ኢትዮ ቴሌኮምን ኬንያና ደቡብ አፍሪካ በሽርክና ሊገዙት እንቅስቃሴ ጀመሩ
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት መሸጣቸው ቁርጥ መሆኑን ከመሰከረባቸው አራት መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶች መሀል አንዱ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮምን ለመግዛት የተለያዮ ሃገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተደጋጋሚ ጥያቄ በማቅረብ ላይ መሆናቸው ተረጋገጠ::
በሕወሓት መራሹ መንግሥት የሥልጣን ዘመን ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ “የምትታለብ ላም” በማለት መንግሥት መቼም እንደማይሸጠው የመሰከሩለት ኢትዮ ቴሌኮምን ለመግዛት የአፍሪካ ሀገራትም ደጅ መጥናት ጀምረዋል:: የኬንያ ትልቁ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ኩባንያ ሳፋሪኮም ፣ ከደቡብ አፍሪካ አቻው ቮዳኮም ጋር በሽርክና ኢትዮጵያ በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ልትሸጥ ካሰበቻቸው ሁለት የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃዶች ውስጥ አንዱን ለማግኘት እየሠራ መሆኑም ታውቋል።
የሳፋሪኮም ተጠባባቂ ሥራ አስፈጻሚው ማይክል ጆሴፍ ፤ በቮዳኮምና በብሪታኒያው ቮዳፎን በከፊል ባለቤትነት ሥር ያለው ኩባንያ፤ በመንግሥት የሚተዳደረው ኢትዮ-ቴሌኮምን በከፊል በመግዛት፤ ከፍተኛ ትርፍ ወደሚያስገኘው የኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ ለመቀላቀል ከውሳኔ አልደረሰም ቢሉም ሮይተርስ ግን ሁለቱ ድርጅቶች ተቋሙን ለመግዛት ቅድመ ስምምነት ከመፈጸማቸው ባሻገር እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን አረጋግጫለሁ ሲል ዘግቧል።
የቴሌኮም ሞገዱን ለማግኘት ከፍተኛ ወጪ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ጆሴፍ፤ ፈቃዱን ለማግኘት የሚፈልጉ ተቋማት የደለበ የገንዘብ ምንጭ ያስፈልጋቸዋል ካሉ በኋላ “ለአየር ሞገዱ በጨረታ መወዳደር ያስፈልጋል፣ ፈቃዱን ለማግኘት በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ወጪ እንደሚጠየቅ እየተነገረ ነው” በማለት ተቋሙ ያገኘውን የመጀመሪያውን ግማሽ ውጤት እና የተጓዘበትን የድርድር መንገድ በተዘዋዋሪ አረጋግጠዋል::
የእነ በረከት ስምዖን መከላከያን ለመስማት ፍ/ቤቱ ለህዳር 24 ቀጠሮ ሰጠ
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳን የመከላከያ ማስረጃ ለመስማት ለህዳር 24 ቀን 2012 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም በዋለው ችሎት፤ዐቃቤ ህግ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት አላቸው ብሎ ያስመዘገባቸውን ባለ 141 ገፅ ተጨማሪ የሠነድ ማስረጃዎች መርምሮ ብይን ለመስጠት ለዛሬ ጥቅምት 21 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ አይዘነጋም።
በዚህ መሠረት ፍርድ ቤቱ በዛሬው ዕለት በዋለው ችሎት ፣ተጨማሪ 141 ገፅ እና ከዚህ በፊት የተመለከተውን 666 ገፅ የሠነድ ማስረጃ መርምሮ ብይን ሠጥቷል።
ፍርድ ቤቱ ” አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርቡ” በማለት ብይን የሰጠ ሲሆን፤የመከላከያ ማስረጃቸውን ለመስማትም ለህዳር 24 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን በፍርድ ሂደቱ የታደሙ የኢትዮጵያ ነገ የባህርዳር ምንጮቻችን አድርሰውናል።
ዛሬ በዕስር ላይ የሚገኙት በአማራው (ብአዴን) ስም ተደራጅተው ለ27 ዓመታት ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ በዘለቀው የሕወሓት መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበሩት በረከት ስምዖን ባቀነባበሩት እና ከአምስት ዓመት በፊት ባስመሰረቱት የፈጠራ ክስ የግዮን መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ፍቃዱ ማ/ወርቅ የሰባት ዓመት ዕስርና የሰባት ሺኅ ብር ቅጣት ማክሰኞ ዕለት የተፈረደበት መሆኑ ይታወቃል::
አዲስ የሆነ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ተላከ
ሁሉንም የወንጀል አይነቶች ለመቀነስ ያስችላል ተብሎ የታመነበት አገር አቀፍ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩ ተሰማ::
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጽ/ቤት እንደገለጸው ከሆነ ፌዴራል መንግሥት ወንጀልን የመከላከሉ ሥራ የወንጀል መንስዔዎች እና ተስማሚ የመከላከያ እርምጃዎችን ለይቶ በሚያስቀምጥ መንገድ ሊተገበር፣ ሊመዘን በሚችል ስትራቴጂ መመራት ስላለበት አዲሱን ስትራቴጂ ማዘጋጀት ግድ ሆኗል ብሏል::
የስትራቴጂው ዋነኛ ዓላማዎች ለወንጀል ድርጊቶች መፈጸም ምቹ የሆኑ ሁኔታዎችን በማስወገድ እና የወንጀል መከላከል ሥራን ሊያግዙ የሚችሉ አሰራሮችን በመዘርጋት፣የወንጀል መከላከል ሥራ ማካሄድ፣ ለኀብረተሰቡ ዋና ስጋት የሆኑ፣ ልዩ ትኩረት የሚሹና ተጽዕኖ የሚፈጥሩ የወንጀል ድርጊቶችን አይነትና መንስኤዎቻቸውን መለየት፣ ድርጊቶቹን ለመከላከል የሚያስችሉ በመረጃ ላይ የተመሰረቱ ስልቶችን መንደፍ መሆኑም ተገልጿል።
በተጨማሪም ስትራቴጂው ተከታዮቹን ነጥቦች መሠረት ያደረገ ዓላማም አለው:-
*በወንጀል መከላከል ሥራ የባለድርሻና አጋር አካላትን ተግባርና ሓላፊነትን በማስቀመጥ ውጤታማ የሆኑ የወንጀል መከላከል ተግባራትን ማከናወን፣ መከታተል የሚያስችል እና የተቀናጀ አሠራር በመካከላቸው እንዲኖር የሚያግዝ ሥርዓት መዘርጋት::
*ወንጀል ጠል የሆነ ማኅበረሰብ በመፍጠር እና በሕዝቦች ንቁ ተሳትፎ የዳበረ ጠንካራ የወንጀል መከላከል ሥርዓት በመዘርጋት የህግ ማስከበር ተግባርን ማጠናከር::
*ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የወንጀል መከላከል ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችል አቅም መፍጠር፣የስትራቴጂውን አፈጻጸም የሚያስተባብር አካልን ተግባርና ሓላፊነት በማስቀመጥ ወንጀልን ከመለካለከል አንፃር ውጤታማ የሆነ የክትትልና ግምገማ ሥርዓት መቀየሰ።
ከላይ በተጠቀሱት ነጥቦች መነሻነት የወንጀል ስትራቴጂዉ ሲዘጋጅም ጠቅላላ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂና፣ የተለዩ የወንጀል አይነቶች በሚሉ በሁለት ዋና ዋና አይነቶች ላይ ተከፍሎ መዘጋጀቱንም ለማወቅ ችለናል።
በተለይም የሽብር ወንጀል፣ በመሰረተ ልማት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች፣ ከባድ የኢኮኖሚና ከገንዘብ ጋር ተያይዘው የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ በህገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር ማሻገር፣ በሰላምና ፀጥታ፣ በሴቶችና ህፃናትና መሰል ከ10 በላይ የሚደርሱ የወንጀል አይነቶች ላይ በመመስረት እንዲሁም በነዚህ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ ተግባራት ውስጥ ምን ምን ተግባራት ይከናወናሉ? ማን ምን ይሰራል? ማንስ ያስተባብራል? የሚሉት ነገሮች በውስጡ ግልጽ ባለ መልኩ እንዲቀመጡ ተደርገዋል።
አገር አቀፍ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ በፌዴራልና በክልል ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ዉይይት ተካሂዶበት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የተላከ ሲሆንየሚኒስትሮች ምክር ቤት ስትራቴጅውን ተመልክቶ ካጸደቀዉ በኋላ በሥራ ላይ ይውላል።
ፌደራል ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ያወጡት መግለጫ የሚጣረስ መሆኑን ቢልለኔ ስዮም ገለጹ
የትናንቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መግለጫ ከሰሞኑ በኦሮሚያ፣ ሐረሪ ክልሎችና እንዲሁም በድሬዳዋ አስተዳደር ተከስተው በነበሩ አለመረጋጋቶች፣ መፈናቀልና ጥቃቶች ጋር በተያያዘ 78 ሰዎች ብቻ መገደላቸውን ያረጋገጠ ሲሆን ከተለያዮ ወገኖች የሚሰማውን የሟቾች ቁጥር ከተገለጸው አሃዝ መላቅ የሚያጣጥል በቂ ማስረጃ ሊያቀርብ ግን አልቻለም ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬስ ሴክሪታሪ ጽሕፈት ቤትን ወክለው መግለጫውን የሰጡት ቢልለኔ ስዩም ከግጭቱ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ 409 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው ሲሉም ተደምጠዋ::የተጠርጣሪዎች ቁጥር ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ግን ጠቆም ከማድረግ ውጪ በዝርዝር ወይም በግምት ከማስቀመጥ ተቆጥበዋል። ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የወጣው መግለጫ ደግሞ የሟቾቹን ቁጥር 67 እንደሆነ የሚገልጽ እንደነበር ይታወሳል።
ቢልለኔ ስዩም ግጭቱ የሃይማኖትና የብሔር ገጽታ እንደነበረው ጠቁመው ለግጭቱ መባባስ በስም ያልጠቀሷቸው አካላትን ተጠያቂ ናቸው ሲሉ አስታውቀዋል። እርሳቸው በስም ያልጠቀሷቸው እነዚህ አካላት አሁን እየተደረገ ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ ይፈልጋሉ በማለትም ወቅሰዋቸዋል።
“እነዚህ ኃይሎች አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ተቀባይነት ማሳጣት የሚሹና በአገሪቱ ፍርሃት እንዲያረብ ፍላጎቱ የነበራቸው ናቸው” የሚሉት ቢልለኔ እነዚህ አካላት አጋጣሚውን ተጠቅመውበታል፤ አባብሰውታልም ሲሉ ይፋ አድርገዋል። ግጭቱ የገዢው ፓርቲ አሁን ለመዋሃድ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ የመጣ አጸፋዊ ምላሽ እንደሆነም አመላክተዋል።
“ጀዋር መሐመድ ጠባቂዎቼ ሊነሱ ነበር ባለበት ምሽት በትክክል የሆነው ምንድነው?” የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች የቀረበላቸው ቢልለኔ ስዮም ፤ በዚያ ምሽት ስለሆነው ነገር በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ማብራሪያ ስለተሰጠ እርሳቸው የሚጨምሩት እንደሌለ ተናግረው ፣ በወቅቱ ከፌደራል ፖሊስና ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን እርስ በርስ የሚጣረሱ መግለጫዎች ይወጡ እንደነበረ እና እርሳቸውም መታዘባቸውን ግን አልሸሸጉም።
ተጠርጣሪዎቹን በተመለከተ በመንግሥት በኩል ገለልተኛ አጣሪ ቡድን ገብቶ ጉዳዩን እንዲያጣራ ፍላጎት ይኖራል ወይ? ተብለው የተጠየቁት ቢልለኔ “አሁን ያለው ምርመራ ሂደት ላይ ስለሆነ እሱ የሚኖረውን ውጤት አይተን የሚያስፈልግ ከሆነ ወደፊት የምናየው ይሆናል” በማለት ምላሽ ሰጥተዋ::
በየጊዜው የሚከሰቱ ግጭቶች በኢንቨስትመንቱ የተሠማሩ ባለሃብቶችን አሽሽቷል ተባለ
በኢትዮጵያ የተፈጠሩ እና እየተፈጠሩ ያሉ አለመረጋጋቶች በኢንቨስትመንቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠሩ መሆናቸው ተነገረ ፡፡
ለኢኮኖሚያዊ ሽግግር የሃገር ውስጥ እና የውጭ ሃገር ባለሃብቶች ኢንቨስትመንት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት በመታወቁ ሀገሪቷ በሯን ለዘርፉ ክፍት አድርጋ ብትቆይም ፤ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተስተዋሉት ግጭቶች የፈጠሩት አለመረጋጋት ለዘርፉ ዕድገት ጋሬጣ ሆኗል:: በኢንቨስትመንት ለማስመዝገብ ከተያዘው ትልቅ ራዕይ ፣ እንዲሁም ባለሃብቶችን ደግሞ ከንብረታቸው ሲያለያይ ተስተውሏል።
የባለሃብቶች የመጀመሪያ ጥያቄ ደህንነት በመሆኑ አሳማኝ መተማመኛን ይሻሉ። የማኀበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አቶ አባድር ሰዒድ፥ ዕምነቱን ጥሎ ለልማት ወደ ሀገሪቱ የመጣ ባለሃብት ነገሮች በተቃራኒው ሲሆኑበት ወደ ሽሽት ማምራቱ የተለመደና አይቀሬ ባህሪይ ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡
የሚፈልጉትን ነገር ገዝቶ ለማምረት መቸገር፣ መሸጥ አለመቻል፣ የትራንስፖርት፣ የሰው ሃይል ዕጥረት፣ የመሰረተ ልማት ውድመት፣ የመንግሥት መዋቅሮች የአገልግሎት መጓደል እና የወንጀል መስፋፋት በጅምር ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ክፉ ደንቃራ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡
ተመሳሳይ ያለመረጋጋት ውጤቶች ባለሃብቶች መዕዋለ ንዋቸውን እንዳያፈሱ ቁጥብ ያደርጋቸዋል የሚል አሳማኝ ምክንያትም አለ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት አቶ ሃይሉ አዱኛ የቁጥብነታቸው መነሻ የኢንቨስትመንት ስጋት ስለሚጨምርባቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ባለሃብቶች ሰላም በሌለባቸው አካባቢዎች ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ ቢፈልጉ እንኳን ብድርና የመድን ዋስትና ለማግኘት እንደሚቸገሩም ጠቁመዋል::
በተለያዪ ዕስር ቤቶች ውስጥ የኖሩ ፣ 840 ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ዓረቢያ ተመለሱ
በሳዑዲ አረቢያ ዕስር ቤቶች ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት ታስረው የነበሩ 840 ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ወደ ኢትዮጵያመመለሳቸውን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ስደተኞቹ ሚኒስቴሩ ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ጋር ባደረገው ተደጋጋሚ ድርድርና ስምምነት መሰረት ወደ ሃገራቸው ሊመለሱ እንደቻሉ ነው የተነገረው።
ኢትዮጵያውያኑ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመጣው ሕገ ወጥ ስደት ወይም ቀይ ባህርን አቋርጠው የሳዑዲን ድንበር ሲሻገሩ የተያዙ እና በሳዑዲ ዓረቢያ ጂዛን ግዛት በሚገኙ የተለያዮ ዕስር ቤቶች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ መሆናቸውን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።
ከስደት ተመላሾቹ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ዮሃንስ ሾዴ ተገኝተው እንኳን ለሃገራችሁ አበቃችሁ ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል።
ዶናልድ ትራምፕን ለመክሰስ የሚያስችል ምርመራ እንዲደረግ ምክር ቤቱ ወሰነ
የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት በአነጋጋሪው የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ክስ ለመመስረት መደበኛ ምርመራ እንዲደረግ የሚያስችለውን ውሳኔ ዛሬ አስተላልፏል። ውሳኔው የምረመራ ሂደቱ የበለጠ ለህዝብ ክፍት የሚሆንበትን መንገድንም በዝርዝር ያስቀመጠ ነው ተብሏል።
በከፍተኛ ሁኔታ ዲሞክራቶች በተቆጣጠሩት ምክር ቤት ውስጥ ዶናልድ ትራምፕን በመከሰስ ሂደት ላይ ያላቸውን ድጋፍ በተመለከተ የተሰጠ ውሳኔ እንደሆነም የተገለጸ ከመሆኑ ባሻገር ፤ የፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት በበኩሉከፓርቲዎች ፉክክር አንጻር የተሰጠ ውሳኔ ነው በማለት የምክር ቤቱን የድምጽ አሰጣጥ በጽኑ ተቃውሞታል።
በምክር ቤቱ ውስጥ የላቀ ድምጽ ካላቸው የዲሞክራቲክ ፓርቲ ተወካዮች መካከል ፕሬዝዳንት ትራምፕ በ2016ቱ ምርጫ ካሸነፉበት አውራጃ የመጡ ሁለት ዲሞክራቶችናሪፐብሊካኖች በጠቅላላው ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል:: በድምሩ በምክር ቤቱ 232 አባላት የድጋፍ ድምጽ ሲሰጡ 196ቱ ፕሬዝዳንቱን ለመክሰስ የሚያስችለው ምርመራ መደረግ የለበትም ሲሊ ድምጽ ከመስጠት ባሻገር ለባለጸጋው ትራምፕ ያላቸውን አጋርነት አሳይተዋል::
የሪፐብሊካን ፓርቲ አባል የሆኑት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቀደም ሲል ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩትና በ2020 ምርጫ ተቀናቃኛቸው ሆነው የቀረቡት ዋነኛ ተፎካካሪያቸው የሆኑት የጆ ባይደን ወንድ ልጅ ላይ ዩክሬን የሙስና ምርመራ እንድታደርግ ግፊት አድርገዋል ተብለው እየተከሰሱ እየተወቀሱም ናቸው።
የዛሬው የምክር ቤቱ ውሳኔ በፕሬዝዳንቱ ላይ የሚያደርገውን ምርመራ ወደ አዲስ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል ተብሎለታል:: ይህ ሂደት በስተመጨረሻ ላይ ፕሬዝዳንቱ እንዲከሰሱባቸው ወደ ቀረቡ ሐሳቦች ሊያድግ እንደሚችል ነው የተገለጸው።
የአሜሪካ ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔን ተከትሎ ምርመራው በዚህ ሂደት የሚተገበር ከሆነ እና ምክር ቤቱ በፕሬዝዳንቱ ላይ የተጠቀሱት አንቀጾች ላይ ድምጽ ከሰጡበት የመጨረሻው ውሳኔ ላይ ለመድረስ የሚያስችለው ሂደት በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት (ሴኔት) የሚካሄድ እንደሚከናወን የተለያዮ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በመዘገብ ላይ ናቸው::
ለወንድሟ ስትል ሕይወቷን የሰጠችው ቻይናዊት የበርካቶችን ቀልብ ስባለች
ቻይናዊቷ ዉ ሁያን ላለፉት አምስት ዓመታት የኖረችው በቀን ሰላሳ ሳንቲም ብቻ ኑ ዓለም ላይ ትልቅ የመነጋገሪያ ጉዳይ ሆኗል። ሕይወቷን በሰላሳ ሳንቲም (ሁለት ዮዋን) ትገፋ የነበረው ቆጣቢ ለመሆን ፈልጋ ሳዬሆን ታማሚ ወንድሟን የማስተዳደር ግዴታ ያለባት ብቸኛ ሰው መሆኑ ደግሞ ብዙዎችን አላቅሷል።
ሰላሳ ሳንቲም (በአሜሪካ ዶላር ምንዛሬ ማለት ነው) በቂ ምግብ ሊገዛላት ያልቻለው የ24 ዓመቷ ምስኪን ቻይናዊት፤ በምግብ እጥረት ሳቢያ ለሕመም ተዳርጋ ሆስፒታል ገብታለች። ይህን በሀዘን አንጀት የሚያላውስ ዜና ያደመጡ የሀገሯ ዜጎች ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ዮዋን (114,000 ዶላር) አሰባስበው በዕርዳታ አበርክተውላታል።
ዉ ሁያን የተሰኘችው ይህች ወጣት የኮሌጅ ትምህርቷን እየተከታተለች፣ ጎን ለጎን ወንድሟን ለማስታመም ለዓመታትስትለፋና ስትደክም ቆይታለች። በያዝነው ወር መጨረሻ ላይ መተንፈስ አቅቷት ወደ ሆስፒታል የሄደችው ቻይናዊት፤ ክብደቷ 20 ኪሎ ግራም ብቻ ደርሶ እንደነበር እየተነገረ ይገኛል። ባለፉት አምስት ዓመታት በቂ ምግብ ባለማግኘቷ የልብና የኩላሊት ችግር እንደገጠማት ሀኪሞች አረጋግጠዋል።
የዚህች አነጋጋሪ ወጣት እናት የሞቱት የአራት ዓመት ልጅ ሳለች ነበር። አባቷ ደግሞ ተማሪ ሆና ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። እሷና ወንድሟን ከሚረዷቸው ዘመድ አዝማዶች የሚገኘው ገንዘብ በአጠቃላይ የአዕምሮ ህመም ላለበት ወንድሟ ህክምና ይውላል። በመሆኑም ቻይናዊቷ በቀን ማውጣት የምትችለው ሰላሳ ሳንቲም ብቻ ነው::በሰላሳ ሳንቲም ቃርያ እና ሩዝ ገዝቶ ከመብላት ውጪ ለዓመታት ምንም ዓይነት አማራጭ አልነበራትም።
ዉ ሁያን እና ወንድሟ የተወለዱበት የቻይናው ጉዋንዡ ግዛት በርካቶች በድህነት የሚማቅቁበት ስፍራ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይነገራል።
ወጣቷ በምግብ ዕጥረት ምክንያት ታማ ሆስፒታል ስትገባ ብዙዎች መንግሥት ተገቢውን ድጋፍ ሊያደርግላት ይገባ ነበር ሲሉ ቁጣቸውን ከማሰማታቸው ፤ ቻይና የኮሚኒስት ፓርቲ አገዛዝን 70ኛ ዓመት ለማክበር ከፍተኛ ገንዘብማፍሰሷን በምክንያትነት በመጥቀስ መንግሥትን ክፉኛ ተችተዋል።
በሌላ በኩል ዜናውን የሰሙ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዉ ሁያን የምትማርበት ኮሌጅ ለምን አልደገፋትም? ሲሉም ተቋሙን ተችተዋል:: ዕውነታውን ዘግይተው የተረዱ የክፍል ጓደኞቿ ወደ 40,000 ዩዋን (5,700 ዶላር) የደጎሙ ሲሆን፤ ከትውልድ ቀዬዋም ተጨማሪ ዕርዳታ ተደርጎላታል።
የቻይና መንግሥት በየወሩ ከ300 እስከ 700 ዩዋን እንደሚለግስም ቃሉን ሰጥቷል። አሁን በድንገተኛ አደጋ ድጋፍ 20,000 ዩዋን እንደሚሰጣትም አረጋግጧል። የቻይና ምጣኔ ሃብት በዚህ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ ቢያድግም በሀገሪቱ ድህነት ሙሉ በሙሉ ካለመወገዱ ፤ አገሪቱ እኩልነት የሰፈነባትም አይደለችም እየተባለ ነው።
ከሁለት ዓመት በፊት በወጣ መረጃ መሠረት 30.46 ሚሊዮን ቻይናውያን ከድህነት ወለል በታች ሕይወታቸውን ይመራሉ። ቻይና በ2020 ድህነትን እቀርፋለሁ ብትልም፤ ከገቢ አንጻር በዜጎቿች መካከል በጣም የተራራቀ ልዮነት ያለባቸው አገሮች ተርታ ተመድባለች::