”ስሙን አልነግራችሁም። ታውቁታላችሁ።” አለን አቶ ሽመልስ የቤተመንግስት ጉብኝቱን እየመራ መሀል ላይ። በቤተመንግስቱ እየተደረገ ያለውን እድሳት ያስጎበኘውን አንድ በስም ያልነገረንን የኦሮሞ ታዋቂ ሰው አጋጣሚ እያጫወተን ነው። ያ ታዋቂ ሰው ማን እንደሆነ አቶ ሽመልስ ፍንጭ እንኳን ሊሰጠን አልፈለገም። በደፈናው ስለአጋጣሚው አወጋን። ታዋቂው የኦሮሞ ሰው ስለአጼ ሚኒሊክ የሰማው ጥሩ አልነበረም። ከልጅነቱ ጀምሮ እየሰማ ያደገው ስለአጼ ሚኒሊክ ጭራቅነት፡ በኦሮሞ ህዝብ ላይ አደረሱ እየተባለ ስለሚነገረው መጥፎ ታሪክ ነበር። ለዚያ የኦሮሞ ልጅ አጼ ሚኒሊክ የኦሮሞ ጠላት ናቸው። ከዚያ ያለፈ ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም።
አቶ ሽመልስ ማስጎበኘቱን አቁሞ ስለታዋቂው የኦሮሞ ሰው አጋጣሚ ወጉን ቀጠለ። ”እናም ይሄን ሰው እዚህ ሚኒሊክ ቤተመንግስት አመጣነውና ስለአጼ ሚኒሊክ የተጻፈውን፡ የተሳለውን፡ በቁም የሚገኙትን የታሪክ ምስክርነቶችን አንድ በአንድ አስጎበኘነው። አጼ ሚኒሊክ ዘመን ተሻጋሪ፡ ባለራዕይ መሪ እንደነበሩ የሚያሳዩ የመጀመሪያ ደረጃ የታሪክ አብነቶችን አዟዙረን አሳየነው። በጣም ተደነቀ። መናገር እስኪያቅተው ተደመመ። ስለአጼሚኒሊክ የሚወራና እየሰማ ያደገው በአንድ ጊዜ መናኛ ትርክት መሆኑ ተገለጸለት። ጉብኝቱን ከጨረሰ በኋላ ምን አለ መሰላችሁ?” አቶ ሽመልስ ጥያቄውን ስንዝሮ በጉጉት አስጠበቀን። ፈገግ አለና ”ለእኚህ ታላቅ መሪማ ስንኝ ቋጥሬ እዘፍንላቸዋለሁ።” የአቶ ሽመልስ ረዘም ያለ ፈገግታ ተከተለ።
የኢሳት የልዑካን ቡድን አባላት በሰማነው አጋጣሚ ተደመምን። እርስ በእርስ እየተያየን ያ ታውቂው የኦሮሞ ሰውን ማንነት በአእምሮ ጓዳችን ማሰስ ጀመርን። ቢያንስ ድምጻዊ መሆኑን የሚያመለክት ፍንጭ ከአቶ ሽመልስ ብናገኝም በትክክል ማን እንደሆነ ሳይነግረን ወደሌላ የጉብኝት ምዕራፍ ይዞን ሄደ። እስከአሁንም ማን እንደሆነ ከግምት ያለፈ አላወቅንም። ይህንኑ አጋጣሚ ጠ/ሚር አብይ አህመድም በጉብኝቱ ወቅት ደገሙልን። እሳቸውም ስለእዚያ በአጼሚኒሊክ ታሪክ ስለተደመመው የኦሮሞ ታዋቂ ሰው ማንነት ፍንጭ ሳይሰጡ በደፈናው አጋጣሚውን ነገሩን።
በቤተመንግስት ጉብኝት ወቅት በአቶ ሽመልስ አብዲሳ ሰፊ ገለጻ የተደረገልን አጋጥሚንም መቼም አልረሳውም። አቶ ሽመልስ የኢትዮጵያን ታሪክ የተረዳበት መንገድ ከአብዛኛው ጽንፈኛ የኦሮሞ ብሄርተኛ አንጻር የሚገናኝ አይደለም። የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና እንደነበረው፡ ስለኢትዮጵያ ከማንም ያላነሰ ዋጋ መክፈሉን፡ ይህ ታሪክ ግን ከራሱ ከኦሮሞ አብራክ በወጡ ልጆቹ በተጣመመና በተወላገደ መልኩ እንዲነገር መደረጉን በቁጭት ሲያነሳ በተመስጦ አዳምጠው ነበር። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ነግሰው የነበሩ የኦሮሞ ጀግኖችን እንደከሃዲ የሚቆጥር ትውልድ መፈጠሩንም ጠቅሶ አሁን ትግላችን ይህን አመለካከት መስበር ነው አለን አቶ ሽመልስ። የምንኮራበትን ታሪክ እንድናፍርበት መደረጉ፡ ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ውስጥ ሚናችን የገዘፈውን ያህል ምንም እንዳልሰራን፡ በተቃራኒው የተበዳይ ታሪክ ተለጥፎልን እንድንሸማቀቅ መደረጉ ለኦሮሞ ህዝብ ትልቅ ጉዳት ነው በማለት አቶ ሽመልስ ሲናገር በዓይኖቹ ውስጥ የሚረጨውን የቁጭት ስሜት ያነበብኩ መሰለኝ። በወቅቱ ልቤን ነክቶታል። የእኔን ብቻ ሳይሆን የባልደረቦቼንም ቀልብ የገዛ ንግግር ነበር።
አቶ ሽመልስ ንግግሩን ያበቃው ”ይህ እንዲህ ሆኖ አይቀርም። የኦሮሞ ህዝብ የፈጸመው ተጋድሎ በጥቂቶች የተዛባ ትርክት ዋጋው ረክሶ የሚቀር አይሆንም። ይቀየራል። ለዚህም ኦዲፒ እየሰራበት ነው። የጎበና ማዕከል በሚል የሚቋቋመው ተቋም የኦሮሞን ህዝብ ገድል የሚያድስና ለአዲሱ ትውልድ የሚያስረክብ ይሆናል።” መሳጭ አቀራረብ ነበር። ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጀግና ራስ ጎበና በኦሮሞ ጽንፈኞች ከሃዲ ተደርገው ለዘመናት የተቀረጹበትን ታሪክ ለመቀየር ኦዲፒ ቆርጦ የተነሳ ነበር የሚመስለው። እነአብዲሳ አጋ፡ ጄነራል ጃጋማ ኬሎ፡ ራስ አበበ አረጋይን ጨምሮ አያሌ የኦሮሞ ስመጥር ጀግኖች አንጸባራቂ ገድላቸው በጥቂት የኦነግ ደቀመዘሙራንና የህወሀትን በምሽግ ውስጥ በተጻፈ ታሪክ ተግተው ባደጉ ዲጂታል ትውልድ ምክንያት ረክሶ እንዳይቀር የለውጡ አመራር በሰፊው እንደሚሰራ አቶ ሽመልስ አረጋገጠልን። እውነት ለመናገር ለሽመልስ የነበረኝ አመለካከት እዚያው ፍርክስክሱ ሲወጣ ተሰማኝ። ከዲጂታል ትውልድ አንዱ አድርጌ የመደብኩት፡ በዘረኝነት አስተሳሰብ የተጠቃ አድርጌ የደመደምኩት ሽመልስ አብዲሳ ሌላ ሰው እስኪመስለኝ ተደመምኩበት። ይህን ሀሳቤን ሌሎችም ባልደረቦቼ እንደተጋሩት አጫወቱኝ። አንዳችንም የአቶ ሽመልስ አስደማሚ ንግግር የቃላት ካራቴ ነው ብለን ለመጠርጠር አልፈለግንም።
አቶ ሽመልስ ከህወሀት አመራሮች ጋር የተደረገውን ትንቅንቅ እንዴት እንደነበረ የነገረን ታሪክ በራሱ ልብ ሰቃይ ነው። ኦህዴድና ብአዴን ኢትዮጵያዊነትን ይዘው ህወሀትን በዝረራ የጣሉበት የብስለት አካሄድም ለአቶ ሽመልስ ነጥብ እንደሰጠው አድርጎኛል። በኦህዴድ ውስጥ የዶ/ር አብይና የአቶ ለማ ጥምረት የሰመረው በእነሽመልስ ዓይነቱ ሰፊ አስተሳሰብና ከዘረኝነት የጸዳ አመለካከት ባለው የኦህዴድ አመራር ድጋፍ ነው የሚል ድምዳሜ ለመስጠት ከቤመንግስት ቅጥር ግቢ እስከወጣ እንኳን አልጠበኩም።
ከሰባት ወራት በኋላ አቶ ሽመልስ አብዲሳ በመስቀል አደባባይ የተናገረውን ስሰማ የቤመንግስቱ ሽመልስ ፊቴ ላይ ድቅን አለብኝ። ከሰፊው አስተሳሰብ፡ ዘመናዊ ከሆነው አመለካከት በዚህ ፍጥነት ወደ ጠባቧ የጎጥ መንደር መግባት አይከብድም ወይ? ኦቦ ሽመልስን ምን ነካው? ያን የመሰለ ልብ የሚያሞቅ አቋም የነበረው ሽመልስ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የመሪነት ወንበር ላይ ሲቀመጥ ምን እንዲህ ለወጠው? ከወንበሩ ወይስ ከሰውዬው? የቤመንግስቱ ሽመልስ ገጸባህሪ ነበር ማለት ነው? የሰማነው የመድረክ ላይ ተውኔት ነበርን? አቶ ሽመልስ በጽንፈኛ የኦሮሞ ብሄርተኞች ተሸነፈ ወይስ የምርጫ ስትራቴጂ ይሆን? የትኛውንም ሀሳብና አመለካከት የማራመድ ውሳኔ የግለሰቡ ቢሆንም ሁለት ጫፍና ጫፍ የረገጡ ተቃራኒ አመለካከቶች በአንድ ግለሰብ ሲቀነቀኑ ግን የጤና አይመስለኝም።