ለአፋን ኦሮሞ መምህራን የተሰጠው ልዮ ጥቅም ከፍተኛ ተቃውሞ ቀሰቀሰ
በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የተመደቡ የኦሮምኛ ቋንቋ አስተማሪዎች ከመደበኛው ክፍያ በተለየ ልዩ ጥቅማ ጥቅምና ደሞዝ እንዲያገኙ መደረጉ በከተማዋ የመንግሥት ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ መምህራን ዘንድ ትልቅ ተቃውሞን ቀስቅሷል::
የኦሮሞ መምህራኑ ሦስት ሺህ ብር የልዮ ጥቅማ ጥቅም ክፍያ እየተፈጸመ ትውልድን ከአንድ ብሔር ቋንቋ ይልቅ በዘለቄታዊ ቋንቋ የሚያንፁ ሌሎች መምህራን ግን የስምንት መቶ ብር የጥቅማ ጥቅም ክፍያ መፈጸሙ የታከለ ኡማ አስተዳደር ከጀርባው ምን ዓይነት ዓላማ እንዳነገበ ያሳያል ተብሏል::
የተሻለ የሥራ ልምድ ያላቸው መምህራን እንኳን ለአፋን ኦሮሞ ትምህርት መምህራኑ የተሰጠው ልዮ ጥቅም ዕድል ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ የሚናገሩት መምህራን ከትምህርት ቢሮ ለመጡ ባለሙያዎችና ሓላፊዎች ጥያቄውን ቢያቀርቡም “አርፋችሁ ሥሩ” መባላቸውን አስታውቀዋል::
በተመሳሳይ መምህራን ውስጥ የሁለት ሺህ ሁለት መቶ ብር የአበል ልዮነት ይዞ የመጣው የኦሮሞ ሕዝብ ተሟጋቹ እና ይምሰል የአዲስ አበባ ከንቲባ አስተዳደር ከኦሮሚያ ለመጡ መምህራን ክፍያ የሚፈጸመው ከትምህርት ቢሮ ሳይሆን ከሌላ አካል መሆኑ አካሄዱ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ከመሆኑ ባሻገር በአንድ ተቋም ለሚሠሩ መምህራን ከተለያየ ወገን ክፍያ የሚያገኙበት ተራና አስቂኝ አሠራር ሆኖ ታይቷል::
መንገዶች ባለሥልጣን አራት የፍጥነት መንገዶችን ሊገነባ ነው
አዲስ አበባን ከክልል ከተሞች ጋር የሚያገናኙ አራት ፈጣን መንገዶችን ለመገንባት በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑ ተነገረ::
የሚገነቡት ፈጣን መንገዶች አዲስ አበባን መዳረሻ በማድረግ ደብረ ማርቆስ ጅማ ነቀምት እና ኮምቦልቻ ከተሞች ላይ ይገነባሉ::
አሁን ላይ ግንባታውን ለማከናወን የአዋጪነት ጥናት ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል:: ጥናቱ በመንግሥት እና በግል አጋርነት ካልሆነም የግንባታና የዲዛይን ውጤቱ እንደሚያመለክተው አዋጭ መንገድ ለመገንባት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ማቀዱን የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው ሰለሞን ወንድሙ ተናግረዋል::
አሁን ባለው የመንገድ ሽፋን ከአዲስ አበባ ደብረ ማርቆስ 305 ኪሎ ሜትር ሲሆን ጅማ 354 ኪ/ሜትር ነቀምት 318 ኪ/ሜትር አላቸው:: እያንዳንዱ መንገዶች በመኪና በአማካኝ ከሦስት እስከ አራት ሰዓት የሚወስዱ በመሆናቸው የፈጣን መንገድ ግንባታው ዕውን ከሆነ በኋላ ግን የሰዓታት ለውጥ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል::
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በ2012 በጀት ዓመት 150 ቢሊዮን ብር የሚገመቱ ዘጠና አንድ ፕሮጀክቶችን እንደሚጀምር መግለፁ ይታወሳል::
አልሻባብ በአሜሪካ ወታደሮች ማሠልጠኛ ካምፕ ላይ ጥቃት ሰነዘረ
ከሶማሊያ የወጡ መረጃዎች እንዳመለከቱት የአሜሪካ ወታደሮች የሶማሊያ አቻቸውን በሚያሰለጥኑበት ወታደራዊ ካምፕ ላይ ጂሃዲስት ኃይሎች ጥቃት መፈጸማቸው ተሰማ::በደቡባዊ ሶማሊያ የታችኛው ሸበሌ ክልል ውስጥ ባሊዶግሌ የአውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ ተኩስና ከባድ ፍንዳታ እንደነበርም ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል::
አክራሪው እስላማዊ ታጣቂ ቡድኑ አልሻባብ እንደሆነ በተነገረው ድረ ገፅ ላይ ጥቃት አድራሹ መኪና ላይ የተጠመደ ቦምብ መግቢያ በሩ አካባቢ ያፈነዳ ሲሆን ከፍንዳታው በኋላ ታጣቂዎቻቸው ወደ ውስጥ እንደገቡም የአይን እማኞች አስረድተዋል::
የወታደራዊ ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት ጂሃዲስቶቹ ከጥቃቱ በኋላ የተኩስ ልውውጥ ሲጀመር ወደ ኋላ እንዳፈገፈጉ የገለጹ ሲሆን አልሻባብ ባወጣው መግለጫ ደግሞ ጥቃቱን እንደፈጸመ አረጋግጧል። “በከባድ የሚጠበቀውን ካምፕ ጥሰው ከገቡ በኋላ ወታደራዊ ተቋሙ ውስጥ ከነበሩት የውጪ ኃይሎች ጋር ታተኩሰዋል” ሲልም በመግለጫው እውነታውን አሳይቷል::
ወታደራዊ ካምፑ ከዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ በስተምዕራብ 100 ኪሎ ሜትሮች ያህል ርቆ ይገኛል:: ካምፑ የአሜሪካና የሶማሊያ ልዩ ኃይሎች እንዲሁም የኡጋንዳ ሠላም አስከባሪዎች የሚገኙበት መሆኑም ተነግሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ የጣሊያን ወታደራዊ ኮንቮይ ሞቃዲሾ ውስጥ በፍንዳታ ጥቃት እንደደረሰበት የጣሊያን መከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል::
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ አሜሪካ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገረው አልሻባብ ላይ የምታካሂደውን የአየር ጥቃት አጠናክራለች። የሶማሊያ ባለስልጣናት እንደሚሉት ቡድኑ በአሜሪካ የሚፈጸምበትን የአየር ጥቃት ለመበቀል ሞዋዲሾ ውስጥ የሚፈጽመውን ጥቃት ጨምሯል።
5 ዓመት የሚቆይ የባህል መድኃኒቶች ጥናትና ምርምር ፍኖተ ካርታ ዛሬ ይፋ ሆነ
የአምስት ዓመት የባህል መድኃኒቶች ጥናት እና ምርምር ፍኖተ ካርታ በዛሬው ዕለት ይፋ ተደርጓል:: በስነ ስርዓቱ ላይ የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማንን ጨምሮ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች፣ የባህል ህክምና አዋቂዎችና ባለ ድርሻ አካላት እንደተገኙም ታውቋል::
ጠቃሚ ነው የተባለው ፍኖተ ካርታ የባህል መድኃኒት ደህንነቱንና ፈዋሽነቱን በማረጋገጥ ወደ ዘመናዊ የህክምና ስርዓት እንዲገባ ማስቻል ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ዶክተር አሚር ገልጸዋል::
በፍኖተ ካርታው በአሁኑ ወቅት ያለውን የባህል መድኃኒት ፖሊሲ እንደ አስፈላጊነቱ ለመከለስ፣ አዋጅና መመሪያዎችን ለማዘጋጀት፣ ለማስተባበርና ቁጥጥርን ለማጠናከር የላቀ ድርሻ አለው ተብሏል::
የባህል መድኃኒት ዕውቀትን በመደበኛው ትምህርት ማካተት፣ ለባህል መድኃኒት ባለሙያዎች ስልጠናና ትምህርት መስጠት ለጤናው ዘርፍ የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነ በተጨማሪነት ተገልጿል:: የባህል መድኃኒትን፣ ሀገር በቀል ዕውቀትንና ዕፅዋትን መጠበቅ፣ መንከባከብና ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑም በፍኖተ ካርታው ተመላክቷል።
ከመድኃኒት አምራቾች ጋር ቅንጅት በመፍጠር መድኃኒትነታቸው በምርምር የተረጋገጡ የባህል መድኃኒቶችን እንዲመረቱ ለማስቻል ዕቅድ የተያዘ ሲሆን ፤ ይህም ጉዳት የማያደርሱ የባህል መድኃኒቶችን በጥናት አስደግፎ ይፋ ማድረግ እና በስፋት ተጠንቶ ጥቅማቸውና ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ የባህል መድኃኒቶችን እንደ አማራጭ የህክምና አይነት እንዲቀርቡ ፍኖተ ካርታው ዕድል እንደሚሠጥ ነው የተነገረዉ::
ይህ ፍኖተ ካርታ ከዛሬ ጀምሮ በቀጣይ አምስት ዓመታት ተግባራዊ ይደረጋል:: ለፍኖተ ካርታው ማስፈፀሚያም በዚህ ዓመት ብቻ 90 ሚሊየን ብር መመደቡን የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን አብራርተዋል::
በኢትዮጵያውያን የተመረተ የጤፍ ቢራ ዛሬ በአሜሪካ ገበያ ላይ ዋለ
በኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባለቤትነት በአሜሪካን የተቋቋመው ንጉሥ ቢራ ኩባንያ በአሜሪካ ከተገኘ ጤፍ የተዘጋጀ ቢራ ዛሬ ለገበያ ማቅረቡ ታወቀ::
ዛሬ መስከረም 19 ቀን ለተጀመረው የገበያ ስርጭት 19 ሺህ 200 የጤፍ ቢራ ተዘጋጅቶ መቅረቡን ሰምተናል:: ከሦስት ዓመት በፊት የተመሠረተው ንጉሥ ቢራ ኩባንያ ቀደም ሲል ንጉሥ ፕሬምየም ክራፍት ላጋር የተሰኘ በአነስተኛ ፋብሪካ የተጠመቀ ቢራ በቨርጂኒያ ግዛት ማናሳስ ከተማ ሲያመርት ቆይቷል:: ኩባንያው ይህንን ቢራውን በዋሽንግተን ዲሲ ኒዮርክ ቨርጂኒያ ኖርዝ ካሮላይናን ጨምሮ ኢትዮጵያውያን እና ጥቁር አሜሪካውያን በስፋት በሚኖሩባቸው ግዛቶች ምርቱን ለገበያ ማቅረቡም ይታወሳል::
ካምፓኒው አሁን ላይ “አዲስ ጤፍ አምበር ኤል” በሚል መጠሪያ በአሜሪካ አገር ከተመረተ ጤፍ የተዘጋጀ ልዮ ቢራ ለገበያ አቅርቧል:: እ.ኤ.አ በ2016 የተመሠረተው ንጉሥ ቢራ ኩባንያ በማሳቹሴት ጆርጂያ ሚኒሶታ እና ካናዳ የማስፋት ዕቅድ ይዞ በመሥራት ላይ መሆኑንም ሠምተናል::
ለቢራ ምርቱ ዋነኛ ግብዓት የሆነውን ከኢትዮጵያ ማስገባት ያልፈለኩት ኢትዮጵያ ውስጥ የጤፍ ምርት እጥረት እንዳይፈጠር በመስጋት ነው ያለው ኩባንያ ከጤፍ ቢራ ምርቱ በማገኘው ገቢ በአገሪቱ የጤፍ እጥረትን በዘላቂነት ማስወገድ እንዲቻልና የምርቱን መጠን ከፍ ለማድረግ በኢትዮጵያ በጤፍ ላይ የሚሠሩ የእርሻ ምርምሮችን በገንዘብ እደጉማለሁ::
አራት የኦሞ ኩራዝ ፋብሪካ ሠራተኞች በሥራ ላይ ሆነው መገደላቸው አነጋጋሪ ሆኗል
በኦሞ ሸለቆ ተፋስ በተገነቡት ሁለት ስኳር ፋብሪካዎች በማገልገል ላይ የነበሩ አራት ሠራተኞች በሥራ ላይ እያሉ መገደላቸውን ተከትሎ ፋብሪካው ሥራ ለማቆም ተገዷል::
በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች መሀል በተደረገ የእርስ በርስ ግጭት በደረሰ ጥቃት የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉም ተረጋግጧል:: እነዚህ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በፋብሪካዎቹ ሠራተኞች ላይ የሚፈጽሙት ግድያ ጥቃት እየጨመረ መጥቶ ሠሞኑን የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ ሾፌርን ጨምሮ በሸንኮራ ማሳ ላይ የተሰማሩ በርካታ ወዛደሮች ለሞትና ለጉዳት መዳረጋቸውን ከደረሰን ዜና መረዳት ችለናል::
የአካባቢው አርብቶ አደሮች እርስ በርስ መጋጨታቸው የሁከቱ ዋነኛ መነሾ ነው የተባለ ሲሆን በፋብሪካው ለሚሠሩ ሠራተኞች ምግብ የሚመጣው ከጂንካ ከተማ ቢሆንም በተፈጠረው አለመረጋጋት የተነሳ የምግብ አቅርቦቱ ተቋርጧል:: ይህን ተከትሎም በርካታ ሠራተኞች ሥራቸውን ለቀዋል::
እስካሁን ድረስ አስር የፋብሪካው ሠራተኞች እንደተገደሉ የሚጠቁሙት የዜና ምንጮቻችን ወደ አካባቢው መከላከያ ገብቶ ለማረጋጋት እየሞከረ ቢሆንም የክልሉ ተወላጅ የሆኑ ሦስት ሠራተኞችና አንድ የማኅበሩ ጥበቃ ሠራተኛ በሥራ ላይ መገደላቸው ቀሪውን የስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች ከባድ የደሕንነት ስጋት ላይ ጥሏል::