ፕሬዝዳንት ሙላቱ በዘንድሮው ፓርላማ መክፈቻ ንግግራቸው አንዳንድ ማሻሻያዎች አንደሚደረጉ ገልጸዋል፡፡ የመንግሥቱን ሥልጣን በበላይነት የሚቆጣጠሩት ህውኃቶች የገጠማቸውን የህዝብ ተቃውሞ ለማስተንፈስ ያስችለናል ያሉትን ግን የማይፈጽሙትን የማሻሻያ ርምጃ ጽፈው ሲሰጡዋቸው ከማንበባቸው በፊት ቢያንስ ሁለት ነገሮችን ሊያገናዘቡ በተገባ ነበር፡፡ አንደኛው በአምናው የመክፈቻ ንግግራቸው ከተናገሩት ያልተፈጸሙት ይልቃሉና የማተገብሩትን ተናገር እያላችሁ ቃል አባይ ፕሬዝዳንት አታድርጉኝ ማለት፣ ሁለተኛው ደግሞ የተባሉት ማሻሻያዎች ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የሚነገሩ ሳይሆን በርግጥ ታምኖባቸው ተፈጻሚ አንዲሆኑ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ከሆነ አንዳንዶቹ ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ህገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መንገድ የህገ መንግስት ማሻሻያ አንዳረጋለን የሚል በንግግራቸው አንዲካተት ማድረግ ይገባቸው ነበር፡፡
የርሳቸው ሲገርም ጠቅላይ ምኒስትሩ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል አስፈላጊ ቢሆን እንኳን..ማለታቸው መንግሥታቸው አሻሽላቸዋለሁ ብሎ በፕሬዝዳንቱ ያስነገራቸው ጉዳዮች አንዳንዶቹ የህገ መንግሥቱን መሻሻል የሚጠይቁ መሆናቸውን አለመገንዘባቸውን ያሳያል፡፡ ይህ ደግሞ ሕገ መንግሥቱን ካለማወቅ ወይንም ከቁብ ካለመቁጠር የሚመጣ ነው፡፡
የህዝቡን ቁጣ ያበርዳል የሥልጣን ፍርፋሪ ናፋቂዎችን በጉጉት ማኖር ያስችላል አውቆ ለሚታለለው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም እጅ መንሻ ይሆነናል ወዘተ ተብሎ ከተነገረው የማሻሻያ ሀሳብ ውስጥ አንዱ የሆነው የምርጫ ሕግ እነርሱ በማን አለብኝነት ካልፈጸሙትና ተቃዋሚው ለእኛ እስከጠቀመ ድረስ ብሎ በዝምታ ካልተቀበለው በስተቀር የህገ መንግሥቱን መሻሻል የሚጠይቅ ነው፡፡ የምርጫ ሕጉን ማሻሻል የተፈለገው ፕሬዝዳንቱ እንደነገሩን የምርጫ ሥርዓቱን ወደ ተመጠጣኝ ውክልና ሥርዓት ለመቀየር ይሁን የቀድሞው ቃል አቀባይ አንደገለጹት ከተመጣጣኝና ከአብላጫ ሥርዓቶች የተዳቀለ ሥርዓት ለመፍጠር ህገ መንግሥቱ ሳይሻሻል የሚሆን አይደለም፡፡ እንዲህ አይነቱን ነገር እነርሱ ሆን ብለው ለማደናገሪያነት የሚያቀርቡት በመሆኑ አይደንቅም አዲስም አይደለም፡.ሌሎች ግን የምርጫ ሕጉን ለመለወጥ ህገ መንግሥቱን ማሻሻል አንደሚጠይቅ ባለማጤን አንደ መልካም ነገር ቆጥረው የተነገረውን አንደ ወረደ ተቀብለው ሲያስተጋቡትና ሲተቹት ማየትና መስማት ያስገርማል፡፡
ወያኔዎች እድሜ ማራዘሚያ መድሀኒት የሆነናል ብለው ካሰቡ ህገ መንግስት ምናቸውም አይደል ፡፡መጀመሪያም መጨረሻም ጉዳያቸው ስልጣን ነውና በነጋሪት ጋዜጣ ያወጁትን በጓዳ ሊሽሩት በአደባባይ የተናገሩትን እንዳልነበረ ሊያደርጉት ግድ አይሰጣቸውም፡፡ ህገ መንግሥቱ ሊሻሻሉ የሚገባቸው አንቀጾች አሉት ብሎ መናገር ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ማፍረስ አስብሎ ሲያስወነጅል በቅርቡም ከዳኝነት ስራ ሲያስባርር ኣይተናል፡፡ ህውኃቶች ግን ሊጥሱትም እስከ መኖሩ ሊረሱትም ሌላውን ሊያጠቁበትም እድሜ ለጠብ መንጃቸው መብት አላቸው፡፡ ይህ ደግሞ ከጫካ ጀምረው ደንባቸውን በመተላለፍ በአዋጅ ያጸደቁትን በጓዳ በማፍረስ ሌሎችን ጥፋት ብለው የወነጀሉበትን አነረሱ ይጠቅመናል ባሉ ግዜ በመፈጸም እያዳበሩት የመጡት አብሮ አደጋቸው ተግባር ነው፡፡
ለዚህ ማሳያ የሚሆኑኝ ሁለት አማስረጃዎችን ልጥቀስና ወደ ርእሰ ጉዳዬ እመለሳለሁ፡፡ ምን ያህል ሰው ልብ አንደሚለው አላውቅም እንጂ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሚል አጠራር ከተጀመረ ሶስት አመት አልሞላውም፡፡ ታሪክ የማይረሳቸው በህገ መንግስቱ ጉባኤ ላይ ብቸኛ ኮከብ የነበሩት ሻለቃ አድምሴ ዘለቀ የጎሳና የቋንቋ አከላለሉን ተቃውመው በተለይ ደግሞ ምስራቁን አካባቢ ሲሆን የሶማሌ ክልል ባትሉት አምቢ ካላችሁ ደግሞ የሚሆነው አይታወቅምና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ብትሉት በማለታቸው የወረደባቸውን ዘለፋና ስድብ አንረሳውም፡፡ ያኔ የነፍጠኛ አስተሳሰብ ያሉት ሰዎች ዛሬ እነርሱ ሲሉት የነፍጠኛ አስተሳሰብ አራማጅ ሆነው ነው ማለት ነው! ወያኔዎች ለሥልጣናችን ማቆያ ይጠቅመናል ካሉ አንዲህ ናቸው፡፡
ዋናው ጉዳይ ግን ይህ አይደለም የሻለቃ አድማሴ ተቃውሞ ኃላ ቀር የነፍጠኛ አስተሳሰብ ተብሎ በህገ መንግስቱ ላይ የሶማሌ ክልል ተብሎ ነውና የሰፈረው ህገ መንግስቱ ሳይሻሻል የተደረገው የስም ለውጥ የህገ መንግስት ጥሰት ነው፡፡ እነርሱ በማን አለብኝነት ጣሱት እኛ በምን አገባኝ ዝም አልን፡፡ ህገ መንግሥታችን እያሉ የሚመጻደቁብን ሰዎች ለህገ መንግስታቸው ያላቸው አክብሮትም ሆነ እውቀት እዚህ ድረስ ነው፡፡
በሁለተኛ ማሳያነት የማቀርበው በሕውኃት ክፍፍል ወቅት ቢኒያም ዮሃንስ የተባሉ ጸሀፊ ህውኃት -ምን ነበር ? ምንድን ነው ? ምን ሊሆን ይችላል?በሚል ርእስ ሪፖርተር መጽሄት ሚያዚያ 1993 እትም ላይ ካቀረቡት ጽሁፍ የተወሰደ ነው፡፡ አንዲህ ይላሉ፤ “ ማሌ ካለ ድል አለ የተባለለትን ማሌን ስሙን አትጥሩ፣ ማሌሊትን አታነሱ፣ማጭድና መዶሻ አታሳዩ፣ ባንዲራውን ደብቁ የሚል ሹክሹክታ የአባላቱን ጆሮ ሞላው፡፡ በፀሐይ የተፎከረለት ማሌ በጨለማ ለመናገር አሳፈረ፣ታጋዩ አመራሩ ምን እንደሚል ለመስማት ቢጠብቅም አመራሩ ግን ዝም ሆነ፡፡ ቢያንስ አቶ መለስ ማሌን አይጥሉትም፣አቶ አለም ሰገድም እንዲህ አያደርጉም ብሎ ጆሮውን አንቅቶ ቢጠብቅ ሁሉም ጭጭ አሉ፡፡ ያን ያህል የተዘመረለት ሌሎችን ‹ፕራግማቲስቶች› አስብሎ ከድርጅቱ ያስገለለ ርዕዮተ ዓለም በየኬላው እየተፈተሸ እንደሚቀር የኮንትሮባንድ እቃ የአንጦጦን ኬላ ሳያልፍ ቀረ፡” ይላሉ፡፡ አዎ በወያኔዎች ዘንድ ሁሉም ይደረጋል ለሀገርና ለሕዝብ ሳይሆን ለሥልጣን ሲባል፡፡
ስለ ሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት የሚገልጸው የህገ መንግሥቱ አንቀጽ 54 በንዑስ አንቀጽ 2 ላይ “የም/ቤቱ አባላት በአንድ ምርጫ ክልል ውስጥ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች መካከል አብላጫ ድምጽ ያገኘ ተወዳዳሪ አሸናፊ በሚሆንበት የምርጫ ሥርዓት ይመረጣሉ፡፡ የተለየ ውክልና ያስፈልጋቸዋል ተብሎ የታመነባቸው አናሳ ብሔረሰቦች አና ሕዝቦች በምርጫ የህ/ተ ም/ቤት አባል ይሆናሉ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡” ይላል፡፡ ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል የተባሉ ጉዳዮች ብዙዎቹ ህጉ ያልወጣላቸው ሲሆን በዚህ አንቀጽ የተገለጸው ዝርዝር ህግ ወጣም አልወጣም አናሳ ብሄረሰቦችን አንጂ ውክልና ያላገኙ ፓርቲዎችን አይልምና ሕገ መንግሥቱን ሳያሻሽሉ ፓርቲዎችን በችሮታ ወደ ፓርላማ የማስገቢያ መንገድ ማበጀት አይቻልም፡፡
ስለሆነም የምርጫ ህጉን እናሻሽላለን የሚለው የፕሬዝዳንቱ ንግግር ኋላም ጠቅላይ ምኒስትሩ ህገ መንግሥቱን ማሻሻል አንኳን አስፈላጊ ከሆነ.. በማለት የገለጹት ይህን የህገ መንግስት አንቀጽ ያላገናዘበ ወይንም ሆን ብሎ የጣሰ ነው፡፡ ሌላው ሰውም ባለማወቅ፣ በየዋህነት ወይንም ሆነ ብሎ ለማስቀየሻነት እየተቀባበለ እንደ ድንቅ ተግባር ያስተጋባዋል፡፡ የተቀውሞው ጎራ በአብዛኛው የፊት የፊቱን እንጂ ግራና ቀኙን አለማስተዋል፤ የእለት የእለቱን አንጂ የትናንቱን አለማስታወስ ለወያኔዎች የማጭበርበር ጉዞ በእጅጉ ተመችቶአቸዋል፣ ጠቅሞአቸዋልም፡፡ መቼም ለበጎ ነገር ህገ መንግሥት ቢጣስ ምን አለበት የሚል ተከራካሪ ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡
ስለሆነም የተወራው የምርጫ ህግ ማሻሻያ የህገ መንግስቱን አንቀጽ መሻሻል የሚጠይቅ መሆኑ ታውቆ ለዚሁ ሲባል የህገ መንግሥት ማሻሻያ አንደሚደረግ አለመገለጹ ጉዳዩ የተነሳው ለማደንዘዣነት አንጂ ለተግባራዊነት አይደለምና በዚህ ለመታለልም ለመደለልም ራስን ማዘጋጀት አያስፈልግም ፡፡ በአንጻሩ ከላይ በማሳያነት አንደቀረበው የሶማሌ ክልልን ስም ያለ ህግ መንግስት ማሻሻያ እንደለወጡት ሁሉ ይህንስ ቢያደርጉት ብለን ብናስብ ህገ መንግሥቱን የጣሱት ለመልካም ተግባር ነውና ግዴለም ተብሎ ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችል አይመስለኝም፡፡
ስለዚህ የምርጫ ህጉን በማሻሻል የተወሰኑ ተቀዋሚዎችን በፓርላማ አንዲታዩ ማድረግ የሚለው ትኩሳት ማብረጃ ከመሆን ባለፈ ቢያንስ በእነዚህ በተጠቀሱት ምክንያቶች ተግባራዊ ሊሆን አለመቻሉ ግልጽ ነው፡፡ የግድ የሀገ መንግስት መሻሻያ ይጠይቃልና፡፡ በማን አለብኝነት ወይንም ለተቀዋሚዎች የሚጠቅም ስለሆነ አይቃወሙትም በሚል ተግባራዊ ቢደረግ ደግሞ የህገ መንግስት መጣስ ወንጀሉን ተቀዋሚዎችንም በእኩል ተካፋይ ያደርጋል፡፡
ከአንጀት ካለቀሱ አንባ አይገድም አንዲሉ ወያኔዎች የምርጫ ሕጉን ሀገራዊ ጉዳት ተገንዝበው እሱን በማሻሻል ለውጥ ለማምጣት ከልብ ያሰቡበትና ያመኑበት ከሆነ እሱን የሚመለከተውን የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ ማሻሻል ለእነርሱ በጣም ቀላል ነው፡፡ ምክንያቱም በህገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሰረት ህገ መንሥቱን የማሻሻል ሰልጣን ያላቸው ፓርላማውም ሆነ የክልል ምክር ቤቶች በህውኃት ቁጥጥር ስር ናቸውና፡፡ ነገር ግን አንድም በመቃብራችን ላይ ካልሆነ በስተቀረ እያሉ ሲፎክሩለት የኖሩትን ህገ መንግሥት በሕዝባዊ አመጽ ተገዶ ማሻሻል ለእነርሱ ከሽንፈትም በላይ ሞት ሆኖ ስለሚታያቸው ሁለትም የህገ መንግሥቱን መሻሻል የሚፈልጉ ብዙ የህዝብ ጥያቄዎች በር ላይ አሉና አንዴ ከተጀመረ ከዚህም ከዛም እየተናደ ሥልጣናችንን የሚያሳጣን ደረጃ ያደርሰናል ብለው ስለሚሰጉ አይነኬ የሚሉትን ህገ መንግሥት ማሻሻል ውስጥ አይገቡም፡፡ ለዚህም ነው ጥያቄ በተነሳና ህዝባዊ ቁጣ በተቀሰቀሰ ቁጥር በህገ መንግስቱ አግባብ የሚለውን ቃል የሚያስቀድሙት፡፡ አቶ ይለማሪያምም የህገ መንግሥቱን መሻሻል የሚጠይቅ ማሻሻያ አንዳላቀረቡ ሁሉ ማሻሻል ቢያስፈልግ አንኳን በማለት የገለጹት፡፡ ስለሆነም የምርጫ ህግ ማሻሻያ ዲስኩሩ ከፕሮፓጋንዳ አልፎ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል አይደለምና ከወያኔም ባህርይ ሥልጣንን የማጥበቅ አንጂ ከሕዝብ የመታረቅ ተግባር አይጠበቅምና፣ ለመሰረታዊ ለውጥ ሳይሆን ለእድሜ ማራዘሚያ ለተግባራዊነት ሳይሆን ለማደናገሪያና ለማስቀየሻ ከወያኔ ሰፈር በሚነገሩ ጉዳዮች አለመዘናጋት የነጻነቱን ቀን ለማቀረብ ይበጃል፡፡