የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 5 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 5 ቀን 2011 ዓ.ም

በኑሮ ዉድነቱ ላይ ከታህሳስ ጀምሮ የሚተገበር የኤሌክትሪክ ታሪፍ ጭማሪ ሊደረግ ነው

ከመጪው ታህሳስ ወር ጀምሮ ሁለተኛ ዙር የታሪፍ ማሻሻያ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል።

በአስከፊ የኑሮ ውድነት ውስጥ እየተንቧቸረ ለሚገኘው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይህ አዲስ የታሪፍ ጭማሪ ሌላ ፈተና እንደሚሆን ከወዲሁ እየተነገረ ነው::

የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ከሁለት ወር በኋላ ተግባራዊ የሚያደርገውን የታሪፍ ጭማሪ አስመልክቶ አንዳንድ ለኢትዮጵያ ነገ አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መንግሥት ከመጠን በላይ ጣራ የነካውን የኑሮ ውድነት ያስተካክላል ብለን ተስፋ ባደረግንበት ወቅት እንዲህ ዓይነት ተጨማሪ ነገር መፈጠሩ አሳዝኖናል ሲሉ ተናግረዋል::

የአገልግሎቱ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አዲሱ የታሪፍ ማሻሻያ የኅብረተሰቡን የመክፈል አቅም ያገናዘበ ነው ከማለታቸው ባሻገር ፤ የኤሌክትሪክ የመሰረተ ልማት ስርቆት ተቋሙን ለኪሳራ እየዳረገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መ/ቤቱ ባለፉት ስድስት ወራት 18 ሚሊየን ብር ኪሳራ እንዳጋጠመው ይፋ አድርገዋል።

አቶ መላኩ 156 የንብረት ስርቆቶ ሲፈፀም 31 ትራንስፎርመሮች እንደተሰረቁም አረጋግጠዋል ። አገልግሎቱ ባለፈው ዓመት 10 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን ፣ በቀጣይም የኤሌክትሪክ መስመር ኔትዎርክ ማሻሻያ በማድረግ ተደራሽነቱን ለማዘመን እየተሠራ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ኅብረተሰቡም በመሰረተ ልማቱ ላይ የሚፈፀም ስርቆትን ለመከላከል የድርሻውን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል።

እሳትና ጭድ የሆኑ ፓርቲዎችን በውሰጡ የያዘው ኢሕአዴግ ሊዋሃድ እንደማይችል ሕወሓት ተናገረ

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ለሰባት ቀናት ሲያካሄድ የነበረውን ስብሰባ በማጠናቀቅ አነጋጋሪ የሆነ መግለጫ አውጥቷል።

ሰፋ ያለውና ከትናንት ምሽት ጀምሮ ብዙዎችን እያነጋገረ ባለዉ መግለጫ ፣ የኢሕአዴግ መዋሃድ ዕርምጃን በተመለከተ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ  ግንባር (ኢሕአዴግ) መስራች እና ዋነኛ አባል የሆነውሕወሓት አጥብቆ እንደሚኮንነው አስታውቋል::

“ከኢሕአዴግ ርዕዮተ ዓለም እና መተዳደሪያ ደንብ ውጪ አንድ ውህድ ፓርቲ ለመመስረት እየተደረገ ያለው ሩጫ ሕገ-ወጥ ነው” የሚለው ሕወሓት ፤ “እንዲፈጠር እየተፈለገ ያለው ፓርቲ በቅርጽ ብቻም ሳይሆን በይዘትም፤ ከነበረው ኢህአዴግ ፕሮግራም በመሰረቱ የተለየ አዲስ ፓርቲ የመመስረት ጥረት ነው :: የኢትዮጵያ ህዝብ ኢህአዴግን የመረጠው በያዘው ፕሮግራም መሰረት ነው፤ አገር እንዲመራ በህዝብ ሓላፊነት ያልተሰጠው አዲስ ፓርቲ ለመመስረት እየተሞከረ ነው ያለው።” ብሏል በመግለጫው።

“ይመሰረታል የተባለው ውህድ ፓርቲ በህዝብ ስልጣን ላይ እንዲቆይ ፍቃድ ያልተሰጠው ፓርቲም ብቻ ሳይሆን፤ ስልጣን ለመያዝ መወዳደር የማይችል ፓርቲ ይሆናል” ሲልም አስጠንቅቋል:: “እሳት እና ጭድ የሆኑ ፓርቲዎች በውስጥ የተሸከመው ግንባር፤ አይደለም ውህደት ፓርቲ በግንባርነት አብሮ የሚያቆይ የጋራ አስተሳሰብ እንኳን የላቸውም” ብሏል::

“በየዕለቱ እርስ በርስ እየተናቆሩ የሚውሉ አባል ፓርቲዎችን ይዘን የሃገር ችግርን በመረዳትም ሆነ ችግርን ለመፍታት በምንከተለው መንገድ ጭምር እርስ በእርሱ በሚጋጩበት ሁኔታ ውሁድ ፓርቲ ለመመስረት መሯሯጥ፤ የጥቂት ግለሰቦች የስልጣን ጥማት ለማርካት ካልሆነ በስተቀር የሃገሪቷን ችግር የሚፈታ ሃገራዊ ፓርቲ ይፈጠራል ብሎ ህወሓት አያምንም” በማለት አቶ ጌታቸው ቀደም ሲል ተናግረው ነበር::

በተጨማሪም ህወሓት ለትግራይ፣ ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ ህዝብ መልዕክት አስተላልፏል፤ “የተከበርክ የትግራይ ህዝብ፤ አሁንም ቢሆን ሁኔታዎች እየከበዱና እየባሱ በመምጣታቸው ደህንነትህንና ህልውናህን ለማስጠበቅ የምታደርገው ትግል ይበልጥ አጠናክረህ ልትቀጥልበት ይገባል” የሚል መልዕክት ለሚያስተዳደርው ክልል ህዝብ መልዕክት አስተላልፏል::

“ህገ መንግስታችንና ህብረ ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርዓታችን የሚሸረሽሩና የሚጥሱ ተግባራት በየቀኑ ማየት የተለመደ ተግባር ሆኗል። መላው የሀገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችም ህብረ-ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓታችንን ለማዳን በሚደረገው ወሳኝ ትግል ከማንኛውም ጊዜ በላይ አገራችንን ለማዳን ሊረባረብ ይገባል” በማለት ለኢትዮጵያ ህዝብ ያለውን ጥሪ አቅርቧል።

በመጨረሻም ህወሓት በመግለጫው፤ ለኤርትራ ህዝብ “የትግራይና የኤርትራ ህዝብ ለጋራ መብትና ጥቅም በጋራ የታገሉ ወንድማማች ህዝቦች ናቸው። የነበረውና አሁንም ያለው ዝምድናና መደጋገፍ ወደ ዘላቂ አስተማማኝ ደረጃ ለማድረስ ባለፈው ዓመት የተጀመረው የሰላም ጭላንጭል በዚህ ዓመትም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል” የሚል መልዕክት አስተላልፏል።

በቤይሩት በሰባት ወር ውስጥ ሠላሳ አራት ኢትዮጵያውያን መሞታቸው ተረጋገጠ

ባለፉት ሰባት ወራት ለሥራ ወደ ሌባኖስ ካቀኑ ኢትዮጵያዊያን መካከል 34ቱ በተለያዩ ምክንያቶች ህይወታቸውን እንዳጡ በሊባኖስ ያሉ የኢትዮጵያዊያንና ሌሎች የበጎ አድራጎት ማህበራት አስታወቁ።

ለኢትዮጵያዊያኑ ህይወት መጥፋት በአብዛኛው እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው በአሠሪዎቻቸው በሚፈጸምባቸው አሰቃቂ ግፍና ጥቃት ሳቢያ ራሳቸውን በማጥፋት፣እንዲሁም ካሉበት ኢ ሰብዓዊ የስቃይ ኑሮ ለማምለጥ በሚያደርጉት ትግልና ጥረት መሆኑ ተሰምቷል።

በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እየገጠማቸው ያለውን አስከፊ ችግር በተመለከተ መንግሥት የኢትዮጵያዊያን ሠራተኞችን ሞትና ስቃይን ለማስቆም አፋጣኝ የሆነ እርምጃ እንዲወሰድ በጠየቁበት እና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ላይ ነው እውነታውን መረዳት የተቻለው።

“አስከሬን ወደ አገር ቤት መላክ ደከመን” በማለት በደብዳቤያቸው ላይ ብሶታቸውን ያሰፈሩት ኢትዮጵያዊያኑ በአገሪቱ ያለው ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ለዜጎቹ ደህንነትና መብት እየሠራ ባለመሆኑ መንግሥት እርምጃ እንዲወስድ በአጽንኦት ጠይቀዋል። “በኢትዮጵያዊያን ላይ እየደረሰ ስላለው ግፍና ሰቆቃ በይገባኛል ስሜት አገርን ወክሎ በመንቀሳቀስ ረገድ በሌባኖስ ያለው የኢትዮጵያ ቆንስላ ሙሉ ሓላፊነትም ሆነ ግዴታ ቢኖረውም፤ እውነታው ግን ፍጹም ከዚህ የራቀ ነው” በማለት በደብዳቤያቸው ላይ የወገኖቹን ጉዳይ ጆሮ ዳባ ልበስ ባለው መንግሥት ላይ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

ለሰባት ዓመታት ሊባኖስ ውስጥ ነዋሪ የነበረችውና ለችግር የተጋለጡ ኢትዮጵያዊያንን ለመርዳት ከሚጥሩት አንዱን ድርጅት የምታንቀሳቅሰው ባንቺ ይመር “ይህ ነገር የቆንስላውን ስም ለማጥፋት የቀረበ ውንጀላ አይደለም” በማለት በተደጋጋሚ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እውነታውን ለማስረዳት መጣራቸውን ለቢቢሲ ተናግራለች።

ቆንስላው ዜጎቹን ለመርዳት ተገቢውን ጥረት ስለማያደርግ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ማህበራትን በመመስረት የቻሉትን ለማድረግ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሳ፤ እሷም በየቀኑ ከአምስት በላይ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሆነው እንደሚደውሉላት ትናገራለች። “እኛ የምንችለውን ከማድረጋችን በፊት ቆንስላው ያጋጠሙ ችግሮችን እንዲያውቅና ድጋፍ ሲጠየቁ ለመስማት እንኳን ፈቃደኞች አይደሉም” ስትልም አማራለች።

በተለያዩ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያዊያን ችግር ውስጥ መሆናቸውን በተመለከተ ሪፖርት ሲደረግላቸውና ሄደው ሲያገኟቸው፣ የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ ተባባሪዎች እንዳልሆኑና መረጃ ለማግኘት ስልክ በሚደወልበት ጊዜ ፈጽሞ መልስ አይሰጡም በሚል የኢትዮጵያውያን ቆንስላ ሠራተኞችን ዜጎች ይወቅሳሉ::

በቆንስላ ጽሕፈት ቤቱ ላይ በኢትዮጵያውያን ላይ የቀረበውን ክስ አስመልክቶ በአራት መደበኛ ስልኮች ላይ በመደወል ለቀናት ምላሽ ለማግኘት ቢቢሲ ጥረት ቢያደርግም ሦስቱ ስልኮቹ ቢጠሩም የማይነሱ ሲሆን፣አንደኛው ደግሞ በደንበኛው ጥያቄ መሠረት እንዲቋረጥ መደረጉን እንዳረጋገጠ ዘግቧል::

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ከሊባኖስ የሠራተኞች ሚኒስቴር በወጣ መረጃ መሠረት ከ150 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በሊባኖስ በተለያየ ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። ይህ ቁጥር በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው ያሉትን የሚያመለክት በመሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች ህጋዊ ሳይሆኑ በአገሪቱ የሚሠሩ በመኖራቸው ቁጥሩ ከዚህ በከፍተኛ ደረጃ ሊጨምር እንደሚችል ይገመታል።

በኢትዮጵያዊያኑ ላይ የሚፈጸመው ግፍ ከሌሎቹ የተለየ እንደሆነ የሚናገሩት እነዚህ አካላት ለሠራተኞቹ መብት መከበር የሚጥሩት ቡድኖች ከክፍያ አንስቶ በሊባኖስ የሠራተኞች ህግ ተጠቃሚ አይደሉም። ኢትዮጵያዊያኑ በቀጣሪዎቻቸው፣ በአስቀጣሪዎቻቸውና ከሄዱበት መንገድ አንጻር የሌላ ሀገር ዜጎች እምብዛም የማይገጥማቸው ተጽእኖ እንደሚደረግባቸው በሊባኖስ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ሊቀመንበር ሳሙኤል ተስፋዬ ፤ “በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ለምሳሌ መከፈል ያለበትን ዝቅተኛ ደሞዝ መጠን፣ አንድ ሰው ሊሠራ የሚገባውን የሥራ ሰዓትና የዕረፍት ቀናቶችን የማግኘት መብታቸው ይጣሳል” በማለት አስታውቋል።

ከሁለት ዓመት በፊት የወጣ አንድ ሪፖርት እንዳመለከተው ከውጪ አገር መጥተው ሊባኖስ ውስጥ በሚሠሩ ሰዎች ላይ ከሚፈጸመው አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ሰቆቃ በተጨማሪ በየሳምንቱ ሁለት ሠራተኞች ህይወታቸውን ያጣሉ። ከእነዚህመካከልም አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

ይህ ሁሉ ስቃይ እየተሰማ አሁንም በርካታ ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው ህጋዊ ባልሆኑ መንገዶች ወደ ሌባኖስ እየመጡ ይገኛሉ።

“ከሁሉ የሚያስደነግጠው ግን የሚፈጸመውን ግፍ ሳይሆን የሥራውን ጫና ለመሸከም የማይችሉ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች መምጣታቸው ነው” የምትለው ባንቺ የታዳጊዎቹ ፓስፖርታቸው ካሉበት የዕድሜ ዕውነታ ጋር የማይነጻጸር ፣ ከ20 ዓመት በላይ እንደሆናቸው እንደሚያሳይም አብራርታለችጀ ለዚህ ደግሞ የቀበሌ መታወቂያን በሐሰተኛ መንገድ ለማውጣት መቻላቸው ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ ተነግሯል::

“ምንም እንኳን ወደዚህ የሚገፋቸው ችግር ቢሆንም፤ ቤተሰብ ልጆቹን ሲልክ በምን ሁኔታ ወደየት እንደሚሄዱና ምን ሊገጥማቸው እንደሚችል መረዳት አለበት” በማለት “ብዙዎች እዚህ ከመጡ በኋላ በሚገጥማቸው መከራና ጭካኔ እንኳን ለቤተሰባቸው ለራሳቸውም እንዳይሆኑ የሚያደርጉ ችግሮች ይገጥማቸዋል” ተብሏል::

ወደሊባኖስ በመሄድ የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ኑሮ ለመለወጥ የወጡ በርካታ ኢትዮጵያዊን የሚገጥማቸው መከራ እንዳለ ሆኖ አንዳንዶች ደግሞ ደብዛቸው እንደሚጠፋ ተሰምቷል። “የት እንዳሉ ሳይታወቅ ከአስር እስከ አስራ አምስት ዓመታት በባርነት ያሉ፣ ድብደባ የሚፈጸምባቸው፣ የሚደፈሩ ሴቶችና ያለፍርድ ዕስር ቤት ያሉ አማራጭን ሲያጡ ራሳቸውን ለማጥፋት ይሞክራሉ” በማለት የግፍና ሰቆቃውን መጠን ቤይሩት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አመላክተዋል::

ኢትዮጵያውያኑ በጻፉት ደብዳቤ ላይ እንዳሰፈሩት በሊባኖስ የሚደርስባቸውን መከራ ጉዳዬ ብሎ የሚከታተልና የሚረዳቸው የቆንስላ ጽሕፈት ቤት እንዲኖራቸው እንደሚፈልጉ አመልክተዋል። “በሊባኖስ ያለውን የኢትዮጵያ ቆንስላ የዜጎች ህመም የማይታየው ፣ በሚሰጠው መረጃ ፍጹም የማይታመን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ዜጎች እንግልትና ስቃይ በሚደርስባቸው ግዜ የድረሱልን ጥሪ ሲያስተላልፉ ምንም እንዳልሰማ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ የዜጎች ስቃይ ችላ የሚል ነው” ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

በሊባኖስ ያሉ ኢትዮጵያውያን ችግር በገጠማቸው ጊዜ ቆንስላው ይደርስልኛል ብሎ መጠበቅ ይቅርና አለ ብለውማሰብም አይፈልጉም::  “ተጠሪ እንደሌለን ነው የምንቆጥረው ” በማለት በመንግሥት ተስፋ የቆረጡ የሚመስል አስተያየት ይሰጣሉ::

በአንዳንድ አጋጣሚዎች ቆንስላው ጣልቃ የሚገባበት ጊዜ ሲኖር ለዜጎቻቸው መብትና ደህንነት ከመቆም ይልቅ በአሰሪዎች ፊት ኢትዮጵያውያንን በማመናጨቅና በማዋረድ ወደነበሩበት የስቃይ ህይወት እንዲመለሱ እስከማስገደድ እንደሚደርሱ የምታመላከተው ባንቺ ፤ በዚህ ሁኔታ ወደ አሠሪዎቻቸው የተመለሱ ሴቶች ሊገጥማቸው የሚችለው መከራና ጥብቅ ቁጥጥር ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ቀላል ነው  ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች::

“ቆንስላው በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚፈጸሙ ግፎችን በተመለከተ አንዳንድ መረጃዎችን ከመሸፈን አልፎ፣ ጥቃት ስለተፈጸመባቸው እንዲሁም ስለተገደሉ ሰዎች በግልጽ የሚቀርቡ መረጃዎችን ማጣራትና መከታተል አይፈልግም። ማንም የሚጠይቃቸው የለም። ብዙ ጊዜ የሚገኙት የሞቱ ኢትዮጵያዊያንን ለመላክ ነው” በማለት ኢትዮጵያውያኑ ቤይሩት የሚደርስባቸውን መከራ በግልጽ አስቀምጠዋል::

ነገ ለሚጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ዛሬ የጸሎት ፕሮግራም ተካሄደ

በየዓመቱ በወርሃ ጥቅምት የሚካሄደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትሪያርክ አጠቃላይ ሰበካ 38ኛ ጉባኤ መካሄድ ተጀምሯል። ይህ ጉባዔከጥቅምት 5 እስከ 8 ቀን 2012 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን ነገ ቅዱሳን ጳጳሳት ብቻ የሚሳተፉበት የሲኖዶሱ ጉባዔ ይጀምራል።

በጉባኤው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና የአህጉረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጆችና የሰበካ ጉባኤ ተወካዮች ዛሬ ተገኝተዋል።

ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘ አክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፥ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስለሕዝቦች ሁለንተናዊ ደኅንነት መጸለይ፣ ማስተማርና መምከር ከእግዚአብሔር የተቀበለችው ዐቢይ ተልዕኮ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ይህም ዘወትር የምታከናውነው ተቀዳሚ ተግባርዋ ቢሆንም፥ በተለይም አሁን ባለንበት ወቅት በከፍተኛ ደረጃ በጸሎትና በማስተማር፣ በመምከርና በማስታረቅ ተግታ የምትሠራበት ጊዜ እንደሆነ እንገነዘባለን ነው ብለዋል። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ዛሬ ሀገሪቱ በተስፋና በሥጋት መካከል ተወጥራ ያለችበት እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን ማዕከላዊ መዋቅር እየተፈተነ የሚገኝበት አሳሳቢ ወቅት እንደሆነም አስረድተዋል።

በዚህ ፈታኝ ወቅት ቤተ ክርስቲያን ትዕግሥት ያልተለየው ጥበብና ብልሃት ተጠቅማ ልጆቿን ወደ አንድነት ማሰባሰብ ከምንም በላይ ተቀዳሚ ተግባር አድርጋ መውሰድ ይጠበቅበታልም ብለዋል።

ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር የተሰጣት የማስታረቅና የማስተማር፣ የመምከርና የማሰባሰብ ኃላፊነት የምታከናውነው አንዱን በማራቅ፣ ሌላውን በማቅረብ አንዱን በመደገፍ ሌላውን በመንቀፍ ሳይሆን ሁሉም ልጆችዋ ናቸውና በእኩልነት፣ በአንድነት፣ በፍቅርና በገለልተኝነት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

ቤተ ክርስቲያኗ ከፖለቲካ ንክኪ ፍጹም ነጻ ሆና ሥራዋን እንድትቀጥል ማድረግ የሁሉም የቤተ ክርስቲያን አመራሮች፣ አገልጋዮችና ሠራተኞች የውዴታ ግዴታ ነው ያሉት ብፁዕነታቸው፥ ሆኖም ስለሰው ልጆች ደኅንነትና እኩልነት፣ ሰላምና አንድነት የእግዚአብሔር ቃልን መሠረት አድርጋ በሰፊው የማስተማር ኃላፊነት እንዳለባት መርሳት የለባትም ሲሉ ገልፀዋል።

ይህ ዓቢይ ጠቅላላ መንፈሳዊ ጉባኤ የቤተ ክርስቲያኗን አንድነት የሚያስጠብቅ፣ የሀብትዋና የንብረትዋ ማእከላዊ አስተዳደርን የሚያስከብር ነውና የሀገሪቱን ሰላምና ልማት፣ የሕዝቡን እኩልነትና አንድነት እንደዚሁም የቤተ ክርስቲያኒቱአንድነትና የሀብቷና የንብረቷ ተጠቃሚነት እውን የሚያደርግ ዓቢይና ላዕላዊ ጉባኤ እንደመሆኑ መጠን እነዚህን ተግባራት በማረምና ሥርዐት በማስያዝ ረገድ በበጀት ዓመቱ ጠንክሮ እንዲሠራ አሳስበዋልበጉባኤው ከ82 በላይ ሀገረ ስብከቶች የስራ አፈፃጸም አቅድ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ነው የተነገረው።በዋነኝነት 2011 ዓ.ም በልማት፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተሰሩ ስራዎች እና በ2012 በሚሰሩ አበይት ተግባራት ዙሪያ የሚመከርበት ጉባኤ ነው ተብሏል።

ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ  ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ግብዣ አቀረቡላቸው

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ግብዣ ማቅረባቸው ተሰማ::

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን በስልክ አነጋግረዋቸዋል።

በስልክ ውይይቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኖቤል የሰላም ተሸላሚ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ እንደገለጹ የጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሴክተሪያት ካወጣው መግለጫ መረዳት ችለናል::።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ  ከተወሰኑ ሳምንታት በፊት ወደ እስራኤል ተጉዘው ይፋዊ ጉብኝት ከማድረጋቸው ባሻገር በተለያዮ ጉዳዮች ላይ ሁለቱ ሀገራት ስለሚሠሩበት ስምምነት መፈጸማቸውን ኢትዮጵያ ነገ መዘገቡ ይታወሳል::

ሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ባደረጉት የስልክ ውይይት ላይ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በእስራኤል ባደረጉት ጉብኝት መደሰታቸውን ጠቅሰው፥ ኔታንያሁ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ይፋዊ ግብዣ አቅርበውላቸዋል::ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ግብዣ ከፖለቲካና ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ አኳያ ዶ/ር ዐቢይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ተቀባይነት ለማሳየት የወሰዱት ዕርምጃ ነው በሚል በፖለቲከኞች እየተተቸ ነው::

ሐኪሞች ለ8 ዓመቷ ታማሚ ሕጻን  ብቻ የሚሆን መድኃኒት ሠሩ

የ8 አመቷ ሕጻን ገዳይ በሆነ የጭንቅላት በሽታ ተጠቂ ነች፤ ይህን ያስተዋሉ ሐኪሞች ለእርሷ ብቻ የሚሆን መድኃኒት ሠርተዋል። ሚላ ማኮቬች፤ የያዛት የጭንቅላት በሽታ እጅግ ክፉኛ ያሰቃያት ነበር። ይህን ተከትሎ የቦስተን ሕፃናት ሆስፒታል ተመራማሪዎች ለሚላ ብቻ የሚሆን መድኃኒት ለመሥራት ደፋ ቀና ማለት ጀመሩ።

ተመራማሪዎቹ የሠሩት መድኃኒት የሚላ ዘረ-መል ውስጥ ገብቶ የጤና እክሏን እንዲፈታ የተዘጋጀ ነው።አሁን ላይሕጻኗምንም እንኳ ከበሽታዋ ሙሉ በሙሉ ባታገግምም፣ ከበፊቱ ስቃይ ተገላግላለች።በእንግሊዝኛው ‘የባተን በሽታ’ በመባል የሚጠራውና ከሚሊዮን አንዴ የሚከሰተው ይህ በሽታ ከጊዜ ጊዜ አደጋው እየከፋ የሚመጣ መሆኑ ተነግሮለታል።

ሚላ ገና የሦስት ዓመት ሕፃን ነበረች፤ ቀኝ እግሯ ወደ ውስጥ መታጠፍ ጀመረ። ከአንድ ዓመት በኋላም በቅርቧ ያለ ነገር ካልሆነ ፈጽሞ ማየት የማትችል ሆነች። አምስት ዓመት ሲሆናት ድንገት መውደቅ ጀመረች፣ አረማመዷም ያልተለመደ ዓይነት ሆነ። ስድስት ዓመቷን ስትደፍን የዓይን ብርሃኗን አጣች፤ መናገርም ይሳናት ያዘ። ድንገተኛ የጭንቅላት እንፍርፍሪትም (ሲዠር) በተደጋጋሚ ያጋጥማት ጀመር።

ሚላን የያዛት በሽታ እየፀና ሲመጣ ጭንቅላቷ ውስጥ ያሉ ሕዋሳትን የመግደል አቅም አለው። የሚላ ቤተሰቦች በሽታው በዘር የሚተላለፍ መሆኑን አላጡትም። ሃኪሞቹም የሚላን የዘር-ቅንጣት በመውሰድ ምርምራቸውን ያጣድፉት ያዙ። ይሄኔ ነው እክሉ ምን እንደሆነ በውል የተገለጠላቸው፤ ሊታከም እንደሚችልም ፍንጭ አገኙ። በመቀጠልም ያዘጋጁትን መድኃኒት በሚላ ሕዋሳት ላይ ሞከሩት። አልፎም ቤተ-ሙከራ ውስጥ ባሉ እንስሳት ውጤቱን ካረጋገጡ በኋላ ከአሜሪካ ምግብ እና መድኃኒት አስተዳደር ፈቃድ አገኙ።

ሚላሰን የተሰኘ ስም የተሰጠው መድኃኒት በይፋ ለሕጻኗ እንዲሰጣት ተደረገ፤  ይህ የሆነው በፈረንጆቹ 2018 የመጀመሪያ ወር ላይ እንደነበር የሚያስረዳው ዜና መሰል መድኃኒቶችን ቤተ-ሙከራ ውስጥ አብላልቶ ለተጠቃሚ ማድረስ ቢያንስ 15 ዓመታት የሚፈጅ ቢሆንም ፣ የሚላን በሽታ ለማከም ቆርጠው የተነሱት ተመራመሪዎች ግን በአንድ ዓመት ተኩል ነው መድኃኒቱን መፈብረክ የቻሉት።

መድኃኒቱ ሚላ የደረሰባትን ሁሉ ሽሮ እንደ አዲስ የሚያስተካክላት ሳይሆን ከተመራማሪዎቹ አንዱ የሆኑት ዶክተር ዩ የመጀመሪያው ዓመት ጥቂት ለውጦች ብቻ የሚታዩበት መሆኑን ጠቁመዋል:: “ከመድኃኒቱ በፊት ሚላ ቢያንስ በቀን ከ15-30 ጊዜ ‘ሲዠር’ (የጭንቅላት እንፍርፍሪት) ያጋጥማት እንደነበር፣ እንፍርፍሪቱ ለሁለት ደቂቃዎች ይቆይ ነበር። አሁን ግን ይህ እክል እየቀለላት ነው። አልፎም ቀጥ ብላ መቆም እና ምግብ በሥርዓቱ መመገብ ጀምራለች” ሲሉቤተሰቦቿ ተናግረዋል።

በሽታው መድኃኒቱን እንዳይላመድ ሐኪሞች በየጊዜው ክትትል ያደርጉላታል።መድኃኒቱ የሚላ አከርካሪ አጥንት ፈሳሽ ላይ እንዲወጋ ነው የተደረገው:: ይህ ለሚላ ብቻ ተብሎ የተዘጋጀው መድኃኒት ሌሎች ቢሹት ሊገዙት ይችላሉ ወይ? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፤ተመራማሪዎቹ መድኃኒቱን ለመፍበረክ ምን ያህል ገንዘብ እንዳወጡ እስካሁን ይፋ አላደረጉም። ነገር ግን ዶ/ር ዩ አዋጭ ባይሆን ኖሮ እናቋርጠው ነበር ሲሉ ተስፋ ያለው ምላሽ መስጠታቸው ተሰምቷል::

LEAVE A REPLY