የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 25 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 25 ቀን 2011 ዓ.ም

በአ/አ የማህጸን ጫፍ ካንሰር ክትባት የወሰዱ 50 ተማሪዎች ራሳቸውን ስተው ወደቁ

በአዲስ አበባ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ብርሃን እና ሰላም ተብሎ በሚጠራው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሃሙስ ጥቅምት 13 ቀን ዕድሜአቸው 14 ዓመት የሆናቸው የማህጸን ጫፍ ካንሰር ክትባት የወሰዱ ሃምሳ ያህል ተማሪዎች ራሳቸውን መሳታቸውን ተከትሎ ክትባቱ በክፍለ ከተማው ቆሞ ምርመራዎች መደረግ መጀመሩን የደረሰን  ዜና ያስረዳል::

በተመሳሳይ ሁኔታ በክፍለ ከተማው ባሉ ሌሎች ትምህርት ቤቶችም ቁጥራቸው ዝቅተኛ ቢሆንም የተወሰኑ ተማሪዎች በተመሳሳይ ራሳቸውን ስተው ወደ ህክምና መሄዳቸውም ታውቋል::

አጋጣሚው ከክትባቱ ጋር ግንኙነት ሊኖረው ይችላል የሚል ጥርጣሬ ይፈጠር እንጂ ከታመሙት ተማሪዎች ውስጥ ክትባት ያልወሰዱ እንደሚገኙ እና ከ9 እስከ 4 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ተማሪዎች ላይ ተመሳሳይ ስሜት ታይቷል ተብሏል:: በወቅቱም ወደ ወረዳ ሦስት ጤና ጣቢያ ተወስደው ሕክምና ያገኙ ሲሆን በተለይም ከፍተኛ የሆነ የድካም ስሜት ይሰማናል ማለታቸውን ተከትሎ ድካማቸውን የሚያስለቅቅ ህክምና አግኝተው ከጣቢያው መውጣታቸውንም አጣርተናል::

920 ሚሊዮን ብር የወጣበት ሆስፒታል በአዲስ አበባ ተከፈተ

በቻይናውያን ባለሀብቶችና በኢትዮጵያ  አጋርነት የተሠራው “አዲስ አበባ ሲልክ ሮድ አጠቃላይ ሆስፒታል” ዛሬ  በይፋ ተመረቀ። 920 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል የተባለው ይህ ግዙፍ ሆስፒታሉ በ13 ወራት ውስጥ ተገንብቶ  እንደተጠናቀቀ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ሰምተናል።

ሲልክ ሮድ አጠቃላይ ሆስፒታል 100 የህመምተኛ አልጋዎች ፣ደረጃውን የጠበቀ የቀዶ ጥገና ህክምና በተለይም የጭንቅላት እና የህብለ ሰረሰር ቀዶ ጥገና ላይ ስፔሻላይዝድ ያደረገ አገልግሎት እንደሚሰጥም ለሚዲያ ባለሙያዎች በተደረገው ገለጻ ላይ መገንዘብ ችለናል።

የኢፌዴሪ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን ሆስፒታሉ ግንባታ ጥራቱን ጠብቆ እንዲከናወን በተለያየ መንገድእገዛ  ላደረጉ አካላት በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ምስጋና አቅርበዋል::

ሞፈሪያት ካሚልና ጀነራል አደም ከአማራና ቅማንት ሕዝቦች ጋር ተወያዮ

በሠላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚል እና በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የተመራ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎች ቡድን ፣ ከአማራና ከቅማንት ህዝቦች የተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አደረገ።

በጭልጋ ወረዳ፣ ሰራባ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ውይይትወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሃመድን ጨምሮ የተለያዪ የመንግሥት የሥራ ሓላፊዎች ተካፋይ ሆነዋል። ከሁለቱም የማኅበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ እናቶችና ወጣቶችም በውይይቱ ተሳትፈዋል።

ምክክሩ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል የነበረውን አብሮነት፣ አንድነትና ሠላማዊ ግንኑነት የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችል መሆኑ ከመገለጹ ባሻገር ፤ ለዘመናት አብረው የኖሩትን የአማራ እና ቅማንት ህዝቦች ችግሮቻቸውን በሠላማዊ መንገድ መፍታት የሚያስችል ቤተሰባዊ  ውይይት ነው ተብሎለታል::

 ”ሁለቱ ሕዝቦች ቤተሰባዊ ናቸው፤ በቤተሰብ መካከል የተፈጠረ ችግር ቤተሰብ ካልፈታ በቀር ማንም ሊፈታው አይችልም” ያሉት የሠላም ሚኒስትሯ ሞፈሪያት ካሚል፤ በግጭቱ ማንም አሸናፊ ሊሆን እንደማይችልና ያለፈው ላይመለስ ለዛሬና ለነገ ሠላማዊ ሂደት ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል ።

ከዚህ በፊት ከነበሩት ሠላማዊ ውይይቶች በተለየ መልኩ ወደ ሠላም መንገድ ሊያደርስ ያስችላል ተብሎ የታሰበ የመጀመሪያ ዙር ውይይት እንደሆነ የጠቆሙት ሚኒስትሯ ፤ በቀጣይም መሠል ሠላማዊ ውይይቶችን ከሕዝብ ጋር እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው ሠላም የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኑየተጀመረው ሠላማዊ ውይይት እንዲያብብ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመላክተው፤ ሠላማዊ ውይይቱ ፍሬያማ እንዲሆን ከሁለቱም ወገኖች የተወጣጡ ምሥጉንና ሚዛናዊ የሀገር ሽማግሌዎች የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸውንም ገልጸዋል። በውይይቱ የተካፈሉ ተሳታፊዎችም የታሠሩ ሰዎች በምሕረት አዋጁ እንዲለቀቁና የተፈናቀሉ ወገኖች ዘላቂ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ለመንግሥት ሓላፊዎቹ ጥያቄ አቅርበዋል::

በኀብረተሰቡ እየተወቀሰ የሚገኘው መብራት ኃይል ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው

 በተደጋጋሚ ከዋጋ ጭማሪና  በሚያጋጥሙ የኤሌክትሪክ  መቋረጥ ችግሮች ምክንያት በተገልጋዮች ክፉኛ እየተተቸ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከዘርፉ ባለድርሻ  አካላት ጋር ምክክር እያካሄደ መሆኑን አስታውቋል።

አገር አቀፍ የባለድርሻ አካላትን የያዘው የምክክር መድረኩ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው የሚገኘው።

በምክክር መድረኩ ላይም የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍሬህይወት ወልደሃና፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ፣ ሌሎች የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የከፍተኛና መካከለኛ ኃይል ተጠቃሚ የኢንዱስትሪ ባለሀብቶች፣ የግሉ ዘርፍ ማህበራት ተወካዮች፣ የሙያ ማህበራትና የመንግሥታዊ ተቋማት አመራሮች በመሳተፍ ላይ እንደሆኑ ተሰምቷል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞቹን እርካታ ለማሻሻል እስካሁን ባከናወናቸው ተግባራት ዙሪያ ምክክር እንደተደረገም መረጃዎች ይጠቁማሉ::

በተገኙ መሻሻሎች፣ ባጋጠሙ ችግሮች እንዲሁም በአጠቃላይ በዘርፉ ነባራዊ ሁኔታና በቀጣይ የትኩረት መስኮቹ ላይ ምክክር እያካሄደ እንደሚገኝ ባለ ሥልጣን መ/ቤቱ አስታውቋል ።

የ60 ዓመቷን አዛውንት የደፈረው የ18 ዓመት ወጣት በዕድሜው መጠን ዕስራት ተላለፈበት

በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ፖሊስ ሰፈር ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ የ60 ዓመቷን አዛውንት አስገድድዶ የደፈረው የ18 ዓመት ወጣት ባለበት ዕድሜ መጠን 18 ዓመት ከ8 ወር በጽኑ እስራት እንዳቀጣ ተወስኗል::

መኪና በመጠበቅ ሥራ ላይ የተሠማራው ግለሰብ ድርጊቱን በፈጸመበት ዕለት ከሌሊቱ 6 ሰዓት ላይ ማደሪያ የሌላቸው ሸራ ወጥረው የሚያድሩና የሳንባ በሽተኛ የሆኑትን እናት ከሚጠብቀው መኪና በአንዱ ውስጥ በተኙበት ድብደባ በመፈጸም ራሳቸውን መከላከል እንዳይችሉ በማድረግ ጥቃቱን ማድረሱን መረጃዎች ያመላክታሉ::

የግል ተበዳዮዋ አንድ የሚያወቁት የመኪና ባለቤት ብርድ በሚሆን ጊዜ በመኪና ውስጥ እንዲያድሩ በነገራቸው መሠረት ለመኪና ጠባቂው ብርድ ልብሳቸውን ይዞ እንዲሄድ ቀድነው ሰጥተውት የቀረ ልብሳቸውን ይዘው የተከተሉት አዛውንት መኪና ውስጥ ገብተው የያዙትን ልብስ ደራርበው ተኝተው ነበር::

ወጣቱ ለተወሰነ ደቂቃ ከመኪናው ርቆ እንቅልፍ እስኪጥላቸው ትንሽ ከጠበቀ በኋላ በሩን ከፍቶ አፋቸውን እንዳፈናቸው በተደጋጋሚ በቦክስ በመማታት ፊታቸውን ካደማቸው በኋላ አስገድዶ እንደደፈራቸው ለፍርድ ቤት በተሰማ ምስክር የህክምና ሰነድ እና የፎቶ ማስረጃዎች መረዳት ተችሏል::

አዛውንቷ በዕለቱ የቅርብ ጓደኛቸው ሌላ ማደሪያ በማግኘታቸው መለያየታቸውንና በቦታው እርሳቸው ብቻ ያሉ በመሆናቸው የሚደርስላቸው ሰው ባለመኖሩ ከአንድ ጊዜ በላይ ጥቃቱ እንደደረሰባቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል::ተከሳሹ በአዛውንቷ ላይ በፈጸመው ድርጊት የ18 ዓመት ከ8 ወር ጽኑ ዕስራት ተፈርዶበታል::

በ31ኛው የናይጄሪያ (ሌጎስ) ዓለም አቀፍ ንግድ ትርዒት ኢትዮጵያ እየተሳተፈች ነው

ለአስር ቀናት በሚቆየውና በናይጀሪያ በመካሄድ ላይ ባለው 31ኛው የሌጎስ ዓለም ዓቀፍ የንግድ ትርዒት ላይ  ኢትዮጵያ እየተሳተፈች መሆኑ ተነገረ።

ከፍተኛ ግብይት ይካሄድበታል በሚባለው የንግድ ትርኢቱ ላይ የኢትዮጵያ የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝምን ዕድሎችን የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኘም ነው የተገለጸው::

ከንግድ ትርኢቱ ጎን ለጎን ከናይጄሪያ የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ማረያና ካታጉማ፣ ከሌጎስ ስቴት ምክትል አስተዳዳሪ ፈሚ ሀምዛት እና ከሌጎስ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ፖል ባባቱንዴ ሩዋሴ የሁለቱን ሃገራት የንግድ ማህበረሰብ ማቀራረብ በሚቻልበት ሁኔታ ላይም እየመከሩ ናቸው ተብሏል ።

በንግድ ትርዒቱ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ በናይጄሪያ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አዛናው ታደሰ በናይጄሪያና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ እንዲያድግ እንሠራለን ብለዋል:: ኢትዮጵያ ለውጭ ኢንቨስትመንት ምቹ ናት ያሉት አምባሳደሩ ሀገሪቱ የያዘችውን በርካታ እምቅ የቱሪዝም ሃብቶቿን በተመለከተም ሠፊ ገለጻ አድርገዋል።

ናይጄሪያ – አቡጃ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሁለቱን ሃገራት የንግድ ትስስር ለማጠናከር ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳለው መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ካሰፈረው መረጃ መረዳት ችለናል።

LEAVE A REPLY