበሳ እና ሸገር ባስ አገልግሎትን ለማሻሻል በጥናት ላይ የተመሠረተ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን እና በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ ዘመናዊ አውቶቢሶች ከውጪ ለማስገባት እና የትራንስፖርት ስምሪቱን ዘመናዊ የሚያደርግ አሰራር ለመዘርጋት እየሰራ መሆኑን ሰምተናል::

በቅርቡ ስብሰባ ላይ መሥሪያ ቤቱን ተችታችኋል በሚል በርካታ ወጣት ሹፌሮችን ከሥራ ያገደው አንበሳ አውቶቢስ ለምን ወቀሳችሁኝ በሚል ሹፌሮችን አባሮ አዲስ ቅጥር ለማድረግ መሯሯጡ ማኔጅመንቱ ግልጽ የሆነ ሥራን የመምራት ችግር ያለበት መሆኑን ያሳያል ይላሉ የዜና ምንጮቻችን::

አስተዳደሩ ሹፌሮቹን በሰበሰበበት ወቅት ሀሳባቸውን በነፃነት እንዲገልጹ ተደጋጋሚ ግፊት በማድረጉ በመድረኩ ላይ እውነታውን በማስቀመጣቸው ብቻ ከሥራ መባረራቸውን የነገሩን የድርጅቱ ሠራተኞች ጉዳያቸውን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸውልናል::

በወለደች 30 ደቂቃ ውስጥ የመጨረሻውን ማትሪክ የተፈተነችው ወጣት መሐንዲስነትን አልማለች

አልማዝ ደረሰ ባሳለፍነው ዓመት በ10ኛ ክፍል ማጠቃለያ ሃገር አቀፍ ፈተና ወቅት ከወለዱ ሴት ተማሪዎች መካከል አንዷ ስትሆን ከወለደች ከ30 ደቂቃ በኋላ ነበር ፈተና ላይ የተቀመጠችው። በዚህን መሠሉ የተፈጥሮ ጸጋና እጅግ አስገራሚ ክስተት ውስጥ ሆና ፈተናውን የወሰደችው ወጣት 3.0 በማስመዝገብ ወደ አስረ አንደኛ ክፍል ተዘዋውራለች::

የትምህርት ፖሊሲው ወደ ቀደመ ይዘቱ መመለሱን ተከትሎ ከወራት በፊት የ10ኛ ክፍል የመጨረሻውን ማትሪክ ፈተና የወሰደችው አልማዝ የኢሉአባቦራ ዞን፤ መቱ ከተማ ነዋሪ ነች:: ነፍሰጡር ሆና ትምህርት ቤት ተመላልሳ፤ ከወለደች ከ30 ደቂቃ በኋላ ሆስፒታል ውስጥ ሆና ፈተና ላይ ብትቀመጥም ያመጣችው ውጤት ግን መላው ቤተሰቡን አስደስቷል::

ስፈተን ሕመም ላይ ስለነበርኩ ይህንን ውጤት አልጠበቅኩም ነበር፤ ቢሆንም አሁን ላይ ውጤቴን ሳይ በጣም ደስ ብሎኛል የምትለው አልማዝ በፈተና ወቅት ምጥ ባይፈትናት  ኖሮ ከዚህም በላይ ውጤት ልታስመዘግብ እንደምትችል ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ ላይ ገልጻለች::

ፈተናው ብቻ ሳይሆን ሙሉውን የትምህርት ጊዜም ነፍሰጡር ሆና ነው ትምህርቷን የተከታተለችው ወጣትየእርግዝናዋ የመጀመሪያዎቹ ወራት ፈታኝ ቢሆኑም ጽንሱ እየገፋ ሲመጣ መነሳት፣ መቀመጥ፣ መተኛት ቢቸግራትም እንዳልተሸነፈች፣ እንዲያውም ማታ ማታ ለመተኛት ስለማይመቻት ቁጭ  ብላ በማጥናት አጋጣሚውን ለፈተና ራሷን ማዘጋጃ አድርጋ እንደተጠቀመችበትም ተናግራለች::

በትዳር 4 ዓመታትን ያስቆጠረችው አልማዝ ደረሰ ፤ እስከ ሰባት ዓመቷ ድረስ ከወላጆቿ ጋር ሆና ብታሳልፍም፤ የሚኖሩት ገጠር በመሆኑ  የተነሳ ከሰባት ዓመቷ በኋላ እናስተምራታለን ያሉ ዘመዶቿ ጋ ወደ ከተማ ሄዳም ነበር::በወቅቱበቤት ውስጥ የሥራ ጫና ስለነበረባት ትምህርቷን በተለያየ ጊዜ ለማቋረጥ ተገዳለች::

ይህን ችግር ተከትሎ ትዳር ወደ መመስረቱ እንዳዘነበለች እና ትዳር ከመሰረተች በኋላም ትምህርቷን እንደቀጠለች ከዚያም ሳታቋርጥ እዚህ እንደደረሰች ያስታወሰችው አልማዝ ፤ “ባለቤቴ እንድማር ብቻ ነበር የሚፈልገው፤ ተማሪ በርቺ እያለ ሁሉንም እያሟላ ይደግፈኝ ነበር” ስትል የትዳር አጋሯ ደጋፊ ባለውለታዋ ጭምር መሆኑን መስክራለች::

“ልጅ እያደገ ሲመጣ ያጓጓል” የምትለው አልማዝ ልጇን ባየች ቁጥር፤ ያኔ የነበረባትን ጭንቅ፣ ፈተናው፣ ነፍሰጡር ሆና ወደ ትምህርት ቤት መመላለሷ ትውስ እንደሚላት ፣በቀጣይም በትምህርቷ ገፍታ ወደፊት መሐንዲስ የመሆን ምኞት እንዳላት ገልጻለች::

“ባለቤቴ ነፈሰጡር ሆናም በጣም ጠንካራ ነበረች፤ ስትንቀሳቀስ የነበረው ነፍሰጡር እንዳልሆነች ሴት ነበር። በቤት ውስጥ እኔና እሷ ብቻ ስለነበርን እኔንም ለመርዳት ጥረት ታደርግ ነበር” ያለው ባለቤቷ ፤ ጥንዶቹ በእርግዝናዋ ጊዜም ቢሆን ትምህርቷን ስለማጠናቀቅ እንጂ አንድም ቀን ስለማቋረጥ በጭራሽ አስበውትም፤ ተነጋግረውበትም እንደማያውቁ አስረድቷል:: በ10ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ወቅት በመላ አገሪቱ 28 ሴት ተማሪዎች መውለዳቸው አይዘነጋም::

LEAVE A REPLY