በጃዋር የአመጽ ጥሪ የተነሳ ሦስት ሰዎች በሐረር ተገድለዋል
አወዛጋቢው ጃዋር መሐመድ ዛሬ ሌሊት በኦሮሚያ ክልል መንግሥት የተመደቡለት ጠባቂዎች የተነሱበት መሆኑን መግለጹን ተከትሎ አመጽ ቀስቃሽ የሆኑ መልዕክቶችን በማስተላለፉ፣በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ደጋፊዎቹ ለአመጽ አደባባይ ወጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትናንት በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በውጭ ዜግነት ባላቸው ሰዎች ሥር ስለሚንቀሳቀሱ ሚዲያዎች ባስተላለፉት ጠንካራ መልዕክት የተበሳጨውና፤ ራሱን “የኦሮሞ ብሔር ተሟጋች” አድርጎ የሚቆጥረው አቶ ጃዋር መሐመድ ንግግሩ እርሱን የሚመለከት እንደሆነ በማረጋገጥ “ሞቴም ኑሮዬም ከዚህ በኋላ ኦሮሚያና ፊንፊኔ ነው” በማለት “ትግሉ ይቀጥላል” ዓይነት የማነሳሻ ጥሪ አቅርቦ እንደነበር ይታወሣል፡፡
ጃዋር የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን አካሄድ በማጣጣል፣ የአክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኝነትን ማራገቡን ተከትሎ እርሱንበመደገፍና ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን በማውገዝ፣ ደጋፊዎቹ ከመጡባቸው ከተሞ መሐል ሐረር አንዷና ቀዳማዊ ናት፡፡ የፍቅርና የሠላም ከተማ የነበረችው ሐረር፣ በተለይም ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ ሕግና ሥርዓት የራቃት፣ የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ወርዶ፣ የኦነግ ዐርማ በይፋ የሚውለበለብባት የሽብር ከተማ ሆና ነበር የከረመችው፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የምክር ቤቱ ማብራሪያ ቀጥሎ የጃዋር መሐመድ ንቀት የተሞላበት ምላሽ እንደተሰማ ትናንት ከቀትር በኋላ በሐረር አውራ መንገዶች ላይ የተደራጁ ወጣቶች፤ የኦነግ አርማና የጃዋር መሐመድ ፎቶን በመኪኖች ላይ በስፋትና በይፋ በመለጠፍ ሲንቀሳቀሱ ታይተዋል፡፡
ዛሬ ማለዳ ደግሞ በግልጽ እንደታየው በሐረር አወዳይ ከተማ ለተቃውሞ የወጡ የጃዋር መሐመድ መልዕክተኞችና ደጋፊዎች ቅዳሜ ዕለት ተመርቆ ለንባብ የበቃው የጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድን “መደመር” መጽሐፍ በብዛት ሰብስበው ሲያቃጥሉ ታይተዋል፡፡ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በእሳት ሲያጋዩ ውለዋል፡፡
ኹከተኞቹ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ማድረጋቸውን ተከትሎ በሥፍራው ከነበሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር ግጭት ውስጥ በመግባታቸው ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አወዳይ የሚገኙ ታማኝ የዜና ምንጮቹን በስልክ ለማነጋገር የቻለው የኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር አረጋግጧል፡፡ በከተማዋ ባንኮች፣ መንግስታዊ መ/ቤቶች፣ ት/ቤቶች፣ ሱቆችና ምግብ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ የተዘጉ ከመሆናቸው ባሻገር በብጥብጡ ሦስት ሰዎች በጥይት ተመትተው ሕይወታቸው ማለፉን ሪፖርተራችን ካነጋገራቸው ምንጮች መረዳት ችሏል፡፡ በተነሳው ከፍተኛ ግጭት በመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይም ከፍተኛ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ከሞቱት ሦስት ሰዎች መሀል ሁለቱ በአውራ ጎዳናው ረብሻ ላይ ወዲያውኑ ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ አንደኛው ወደ ሆስፒታል ከተወሰደ በኋላ መሞቱ ተረጋግጧል፡፡
በባሌ ሮቤ ሥራና ትምህርት ተቋርጦ፣ ሕዝቡ አደባባይ ለተቃውሞ ወጣ
ሰሞኑን በአክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኞች አማካይነት ከፍተኛ የሆነ ዕንቅስቃሴ ሲደረግበት የሰነበተችው ባሌ ሮቤ ከተማ ዛሬ ወደለየለት ብጥብጥና ሠላማዊ ሰልፍ ተሸጋግራለች፡፡
ከዚህ ቀደም በኦነግ ዋና መናኸሪያነት የምትታማው ባሌ፣ ለወራት በተወሰነ ደረጃ መረጋጋት ቢታይባትም በተለይ ካለፈው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ፣ “መደ ወላቡ” የተመደቡ የዩንቨርስቲ ተማሪዎችን መግባት ተከትሎ፤ የአክራሪ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴው ዳግም ማገርሸቱን በከተማዋ የሚኖሩ ታማኝ የዜና ምንጮች ለኢትዮጵያ ነገ ገልፀዋል፡፡
በሮቤ ከተማ ውስጥ ቀደም ሲል ረገብ ብሎ የነበረው ይህ መሠሉ ጽንፍ የያዘ የብሔርተኝነት ስሜት፣ የተማሪዎቹን መምጣት ተከትሎ መዳ ወላቡ ዩንቨርስቲ የሚገቡ ተማሪዎች ላይ ራሳቸውን “ቄሮ ነን” ብለው የሰየሙ ቡድኖች፣ የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ የዩኒቨርስቲው መምህራንና ሠራተኞች፣ ፖሊሶች እና የተለያዩ ግለሰቦች ጥምረት በመፍጠር፤ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን የኢትዮጵያ ባንዲራን የሚገልፁ ቀለሞች ያለባቸውን ልብሶች፣ ደብተሮችና መጽሐፎች እየነጠቁ አቃጥለዋል፡፡
ይሄ አክራሪ ቡድን በአንገት ማህተባቸው ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከለርን በመስቀልም ይሁን በሌላ መንገድ የተጠቀሙተማሪዎችን እና የከተማዋን ነዋሪዎችን ማህተማቸውንእንዲበጥሱ በማስገደድ አስነዋሪ ተግባር ፈፅመዋል፡፡
ትናንት እና ዛሬ ደግሞ ሠሞኑን በከተማዋ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የታየውን አማርኛ ጽሁፍ የማጥፋት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ቀጥሎ በ”ሮቤ” ከተማ የሚገኙ የአማርኛ ጽሁፍ ያላቸው ማንኛውንም አይነት ታፔላዎች፣ ሙሉ በሙሉ ተነቅለው እንዲጣሉ ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ያለባቸው ማናቸውም መኪናዎችና ሰዎች ላይም ጉዳት የማድረሱ ነገር ዋነኛ ሥራ ሆኗል፡፡
ላለፉት ሀያ አራት ዓመታት በባሌ ሮቤ ከተማ የኖሩ ታማኝ ምንጮቹን በስልክ ያነጋገረው ሪፖርተራችን እንደገለፀው፤ አሁን ላይ “ጃዋር ልታሰር ነው፣ ሊገድሉኝ ነው ድረሱልኝ” ሲል ያስተላለፈውን መልዕክት ተከትሎ፤ ሙሉ ለሙሉ ት/ቤቶችና የመንግሥት ተቋማት ተዘግተው ደጋፊዎቹ አደባባይ በመውጣት ሁከት በመቀስቀስ ላይ እንደሆኑና፤ በቀጣይ ከኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ውጭ የሆኑ ኢትዮጵያውያን የጽንፈኝነት ፖለቲካው የጥቃት ሠለባ እንዳይሆኑ ብዙዎች ስጋት ላይ መውደቃቸውን ይፋ አድርጓል፡፡
የአዳማ ነዋሪዎች መንገድ ከዘጉት ቄሮዎች ጋር መጋጨታቸው ተነገረ
የጃዋር መሐመድን በፍርኃት የተለወሰ የውድቅት ሌሊት የድረሱልኝ መልዕክት ተከትሎ በአዳማ ለተቃውሞ ማልደው አደባባይ በወጡ ደጋፊዎቹና የከተማዋ ነዋሪ በሆኑ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ተወላጆች መሀል አለመግባባት ተፈጥሮ እርስ በርስ ግጭት ውስጥ መግባታቸውን በአዳማ የሚገኙ የኢትዮጵያ ነገ ምንጮች ካደረሱን ዜና መረዳት ችለናል፡፡
የጃዋርን ፎቶግራፍና እሱን የሚያወድሱ መፈክሮችን ይዘው የወጡ ጥቂት የአዳማ ነዋሪዎችና ከቆይታ በኋላ ከተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች የመጡ ቄሮዎች በጥምረት ወደ አዲስ አበባ የሚወጡ መንገዶችን በመዝጋት የተለመደ የሽብርና የተቃውሞ እንቅስቃሴያቸውን ሲያካሂዱ ታይተዋል፡፡
ጃዋርን በመስማት ለአመጽ አደባባይ የወጡ ቄሮዎች የወሰዱት መንገድ የመዝጋት ተግባር ያልተዋጠላቸው ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች መንገድ መዝጋቱን በማውገዝ ድርጊቱ እንዲቆምና ወጣቶቹም ተቃውሞቸውን በሌላ መንገድ እንዲያቀርቡ መጠየቃቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ውዝግብ ተፈጥሮ በሁለቱም ወገን ባሉ ጥቂት ሰዎች መሀል ጉዳት ሊደርስ መቻሉን የዜና ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
በከተማዋ ማለዳ ላይ በአንዳንድ ቦታዎች አማርኛ ጽሑፍ የሰፈረባቸውን የሆቴል፣ ካፌና ቡቲኮች ታፔላ በጥቂት ጎረምሶች ለመነቃቀል ተሞክሮ እንደነበር ያስታወሱት የአዳማ ነዋሪዎች በርካታ ወጣቶች እንቅስቃሴው በፍጥነት እንዲቆም ቆራጥ ዕርምጃ በመውሰዳቸው በከተማዋ ሊደርስ የነበረው ከፍተኛ ጥፋትና ዕልቂት እንዲወገድ ዓይነተኛ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል፡፡
ፌደራል ፖሊስ ጀዋር መሐመድ በፍርኃት ያስተላለፈው ጥሪ ከዕውነት የራቀ መሆኑን ገለጸ
በአክቲቪስት ጃዋር መሃመድ ላይ በመንግስትም ሆነ በፓሊስ በኩል ምንም ዓይነት ዕርምጃ እንዳልተወሰደ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ዛሬ ረፋድ ላይ ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፓሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው ጣሰው በሰጡት መግለጫ፤ አክቲቪስት ጃዋር መሃመድ ለደጋፊዎቻቸውና ለተከታዮቻቸው “ልታሰር ነው፤ጥቃት ሊደርስብኝ ነው” በማለት መልዕክት ማስተላፋቸውን አስታውሰው አወዛጋቢው ሰው ያሰራጨው መረጃ ግን ከዕውነታው የራቀ መሆኑን ያመላከተ ጥቆማ ሰጥተዋል።
በአክቲቪስት ጃዋር መሀመድ ላይ በመንግስትም ሆነ በፓሊስ በኩል ዕርምጃ እስካሁን አልተወሰደም ሲሉ የአክቲቪስቱን የፍርሀት መልዕክት አጣጥለዋል። “ግለሰቡ እንደተለመደው የየዕለት ተግባራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ” ሲሉም ኮሚሽነሩ በግልጽ አስቀምጠዋል።
ፖሊስ ለውጡን ተከትሎ፣ ወደ ሀገር የገቡ አክቲቪስቶች እና ፖለቲከኞች በሚኖሩበት አካባቢ ችግር እንዳያጋጥማቸው የጥበቃ ከለላ ሲያደርግ ቆይቷል ያሉት ሓላፊ፤ “በሀገሪቱ ያለው ሁኔታ እየተረጋጋ እና ሰላም እየተረጋገጠ በመምጣቱ፣ እንደማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል በሰላም መንቃሰቀስ እንደሚችሉ ከግንዛቤ በማስገባት የግል ጠባቂዎችን ስናነሳ ቆይተናል” በማለት የጃዋር መሐመድ ጠባቂዎች ዛሬ ሌሊት የተነሱበትን ምክንያት አስረድተዋል።
ለወደፊትም ባሉት አሠራሮች መሰረት አስፈላጊ በሆነበት እና ባልሆነበት ሥፍራን በመለየት ይህ ሥራ በፖሊስ ውስጥ ሲከናወን የነበረ ተግባር ነው፤ወደ ፊትም ይከናወናል በማለት የጃዋርን ኹከት ቀስቃሽ ጥሪ ያጣጣሉት ኮሚሽነሩ፤ “በመሆኑም በየትኛውም ፓሊስ ሆነ አካል የተወሰደ እርምጃ እንደሌለ፣ ኅብረተሰቡም ይህንን በአግባቡ እንዲያውቅ እንፈልጋለን” ካሉ በኋላ ወጣቶች፣ ኅብረተሰቡ እና የፀጥታ አካላት የተዘጉ መንገዶች እንዲከፈቱ በማድረግ ህብረተሰቡ በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀስ እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።