ቢቢሲ ቆይታ ከአቦይ ስብሃት ነጋ ጋር || “ህወሓትን የሚተካ የፖለቲካ ኃይል...

ቢቢሲ ቆይታ ከአቦይ ስብሃት ነጋ ጋር || “ህወሓትን የሚተካ የፖለቲካ ኃይል የለም”

አቶ ስብሃት ነጋ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ከተራ ታጋይ ተነስተው እስከ ከፍተኛ የህወሓት አመራር የደረሱ ግለሰብ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ፡ ‘በክብር’ ከተሰናበቱት ባለሥልጣናት መካከል አንዱ ናቸው።

በትጥቅ ትግሉ ወቅት ስለነበራቸው ሚና እንዲሁም ስለወቅታዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካዊ ሁኔታ ከቢቢሲ ትግርኛ ጋር ቆይታ አድርገዋል።


ቢቢሲ፡ ህወሓት ከተመሰረተበት ግዜ አንስቶ በክብር እስከተሰናበቱበት ድረስ አመራር ላይ ነበሩ ከልምድዎ እጅግ የሚኮሩበት ወይም እንዲህ ባደርግ ኑሮ ብለው በግል ወይም እንደ ድርጅት የሚቆጩበት ነገር አለ?

ቦይ ስብሃት፡ እንደ ድርጅት ድክመት አልነበረብንም አልልም፤ ብዙ ድክመቶች ነበሩብን። በግልም ስህተቶችን አልፈጸምንም አልልም።

እኔም በግሌ አንዳንድ ስህተቶችን ፈጽሜያለሁ፤ ሆኖም በቅጽበት ይታረም ነበር። የሓኽፈን ውጊያ የኔ ስህተት ነበር ውግያው ድል አልነበረም። ግን በፍጥነት ተምረን በፍጥነት ነበር የምናርመው።

ከድክመት እንማር ነበር፤ በድልም የመርካት ሁኔታ እንዳይኖር እንማርበት ነበር። በድል መስከር አይገባም። የኢትዮጵያ መጻኢ ታሪክ ተጽፏል፤ ፕሮግራም ላይ ሰፍሯል። ከዚሁ በመነሳት ነው ‘ትግሉ ረጅምና መራራ ነው፤ ድል ግን አይቀሬ ነው’ ነው የተባለው።

ቢሲ፡ ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ርዓቱ በሙስና በስብሷል ይሉ ነበር። እርስዎና ቤተሰብዎ ግን በሙስና ትታማላችሁ ምን አስተያየት አለዎት?

ቦይ ስብሃት፡ ሙስና ቀስ እያለ የሚመጣ ችግር ነው። ሙስና አለ በሚለው ላይ ‘መጠኑ ትንሽ ነው፤ አይደለም መጠነ ሰፊ ነው’ የሚል ክርክር ነበር። ይብዛም ይነስም ምልክቱ ሲታይ ቶሎ መታረም ነበረበት። ኋላ ላይ እያደገ መጥቶ ሙስናን መጸየፍ እየደከመ መጣ።

ሙስና የሥርዓታችን ዋነኛው ጠላት ነው እየተባለም ጥንቃቄያችን ግን እየቀነሰ መጣ። በ2008 እናጽዳው ተብሎ ታወጀ። ጸረ ዴሞክራሲያዊ ጣባብ ብሔረተኝነት (ጠባብነትና ትምክህት ማለት ነው)፣ የሃይማኖት አክራሪነት ጠላቶቻችን ናቸው ብለን ለይተን አስቀመጥን።

ዋናው ተጠያቂ ደግሞ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር ነው፤ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትሉ ናቸው ብለን አስቀመጥን። ስለዚህ በፍጥነት መታደስ አለብን ብለን ወሰንን። ዶክተር ዐብይ ከተመረጠ በኋላም አሁንም በፍጥነጥና በጥልቀት መታደስ አለብን ካልሆነ ኢትዮጵያ አደጋ ውስጥ ነው ያለችው አልን።

ይህ ሳይተገበር ቀረ፤ እንዴት ቀረ? ማን አስቀረው? ተአምር ነው።

አንድን ነገር ሊሆን አይገባውም ካላልክ በስተቀር ይለመዳላ፤ አሁን እየተለመደ ነው። ይህ ጉዳይ እንዴት ጠፋ ስትል፤ እኔ ጠፍታ ዳናዋ ካልተገኘው የማሌዥያ አውሮፕላን ጋር ነው የማመሳስለው።

ቢቢሲ፡ እርስዎን በተመለከተ ሰለሚነገረውስ?

ቦይ ስብሃት፡ የዚያው አካል ነው። መጣራት አለበት እሱ እንዲሆን እኮ ነው እየተጠየቀ ያለው። ሙሰኛ ማነው? አቶ እገሌ ወይስ ወይዘሮ እገሊት? ደፍሮ የሚያወጣው ነው የታጣው። ወኔ የለም፤ ድፍረት እኮ ነው የታጣው።

የአገር ውስጥ ሙያተኞች ከውጭ ባለሞያዎች ጋር ሆነው እንዲሰሩ ‘ፕሮፖዛል’ ለአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ ደመቀ መኰንንና አቶ አባይ ወልዱ ቀርቦ ነበር። እንገባበታለን ተብሎ ቀረ።

ነጻና ገለልተኛ በሆነ አካል መጣራት ነበረበት። አንተስ ብትለኝ እዚያው ውስጥ መጣራት አለብኝ።

ቢቢቦይ ስብሃት በአሁኑ ሰዓት ምን ዓይነት ሚናና ሃላፊነት አለዎት?

ቦይ ስብሃት፡የእኔ እምነት የህወሓት/ኢህአዴግ ፖለቲካዊ ፕሮግራም ነው። አሁን አለ ወይስ የለም የሚለውን ቆይቼ እገልጸዋለሁ። በግል የህወሓት ደጋፊ ነኝ። ትግራይ ውስጥ ትግራይን፤ ከትግራይ ደግሞ ለኢትዮጵያ፤ ህወሓትን የሚተካ የፖለቲካ ኃይል የለም።

በመተዳደርያ ሕጉ መሰረት [የህወሓት] አባል አይደለሁም። እየተናገርኩ ያለሁትም ህወሓትን ወክዬ ሳልሆን እራሴን ወክዬ ነው። የህዋስ አባልም አይደለሁም፤ የአባልነት ክፍያም አልከፍልም።

ነገር ግን የህወሓት ደጋፊ ነኝ። ህወሓት ለትግራይ ህዝብ አማራጭ የለውም። የትግራይ ህዝብ ሀገርን እንዲጠቅም ካስፈለገ ህወሓት መተኪያ የለውም።

ቢቢሲ፡ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ ናቸው የሚለው ሃሳብ እያከራከረ ነው። በአንድ ወገን ህወሓት እንደ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች አዳራሽ ውስጥ የተመሰረተ ሳይሆን ከትግራይ ህዝብ አብራክ የተገኘ ነው። ይህን የሚቃወሙ ድርጅቶችና ግለሰቦች በበኩላቸው ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ ከሆኑ ታድያ ለምን አማራጭ ይል ያስፈልጋል? ምርጫስ ለምን ያስፈልጋል? በማለት ሚከራከሩ አሉ። እዚህ ላይ ያለዎትን አቋም ይንገሩኝ?

ቦይ ስብሃት፡ አሁን ባለው ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ህወሓት መተኪያ የለውም። በሌላ የፖለቲካ ድርጅት ሊተካ አይችልም። ህወሓት ደግሞ መጥፋት አለበት።

መጥፋት አለብኝ ነው ሚለው፤ መጥፋትም አለበት። ህወሓት የትግራይን እና የኢትዮጵያን ህዝብ ለመለወጥ ሚናዬን መጫወት አለብኝ ሲል፤ ራሱን ህወሓትን እና ኢህአዴግን ለማጥፋት ነው። ይህ ምን ማለት ነው?

የህወሓትን ህዝባዊ መሰረት ካየነው ገበሬው፣ ወዛደሩ፣ ንዑስ ባለሃብቱና አብዮታዊ ምሁሩ ናቸው። ዋነኞቹ ደግሞ ገበሬውና ወዛደሩ ናቸው። ገበሬው ከተለወጠ ህወሓት የእኔ መጥፋት ጸጋ ነው ብሎ ይቀበላል። ትግራይ የወዛደር እና የልማታዊ ባለሃብት መሆን አለባት።

ገበሬው ቢበዛ ከሦስት እስከ አራት በመቶ ነው መሆን ያለበት። ገበሬው ባለሃብት መሆን ይኖርበታል። ሰለዚህ የወዛደር ድርጅት በግራ፤ የሃብታም ባለሃብት ድርጅት ደግሞ በቀኝ፤ የህወሓት ወራሾች ሆነው መምጣት አለባቸው።

እነዚህ ድርጅቶች ገና አልተወለዱም። በትግራይ ተተኪ ድርጅት መምጣቱ ጸጋ ነው። ዛሬ ካልተወለደ ነገ መወረስ አይችልም። ሰለዚህ ወዛደሩን ወይም ባለሃብቱን መሰረት ያደረገ ድርጅት መምጣት አለበት። መደብ መሰረት ያላደረገ የፖለቲካ ድርጅት ጫጫታ ነው።

ስብሓት ነጋ

ቢቢሲ፡ ስለዚህ ተተኪው ድርጅት እስኪመጣ ድረስህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ ናቸው እያልን ነው?

ቦይ ስብሃት፡ አዎ አንድ ናቸው። ወያኔ ይህ ድክመት አለበት ተብሎ፤ ድርጅት ይመሰረታል እንዴ? ፖለቲካዊ ድርጅት ማለት ፖለቲካ ማለት ነው፤ ፖለቲካ ደግሞ መደብ ነው። ወያኔ ወዛደሩን እና ባለሃብቱን መሰረት ያደረጉትን የፖለቲካ ድርጅቶች እንደ ጸጋ ነው የሚያያቸው፤ ልጆቹ ናቸው።

ቢቢሲ፡ትግራይ ውሰጥ የሚንቀሳቀሱ አራት የፖለቲካ ፖርቲዎች አሉ። እነዚህ ፓርቲዎች እንዴት ነው የሚያዩዋቸው?

ቦይ ስብሃት፡ እኔ የፖለቲካ ፓርቲዎች አልላቸውም። እየነገርኩህ ነው፤ መደብ መሰረት ያደረገ ነው የፖለቲካ ፓርቲ የሚባለው። ይህ አውሮፓ ውስጥም ቢሆን ረዥም ዓመታት ያሰቆጠረ ትርጓሜ ነው።

ይህ መደብ ይህን ሥራ እየሰራ ነው ብሎ የሚመሰረት መሆን አለበት። ማህበራዊ መሰረት ከሌለው ፖለቲካዊ ፓርቲ አይደለም። ገዢ መደብን ተጠቃሚ ያደረገ ፓርቲ ነው። እራሳችንን አናሞኝ።

ቢቢሲ፡ ህወሓት/ኢህአዴግ ደርግን አሸንፎ ፌደራላዊ ርዓትንበመመስረቱ የሚያደንቁት ወገኖች እንዳሉ ሁሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያን አንድነት ከፋፍሏል ብለው የሚወቅሱት አሉ። የእርይታ ምንድን ነው?

ቦይ ስብሃት፡ መመዘኛ መቀመጥ አለበት። ስሜታዊ ሳትሆን መስፈርት አስቀምጠህ መመዘንና መስፈርት ሳይኖርህ አስተያየት መስጠት ይለያያል። መስፈርት ሳታስቀምጥ አስተያየት መስጠት መፈረጅ ይባላል። ስለዚህ መመዘን እና መፈረጅ ይለያያሉ።

ደርግን ሲታገሉ የነበሩ አብዛኞቹ ብሔራዊ ፓርቲዎች ከኢትዮጵያ የከፋ ሀገር የለም ይሉ ነበር፤ ልክ ናቸው። ፈታኙ ትግል የነበረው ኢትየጵያ ውስጥ አብሮ መኖር አይቻልም የሚለው ነው።

ህወሓት አብሮ መኖር ይቻላል፤ የሽግግር መንግሥቱ ላይ ቁጭ ብለን እንየው ብሎ ነው የታገለው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሕገ መንግጅት ለማጽደቅ የነበረው ችግር ለማመን የሚከብድ ነበር።

አብሮ መኖር ማለት ተአምር ማለት ነው ተባለ፤ አብዛኞቹ ፓርቲዎች ከኢትዮጵያ ለመነጠል ነበር ሲታገሉ የነበረው። ህወሓት ተአምር ይሰራል፤ አብረን እንኖራለን ብሎ ታገለ።

ስለዚህ ኢህአዴግ እዚህ ላይ አጥብቆ ባይይዝ ኑሮ ኢትዮጵያ የምትባል አገር አትኖርም ነበር። ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንድትኖር ህወሓትና የትግራይ ህዝብ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል።

ህወሓት ወደ ስብሰባ አዳራሽ ከመግባቱ በፊት ይለምናቸው ነበር። በህገ መንግሥት ላይ የተመሰረተች ሀገር ኢትዮጵያን በመፍጠር ወያኔን የሚደርስበት የለም።

ቢቢሲ፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት እንደነበር እና መፈንቅለ መንግት እንደተደረገ አንድ ስብሰባ ላይ ተናግረው ነበር። በለውጡ ሂደት ህወሓት የኢህአዴግ አባል እና አካል አልነበረም ወይ?

ቦይ ስብሃት፡ አሜሪካ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት እንደማትፈልግ የታወቀ ነው። የትኛውንም ሉአላዊ ሀገር እንደማትወድም የታወቃል። ልማታዊት ኢትዮጵያን እንደማትወድም የታወጀ ጉዳይ ነው። አሜሪካዊያን እገሌን አቅርቡት፤ እገሌን ደግሞ አርቁት ነው የሚሉት።

የእኛ አቋም ደግሞ ሉአላዊት ኢትዮጵያ እናንተ እንደምትፈልጓት አትሆንም የሚል ነበር። በዚህ አቋማችን ኢህአዴግን በጣም ይጠሉታል። ሁለተኛ ልማታዊ መንግሥትን አይወዱም። ልማታዊ መንግሥት ማለት ገበያ ላይ ድክመት ሲኖር ጣልቃ የሚገባ ማለት ነው።

እነሱ ደግሞ እሱን ተዉት፤ እኛ እንገባበታለን ይላሉ። ቤታችሁን ክፍት አድርጉት፤ እናንተ ያቃታችሁን ነገር እኛ እናደርገዋለን ይላሉ። ጥላቻቸውን ለረጅም ጊዜ ሲገልጹ ነበር። ‘ሶርያ ሂጂ ብለናት የማትሄድ ኢትዮጵያ፤ ቻይናን ምታስገባ ኢትዮጵያ ምን እናደርጋታለን’ ይሉ ነበር። ይህ አያስደስታቸውም።

ከዚያ በኋላ መሃል አዲስ አበባ ያለውን መንግሥት ብቻ ገልብጠህ ወዳጅ አታፈራም ብለው ስላሰቡ፤ ራሳቸውን የቻሉትን የክልል መንግሥታት ለመገልበጥ ተነሳሱ። በኋላም ከአሜሪካ ሲቀሰሩ የነበሩ እጆች ገቡ። እኛ ላይ ጣታቸው ይቀስሩ እንደነበር እናውቃለን።

ኢህአዴግን አፍርሱ ነበር የሚሉት፤ ነገር ግን ትዕዛዝ ከሰጡት በላይ የፌደራሊዝም ሥርዓቱንም ህገ መንግሥቱንም አፈረሰ።

ቢቢሲ፡ ማን?

ቦይ ስብሃት አዲስ አበባ ላይ ያለው መንግት።

ቢቢሲ፡እና ይህ ተግባር ህወሓትንስ አይመለከተውም?

ቦይ ስብሃት፡ ከደከምን በኋላ እኮ ነው የገቡት። አሜሪካ ላይም እኮ ማልቀስ የለብንም፤ ተጠቀሙበት እንጂ ዋናው ችግር የእራሳችን ውስጣዊ ድክመት ነው። ስለዚህ ውስጣዊው ድክመት ላይ ህወሓትም አለበት። ሁላችንም ድርሻችን እንውሰድ ነው እያልኩ ያለሁት። ውስጣዊ ድክመት ባይኖረን የውጭ ጠላት አይረብሸንም ነበር።

ቢቢሲ፡ እድሜዎት ከ80 በላይ ሆል። ከስልጣን በመነሳትዎ ደስ እንዳላለዎትና ቅር እንደተሰኙ ይነገራል። ለምን ማረፍ አልፈለጉም?

አቦይ ስብሃት፡ ከፓርቲው መሪነት ከተተካሁ በኋላ አንድ ሁለት ሳምንት ሳልመደብ ቆየሁ። ከዚያ በኋላ ስዩም መስፍን ”ሳንመድብህ ዘገየን” አለኝ። እኔ አሁን መጦሪያዬ ነው፤ የምን አይነት ሥራ ትሰጡኛላችሁ? አልኩት። ጡረታ ከወጣሁ በኋላም ዶክተር ዐብይ አግኝቶኝ ነበር።

”ጡረታ በመውጣትህ ቅር ይልህ ይሆን?” አለኝ። እኔ ከ23 ዓመት በፊት ጡረታ መውጣት ይገባኝ ነበር። 84 ዓመት ሆኖኝ ለምን በመንግሥት እጦራለሁ? ፖለቲካ ላይ ጡረታ የሚባል ነገር የለም። ልታጠፋም ልታለማም ትችላለህ።

ስለዚህ ከ23 ዓመት በፊት ጡረታ መውጣት የነበረብኝ ሰው እንዴት ጡረታ ወጣሁ ብዬ ቅር ይለኛል? ይህን አንተ እንጂ ሌላ ሰው እንደዚያ አይለኝም…አልኩት (ሳቅ)

ስብሓት ነጋ

ቢቢሲ፡ በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ የትግራይ ተወላጆች ከኢትዮጵያ ጋር ተከባብረን መኖር ካልቻልን ተገንጥለን ሀገረ ትግራይ መመስረት አለብን የሚል አሰተያየት ሲሰጡ ይሰማል። እንደ ነባር ታጋይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?

አቦይ ስብ መገንጠል ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው። ሆኖም መቅደም ያለበት፣ ለመገንጠል ምክንያት እየሆነ ያለውን ኃይል መታገልን ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ችግር እየፈጠረ ያለው ጠባብና ትምክህተኛ የልሂቅ ኃይል ነው። ይህን ኃይል አሸንፎ አብሮ የመኖር እድል ይሰፋል። ደግሞም በቀላሉ ተሸናፊ ነው። መገንጠል ከባድ ነው። ይህንን ኃይል ማሸነፍ ግን ቀላል ነው።

የትግራይ ህዝብ ፍላጎት ዴሞክራሲያዊ ልማዊት ኢትዮጵያን ማየት ነው። የአማራና የኦሮሞ እንዲሁም የሌሎች ህዝቦች ፍላጎትም ተመሳሳይ ነው። ይህንን የሚያግተው ትምክህተኛና ጠባብ ኃይል ነው። ከመገንጠል ይህን ኃይል መተጋል ይቀላል።

መገንጠል ብትፈልግም፤ ይህንን የጥፋት ኃይል ካላሸነፍክ አትችልም፤ ወደ ጦርነት ነው የምትገባው።

ቢቢሲ ቀደም ሲል በይፋም ሆነ በድብቅ ከፕሬዝዳንት ኢሳይያስ [ኤርትራ መንግት] ጋር ለመነጋገር ሞክራችሁ ነበር ይባላል። ምንድነው አስተያየትዎ?

አቦይ ስብሃት፡ እኔ አልሞከርኩም፤ ሞኝ አይደለሁም። ኤርትራ ውስጥ ከማን ጋር ነው የምትነጋገረው? ብቸኛው የተደራጀው ኃይል ያለው፤ ህግዴፍ [በስልጣን ያለው ፓርቲ] ነው። እሱ ደግሞ በፕሬዝዳንት ኢሳይያስ የሚመራ ነው። ኢሳይያስ “በአፍሪካ ቀንድ የጎበዝ አለቃ መሆን እችል ነበር። ላለፉት 27 ዓመታት፤ የወያኔ ሥርዓት ነው እንቅፋት የሆነብኝ” ነው የሚለው።

ለፕሬዝዳንት ኢሳይያስ፤ ኢትዮጵያ የመላው የአፍሪቃ ቀንድ በር ነች፤ ቀይ ባህር ደግሞ ሜዳው ነው።

ለእንዲህ ላለውና የጎበዝ አለቃ መሆን ለሚያምረውን ሰው፤ ‘አባክህን የጎበዝ አለቃ መሆን አምሮህ ነበር፤ አንቅፋት ሆንንብህ፤ ይቅርታ አርግልን እንክፈትልህ’ ብዬ ነው የምለምነው?

ቢቢሲስለ ዕርቅና ሰላም. . .

አቦይ ስብሃት ‘እኔ የጎበዝ አለቃ ነኝ፤ በሩን ክፈቱልኝ ልግባ’ አለ፤ ተዘጋበት። አንዳች የሚያነጋግር ጉዳይ የለንም።

ቢቢሲ ታድያ የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦች ግንኙነት እንዴት የሚሻሻል ይመስልዎታል?

አቦይ ስብሃትመጀመርያ የኤርትራ ህዝብ ነው ቤቱን ማስተካከል ያለበት። ለራሱ ያልሆነ መሪ ለሌላ ሆኖ፤ መነጋገር አይችልም።

ለዚህ ደግሞ መጀመሪያ ኤርትራ ውስጥ ያለው ነገር መስተካከል አለበት። ይሄንን የማድረግ ብቸኛው ኃላፊነት ደግሞ የኤርትራ ህዝብ ነው። ሁለተኛ፤ የእኛም ቤት መጠበቅ አለበት። ችግሩ በዚህ መንገድ ነው መፈታት የሚችለው።

ቢቢሲህወሓትን መውቀስ የሚፈልጉ ሰዎች ስብሃትን ነው ቀድመው የሚያነሱት። ህውሓት ዘረኛ ድርጅት ነውም ይላሉ። እስቲ የሚሰማዎትን በግልጽ ይንገሩኝ?

አቦይ ስብሃትይሄን እነሱን ብትጠይቃቸው ይሻላል ነው የምለው። እንደሱ የሚሉ ሰዎች እንዳሉ በስሚ ስሚ እስማለሁ፤ በእርግጠኝነት ባለማወቅ የሚሳሳት ሰው አለ። ይሄ ሆን ተብሎ ነው ወይስ ባለማወቅ የሚደርግ ስህተት ነው- መታየት አለበት።

መሳሳት ማለት፤ እውነተኛ መረጃ ያለማግኘት ነው። ሆን ብሎ የሚያስወራው ግን፤ አንድም የጨነቀው ጠላት ነው፤ አልያም የሌላ ተላላኪ ነው። ሰለዚህ ተሳስተው ነው እንደሱ የሚሉት ወይስ ተልከው፤ የሚለውን እኔ ማውቅ አልችልም። እነሱ ናቸው የሚያውቁት።

ቢቢሲመቀሌ የሌቦች መደበቂያ ሆናለች፤ ህወሓት እውነት ካላት ለምን በህግ የሚፈለጉትን ለህግ አታቀርብም?’ ‘እርሶን ጨምሮ ከፍተኛ የህወሓት አመራር መቀሌ ሂዶው ተሰብስበዋል’- የሚል ነገር ተደጋግሞ ይሰማል። ምንድን ነው ምላሽዎ?

አቦይ ስብሃትትግራይ ውስጥ ወንጀለኛ ተደብቋል የሚባለውን አልቀበለውም። የተከሰሰ ሰው እዚህ እንደሚኖርም አላውቅም። ዋናው ቁም ነገር ቅድም እንዳልኩህ ነው። በግምገማ ያስቀመጥናቸው ድክመቶች ነበሩ።

ሌባና ንጹሕ እንዲጣራ፤ ግፈኛና ፍትሃዊ ማን እንደሆነ እንዲታወቅ። ‘የሌብነት መንገድስ እንዴት መጣ?’ የሚለው እንዲጣራ ነበር የተባለው። ከማለቃቀስ የተሻለው መፍትሄ ይሄው ነው። ትግራይ ውስጥ እኔን ጨምሮ፤ በአገር ድህንነትና በመከላከያ የነበሩ በርካታ ሰዎች አሉ። ሲቪል የነበሩም እንዲሁ። እነዚህ ስለ አገራቸው ስለ ኢትዮጵያ ሲሰሩና ሲጨነቁ ነው የማውቀው።

እየከሰሱ ያሉ ሰዎች፤ ስለ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጨነቁ ከሆነ፤ ኢትዮጵያ ወደ አርማጌድዮን ያስገባታል የተባለው ችግር፤ እንደመጣ ያውቃሉ? ሌብነት፣ ግድያና እስራት፤ ኢህአዴግ ከዚህ በፊት አጥፍቻለሁ ካለው በላይ እየቀጠለ እንደሆነ አያወቁምን?

በክልሎች የመፈንቅለ መንግሥት ሲደረግ ምን ይሰማቸዋል? መሰረታዊ የአገሪቱ ችግር አውቀው ወደዚህ ቢመጡም እሺ እናጣራው ባልን። እውነተ ካለቸው፤ በአንድ ዓመት ከአምስት ወር ውስጥ የተካሄደው እስራት፣ የወደመ ንብረት፣ የጠፋው ብርና የተካሄደው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መጣራት አለባቸው።

ቢቢሲየኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን የሚሆን ይመስልዎታል?

አቦይ ስብሃትአሁን ባለው መንገድ የምንቀጥል ከሆነ አደገኛ ነው፤ ፌዴራላዊ ሥርዓቱን የማዳን ሥራ መሰራት አለበት። ቀጥሎ ኢህአዴግ የሚባል ድርጅት፤ ምን እንደሆነ እንዲፈተሽ መደረግ አለበት። አሁን ስልጣን ላይ ያለው እንደሆነ በህዝብ ተቀባይነት የለውም። ነገ ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንደሚገባ ግልጽ ነው።

ይሄ ሳይንሳዊ አባባል ነው፤ ደስተኛ ያልሁነ ሆኖም መብቱን የሚያውቅ ህብረተሰብ ይዘህ፤ በክልሎች ውስጥና በክልሎች መካከል የማይቀር እልቂት ይኖራል። ያልተደሰተ ህብረተሰብ አቅፈኽው ይተኛል እንዴ? አይተኛም።

LEAVE A REPLY