የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 24 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 24 ቀን 2011 ዓ.ም

ቅዱስ ሲኖዶስ ለአማኞች በሙሉ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ማሰልጠኛ እንዲከፈት ወሰነ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ የዕምነቱ ተከታዮች በቋንቋቸው ማስተማርና ማገልገል እንዲቻል በሁሉም የአፍ መፍቻ ቋንቋ ማሰልጠኛ ማዕከል እንዲከፈት ውሳኔ አሳልፏል። ከጥቅምት 11 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ በመስጠት ተጠናቋል።

በሀገሪቱ በተለያዩ ክልሎች የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች በብዛት የሚገኙ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት እና የዕምነቱ ተከታዮች በቋንቋቸው ማስተማርና ማገልገል እንዲችሉ፣ በቀጣይ በሁሉም በአፍ መፍቻ ቋንቋ የማሰልጠኛ ማዕከል ለመክፈት መወሰኑን ቅዱስ ሲኖዶሱ ይፋ አድርጓል።

የሀገር ሰላምን ጉዳይ አስመልክቶ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የሰው ሕይወት መጥፋትና የዜጎች ንብረት መውደም ቅዱስ ሲኖዶሱን በእጅጉ ያሳዘነ መሆኑንም አንስቷል። ስለሆነም መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ሰላምን እንዲያስከብር፣ የዜጎች ደህንነት እንዲጠበቅ እንዲያደርግ፣ የተፈናቀሉትም ወደቀያቸው እንዲመለሱና ለጠፋው ንብረታቸው ማቋቋሚያ እንዲደረግላቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተለይም በክርስቲያኖችና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ እየደረሰ ያለው ስደትና መከራ ጐልቶ እየታየ በመሆኑን የገለጸው ሲኖዶሱ፥ መንግስት የጥፋቱ መልዕክተኞችን በሕግ እንዲጠየቁ እንዲያደርግ አሳስቧል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሀገራችንና በአፍሪካ ጭምር ላበረከቱ የሰላም ተልዕኮ አስመልክቶ ዓለም አቀፍ የኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸው አድናቆቱን ገልጿል።

ሀገሪቱ በጀመረችው የልማት አቅጣጫ በስፋት ለማስቀጠልና በተለይም ዜጎችን ከድህነት ለማላቀቅ በእጅጉ ተስፋ የተጣለበት የዓባይ ግድብ በተያዘው የግንባታ ሥራ ተፋጥኖ ግድቡ እንዲጠናቀቅና ሥራ እንዲጀምር ለማስቻል መላው የሀገራችን ሕዝቦች አስፈላጊውን ዕገዛ በማድረግ እንዲቀጥሉ ቅዱስ ሲኖዶስ መክሯል።

የ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ በጀት አስመልክቶ ከበጀትና ሂሣብ መምሪያ በቀረበው እቅድ ላይ በመነጋገር የቀረበው በጀት ላይ ማሻሻያ በማድረግ የ2012 ዓ.ም በጀት በማጽደቅ በሥራ ላይ እንዲውል ከመወሰኑ ባሻገር በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች እየታየ ያለው ችግር እንዲያበቃና እግዚአብሔር አምላክ ምህረቱን እንዲሰጥ የተጀመረው ሱባኤ እንዲቀጥል መወሰኑንም አስታውቋል::

የመጀመሪያው የሳይበር ደህንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት ዛሬ ተጀመረ

በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አማካይነት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የተዘጋጀው አንደኛው ብሄራዊ የሳይበር ደህንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት ዛሬ በይፋ ተጀምሯል። “ትኩረት ለሳይበር ደህንነት” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የስብሰባ አዳራሽ ነው እየተካሄደ ያለው።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ኤፍራህ አሊ በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንትን የማክበር ዓላማ በዘርፉ ያለው ንቃተ ህሊናን ለማሳደግ ያለመ እንደሆነ ተናግረዋል። በሀገሪቱ ከዓመት ዓመት እየደረሱ ያሉት የሳይበር ጥቃቶች እየጨመሩ በመምጣታቸው ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ከምን ግዜውም በበለጠ ለሳይበር ደህንነት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ተብሏል።

የሰላም ሚንስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘይኑ ጀማል በበኩላቸው፥ እየተከበረ ሚገኘው የሳይበር ደህንነት ሳምንት ወቅቱን የጠበቀ እና የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ አጋዥ መሆኑን ጠቁመው፤ ዓለም በሳይበር ምህዳር አንድ መንደር በሆነችበት በዚህ ዘመን የሳይበር ሃይል ከገንዘብ፣ ከጦር መሳሪያ እና መሰል አቅሞች በላይ የሆነ የዘመናችን ቁልፍ መወዳደሪያ አቅም ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

የሳይበር ደህንነት ለኢትዮጵያ አዲስ እና በርካታ የሰለጠነ የሰው ሃይል የሚፈልግ መሆኑን ነው የሚሉት አቶ ዘይኑ በዘርፉ የተሠማራውን የሰው ሃይል አቅም በመገንባት እና አዲስ የሰው ሃይል በማልማት አስፈላጊውን የቴክኖሎጂ ግብዓት ማሟላት አስፈላጊ እንደሆነና ይህ አካሄድ በሀገሪቱ ላይ ሊቃጣ የሚችልን ማናቸውም ጥቃት በራስ አቅም ለመመከት የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።

የኅብረተሰቡን አስተሳሰብ በመቀየር ረገድ የመሪነት ሚናን የሚጫወቱት የመገናኛ ብዙሃን እንደሆኑ ያመላከቱት ሚኒስትሩ፣ የሳይበር ደህንነት ጉዳይ የሁሉም ሓላፊነት መሆኑን በመረዳት የፕሮግራሞቻቸው አንድ አካል አድርገው በመቅረጽ ሊሠሩ ይገባል ሲሉም አስጠንቅቀዋል::

የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ ከ 2 ቀናት በኋላ ይጀመራል

የዛሬ ሦስት ወር ገደማ ለበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋት መንስዔ የሆነው የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄን የሚወስነው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ ከሁለት ቀናት በኋላ የሚጀመር መሆኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ አድርጓል።

ከአስራ ስድስት ቀናት በኋላ ህዳር 10 ቀን 2012 ለሚካሄደው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ድምጽ መስጠት የሚፈልጉ ዜጎች ከጥቅምት 26 እስከ ህዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ባሉት 10 ቀናት ውስጥ መመዝገብ ያለባቸው መሆኑን ቦርዱ አስታውቋል ።

የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን መከታተል የሚፈልጉ እና ህጋዊ ምዝገባ ያላቸው የመገናኛ ብዙሃን እስከ ማክሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2ዐ12 ዓ.ም እስከ ቀኑ 11 ሰዓት ከ30 ድረስ ለሥራው የሚመድቡትን ጋዜጠኛ ( ቢበዛ ሁለት) ስም በጽሑፍ በማሳወቅ የፍቃድ ጥያቄ ማቅረብ የሚችሉ መሆኑም ተገልጿል።

በተያያዘ ዜና የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠዉ መርሃ ግብር መሰረት እንዲካሄድ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ሊዳሞ ተናግረዋል።

በሲዳማ ዞንና በሀዋሳ ከተማ መስተዳድር አጠቃላይ 598 ቀበሌዎች 1692 የምርጫ ጣቢያዎች መቋቋማቸውን ነው አስተዳዳሪው በመግለጫቸው ላይ የጠቆሙት።

ካሉት የምርጫ ጣቢያዎች በተጨማሪ 90 ጣቢያዎች እንዲጨመሩ ምርጫ ቦርድን መጠየቁንም የገለፁ ሲሆን፥ ቦርዱም በምዝገባ ወቅት መጨናነቅ እንዳይፈጠር ሁኔታዎችን እያመቻቸ መሆኑን አስታውቀዋል።

የተዘጋጁት የምርጫ ጣቢያዎች ለድምፅ ሰጪዎችም ሆነ ህዝበ ውሳኔውን ለሚያስፈጽሙና ለሚታዘቡት ምቹ እንዲሆን ከመደረጉ ባሻገር፤ የህዝበ ዉሳኔ አስፈፃሚ አካላት ከዛሬ ጥቅምት 24 2012 ዓም ጀምሮ ወደየምርጫ ጣቢያዎች እንደሚገቡም አረጋግጠዋል:: ህዝበ ውሳኔዉ ሰላማዊ እንዲሆን የፀጥታ አካላት ሙሉ ዝግጅት አድርገዋል ተብሏል::

ጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ (የተሰባሰበው የኦሮሞ አመራር) መግለጫ አወጣ

በአንድ ጥላ ስር የተሰባሰበው የኦሮሞ አመራር (ጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ) በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ መግለጫ አውጥቷል። በአንድ ጥላ ስር የተሰባሰበው የኦሮሞ አመራር በትናንትናው ዕለት ያካሄደው ስብሰባ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በግልፅና በስፋት በመምከር በስኬት መጠናቀቁን በመግለጫው ላይ ጠቁሟል።

በኦሮሞ የፖለቲካ ሀይሎች መካከል አለመግባባት ከተፈጠረ በውይይት ከመፍታት ባለፈ አንዱ በአንዱ ላይ ዘመቻ መክፈት ለማንም እንደማይጠቅም በውይይቱ ላይከስምምነት መደረሱ ተገልጿል።

“አሁን ያለንበት ወቅት በጣም ወሳኝ በመሆኑ እያንዳንዱ ዕርምጃ የኦሮሞን ህዝብም ሆነ የሀገሪቱን ብሄር ብሄረሰቦች የነገ ተስፋ ወደ ብርሃን የሚያሻግር አልያም ለከፍተኛ አደጋ ሊዳርግ የሚችል” ነው ያለው መግለጫ ፤ በስብሰባው ከዚህ ቀደም እንደዚህ አይነት በአንድ ጥላ ስር የተሰባሰበው የኦሮሞ አመራር ቢኖር ኖሮ በመካከላቸው ያለው ጥርጣሬ ዛሬ ያለበት ደረጃ ላይ አይደርስም ነበር ብሏል። ካሁን በኋላ ግን በአንድ ጥላ ስር የተሰባሰበው የኦሮሞ አመራርን በማጠናከር በመካከላቸው ለተፈጠሩ እና ለሚፈጠሩ ችግሮች በጋራ በመሆን መፍትሄ የማፈላለግ ሥራ እንደሚሠራም አስታውቋል ።

ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲ አንድ የሚያደርገው ጉዳይ የኦሮሞን ህዝብ እና የሀገሪቱን ብሄር ብሄረሰቦች ጥቅም ማስጠበቅ እንደመሆኑ አሁን ያለውን ህብረ ብሄራዊ የፌደራል ስርዓት ለማጠናከር እና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ መስራት ይጠበቃልም የሚለው በአንድ ጥላ ሥር የተሰባሰበው የኦሮሞ  አመራር፤ እኩልነት፣ ነፃነት እና የህዝቦች ወንድማማችነት የተረጋገጠበት እንዲሁም ዴሞክራሲ ያበበበት እውነተኛ ህብረ ብሄራዊ የፌደራል ስርዓት እንዲተገበር ለማድረግ በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በመስማማት አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል።

በኦሮሚያ ክልል የሚስተዋሉ የሰላም ችግሮችን እንዲሁም ከሰሞኑ በክልሉ ለተከሰቱ የፀጥታ ችግሮች መንስኤ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግም፤ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የስራ ክፍፍልም አድርጓል።

መጭው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ እንዲሆን ምን አይነት መንገድ መከተል እንዳለባቸው የሚያሳይ አጭር ጥናት ከተካሄደ በኋላ ሰፊ እና ጥልቅ ውይይቶችን በማካሄድ ቀጣይ አቅጣጫዎችን በጋራ ለማስቀመጥም አመራሩ ውሳኔ አሳልፏል ነው የተባለው።

እንደ ሀገር የተጀመረውን ለውጥ በጠንካራ እና አስተማማኝ መሰረት ላይ ለማቆም ከሁሉም የሀገሪቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ቀጣይነት ያለው ውይይት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በማመንም፥ በሀገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ ከሁሉም የፖለቲካ ሀይሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር በጋራ መስራት የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች ላይ ለመምከርም በአንድ ጥላ ስር ተሰባስቤያለሁ ያለው አመራር አስታውቋል::

የመንግሥት ሠራተኞችና የፖሊስ ሓላፊ ጉቦ ሲቀበሉ  እጅ ከፍንጅ ተያዙ

ሁለት የመንግሥት ሠራተኞችና አንድ የፖሊስ የምርመራ ሓላፊ ጉቦ በመቀበል የሙስና ወንጀል ሲፈፅሙ እጅ ከፍንጅ መያዛቸው ታወቀ።

እነዚህ ተጠርጣሪዎቹ የቦሌ ክፍለ ከተማ ሠራተኞች ሲሆኑ፣ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ውስጥ እየተገነቡ የሚገኙ ቤቶችን ከመቆጣጠርና ከመሰል ሥራዎች ጋር ሓላፊነት ተሰጥቷቸው ሢሰሩ የነበሩ ናቸው ተብሏል።

የማይገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ የግል ተበዳይ ናቸው ከተባሉት ግለሰብ ላይ ከፊኒሽንግ ሥራ ጋር በተያያዘ ፍቃድ ወይም ሥራ ለመስጠት በሚል 10 ሺህ ብር ከጠየቁ በኋላ ፣ በመደራደር 8 ሺህ ብር ጉቦ ሲቀበሉ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ነው የሰማነው።

የሴቶችና ህፃናት ወንጀል ምርመራ ሓላፊ የነበሩት የፖሊስ አባል፣ ከሴቶች ጥቃት ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪ የሆነን ግለሰብ “የክስ መዝገቡ እንዲዘጋና እንዲቋረጥ አስደርግልሃለሁ” በማለት 20 ሺህ ብር በመጠየቅና በመደራደር 1 ሺህ ብር ሲቀበል እጅ ከፍንጅ መያዙን ነው የሰማነው።

በአማራ ክልል በሦስት ወር ውስጥ 100 አዳዲስ ት/ቤቶች ተገንብተዋል ተባለ

በአማራ ክልል በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ፣ 75 የመጀመሪያ እና 25 አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አዳዲስ ተገንብተው መከፈታቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው የ2012ዓ.ም የመጀመሪያው ሩብ አመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማን የዞን ትምህርት መምሪያ ሓላፊዎች፣ የመምህራን ማኅበር አመራሮች፣ የቡድን መሪዎች እና የተማሪ ወላጅ ማኅበር አመራሮች በተገኙበት እያካሄደ መሆኑንም ሰምተናል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ብዙነህ፥በክልሉ ያለውን የትምህርት ተሳትፎና ተደራሽነትን ለማሳደግ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 75 የመጀመሪያ እና 25 አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው መከፈታቸውን ተናግረዋል። ይህን ተከትሎ በአጠቃላይ በክልሉ ከዚህ በፊት የነበሩት 9 ሺህ 13 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ወደ 9 ሺህ 88 ማደጋቸውን ፣ እንዲሁም በተመሳሳይ በክልሉ 566 የነበረው የሁለተኛ ደረጃ ተምህርት ቤት ቁጥር ደግም 591 መድረሱን አቶ ሀብታሙ ጠቁመዋል።

የ2012 ዓ.ም መጀመሪያ ሩብ ዓመት የክልሉ ጥቅል የትምህርት ተሣትፎ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 16 በመቶ ወደ 19 ነጥብ 83 በመቶ እንዳደገና ፤ በዚህም በቅድመ መደበኛ 943 ሺህ 57 ለመመዝገብ ታቅዶ 635 ሺህ 533 ተማሪዎች ወይም 67 ነጥብ 4 በመቶ ማሳካት መቻሉ በሪፖርቱ ተገልጿል።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተሳትፎን በተመለከተ 4 ሚሊየን 569 ሺህ 952 ለማድረስ ታቅዶ፤ 4 ሚሊየን 48 ሺህ ተማሪ ተመዝግበው በመማር ላይ ይገኛሉ:: በሌላ በኩል በ9ኛ እና 10ኛ ክፍል 679 ሺህ 820 ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ 590 ሺህ 678 ወይም 86 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ተመዝግበው በመማር ላይ ናቸውም ተብሏል። የመሠናዶ የትምህርት ተሣትፎ ለማሣደግ በተሠራው ስራ 194 ሺህ193 ተማሪ ለመመዝገብ ታቅዶ 246 ሺህ 617 በመመዝገብ የእቅዱን127 በመቶ መፈፀም መቻሉ ታውቋል።

የአፍሪካ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

የአፍሪካ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሊካሄድ መሆኑ ታወቀ:: ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚካሄደው አህጉራዊ ጉባኤ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች፣ የፈጠራ ባለሙያዎች እና ፖሊሲ አውጭዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ከወዲሁ ተገምቷል።

በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሄደው ይህ ታላቅ ጉባኤ የፋይናንስ ቴክኖሎጂን በአፍሪካ ማስፋፋት ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚካሄድ እንደሆነ ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ችለናል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመዘገበ ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ እየተስፋፋ የመጣው መሰረተ ልማት ዝርጋታ ፤ በተለይም የግሉ ዘርፍ በግዙፍ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳተፍ የሚያስችሉ ማሻሻያዎች መተግበራቸው ጉባኤው በአዲስ አበባ እንዲካሄድ እንዲደረግ አስችሏል ነው የተባለው።

ጉባኤው በባንክ ሥራ ዘርፍ፣ በሞባይል ባንኪንግና የገንዘብ ዝውውር፣ በውጭ ምንዛሪ ክምችት፣ በገንዘብ ዝውውር፣ በዘርፉ ፖሊሲዎችና ደምቦች ላይ በስፋት ከመምከር ባሻገር አዳዲስ ውጤታማ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ታምኖበታል።

LEAVE A REPLY