ጠ/ሚ/ር ዐቢይ መቀሌ የመሸጉትን የሕወሓት ሹማምንት ” ውስኪ ጠጪ ኢሕአዴጎች” ሲሉ ተሳለቁባቸው
‘መደመር’ የተሰኘው መጽሐፋቸው ምርቃ ሥነ ሥርዓት ማብቂያ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ለተቺዎቻቸው ከበድ ባሉ ቃላት የስላቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።
“የመደመር ፍልስፍናን የምናምን ሰዎች በውይይት ስለምናምን ምንም እንኳን ሰነዱ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ሙሉ ተጠንቶ ያለቀ ቢሆንም ላለመበተን ስንለማመን፣ ስንወያይ ከርመናል”ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ “አሁንም ውይይቱ አልተቋጨም በማለት አንዳንዶች ይህ የፓርቲ ውህደት መጨፍለቅ ነው፤ ኢትዮጵያን ከፌደራል ሥርዓት ወደ አሃዳዊ ሥርዓት የሚወስድ ነው በማለት የሚሰጡት መግለጫ በእኛ ውስጥ ታስቦና ታልሞ የማያውቀውን መርዶ ነው ያረዱን” ብለዋል። “እኛ ኢሕአዴጎች ለ30 ዓመታት አንድ መሆን ተስኖን እንዴት ነው ኢትዮጵያን አንድ ማድረግ የምንችለው?” ሲሉ በድርጅታቸው ውህደት ላይ ትችትን ለሚሰነዝሩ ወገኖች ጥያቄ አቅርበዋል።
“ኢሕአዴግ ባለፉት ዓመታት ሕገ መንግሥቱን በብዙ መንገድ ሲጥሰው ቆይቷል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር “ከዚያ ውስጥ አንዱ ሕገ መንግሥቱ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኀበረሰብ መፍጠፈር ቢልም እንኳን፤ ፓርቲው ኢትዮጵያን አንድ ሊያደርግ ቀርቶ ራሱ አንድ መሆን ተስኖት ቆይቷል” በማለት በይፋ ድርጅታቸውን አብጠልጥለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መደመር ፍልስፍና ከሆነና ፓርቲውን ወደ ውህደት ካመራ ወደ እልቂት እናመራለን የሚለውን ሀሳብም በማንሳት “እልቂትን ምን አመጣው?” በማለት ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ “አንድ ፓርቲ መሆንና መደመር የማያዋጣ ከሆነ ጀግና ሰው ውስኪውን አስቀምጦ ‘መባዛት’ የሚል አማራጭ ሃሳብ ይዞ ይመጣል፤ ያኔ መደመርና መባዛት የሚለውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ለጎን በማስቀመጥ ‘መደመር አያስፈልገንም’ ይላል እንጂ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ምን ያገዳድለናል?” ሲሉም መደመርና የኢሕአዴግን ውህደት ለሚያወግዘው ሕወሓት መልዕክት አስተላልፈዋል።
እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚቀጥለው አማራጭ መገዳደል ነው የሚለው አሮጌ አስተሳሰብ ነው በማለት ካጣጣሉ በኋላ፤ “እኛ ውስኪ ጠጪ ኢህአዴጎች፤ እባካችሁ ውሃ የናፈቀው ሕዝብ እንዳለ አትርሱ ይላል መደመር” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መቀሌ የመሸጉትን ባለሥልጣናት ተሳልቀውባቸዋል::
ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ ከሦስት ወር በፊት ወደ ትግራይ ተጉዘው የአክሱም ከተማ ነዋሪዎችን ባነጋገሩበት ወቅት በንጹሕ መጠጥ ውሃ ችግር ለዘመናት የተሰቃየው ሕዝብ ” እርስዎ ጉድጓድ ቆፍረው ውሃ ያውጡልን እኛ ፣ሐውልት እናቆምልዎታለን” ማለቱ አይዘነጋም::
“መደመር ሌብነትን ቀይ መስመር ነው ያለበት ምክንያት፣ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከሀገር ውጪም ቤት ደርድሮ ለህዝብ አስባለሁ ማለት ስላቅ ስለሆነ ነው። ሆቴል ተቀምጦ ዳቦ የራበውን ሕዝብ ለአንተ ቆሜልሃለሁ ማለት ተረት ተረት ነው ” ካሉ በኋላ በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ ወጣቶችም “የምንቀልድባችሁን ቀላጅ ፖለቲከኞች ወደጎን አራግፋችሁ አገራችሁን ጠብቁ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “በተሰጠው እድል መጠቀም ሳይችል፤ እድል ሲነጠቅ በትውልድ እድል መቀለድ አይቻልም” ሲሉም ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላልፈው፤ “ኢህአዴግ እንዴት ይዋሃዳል? ምን ስምና ግብር ይኖረዋል የሚለውን እኔ አልወስንም፤ እኔ ዲሞክራት መሪ ስለሆንኩ ለውይይት ሃሳቤን አቀርባለሁ፣ የተሻለ እና የኢህአዴግ ብዙኀን አባል ድርጅቶች ሃሳብ የሆነውን ግን በቅርቡ ለሕዝባችን እንገልፃለን” ሲሉ ተደምጠዋል።
‘መደመር’ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ተስፋ የሚያደርግባት ሀገር ትኑር ይላል በማለትም እያንዳንዱ ዜጋ ሀገሬን ልመራ እችላለሁ ብሎ የሚዘጋጅባት ለሁሉም እኩል የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠር ያስባልም ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ዓመት የሚካሄደውን ምርጫ በተመለከተም ሲናገሩ “ምርጫው የምናላግጥበት ሳይሆን ሀሳብ ይዘን ቀርበን፤ በሃሳብ ተወያይተን አብዛኛው ወጣት የሚያድግበት አማራጭ ተሰንዶ የምንወዳደርበት ብቻ ይሆናል” ሲሉ አሳውቀዋል።
“ኢትዮጵያዊያን በፍፁም መገዳደል የለብንም ሀሳብ ብቻ ነው ማፍለቅ ያለብን በሀሳብ ብቻ ነው መሟገት ያለብን፣ መደመር’ የተሻለ ሀሳብ ለመምረጥና ለመቀበል የኢትዮጵያዊያን ጭንቅላት ያንሳል ብሎ በፍፁም አያምንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ይህችን ታላቅ ሀገር መልሰን ታላቅ ብቻ ሳይሆን፤ የበለጸገች እናድርጋት ብሎ ያምናል ደግሞም ያደርጋል።” ሲሉ ዓላማቸውን በግልጽ አስቀምጠዋል::
ኢትዮጵያ የወደፊት ተስፋ እንዳላት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ብዙዎች የብልፅግና ጉዞው የሚደናቀፍና የሚቆም ይመስላቸዋል በማለት “ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው ኢትዮጵያ ትበለፅጋለች… ካለችበት ሁኔታ ከፍ ትላለች ኢትዮጵያ እንዳትበለጽግ የሚፈልጉ ይጠፋሉ አንጂ የኢትዮጵያ ብልፅግና አይጠፋም” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቅርቡ ያገኙትን የኖቤል ሽልማት አስመልክቶ ሲናገሩም “እኔ ከበሻሻ የወጣሁ፣ ጥሩ የምስክር ወረቀት እንኳ ያላየሁ ነኝ፤ ይህ የእናንተ ውጤት ነው ልትጠብቁት ይገባል ፣ አሁን በሌሎች ዘርፎችስ እንዴት ነው ኖቤሎችን የምናመጣው የሚለውን ማሰብ አለብን” በማለት ተናግረዋል::
1 ሚሊየን ኮፒ የታተመው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “መደመር” መጽሐፍ ተመረቀ
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ‘መደመር’ የተሰኘው የመጽሐፍ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ዛሬ አዲስ አበባ በሚሊኒየም አዳራሽ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ተከናውኗል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ ሚኒስትሮች፣ የክልል ባለሰልጣናትና የኪነጥበብ ባለሙያዎች መገኘታቸውን በምረቃ ስነ ሥርዓቱ ላይ ታዝበናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ባለቤታቸው ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ፣ እንዲሁም የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ መደመር የሚል ጽሑፍ የሰፈረበትን ኬክ በመቁረስ ነበር የመጽሐፉን መመረቅ ያስጀመሩት ። በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ከእንግዶቹ ጀርባ ተማሪዎች የተገኙ ሲሆን ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተማሪዎቹ መጽሐፉን በስጦታ መልክ አበርክተውላቸዋል።
ዛሬ ከተመረቅው መጽሐፍ ባሻገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥነ ሥርዓቱ ላይ አራት የታተሙ ፣ ሁለት ያልታተሙ መጽሐፎች እንዳሏቸውና የታተሙት መጽሐፎች ‘ዲርአዝ’ በተሰኘ የብዕር ስም እንደቀረቡ ገልፀዋል። ከመጽሐፎቻቸው መካከል ‘እርካብና መንበር’፣ ‘ሰተቴ’ የተሰኙ የሚገኙ ሲሆን ይህ መጽሐፍ በስማቸው የታተመ የመጀመሪያው ሥራቸው ሆኖ ተመዝግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባደረጉት ንግግር ላይ መደመር ነገን ያያል በማለት “የእኔና የእናንተ፣ የሁላችንም መጽሐፍ ነው” ካሉ በኋላ መጽሐፉን የሚያነቡ ሰዎች መተቸት ብቻ ሳሆን የተሻለ አማራጭ ሃሳብ በማምጣት ሀሳቡን እንዲያዳብሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
መደመር መነሻውም መድረሻውም ሰውና ተፈጥሮ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር አስተሳሰብ አገርኛ ነው ሲሉ ተናግረዋል። የሚሊኒም አዳራሽ ዝግጅትን ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ከመጽሐፉ መግቢያ ላይ በአማርኛና በኦሮምኛ በማንበብ ሲያስጀምሩም ተመልክተናል።
መጽሐፉ በዛሬው ዕለት ከ20 በላይ በሀገሪቱ ከተሞች እየተመረቀ መሆኑንም በወቅቱ ተገልጿል። ኢትዮጵያ ነገ የመጽሐፍ ምርቃቱን በተመለከተ ሰፊ መረጃ ከቀናት በፊት ማድረሱ አይዘነጋም:: ደራሲና ጋዜጠኛ አዜብ ወርቁ ከ’መደመር’ መጽሐፍ ቀንጭበው ያነበቡ ሲሆን አቶ ሌንጮ ባቲ ደግሞ ዳሰሳ አቅርበዋል።
ዋና ዋና ነገሮች የኢትዮጵያን መሰረታዊ የህብረተሰባዊ ግንኙነት ስብራት፣ የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሃብት ችግሮች የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ ችግሮች ይፈታል ወይ? በማለት በመጠየቅ ኦቦ ሌንጮ ጽሁፋቸውን ሲያቀርቡም በምረቃ ስነ ሥርዓቱ ላይ ተመልክተናል።
እንደ አቶ ሌንጮ ሃሳብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መጽሐፍ ውስጥ በስፋት የመደመር ፍልስፍና “ትልቁ የመደመር እሳቤ የማደራጀት አቅም አለው፤ የለውም የሚለው ነው” በማለት ዳሰሳቸውን ሲያስቃኙ ተጨባጭ የሆኑ ጉዳዮችን መጽሐፉ ይዟል ያሉት አቶ ሌንጮ መጽሀፉ አራት ዋና ዋና ምዕራፎች እንዳሉት ተናግረዋል።
ቀዳሚው ምዕራፍ የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች ምንድን ናቸው፣ ፖለቲካዊ ዕይታን ሦስተኛው መምጣኔ ኃብት፣ አራተኛው የውጪ ግንኙነትን ይዟል ያሉት የቀድሞ የኦነግ ሊ/መንበር ፤ መጽሀፉ እንደ ህዝብና እንደ ሀገር እንዴት ነው የምንቀጥለው የሚለውን ለመፍታት እንደሚሞክርና ደራሲው የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር ብቸኝነት ነው ሲል እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል። ይህ ብቸኝነት በአንድ ላይ ተሰባበስበን ችግራችንን ለመፍታት አቅም አሳጥቶናል ሲሉ የመደመርን አስፈላጊነት አስረድተዋናል።
ፉክክርና ትብብር ሚዛን አለመጠበቃቸውን በመጽሐፉ ላይ ተጠቅሷል ያሉት አቶ ሌንጮ፤ በአጠቃላይ ፍላጎትን፣ አቅምን፣ ሀብትን በማሰባሰብ እና በማከማቸት አቅም ፈጥረን ወደ ማካበትና ወደ ውጤት መምራት አለብን የሚል እይታ አለው ብለዋል። የተሰሩ መልካም ሥራዎችን ጠብቆ ማቆየት ያስፈልጋል የሚል ሀሳብ በመጽሐፉ ውስጥ መነሳቱን የጠቀሱት አቶ ሌንጮየመደመር እሳቤ ከዜሮ አይነሳም በማለት እስካሁን ለተሰሩት ትልልቅ ሥራዎች እውቅና ይሰጣል በማለት መሰረተ ልማት ላይ፣ ጤና ላይ፣ ትምህርት ላይ ለተሰሩት ሥራዎች እውቅና ይሰጣል ብለዋል።
የመደመር ግብ የዜጎችን ክብር ማረጋገጥ ነው ያሉት አቶ ሌንጮ ይህ ደግሞ ሀገራዊ አንድነት ሲኖር ነው ሲሉ፤ የብሔራዊ አንድነት ሊኖር እንደሚገባ ከዚያም ሁሉን አቀፍ የሆነና ዙሪያ መለስ ብልጽግና እንደሚመጣ ገልጸዋል።
የመደመር እንቅፋቶች ተብለው በመጽሐፉ ውስጥ ከተጠቀሱት ነጥቦችም መካከል በማንሳት ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ፖለቲካ፤ ያለ ችግርን ሁሉ ትናንትናና ዛሬ ላይ ማላከክ እንዲሁም በአስተሳሰብም በተግባርም የሚፈጸም ሌብነት ነው ሲሉ አቶ ሌንጮ ባቲ ተናግረዋል። ለእድገትና አብሮ ለመሆን ታታሪነት ወሳኝ ነው፤ ጉልበት እንኳ ባይኖር መልካም ፈቃድ መኖር አለበት ሲሉም ተናግረዋል
ዶ/ር ምሕረት ደበበ በበኩላቸው ይህ የመደመርን የሀሳብ ዘር የተሸከመ “የመደመር ፍሬ” ነው በማለት መጽሐፉ ሁለት ዕይታዎችን እንድናይ ያደርገናል በማለትም እነዚያም ሀሳብና ሰው መሆናቸውን ገልፀዋል። ሀሳብ በሰዎች ውስጥ አድረጎ በሰው ውስት ትልቅ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት አለው ብለው እንደሚያምኑም በንግግራቸው ላይ በግልጽ አስቀምጠዋል።
ዛሬ መቀሌ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ የዮንቨርስቲ ተማሪዎችና ቤተሰቦቻቸው በፖሊስ ተበተኑ
ህድሪ ሰብ’ የተሰኘ ማህበር ዛሬ ቅዳሜ መቀሌ ከተማ ውስጥ ሊካሄድ ተጠርቶ የነበረው ሠላማዊ ሰልፍ ህጋዊ አይደለም ተብሎ በፖሊስ መበተኑ ታወቀ። ይህ ሠላማዊ ሰልፍ የተጠራው የትግራይ ክልል የከፍተኛ የትምህርት ተቋም ተማሪዎች ችግር ያጋጥማቸዋል ወደተባሉ ቦታዎች እንዲሄዱ እንዳይደረግ በክልሉ መንግሥት ላይ ግፊት ለማድረግ እንደነበረ ሰምተናል።
ሠላማዊ ሰልፉን የጠራው ማህበር ሊቀ መንበር መሃሪ ዮሐንስ ስለሰልፉ ለማሳወቅ ለመቀሌ ከተማ ከንቲባ ጸሐፊ ደብዳቤ ማስገባታቸውንና ግልባጩንም ለዞኑ ፖሊስ ለማስገባት ሙከራ ባደረጉበት ወቅት አንቀበልም መባላቸውን ተናግረዋል። በተጨማሪም ሠላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ መንግሥት ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ማሳወቅ እንጂ የመፍቀድና የመከልከል ህጋዊ መብት የለውም ብለዋል።
ዛሬ ጠዋት ሠላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ሮማናት ተብሎ በሚጠራው የመቀሌ ከተማ አደባባይ መሰባሰብ በጀመሩበት ጊዜ ፖሊሶች ወደ ስፍራው መጥተው ሰልፉ ህጋዊ ስላልሆነ እንዲያስቆሙ መታዘዛቸውን በመግለጽ ሰልፈኞቹ እንዲበተኑ ማድረጋቸውን የሰልፉ አስተባባሪዎች ይናገራሉ።
አስተባባሪዎቹም ከፖሊስ ጋር ግብግብ መፍጠር ተገቢ ባለመሆኑ ሰልፉን ለማካሄድ ለሁለተኛ ጊዜ ለፖሊስ የማሳወቂያ ደብዳቤ እንደሚያስገቡ ነው የጠቆሙት። የመቀሌ ከተማ ምክትል ከንቲባ ስለተከለከለው ሠላማዊ ሰልፍ ተጠይቀው “ሰልፉ ሊከለከል አይገባም። ቢሆንም የጸጥታውን ሥራ በተመለከተ ማን ተጠይቆ ምን መልስ ተሰጠ? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ይገባል” ብለዋል።
የሠላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ደብዳቤውን ተቀብሎ ወደሚመለከተው አካል ያላቀረበ ግለሰብ ካለ እንቀጣለን” ያሉት አቶአቶ ብርሐነ፤ ለፖሊስ ቀርቦ ነበር የሚለው ቅሬታን ተከትሎ ፖሊስ የመከልከል መብት ስለሌለው ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል።
በትግራይ ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ተጠይቆ ሲከለከል በዚህ ሳምንት ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን፤ ከቀናት በፊት በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃትን ለማውገዝ በተመሳሳይ መቀሌ ውስጥ ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ጥያቄ ቀርቦ እንደተከለከለ ኢትዮጵያ ነገ መዘገቡ አይዘነጋም።
ታከለ ኡማ ከሥልጣን እንደሚነሱ በተነገራቸው መሠረት የጉዞ ትኬታቸውንና ፕሮግራማቸውን ሰርዘው ነበር
በያዝነው ሣምንት መጀመሪያ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ከሓላፊነታቸው እንዲነሱ መወሰኑና በምትካቸው ሌላ ሰው ሊሾም መሆኑ ተሰምቶ ነበር። ሐሙስ ዕለት የከንቲባው ጽህፈት ቤት “ከንቲባው በሥራ ላይ ናቸው” በማለት ከሥልጣን አለመነሳታቸውን በመግለጽ ወሬውን ‘ሐሰት ነው’ በማለት ካጣጣለ በኋላ የተለያዮ መረጃዎች ከቅርብ ምንጮች አፈትልከው በመውጣት ላይ ናቸው።
የተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ከዚህ ጉዳይ ጋር ቅርበት አለን የሚሉ አካላትን አናገርን በማለት ሲዘግቡ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ግን ምንም አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቦ ቆይቶ ነበር።
ከፍተኛ ተሰሚነት ያለው ቢቢሲ ኦሮምኛም በጉዳይ ላይ በቂ መረጃ ካላቸው ሰዎች አጣርቶ ምክትል ከንቲባው ከሓላፊነታቸው ሊነሱ መሆኑ “እውነተኛ እንደሆነ” ዘግቦ ነበር።
በወቅቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ያሉ መረጃዎችን መሰረት አድርጎ ለሚናገር ማንኛውም ግለሰብ፤ የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት ያካሄደውን ስብሰባውን እስከ አጠናቀቀበት ድረስ ጉዳዩ ያለቀለት ይመስል ዝምታን መምረጡና በፍጥነት አለማስተባበሉ ዜናው እውን ሊሆን የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው የሚል ግምት በኅብረተሰቡ ላይ ፈጥሯል።
ሐሙስ ዕለት አመሻሽ ላይ የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) ለሁለት ቀናት ያካሄደውን ስብሰባ ማጠናቀቁ በተገለፀ በጥቂት ሰዓት ውስጥ የከተማ አስተዳደሩ ዝምታውን በመስበር “ኢንጂነር ታከለ ኡማ ሥራ ላይ ናቸው፣ ከሥልጠጣናቸው ተነስተዋል ተብሎ የወጣው ወሬ ስህተት ነው” በማለት በማህበራዊ መገናኛ ገጹ ላይ አስፍሯል።መረጃው የወጣው የኦዲፒ ስብሰባ መጠናቀቁን ተከትሎ የኦዲፒ ጽህፈት ቤት ሓላፊ አቶ አዲሱ አረጋ የስብሰባውን መጠናቀቅ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ከገለጹ ከአንድ ሰዓት በኋላ ነበር።
ቢቢሲ ኦሮምኛ ያገኛቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት ምክትል ከንቲባው ከስልጣናቸው እንዲነሱ ከሳምንት ቀደም ብሎ ከበላይ ሓላፊዎች ጋር በመነገሩ ምክትል ከንቲባው አስቀድመው ይዘዋቸው የነበሩ ፕሮግራሞቻቸውን ሰርዘው ነበር። በተመሣሣይ ለአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ከሥልጣን መነሳታቸውን የሚገልፅ ምንም ዓይነት ደብዳቤ እጃቸው ላይ እንዳልደረሰ በዚህ ጉዳይ ላይ ቅርብ የሆኑ ሰዎችን በመጠየቅ አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል ከጥቅምት 8 በፊት ምክትል ከንቲባው “በእጆችህ ላይ ያሉትን ሥራዎች አጠናቅቀህ ጨርስ፤ ሌላ ሠው ያንተን ቦታ ይተካል” ተብሎ ተነግሯቸው እንደነበር ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች መረጃውን አድርሰው ነበር።
ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከሓላፊነታቸው መነሳት እንደማይፈልጉና ይህም ጉዳይ ለእርሳቸው ከተገለጸላቸው በኋላ ደስተኛ እንዳልነበሩ፣ በሥራቸውም ላይ ጫና ፈጥሮ እንደነበር በሥራ አጋጣሚ ለእርሳቸው ቅርበት ያላቸው ሰዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ባለፈው ማክሰኞ የአድዋ ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክትን ጨምሮ ሌሎች ሥራዎችን እያስመረቁና እያስጀመሩ መቆየታቸው ለዚህ ሌላው ማሳያ ነው የሚሉት እኚህ ግለሰብ የተለያዩ አካላት ‘በአንድ ጊዜ ይህንን ሁሉ ሥራዎች ለመስራት ለምን ተጣደፉ?’ የሚለው አስተያየት ተነሺነታቸውን ያመላከተ ነበር::
ምክትል ከንቲባው ማክሰኞ ዕለት ቢሯቸው ቆይተው እንደወጡና የከንቲባው ጽሕፈት ቤትና ሌሎች የከተማው አስተዳደር ቢሮዎች አካባቢ የነበሩ ሠራተኞች ላይ ይታዩ የነበሩ ስሜቶችም ከንቲባው ይለቃሉ በሚል የሀዘን ድባብ ያጠላበት እንደነበር ምንጮቹ አስታውሰዋል። ከንቲባው በመጨረሻ የከተማ አስተዳደሩ ፕሮግራም ላይ የተናገሩት መልዕክት የስንብት መሆኑን እንደተረዱ በስፍራው የነበሩና ቢቢሲ ያናገራቸው ሰዎች ይገልጻሉ።
“እርሳቸውን የማንሳት ውሳኔ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጣ ነው ብለን እንጠረጥራለን” ምንጮች ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በእርግጠኝነት ከአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባነታቸው ሊነሱ እንደነበር ተጨማሪ ማስረጃዎችን በመጥቀስ ያስረዳሉ።
ነሐሴ 27/2011 ዓ.ም የከንቲባው ጽህፈት ቤት በፌስ ቡክ ገፁ ላይ እደገለፀው ኢንጂነር ታከለ በኮፐንሃገን የዓለም አቀፍ ከንቲባዎች ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ ተጋብው ነበር። ይህ ጉባኤ ከመስከረም 28 እስከ ጥቅምት1/2012 ዓ.ም ድረስ ይካሄድ ለነበረው ጉባኤ ላይ ኢንጂነሩ ከልዑካን ቡድናቸው ጋር በመሆን ለመሳተፍ ይዘውት የነበረውን ዝግጅት እንዲቀርና የአየር ቲኬታቸውም እንዲሰረዝ መደረጉን ሰምተናል። በተመሳሳይ የሮማ ካቶሊክ ጳጳስ ለምክትል ከንቲባው ባደረጉት ግብዣ ወደዚያው ለማቅናት ይዘውት የነበረው ፕሮግራምም መሰረዙን ከምንጮቻችን ለመረዳት ችለናል።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፣ መጀመሪያ ወደ ስልጣን ሲመጡ ሁሉም በደስታ ስሜት አልተቀበላቸውም ፤ በከተማዋ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ የተለያዩ አካላት የእርሳቸውን ሹመት ተከትሎ የተለያዩ የተቃውሞ ድምጾችን ሲያሰሙ እንደነበር ይታወሳል። ምክትል ከንቲባው ግን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በማስጀመር የከተማዋ ነዋሪዎችን ቀልብ ለመሳብ የሚያስችሉ ሥራዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል።
ከእነዚህ መካከል ለከተማው ተማሪዎች ደብተርና የደንብ ልብስ በነጻ እንዲሰጥ ማድረጋቸው፣ በተለይ ደግሞ ለ300 ሺህ ተማሪዎች የዘወትር ምሳና ቁርስ ምገባ እንዲጀመር ማድረጋቸውም የከተማዋ ነዋሪዎችን ልብ ካሸነፉበት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ምክትል ከንቲባው ላይ ቅሬታ የነበራቸው አካላት መግለጫ ከማውጣት ባለፈ በግልፅ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ተደምጧል።
በከንቲባው ላይ ከውጪ ከሚሰማው ተቃውሞ በተጨማሪ በዙሪያቸው ካሉ የገዢው ፓርቲ አባላት ጭምር ለዚህ ቦታ ሲታጩ ጀምሮ መሾማቸውን የሚቃወሙ ግለሰቦች ስለነበሩ የሥልጣን ጊዜያቸው የተደላደለ እንዳልሆነ ይነገራል።
በአዲስ አበባ መስተዳደር ውስጥ የሚገኙ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ግለሰብ ደግሞ ሐሙስ ወደማታ አካባቢ በከንቲባው ጽህፈት ቤት ሰራተኞች መካከል የነበረውን ስሜት ሲገልፁ “እንኳን ደስ አላችሁ፤ ውሳኔው ተቀልብሷል” እየተባባሉ እንደነበር በመግለፅ ከንቲባው ተመልሰው በሥራቸው ላይ አንዲቆዩ መደረጉ የፈጠረውን ስሜት ይናገራሉ።
አርብ ዕለት ጠዋት የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ በስብሰባው ላይ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በተመለከተ በመግለጫው ስለምክትል ከንቲባው ጉዳይ ምንም ነገር አላለም። ይህ የውሳኔ ሃሳብ በኦዲፒ ስብሰባ ላይ ቀርቦ መቀየር አለመቀየሩን ለማጣራት ያደረግነው ሙከራ ሙሉ ለሙሉ ባይሳካም ለጊዜውም ቢሆን በቦታቸው እንዲቀጥሉ የተደረገው ከግምገማው በኋላ እንደሆነ አንዳንድ ጥቆማዎች ደርሰውናል።
ምክትል ከንቲባው በሥራ ላይ ናቸው የሚለው መረጃ የኦዲፒ ስብሰባ መጠናቀቁ ከተገለጸ ከአንድ ሰዓት በኋላ መውጣቱ ግን ጉዳዩ ተገጣጥሞ ነው ለማለት ግን እንደሚያስቸግር በርካቶች ይስማሙበታል። ከተለያዩ ወገኖች መነሳታቸውን በተመለከተ የተሰማው መረጃ ተከትሎ የቀረበው ተቃውሞ ውሳኔው እንዲቀለበስ ድርሻ እንደነበረው ግምታቸውንም የሚያስቀምጡ አልጠፉም።
ኢሕአዴግ ወደ ውህደት የሚያደርገውን ጉዞ በተመለከተ ምሁራን ማስጠንቀቂያ ሰጡ
ኢሕአዴግ ወደ ውህደት የሚያደርገው ጉዞ የ27 ዓመታቱን ፀረ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ በመቀየር ላይ ሊመሰረት እንደሚገባው ምሁራን አስጠናቀቁ።
በኢሕአዴግ ውህደት ጥናት ከተሳተፉት መሀል ረዳት ፕሮፌሰር አንተነህ ሙሉ ውህደቱ ጽንፈኝነትን በማለዘብ ህብረ ብሄራዊነትን ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
ከዓመት በፊት ውህደቱን በተመለከተ ጥናት ሲደረግ በስጋትነት ከታዩት ጉዳዮች መካከል የብሄራዊ ድርጅቶቹ የአስተሳሰብ አንድነትን የተመለከተው ጉዳይ አንዱ ነው ሲሉ አስረድተዋል። በወቅቱ አብዛኛዎቹ የጥናቱ ተሳታፊዎች ውህደቱ ቢፋጠን የተሻለ ድርጅታዊ አንድነት ይመጣል የሚል ዕምነት እንደነበራቸውም አመላክተዋል።
አዲስ ውህድ ፓርቲው የብሔራዊ ድርጅቶቹን ጠርዝ የለቀቀ አካሄድ ፈር በማስያዝ እና ልዩነቶችን በማጥበብ ወደ አንድ ያመጣቸዋል የሚል ዕምነት እንዳለም በውይይቱ ላይ ሰምተናል፡፡ ቀደም ሲል የኢሕአዴግን መዋሃድ የሚደግፉ አካላት አሁን ላይ ውህደቱ አሃዳዊነትን ያሰፍናል፣ ለፌደራል ሥርዓቱም ፈተናን ይደቅናል በሚል የሚያሰሙት ተቃውሞም መሰረተ ቢስ ነው ተብሏል።
የፖሊሲ ጉዳዮች ምሁሩ ዶ/ር አንዳርጌ ታዬ በበኩላቸው፥ የህዝብ ምሬት ያላስተማራቸው ቡድኖች በሚፈጥሩት የውስጥ ትግል ውህደቱን ለመፈተን ሲታገሉ እንደሚስተዋል፤ እንዲሁም የቀድሞውን ጸረ ዴሞክራሲ ቅርጽ እና ይዘት ይዞ መቀጠል እንደማይቻል እየታወቀ፣አፍራሽ ጉዞ የሚከተለው ቡድን እስከ መጨረሻ መታገሉን ይቀጥላልም ነው ያሉት።
ምሁራኑ ኢሕአዴግ በቅርጽና ይዘት ይቀየር ሲባል ህዝብን ከሚከፋፍል እና ፍረጃን መሰረት ካደረገው አስተሳሰቡ ይላቀቅ ማለትን ያካትታል ነው የተባለው። ኢሕአዴግ በሀዋሳ 11ኛውን ድርጅታዊ ጉባኤ ሲያካሂድም ወደ አንድ ውህድ ፓርቲነት እንደሚመጣ ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም። በዚህም ይዘትና ቅርጹን ቀይሮ ፓርቲ ሆኖ ለመዋሃድ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
ከአራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች ውጭ ያሉትን አጋር ድርጅቶች ወደ ውህድ ፓርቲነት ሲሸጋገሩም በማቀፍ እኩል ተሳታፊ እና ወሳኝ እንደሚያደርጋቸውም ተገልጿል። የኢህአዴግ የ30 ዓመታት የግንባርነት ጉዞ በአጭር ጊዜ በመውጣት ውህደቱን ማረጋገጥ አለበት የሚሉት ምሁራኑ፥ በውህደቱ የሚመጣው ለውጥ ሀገሪቱ ከዚህ ቀደም ከነበረችበት ችግር ለመውጣት ትልቅ ዋስትና እንደሚሆናት አስረድተዋል። ውህድ ፓርቲው ህዝብን አዳምጦ ለብሶቱ ምላሽ መስጠትን ሊያተኩርበት እንደሚገባም ምሁራኖቹ አበክረው መክረዋል።
ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር በባቡር ዘርፍ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመች
ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር በባቡር ዘርፍ አብረው ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል:: ስምምነቱን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል እና የቱርክ ስቴት “ሬል ዌይስ” ሥራ አስኪያጅ አሊ ኢሻን ኡዊገን በመፈራረም ስምምነቱን ዕውን አድርገውታል፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል፥ የባቡር ትራንፖርት መሰረተ ልማቶች፣ ትራንስፖርት ኦፕሬሽን እና የሰው ሃብት ልማት በመግባቢያ ሰነዱ ቅድሚያ የተሰጣቸው የትኩረት መስኮች እንደሆኑ በፊርማ ስነ ሥርዓቱ ላይ አስረድተዋል፡፡
የቱርክ ስቴት “ሬል ዌይስ” ሥራ አስኪያጅ አሊ ኢሻን ኡዊገን በበኩላቸው፤ ስምምነቱ ቱርክ በዘርፉ ያላትን የ163 ዓመት ልምድ ለኢትዮጵያ እንድታካፍል የሚያስችል ዕድል ነው ሲሉ አጋጣሚውን ጠቁመው ፤ ሀገራቸው በባቡር ትርንስፖርት ዘርፍ ግንባታ እና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራትን ትስስር የሚያጠናክር እንደሆነም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ከቻይና ጋር በባቡር ዘርፍ ከከተማ ፈጣን ባቡር ዝርጋታ እስከ አገር አቋራጭ የበባቡር መስመር ገጠማ ድረስ በርካታ ሥራዎችን ለመሥራት ስምምነት መፈጸሟ ይታወሳል::