የአጋች ታጋች ድራማ || ሙሼ ሰሙ

የአጋች ታጋች ድራማ || ሙሼ ሰሙ

የስቶክሆልም ሲንድረም በመባል የሚታወቀው የአጋች ታጋች ድራማ ዓለም አቀፍ የስነ-ልቦና ጠበብትንና የፍልስፍና ምሁራንን ትኩረት በእጅጉ የሳበና እስካሁንም ድረስ እያወዛገበ የሚገኝ ባንክ በመዝረፋ ተጀምሮ በስነ ልቦና ቀውስ የተጠናቀቀ ክስተት ነው፡፡

ዛሬ ላይ ዘጠኙ ክልሎች በሕገ-መንግስታቸው አማካኝነት ያቋቋሙት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሪፖብሊክ መንግስት በየክልሉ የተደራጁና ሕጋዊ መሰረት የሌላቸው ሃይሎች በፈጠሩት የሆስቴጅ ድባብና ተጽእኖ ስር መውደቁ እየታየ ነው፡፡ ይህ ሳያንስ ደግሞ ከፍተኛ አመራሮቹ የፌደራል መንግስታቸውን ሆስቴጅ ካደረገው ሃይል ጋር አይዲዎሎጂ በመጋራትና አጀንዳ በመቀባበል የትግልና የትብብር ስምምነት ማረጋገጫቸውን በየሚዲያው ሲለዋወጡ ማየት የአጋች ታጋች ድራማው የስቶክሆልሙን ሲንድረም እንዳስታውስ ያደረገኝ ክስተት ነው።

እ.ኤ.አ. ኦገስት 1973 ዓ. ም ስዊድን ውስጥ አራት የስቨርዥ ክሬዲት ባንክ ሰራተኞች ለስድስት ቀን ይታገታሉ፡፡ አጋቻቸው በመሳርያ የታጋቾችን ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ቢጥለውም፣ ታጋቾች ግን ከሕጋዊ ተቋምና ከፖሊስ ሃይል በተቃራኒው በመቆም እጅግ ከፍተኛ በሆነ ንቃት፣ ለታጋች ስነ ልቦናዊና ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ እገታ እስኪከሽፍ ተባብረውታል፡፡ አንዷ ታጋችም በወቅቱ የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስቴር ለነበሩት ኦሎፍ ስልክ በመደወል “ከአጋች ተግባር ይልቅ” የሚያሰጋቸው ሕግ አስከባሪው ሃይል ሕግ ለማስከበር ሲሞክር የሚያደርስባቸው ጉዳት መሆኑን አሳሰባ ነበር፡፡
ሌላው የስቶኮልም ሲንድረም ዓይነተኛ መገለጫ ሆኖ የሚጠቀሰው በኢራን የሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ ሰራተኞች ላይ የተፈጸመው እገታ ከተጠናቀቀ በኃላ አንዳንድ ታጋቾች ከአጋቾቹ ጋር የስነ ልቦናና የአይዲዮሎች ጥምረት በመፍጠር፣ መታገታቸው ለነጻነትንና መብትን ለማስከበር የተወሰደ እርምጃ ነው በሚል ለአጋቾች የአይዲዮሎጂና የሞራል ድጋፍ ማድረጋቸው ይጠቀሳል፡፡ ሌሎችም ምሳሌዎች መጨመር ይቻላል፡፡

ላለፉት ሶሰት ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ምህዳር ውስጥ የተለያዩ ሃይሎች በሃይል ሚዛን አሰላለፍ ዙርያ እርስ በርስ በመጎሻሸምና ትከሻ ለትከሻ በመገፋፋት በሕዝብ፣ በሃገርና በመንግሰት ሉዕላዊነት ላይ የአጋች ታጋች ድራማ ሲተውኑና በሰው ልጅ ሕይወት ላይ ሲቆምሩ መክረማቸው ይታወቃል፡፡ ጫናው በበዛና ደም በፈሰሰ ቁጥር መንግስት ሕጋዊ ርምጃን ከመውሰድ ይልቅ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ያለገደብ አስከብራለሁ የሚል መከላከያ ሲያቀርብ ይደመጣል፡፡ ሃቁ ግን፣ መንግስት በታጋችነት የተጽእኖ ድባብ ስር በመወድቁ ሕግ ማስከበር እየተሳነው እንደሆነ የሚያሳየው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በየክልሎች በተለይ መጤና አናሳ ተብለው የተፈረጁ ዜጎች ላይ የሚፈጸመው አሰቃቂ ግድያና እየወደመ ያለው ንብረት ማሳያ ነው፡፡

በፖለቲካ ውስጥ በስልጣን ላይ ለመቆየትም ሆነ ስልጣንን ለማጣት የሃይል ሚዛን ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ሃገር አቀፍ ድጋፍ ያለው አካል የሃይል ሚዛን ላይ ትርጉም ያለው ሕጋዊ ካሳደረ በሕጋዊ መንገድ ድርድር ማድረግ ተቀባይነት ያለው አካሄድ ነው፡፡ ሃገር አቀፍ ተቀባይነት የሌለውና የአንድ አካባቢ ድጋፍ ብቻ ያለው አካል የሃይል ሚዛኑን ሲቆጣጠር ጉዳዩ የቡድኑና የወኪሎቹ ብቻ ስለሚሆን ክልሉ በስልጣኑ ልክ በሕጋዊ መንገድ ችግሩን ሊፈታው ይገባል፡፡

የፌደራል መንግስት ውክልና ሃገራዊ መሆኑ እየታወቀ አካባቢያዊ የአደረጃጀት መስመርን ተከትሎ በፌደራል መንግስት ውስጥ ካሉ አንድንድ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ስርዓቱን ተጽእኖ ስር የመጣሉና ሆስቴጅ የማድረጉ አዝማሚያ ለሃገር አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ የፌደራል መንግስት በዚህ መልኩ የሚታገትበት እድል እየሰፋ የሚሄድ ከሆነ ሁሉም ክልሎች ለጋራ ህልውናቸው ሲሉ በሕጋዊ መንገድ እገታውን የማምከን ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ዜጎች አንዳችም ውክልና ባልሰጡት አካል ተጽእኖ ስር መወድቅና መታመስ የለባቸውም፡፡ ከዚ አኲያ አሁን ያለንበት ተጫበጭ እውነታ የሚያሳየን ግን አንድ ፓርቲ የሁሉም ክልሎች መንግስት የሆነ እኪመስል ድረስ በፓርቲና በፌደራል መንግስት መካከል የተፈጠረውን የመሪነት፣ የተመሪነትና የኃላፊነት መደበላለቅን ነው፡፡ ይህ የሚያመለክተው ደግሞ ሁሉም ክልሎች በጋራ የመሰረቱት የፌደራል መንግስት በአንድ ፓርቲና ፓርቲው ውስጥ ከሚገኙ ቡድኖች ጋር በተቀናጁ ሕጋዊ መሰረት የሌላቸው ሃይሎች ሆስቴጅ መሆኑን ነው፡፡

በዓለም ላይ በስቶክሆልም ሲንድረም የተጠቁ ግለሰቦች ካልሆኑ በስተቀር በሆስቴጅ ስነልቦና ተጠልፈው በአጋቾቻቸው ስነልቦናዊ ድባብ ውስጥ በመውደቅ ከአጋቾቻችን ጋር አብረን እንቆማለሁ ወይም አብረን እንሰራለን የሚሉ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችና አካላት የተከሰተባት ሃገር ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አትቀርም፡፡ ሰሞኑንን የተከሰተው የአጋች ታጋች ድራማም የመንግስት አካላት ልክ እንደ ስቶክሆልሙ ሲንድረም የበዳይ ተበዳይ የጋራ ትብብር የታወጀበትና ከተለመደው የመንግስትና የሕዝብ መስተጋበር ማዕቀፍ የወጣ አካሄድ የተንጸባረቀበት ነው፡፡ በመርህ ላይ ሳይሆን በወንድማነችነት ጭምር የተሞካሸው የትብብርና አብሮ የመስራት ጥሪው ከመንግስትና ከሕገ-መንግስታዊ የአስተዳደር ስርዓት ያፈነገጠና በአንድ አካባቢ ያውም ከጥቂት ቡድን ውጭ የአብዛኛውን ህዝብ ፍላጎት የተጻራሪ አካሄድ እንደሆነ ከሞላ ጎደል መገምገም ይቻላል፡፡

በሕገ መንግስታዊ ስርዓት አማካኝነት በውክልና ሃገር እያስተዳደረ ያለ መንግስት ባለበት በዚህ ወቅት ኢ-መደበኛ በሆነ አደረጃጀት የሚፈጠረን አለመረጋገት ተገን በማድረግ ሕገ መንግስታዊ ጥበቃ ያለውን የመንግስት ሞኖፖሊ ኦፍ ቫየለንስና ሕገ መንገስታዊ ሉዓላዊነቱን አደጋ ላይ ከሚጥልበት በተለይ ደግሞ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ውክልና ከሌለው ሃይል ጋር የዓላማ፣ የሞራላ፣ የአይዲዎሎች፣ የአንድነትና የድጋፍ ትስስር እየፈጠሩ፣ ከክልል ባሻገር ኢትዮጵያን እንደ ሃገር በጥቅሉ እንዴት ለመምራት እንደታሰበ መረዳት አዳጋች ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በመንግስት ላይ እምነቱን የጣለው ሕዝብ በአንድ ቡድን የተጽእኖ ድባብ ስር የፌደራል ስርዓቱ መውደቁ ሉዕላዊነቱን የሚዳፈር ጉዳይ አደርጎ በመውሰድ ሃገሪቱን ወደ ማንቆጣጠረው ትርምስ ሊመራት እንደሚችል ከጎረቤት ሃገሮች ለመማር አለመቻሉ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡

በጥቅሉ ሂደቱን ስናጤነው መንግስት ሕጋዊነት በሌለው አካሄድ የሚፈጠርን ተጽእኖ መቋቋም አቅቶት በተጽእኗቸው ድባብባ ስር እንዲወድቅ ምክንያት ከሆኑት ሃይሎች ጋር የዓለማና የግብ አንድነት ስላለን እንተባበራለን የሚለው አቋም የስቶኮልሙ ሲንድረም ዓይነት ቀውስን ያመላክታል፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ በሕጋዊም ሆነ በሕግ አልባ መንገድ ፍላጎትን ለመጫን በጥምረትና በመናበብ የሚሰራ ሃይል እንዳለ መገመት ተገቢ ነው፡፡ ይህ ክስተቱ በሁሉም የፌደራል መንገስታት ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ሲሆን፣ ስነ ልቦናዊ ቀውሱ ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ አዲስና አስደማሚ የመንግስት፣ የሕዝብና የኢ-መደበኛ ሃይል አሰላለፍና ግንኙነት በምሁራን ዘንድ ውይይትና ክርክር ሊቀሰቅስ የሚገባው ጉዳይ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡

LEAVE A REPLY