ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የማን ተወካዮች ናቸው? || ታምሩ ገዳ

ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የማን ተወካዮች ናቸው? || ታምሩ ገዳ

በመካከለኛ ምስራቅ አገር ኳታር እ.ኤ.አ ከመስከረም 27 እስከ ጥቅምት 6 2019 የተካሄደው 17ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር አስገራሚ እና አሳዛኝ ክስተቶችን አስተናግዷል።

በመናገሻ ከተማዋ፣ ዶሃ፣ በሚገኘው የካሊፋ አለማቀፍ ስታዲዮም ሰሞኑን በተካሄዱት የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ አትሌቶች አደገኛው ሙቀትን በመቋቋም እና ተፎካካሪዎቻቸውን በማንበርክክ ለአገራቸው እና ለራሳቸው 5 የተለያዩ ሜዳሊያዎችን በማምጣት በሰንጠረዥ ደረጃ ኢትዮጵያን በአለም ለ8ኛ በአፍሪካ ደግሞ ለ2ኛ ደረጃ በማብቃት አትሌቶቹ ደስታቸውን በጋራ ሲቋደሱ፣ በስፍራው የተገኙ አንዳንድ ደጋፊዎች ግን የአትሌቶቹ ጥንካሬን፣ አይበገሬነትን፣ ድል አድራጊነትን ከማወደስ፣ ኢትዮጵያዊነትን ከማጀገን በዘመን አመጣሽ የጎጥ ፓለቲካ ውስጥ ተጠምደው በነገር ሲጎነታተሉ እንደነበር ተስተውሏል።

ዜና አገልግሎት አሶሴትድ ፕሬስ (AP) ከስፍራው እንደ ዘገበው ባለፈው መስከረም 30,2019 በተካሄደው የወንዶች 5000 ሜትር ውድድር ላይ አትሌቶቹ የቡድን እና የተናጥል ታክቲክን ተጠቅመው ድል ሲቀዳጁ ደስታቸውን በህብረት ሲያሳዩ በቦታው ተቧድነው የታደሙት የተወሰኑ ኢትዮጵያውያኖች ግን በኢሕአዲግ የጸደቀው እና በስራ ላይ ያለው የወቅቱ ሰንደቅ አላማን ጨምሮ በቀኃስ እና በደርግ ዘመኖች የነበሩት ሰንደቆችን በማካተት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችም የኦነግ አርማን በማውለብለብ፣ አንዱ ከሌላኛው በልጦ ለመታየት የሌላኛውን ቡድንን ድምጽን ለመቅበር እና ለመድፈቅ ስታዲዮምን በከፍተኛ ጩኸት አናውጠውት እንደነበር፣ በአንድ ወቅትም የኳታር የጸጥታ አስከባሪዎች ጣልቃ በመግባት ደጋፊዎቹን አደብ እንዲገዙ እና ከጸብ እንዲታቀቡ ማድረጋቸውን በስፍራው የተገኘው ዘጋቢው ትዝብቱን አስፍሯል።

ከተስተዋሉት አሳዛኝ ክስተቶች መካከል የወንዶቹ የአምስት ሺህ ሜትር ውድድር ላይ በበርካቶች ዘንድ ያሸንፋሉ ተብሎ ቅድመ ግምት ተተሰጣቷቸው የነበሩት የአሜሪካ፣ የካናዳ እና የኖርዌይ አትሌቶችን የቡድን እና የግል ጥበብን በመጠቀም ከአትሌት ሰሎሞን በርጋ እና ጥላሁን በቀለ ጋር በመሆን አትሌት ሙክታር እድሪስ ሻምፒዮናነቱን ዳግም ባሰከበረበት ወቅት በስታዲዮሙ ውስጥ ቀድመው የነበሩ ደጋፊዎች መካከል የተወረወረለትን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (የኦነግ) አርማን አንስቶ እንደለበሰው በሁዋላ ግን አትሌቱ ከጋዜጠኞች ፊት ሲቀርብ የወቅቱን ሰንደቅ አላማን እንደለበሰ ተስተውሏል።

እዚህ ላይ በዘንድሮው በብሔራዊ ውድድሮች ደረጃ አስራ ሰባተኛ ላይ የሚገኘው ዶሃ፣ ኳታር፣ ላይ የቡድን ታክቲክ እና እድል ታሪክ እንዲሰራ የረዱት አትሌት ሙክታር እድሪስ በስፍራው ለነበሩት የኦነግ ደጋፊውች ፍላጎታቸውን እንዳሳካላቸው አድርገው የገመቱት አልጠፉም።

ይሁን እና ከድል በሁዋላ ለአፍታ ለብሶት ስለነበረው የኦነግ አርማ ጉዳይ ለአትሌት ሙክታር በአትሌቶች ተወካይ እና አስተርጓሚ በኩል ለቀረበለት ጥያቄ ተወካዩ” ማንኛቸውም አትሌቶች የሚወክሉት አገራቸውን እንጂ የማንም የፖለቲካ ፓርቲን አላማን አይደለም” በማለት ቁርጥ ያለ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

በውድድሩ ኢትዮጵያዊቷ ለተሰንበት ግደይን በማስከተል የሴቶች የ10ሺህ ሜትር ሻምፒዮን የሆነችው በትውልድ ኢትዮጲያዊት በዜግነት ሆላንዳዊት የሆነችው ሲፋን ሀሰን የወርቅ ሜዳሊያዋን ስታጠልቅ በአንዳንድ ደጋፊዎች መካከል የዘር ጉዳይ ወይስ የዜግነት ስሜት ይቅደም የሚለው ልዩነት ጎልቶ መታየቱ ተስተውሏል።

ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ አሁን ድረስ መቋጫ ያልተገኘለት የእግር ኳስ ውድድሮችን ለማስረዝ፣ በርካታ ደጋፊዎችን ለጉዳት እና አንገት ለመድፋት እንዲሁም ክለቦችን ለኪሳራ የዳረገው የአንዳንድ የ እውነተኛ የስፖርት አላማ እና የ ደጋፊነት ትርጉም ያልገባቸው ስሜታዊ እና ጭፍን የፖለቲካ ደጋፊዎች የብስ እና ባሕርን አቋርጠው ከኳታር የ አትሌቲክስ ውድድር ላይ ከፍተኛውን ሙቀት በመቋቋም ለአገራቸው እና ለህዝባቸው ሜዳሊያ ያመጡ አትሌቶችን ለፖለቲካ አላማ ማሳኪያነት ለማድረግ መሞከሩ ብዙዎችን አሳዝኗል።

ጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ (አቤ) አኤእ መስከረም 10,1960 በጣሊያን፣ ሮም በተካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር ላይ በባዶ እግሩ ሮጦ የወርቅ ሜዳሊያ ሲያጠልቅ የመጀመሪያው አፍሪካዊ እና ኢትዮጵያዊ የማራቶን ጀግና ተባለ እንጂ የግርማዊነታቸው ወታደር አልተባለም ወይም የዘር ሀረጉን ወክሎ አልሮጠም።

ሩሲያ እኤአ 1980 አስተናግዳው በነበረው የሞስኮ የኦሎምፒክ ውድድር ላይ ከአገሩ ልጅ ከመሀመድ ከድር ጋር ተፎካካሪዎቹን ጉድ በመስራት የ5000 እና የ 10,000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አጥላቂ የሆነው (ማርሽ ቀያሪው) ሻምበል ምሩጽ ይፍጠር በወቅቱ የሮጠው ለደርግ መንግስት ወይም ትግራዊነትን ለማጀገን ሳይሆን በረሃብ፣ በበሽታ እና በጦርነት የምትታወቀው የኢትዮጵያ እና የህዝብ ስምን በአለም መድረክ ላይ በመልካም ገጽታ ለማስጠራት ነበር።

ዜሬም ካሉን እጅግ ድንቅ እና አይበገሬ አትሌቶቻችን መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነው የ5000 እና 10,000ሜትሮች የአለም ሪኮርድ ባለቤቱ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ (ቀነኒ ኬኛ) ሰሞኑን በጀርመን በርልን ላይ በተካሄደው የ ቢ ኤም ደብሊው (BMW) የማራቶን ውድድር ላይ የአለምን ሪኮርድን ወደ ቤቱ ዳግም ለማምጣት ሁለት ሴኮንዶች እንደቀሩት አለም በመገረም ዘግቦለታል። አትሌት ቀነኒሳም ቢሆን ይህንን አስገራሚ ውጤትን ያስመዘገበው የማንንም ብሔር፣ እቁብ እድር ወይም የወቅቱ የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ኢሕአዲግን ለማስደሰት ሳይሆን ኢትዮጵያ እና ህዝቦቿን ወክሎ ለመሆኑ አሌ አይባልም።

እዚህ ላይ የሴቶች ቁንጮ አትሌቶቻችን ከሆኑት መካከል እነ ፋጡማ ሮባ ፣ፍልቅልቋ ደራርቱ ቱሉ፣ አይበገሬዋ መሰረት ደፋር፣ ጌጤ ዋሚ፣ጥሩነሽ ዲባባ እና እህቶቿን ፣ወርቅ ነሽ ኪዳኔ ፣መሰለች መልካሙን እና መሰል አትሌቶችን ሰለኢትዮጵያ እና ልጆቿ የከፈሉትን የዜግነት ውለታን ለአፍታም አንዘንጋውም።

እውነተኛ የስፓርት አፍቃሪ እና ደጋፊ የተጨዋቾች እና የተወዳዳሪዎች ምስሎችን፣ ስሞችን የያዙ ፖስተሮችን በመያዝ፣ ቲሸርታቸውን በምስል አድርጎ በመልበስ አድናቆትን ይገልጻል፣ ድል ሲያደርጉ ይፈነድቃል፣ ሲሸነፉም አብሮ ያዝናል እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እንደምናየው እና እንደምንሰማው “እነ እገሌ ይህንን ካደረጉ እኔም ይህንን ማድረግ አለብኝ” ብሎ ለጸብ እና ለፍጥጫ ወደ ስታዲዮም አይጎርፍም፣ እራስን ለአደጋ አገርንም ለትዝብት አይዳርግም።

LEAVE A REPLY