የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም

እስክንድር ነጋ  “እሁድ መስቀል አደባባይ ከፊት ቆመን የሚመጣውን ነገር  እንጋፈጣለን”  አለ

እሁድ ጥቅምት 2 ቀን በአዲስ አበባ ከተማ የተጠራው ሰልፍ ላይ አዲስ አበቤ በነቂስ በመውጣት ድምጹን እንዲያሰማ የባለአደራው ሊቀ መንበር እስክንድር ነጋ መልዕክት አስተላለፈ::

ዛሬ ምክር ቤቱ ጉዳዮን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰልፉ ሕጋዊ ዕውቅና ያለው መሆኑን በመግለጽ የከተማው መስተዳድርም ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው ሰልፉ ስለመከልከሉ ወይም ዕውቅና እንደሌለው የሚገልጽ አንዳችም ይፋዊ መግለጫ እንዳልሰጠም አስታውቋል::

ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ጥያቄ ቀርቦ በ24 ሰዓት ውስጥ የመከልከያ ምላሽ ካልተሰጠ ሰልፉ እንደተፈቀደ ሕጉ ይደነግጋል ያለው እስክንድር ነጋ እኛም ይህንን ሕገ መንግሥታዊ መብታችንን እንጠቀማለን ካለ በኋላ ቀደም ሲል በባልደራስ ምሥረታና ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ መንግሥት እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ ምንም ምላሽ ሳይሰጥ ቆይቶ በዕለቱ ግን በቂ የፖሊስ ኃይል በመመደብ ጥበቃ መደረጉን አስታውሷል::

በዕለቱ ሰልፉ በመንግሥት ካልተከለከለ መስቀል አደባባይ ከማንም ቀድመን  የምንገኘው ከፊት ለፊት በመሆንም የሚመጣውን ነገር ሁሉ በቀዳሚነት የምንጋፈጠው የባለአደራው ም/ቤት አባላት እንደሆንን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ በማለት የተናገረው ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ እስክንድር ነጋ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ነበርንበት የለውጥ ተስፋ ዳግም እንድንመለስ በይፋ ከሕዝብ ጋር ሆነን ጥያቄያችንን እናቀርባለን ማለቱን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የታደመው የኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባ ሪፖርተር አድርሶናል::

ቄሮ የባላደራውን ጋዜጣዊ መግለጫ ለማስተጓጎል ያደረገው ሙከራ በአ/አ ልጆች ከሸፈ

የተደራጁ እና ሕጋዊ ጥበቃና ከለላ ከአዲስ አበባ ፖሊስ እና ከበላይ አካላት የተሰጣቸው ቄሮዎች የባለአደራው ም/ቤት እሁድ በመስቀል አደባባይ ስለሚካሄደው ሕጋዊ ሰላማዊ ሠልፍ ዛሬ ሊሰጥ የነበረውን ጋዜጣዊ መግለጫ ለመረበሽ ያደረጉት ሙከራ ከሸፈ::

ከወራት በፊት በአማራ እና ኦሮሚያ ክልልሎች በጅምላ የታሰሩ ወጣቶችን እንዲሁም በግፍ ለዕስር የተዳረጉትን የባላአደራው ም/ቤት አባላት እና ጋዜጠኞች ጉዳይ አስመልክቶ ሊሰጥ የነበረውን ጋዜጣዊ መግለጫ ጋጥወጥነት በተላበሰ ድርጊት ያስተጓጎሉት ቄሮዎች ዛሬም ያንን አሳፋሪ ተግባር ለመድገም ፈልገው ነበር::

ይሁንና አዲስ አበቤ እየተገፋ በረቀቀ ስልት ከተማዋን በኦሮሞ ማኅበረሰብ ለመውረር የሚደረገውን የጽንፈኝነት ሴራ በመረዳት በተለይም ከቅርብ ቀናት ወዲህ ከፍተኛ ድጋፉን ለባለአደራው ሲሰጥ የታየው የሸገር ወጣት  ከየሰፈሩ በመሰባሰብ የታከለ ኡማና የጃዋር መሐመድ መልዕክተኛ ናቸው የተባሉት ወጣቶችን ምንም ሳይፈጥሩ በባዶ ጩኸት እንዲመለሱ አድርጓል::

ከጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከፍ ብሎ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መ/ቤት ፊት ለፊት የሚገኘው የባላደራው ም/ቤት ጽ/ቤት ስንደርስ የአዲስ አበባ ወጣቶች በቅንጅት አካባቢውንና ጽ/ቤቱን በንቃት ሲጠባበቁ አግኝተናቸዋል::የነበረውን ከፍተኛ ፍተሻ በማለፍ ጋዜጣዊ መግለጫው የሚሰጥበት አዳራሽ እስክንገባ ድረስም የተለያዮ ሆቴሎች ፣ ናይት ክለቦች እና ኮንሰርቶች ላይ የሴኩሪቲ አገልግሎት በሚሰጡ ብዛት ያላቸው ጋርዶች ታጅበን ነው::

ወደ ጋዜጣዊ መግለጫው የተጓዙና ያለፈው ችግር ይደገም ይሆን እያሉ ስጋት ውስጥ የወደቁ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎች ደጅ አካባቢ የነበረውን ጤናማ ያልሆነ ሂደት አልፈው ሥራቸውን በአግባቡ እንዲሠሩ አስተማማኝ ማረጋገጫ ለሰጧቸው የአዲስ አበባ ወጣቶች ከፍተኛ የሆነ ምስጋና ሲያቀርቡ ተመልክተናል::

በመንግሥት መኪናዎች እየመጡ በአካባቢው እንዲሰፍሩ የተደረጉት ቄሮዎች ሲቪል ልብስ ከለበሱ ፖሊሶች ጋር መረጃ ሲለዋወጡ እና አንዳንድ ምክክሮችን ሲያደርጉ የኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር በግልጽ ተመልክቷል:: ለረብሻ የተላኩት ቄሮዎችን እንቅስቃሴ በመታዘብ በ15 ሜትር ርቀት ላይ ለሚገኙት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ሪፖርት ቢያደርጉም ምንም ዓይነት ትብብር ሊደረግላቸው ባለመቻሉ የሸገር ልጆች ሙሉ ጥበቃውን በራሳቸው መንገድ ተወጥተውታል::

ጋዜጣዊ መግለጫው ከተጀመረ በኋላ ለማቋረጥ እና ለመበጥበጥ አቅደው የነበሩት ቄሮዎች በብዛት የተደራጁት ወጣቶች ሁኔታ ስላስፈራቸው በቅርብ ርቀት ሆነው “ፊንፊኔ ኬኛ” እያሉ በመጮህ ጊዜያቸውን በከንቱ አቃጥለው ተመልሰዋል:: እነዚህ ጸብ ለመጫር የመጡት ቄሮዎች “የአዲስ አበባ ሕዝብ ሌባ” የአዲስ አበባ ወጣት ዱርዬ ” እያሉ ሲጮሁ ሙሉ ለሙሉ ሲያዳምጡ የነበሩት የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ሕገ ወጥ የነበሩትን ቄሮዎች ከማባረር ይልቅ ትክክል ናችሁ በሚል ስሜት በፈገግታ ተውጠው ሲያዩዋቸው ነበር::

እነዚህ ፖሊሶች ጋዜጣዊ መግለጫው ተጠናቆ እስክንድር ነጋ ድጋፍ ያደረጉለትን ወጣቶች በሚያመሰግንበት ወቅት   ወጣቶቹ “አዲስ አበባ ቤቴ” እያሉ ሲጨፍሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የታጠቁ ፖሊሶች ከፖሊስ ኮሚሽኑ ግቢ በመውጣት “መጮህ አይቻልም” በሚል የአዲስ አበባ ወጣቶችን ከበው ለመደብደብ ሙከራ አድርገዋል: : የቄሮዎቹን እንቅስቃሴ ያከሸፉና ጥበቃውን ሲያስተባብሩ የነበሩ ጥቂት ወጣቶችንም እንፈልጋቸዋለን በማለት ወስደው ለማሰር ሞክረው ነበር::

የአዲስ አበባ ልጆች በተደራጀ ሁኔታ እንዲሁም ጨዋነት ሥነ ምግባር ከጬኸት ውጪ ምንም ሳይፈጥሩ በሀፍረት እንዲመለሱ ማድረጋቸው በእጅጉ ያበሳጫቸው በርከት ያሉ የኦሮሚያ ተወላጅ የሆኑ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት የአዲስ አበባ ወጣቶች ኅብረትና አንድነት በመሸርሸር ከበታተኑ በኋላ ለመደብደብ ሲቁነጠነጡ የኢትዮጵያ ነገ  ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ ታዝቧል::

ተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ ዑመር እንድሪስ ከጠ/ሚ /ሩ ሽልማት ሌሎች የሀገሪቱ ባለሥልጣናት እንዲማሩ መከሩ

የጠ/ሚ/ር ዐቢይ ሽልማት በተለያየ ደረጃ ያሉ የሀገሪቱ መሪዎች ለሰላም ቁርጠኛ ስራ መስራት እንዳለባቸው ያመለከተ ነው ሲሉ ሐጂ ሙፍቱ ኡመር እድሪስ ተናገሩ::ተቀዳሚ ሙፍቲ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጅ ኡመር ኢድርስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት በማግኘታቸው የእንኳን ደስ አልዎት መልዕክትምአስተላልፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የሰሯቸዉ ስራዎች ከዚህም በላይ ሊያስመሰግኗቸውና ሊያሸልሟቸው የሚችሉ በመሆናቸው ኮርተንባቸዋል ያሉት የሃይማኖት አባት ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልቅ ሽልማት የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ መሆን ነው ያሉት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጅ ኡመር በዚህም መላዉ የኢትየጵያ ህዝብ ደስ ሊለው ይገባል ብለዋል::

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጅ ኡመር ኢድሪስ መልካም ተግባር መስራት ምን ያህል አስፈላጊና ተጽእኖ መፈጥር እንደሚችል ማሳያ መሆኑን ጠቁመው ፤ ሽልማቱ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉ ለሰላም ለሚሰሩ በተለይም ለአፍሪካ መሪዎች ትልቅ መልእክት የሚያተላልፍ እንደሆነም አስታውቀዋል::

በየትኛውም ደረጃ በመሪነት ላይ ያሉ የሀገራችን መሪዎች ለሰላም ቁርጠኛ ሥራ መስራት እንዳለባቸው ሽልማቱ ያመላክታል  ያሉት ተቀዳሚ ሐጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኖቬል የሰላም ሽልማት አሸናፊ በመሆናቸዉም በእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት እና በመላዉ ህዝበ ሙስሊም ስም እንኳን ደስ አለዎት ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል::

የኖቤል የሠላም አሸናፊ የሆኑት ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ 900 ሺኅ ዶላር ይሸለማሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የ2019 የኖቤል የሠላም ሽልማት አሸናፊ ሆኑ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለዚህ ሽልማት የበቁት ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በአገሪቱ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት መውሰድ በጀመሯቸው እርምጃዎችና በተለይ ከኤርትራ ጋር ሠላም ለማውረድ ባደረጉት ጥረት ነው ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኖቤል ሰላም ሽልማት 100ኛው አሸናፊ በሆኑበት በዘንድሮው ውድድር የአየር ለውጥ መብት ተሟጋች የሆነችው ስዊድናዊቷ የ16 ዓመት ታዳጊ ግሬታ ተንበርግ ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው መካከል አንዷ ነበረች።

የኖቤል የሰላም ሽልማትን የሚያሸንፉ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች 900 ሺ ዶላር የሚሰጣቸው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመጪው ታህሳስ ወር በኦስሎ ሽልማታቸውን እንደሚወስዱ ታውቋል:: በአጠቃላይ 301 እጩዎች ለዚህ ታላቅ ክብር ከታጩት መካከል 223 ግለሰቦችና 78 ድርጅቶች ይገኙበታል::

የኖቤል ሽልማት በየዓመቱ በፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ሕክምና፣ ሥነጽሑፍና ሰላም ዘርፎች በየዓመቱ ይሰጣል። ሽልማቱ የሚሰጠው ባለፉት 12 ወራት “ለሰው ልጅ የበለጠ አበርክቶ” የሚያደርጉ ነገሮችን ላከናወኑ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ነው። ኖቤል የሚለው ስያሜ የተወሰደው ከሲውዲናዊ ነጋዴ እና የድማሚት ፈጣሪ አልፍሬድ ኖቤል ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ሽልማቱ መሰጠት የጀመረው እኤአ በ1901 ግለሰቡ በለገሰው ገንዘብ ነው ።ናቸው።

የኖቤል የሠላም ሽልማት እጩ እና አሸናፊ የሆኑት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ከአጼ ኃይለሥላሴ ቀጥሎ ለሽልማቱ በመታጨት ሁለተኛው የኢትዮጵያ መሪ ሆነዋል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐብይ ዘንድሮ ለሽልማቱ በመታጨት ከቀረቡት ተፎካካሪዎች መካከል ለአሸናፊነት ተስፋ አላቸው ተብሎ ከሚጠበቁት ጥቂት እጩዎች አንዱ እንደሆኑ ሰሞኑን በስፋት ሲነገር ነበር።

ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለኖቤል ሽልማት ታጭተው የነበሩት ከዛሬ 80 ዓመት በፊት እንደ አውሮፓዊያኑ በ1938 እንደነበር የሽልማት ድርጅቱ መረጃ ያመለክታል።  ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በኖቤል የሠላም ሽልማት ታሪክ ውስጥ በዕጩነት ከቀረቡ ስድስት ንጉሣዊያን መካከል አንዱ ሲሆኑ፤ ከእርሳቸው ቀደም ብለው የሩሲያው ንጉሥ ዳግማዊ ኒኮላስ፣ የስዊዲኑ ልዑል ካርልና የቤልጂየሙ ንጉሥ ቀዳማዊ አልበርት ታጭተው የነበሩ ሲሆን ከእሳቸው በኋላ ደግሞ የግሪኩ ንጉሥ ቀዳማዊ ፖልና የኔዘርላንድስ ልዕልት ዊልሄልሚና ታጭተው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕጬ የሆኑበት የዚህ ውድድር አሸናፊ ዛሬ አርብ ኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ ውስጥ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ላይ ይፋ ተደርጓል:: የሌሎቹ የኖቤል ሽልማቶች የሚሰጡት ስዊዲን ስቶክሆልም ውስጥ ነው።

በዚህ ዓመት በተለያዩ የኖቤል ሽልማት በእያንዳንዱ ዘርፍ አሸናፊ የሚሆኑ ግለሰቦች ዘጠኝ ሚሊዮን የስዊዲን ክሮነር ወይም ከ900 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ የገንዘብ ሽልማት ይበረከትላቸዋል። በተለያዩ መስኮች ፍር ቀዳጅ ተግባራትን ያከናወኑ ግለሰቦችንን ተቋማት በየዓመቱ የሚሸለሙበት የኖቤል ሽልማት በዓለማችን ከሚሰጡ ዕውቅናዎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

አልፍሬድ ኖቤል ኅዳር 18/1888 ዓ.ም በፈረመው ኑዛዜ ያለውን አብዛኛውን ሃብቱን የኖቤል ሽልማት ተብለው ለሚሰጡ ሽልማቶች እንዲውል ተናዟል። በኑዛዜው ላይ እንደተገለጸው ከዚህም መካከል አንዱ የሠላም ሽልማት ሲሆን፤ ሽልማቱም “በመንግሥታት መካከል ወንድማማችነት እንዲሰፍን አብዝተው ወይም የተሻለ ሥራን ላከናወኑ፣ የጦር ሠራዊቶች ቅነሳና ለሠላም መስፋፋት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ይሰጥ” ይላል።

ከአውሮፓዊያኑ 1901 ጀምሮ 99 የኖቤል የሠላም ሽልማቶች ተበርክተዋል። ሽልማቱ ከተጀመረ በኋላ ሁለቱ የዓለምጦርነቶች በተካሄዱባቸው ዓመታትና በሌሎችም ምክንያቶች ለ19 ጊዜያት ሳይሰጥ ቀርቷል።የኖቤል የሽልማት ድርጅት እንደሚለው በመጀመሪያውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ወቅት ጥቂት የሠላም ሽልማቶች የተሰጡ ሲሆን በሌላ ጊዜ ደግሞ በእጩነት የቀረቡት ተቋማትም ሆነ ግለሰቦች ለሽልማቱ የሚጠበቀውን ያህል አስተዋጽኦቸው የጎላ ነው ተብሎ ካልታሰበ ነው ፤ በዚህም የሽልማቱ ገንዘብ በድርጅቱ እጅ ስር እንዲቆይ ይደረጋል።

400 የኦጋዴን ንቅናቄ ታጋዮች የተካተቱበት ከ3ሺኅ በላይ ፖሊሶችን ሙስጠፌ መሐመድ አስመረቁ

ለውጡን በአግባቡ የተጠቀመበት የሶማሌ ክልል በጅግጅጋ የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ ያሰለጠናቸውን ከ3ሺህ በላይ ፖሊሶችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል::

ቁርጠኛውና ብልሁ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ ሙሀመድአዲስ ተመራቂ ፖሊሶችየህግ የበላይነት እና የዜጎችን ሰባዓዊ መብት በማስጠበቅ ረገድ ከፍኛ ሚና እንደሚጠበቅባቸው በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የኮሚዩኒቲ ፖሊስ አገልግሎት ስልጠናዎችን ተመራቂዎቹ መውሰዳቸውንም ገልጸዋል፡፡

ከተመራቂ ፖሊሶቹ መካከል 400 ያህሉ የኦጋዴን ብሄራዊ ንቅናቄ ግንባር አባላት የነበሩ  እንደደሚገኙበትም የሶማሌ ክልል ሬዲዮና ቴልቪዥን ይፋ ካደረገው መግለጫ ሰምተናል::

የአ/አ ከተማ  አስተዳደር በያዝነው ዓመት 500 ሺኅ ቤቶችን እገነባለሁ አለ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በያዝነው ዓመት በመሃል ከተማ የ500 ሺ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ በተለያዩ አማራጮች ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ:: የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ በከተማዋ አዲስ በሚጀመሩ ቤቶች ግንባታ ዙሪያ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥቷል።

የቢሮው ሓላፊ ኢንጂነር ሰናይት ዳምጠው ፣ የከተማ አስተዳደሩ በ2012 ቀደም ሲል ከነበሩ ዲዛይኖች ላይ መጠነኛ ማሻሻያ በማድረግ 500 ሺህ መኖሪያ ቤቶችን በከተማው ለማስገንባት በተለያዩ የግንባታ አማራጮችን ይዞ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሠረት በመንግስት የሚገነቡ 150 ሺ ቤቶችን በ20/80 እና 40/60 ፕሮግራም ተመዝግበው ለሚገኙ የሚነገቡ ሲሆን ፤ በ75 ሄክታር መሬት ላይ 25 ሺህ ኪራይ ቤቶች ግንባታ፤ ለዚህኛው በተለየ መልኩ በ10ሩም ክፍለ ከተሞች መታደስ እና መቀየር የሚገባቸውን የቀበሌ ቤቶች የሚገኙበትን ይዞታ በመጠቀም እንደሚገነባ ነው የተነገረው:: ይህን መሠረት አድርጎ የፓይለት ስራው በሁለት ክፍለ ከተሞች ተጀምሯል።

የከተማዋ ኪስ ቦታዎች በመጠቀም የ175 ሺህ የማህበር ቤቶች ግንባታ በማካሄድ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግባለሃብቶችን በማሳተፍ አቅም ላላቸው ነዋሪዎች የአፓርታማዎችን ግንባታ ማከናወን ልላኛው ዕቅድ ነው:: ከተለያዩ የሃገር ውስጥ እና የውጪ ሃገር ባለሃብቶች ጋር በመሆን በተያዘው ዓመት 25 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ ተይዟል፡፡

ከሪል ስቴት አልሚዎች ጋር በመሆን 75 ሺ ቤቶች ግንባታምይጀመራል። ከላይ የተጠቀሱት የግንባታ አማራጮችን በ2012 ዓ.ም በመጀመር በዓመቱ መጨረሻ የግንባታዎቹን 30% ለማጠናቀቅ ይሠራል ነው የተባለው::በተጨማሪም በግንባታ ላይ የሚገኙ 139 ሺህ በላይ ቤቶች ግንባታቸውን በማጠናቀቅ ለነዋሪዎች ይተላለፋሉም ተብሏል::

LEAVE A REPLY