ምን አስቸኮለህ ነገ ትሰማዋለህ አትሉኝም። ለማንኛውም፤
ለምጣዱ ሲባል ትለፍ ብለን ያቀበጥናት አይጥ ምጣዱን ሰብራ እንዳትገላግለን። ደሞ አይጥ በምን አቅሟ ነው ምጣድ የምትሰብረው ትሉ ይሆናል። አይሆንም ትተሽ ይሆናልን ያዢ ነው ነገሩ። ዘንድሮ አይህንም የተባለው ሁሉ እየሆነ፤ ይሆናል ያልነው ሳይሆን እየቀረ ብዙ ታዝበናል። ዘመነ ግርንቢጥ።
በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ Blackstone’s ratio ወይም Blackstone’s formulation የሚባል ሃሳብ አለ። እሱም ምንድን ነው አንድ ንጹ ሰው ያለአግባብ ተይዞ ካለጥፋቱ ከሚማቅቅ አሥር ወንጀለኞች ቢያመልጡ ይሻላል (It is better that ten guilty persons escape than that one innocent suffer.)
እንግዲህ የሰው ልጅ ክብር ባገኘበት እና የሕግ የበላይነትም በሰፈነበት አለም ለንጹ ሰው ይሕን ያህል ጥንቃቄ ይደረጋል። በተቃራኒው መድሎ፣ ዘረኝነት፣ ሙስና፣ አንባገነናዊ ሥርዓት እና አፈና በነገሱበት አለም ደግሞ ለአንድ ወንጀለኛ መቶ ንጹሃን ሊታጨዱ፣ ሊጨፈለቁ፣ ሊረሱ፣ ደማቸው ደመከልብ ሊሆን ይችላል።
መቼም የፍትህ ሥርዓቱን በማዘመን እና ነጻ በማረግ ጎንበስ ቀና ሲሉ የከረሙት የለውጡ መሪዎች ለአንድ ወንጀለኛ ብዙዎችን ጭዳ የሚያደርገውን ሥርዓት መልሰው እንደማያሳዩን ተስፋ እናደርጋለን። የንጹሃን ደም ፍትሕ፣ ፍትሕ፣ ፍትሕ፣ ፍትሕ፣ ፍትሕ ትላለች።
ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ እና ሌሎች ዛሬ አብረውት የተፈቱ ንጹሃን ዜጎች ከጨለማዎቹ ክፍሎች ወጥታችው ከቤተሰቦቻችው ጋር ተቀላቅላው በማየቴ ደስታዮ የላቀ ነው። ዛሬ በሰጣችሁት ቃለ ምልልስ ላይ ከማዕከላዊም በከፋ ጨለማ ቤት ውስጥ ነበርን፤ ድብደባ የለም ንጂ ያላችሁት ነገር ልቤን ነክቶታል። ምክንያቱም የጠቅላይ አቃቤ ሕጉ መግደፍ በለመደው አፋቸው በቅርቡ ለመንግስት ሚዲያ መግለጫ ሲሰጡ ጨለማ እስር ቤት የለንም፤ እሱ ዱሮ ቀረ ብለው ነበር። ለነገሩ ከሦስት አመት በፊትም እኚሁ ሰው እስር ቤቶቻችን ውስጥ የማሰቃየት ተግባር አይፈጸምም፤ ተበደልን የሚሉት ውሸት ነው ብለው አይናቸውን በጨው አጥበው በግፉአን ስቃይ ይዘባበቱ ነበር።
ቸር አሰማን!