‹‹ወሎን ከፍቶት ማን ሊደሰት?›› || መላኩ አላምረው

‹‹ወሎን ከፍቶት ማን ሊደሰት?›› || መላኩ አላምረው

 ‹‹ወሎ›› ስሙ ሲጠራ ብዙ ነገሮች ወደ አእምሮዬ ይመጣሉ፡፡ ‹‹ፍቅር›› ቀዳሚው ነው፡፡ እስላም ክርስቲያኑ፣ በረኸኛው ከደገኛው፣ ብሔረሰብ ሕዝቡ፣ ተፈጠሮና ሰው… ሁሉም በፍቅር የሚኖርበት ምድር ነው ወሎ፡፡ ወሎ በጥንተ ግዛቱ ከራያ እስከ አሰብ የተዘረጋ የብዙኅነት ምድር ነው፡፡ የቤተ አምሓራ ምድር፣ የአካለ ወልድ ደብር፣ የሼኅ ሁሴን መስጂድ፣ የንጉሥ ሚካኤል ቤተ መንግሥት፣ የላይበላ መቅደስ፣ ‹የራያ-አገው-ኦሮሞ-አፋር› ሕብር………. ስለ ወሎ ስንቱ ይነገራል? ወሎን ‹‹ፍቅር›› ከሚለው ቃል በላይስ ምን ሊገልጠእ ይችላል?

‹‹ወሎ›› ስሙ ሲጠራ ‹‹ገራዶና ደሴ›› በአእምሮ ይከሰታሉ፡፡ ‹‹የገራዶ ሜዳ ግን ለምን ‘ገራዶ’ ተባለ?›› ….መልሱን ‹‹የሆነ… የተጋረደ ቦታ ስለሆን… ከደሴ የአብዛኛው ሰፈር እይታ ስለተጋረደ.. ወዘተረፈ” ካላችሁ… ተሳስታችኋል ወይም መልሱ ሙሉ አይደለም። ገራዶ “ገራዶ” የተባለበት ምሥጢር በዋናነት ፍቅርን ከመናገሻችን ከ4 ኪሎም ሆነ በአጠቃላይ ከሀገራችን ጋርዶ ደሴ ላይ ስላስቀመጠ ነው/ይመስለኛል)።

ፍቅርን ከሀገሬ ምን መንፈስ ወሰደው?
ሳስበው ፥ ሳስበው…
ደሴ ላይ ከትሞ – ገራዶ ጋረደው !!!

ገራዶ የጋረደውን ፍቅር እየቀዱ ለሀገር ማብቃት ያሻል። በዚህ ዘመን፥ የሰው ልጅ ልብ ፍቅርን ይዞ መኖር ሲያቅተውና አንደበቱ ጥላቻ ጥላቻ ሲያቀረሽ፥ አፍንጫው ባሩድ ብቻ ሲያሸት፥ ጆሮው የሽብርና የጦርነት፣ የመከፋፈልና የዘረኝነት ወሬ ብቻ ሲሰማ፣ ዓይኖቹ ደም ሲለብሱና ውስጠቱ በቀልን ተመልቶ ምድሩን በደም ሊያጨቀያት መንገዱን ሲጠርግ እያየን… ፍቅርን እንደ ደሴ ካሉ የፍቅር አድባራት ኮረጅ ! ኮረጅ ! አድርገን ለሌሎችም በፍጥነት ካላከፋፈልን እንዴት እንዴት እንደምንዘልቅ እንጃ!?!

‹‹ኢትዮጵያ የፍቅርና የመቻቻል ተምሳሌት ናት›› የሚለውን አባባል ‹‹ፍጹም ቅጥፈት ነው ፣ ውሸት ነው›› እንዳልል ከሚያደርጉኝ አካባቢዎች አንዱ ወሎ ነው!!! በኢትዮጵያ ‹‹መቻቻል አለ›› እውነት ነው! ‹‹ሀገራችን ፍቅር በፍቅር ናት›› ካልን ግን ቅጥፈት ነው። መቻቻልንና ፍቅርን ለዩ፡፡ መቻቻልማ… ወደህ ትችላህ!!! ለመኖር የማይቻል የለም፡፡ ነገር ግን በመቻቻል የሚኖር ሁሉ የማይቻል ሲመጣ መቆጣቱ አይቀርም፡፡ አሁን መቻቻልም ያቃተን ይመስላል፡፡ መቻቻል ገደብ አለው፡፡ ፍቅር ግን ገደብ የለውም፡፡ በፍቅር የሚኖር ሁሉን ስለፍቅር ይተዋል፡፡

ወዳጄ? በሀገራችን…… ፍቅር እስከሙሉ ግርማ ሞገሱ ቁጭ ያለው ወሎ ውስጥ ነው። ካላየሁ አላምንም ካልህ ዝለቅ። እምወድህዋ ብሎ ተቀብሎ ፍርን ከእግር እስከራሱ ያስጎበኝሃል።

(የወሎን ፍቅር ግርማ ሞገስ ለማኮሰስ ከግራም ከቀኝም እየጎነታተሉት ሊሆን ይችላል። ሰሚ ግን አያገኙም። የተነቃነቀ ሁሉ አይወድቅም፣ ነፋስ አቧራን እንጅ አለትን አያነሳም። የወሎ ፍቅር በጽኑ የአለት መሠረት ላይ እንጅ በአሸዋ ላይ አልታነጸም። ባይሆን ይህን ጽኑ ፍቅር እየኮረጁና እያባዙ ለሁሉም ማዳረስ ይቻላል – የተፈቀደ ነው፡፡)
.
‹‹ወሎ ደሴ መጀን
ፍቅር ነው ያበጀን››
.
ለወሎ የሚመጥነው ብቸኛ ቃል ፍቅር ነው። ሰብዓዊ ፍቅርርርር ! ወሎ ደሴ ሄደህ ምን አጥተህ ! ፍቅር ካለ ምን ጎድሎ….
-›
‹‹አይጠየፍ›› ሌላው ወሎን የሚገልጽ ቃል ነው፡፡ አይጠየፍ አዳራሽ ነው፡፡

“ለምን አይጠየፍ ተባለ?” ….አይጠየፍ ማለት በቃ፥ ማንንም የማይጠየፍ፣ የሁሉም ቤት ማለት ነው። ያኔ በንጉሥ ሚካኤልም ሆነ በሌሎች ደጋግ ሰዎች ዘመን ድሃንና ነዳያንን የሚጠየፍ ዓይን አልነበረም። አቅመ ደካማ በፍጹም አይገፋም… ድሃ አይረገጥም! ነገሥታቱና መኳንንቱ ሕዝቡን በተግባር ይወዱ ነበር። በየጊዜያቱም ከማጀታቸው ደግሠው፣ በእልፍኛቸው አስቀምጠውና በእጃቸው አጉርሰው ይሸኙት ነበር። ግብር ያበሉት ነበር። አሁን “ከሕዝብ ግብር” የሚሰበስብ እንጅ ለሕዝብ ግብር የሚያበላ መንግሥት ስለጠፋ የንጉሥነት ክብሩ ቀሏል። በንጉሥና በሕዝብ መካከል ቤተሰባዊነቱ ቀርቶ እየተደባበቁ መኖር ሆኗል። አለመተማመን ነግሷል።

‹‹ወሎ›› ስሙ ሲጠራ ‹‹ቤተ አምሓራ›› / ‹‹አምሓራ ሳይንት›› የሚሉ ስሞችም ተከሳች ናቸው፡፡ ያ ቀዬ የአማራን አቃፊ ደጋፊነት በፍቅር እጅ ኮትኩተው ያሳደጉ ነፍሶች መናኸሪያ ነው። አማራነትን ከስም እስከግብሩ በምልዓት ለማግኘት ከቤተ አማራዎች ቀየ ዝለቅ። ሰው በልዩ ማንነቱ ሳይገፋ፣ ሳይነቀፍ፣ በፍቅር ታቅፎ ከልብ ተደግፎ የሚኖርበት ምድር ነው – ቤተ አምሓራ – ወሎ።

እና ወሎን አምበጣ ወሮት ዝም ማለት ይቻለናል? ወሎን ከፍቶት ማን ሊደሰት? ወሎ ሲከፋ የሚያዝነው ፍቅር ነው። የሚከፋው መቻቻል ነው። የሚቆዝመው አብሮነት ነው። ወሎን ሲከፋው መላው አማራ ይከፋል። ኢትዮጵያ ታዝናለች። ፍቅር ተከፍቶ ማን ሊደሰት?

ይህን የአንበጣ ወረርሽኝ ጊዜ ሳንፈጅ እንፍጀው! ዛሬ ነገ ማለት አያስፈልግም። ሁሉም በየአቅሙ በየድርሻው ይረባረብ። አንዱ አንዱን ሳይጠብቅ ይዝመት። መንግሥት የመንግሥትነቱን ሕዝብ የሕዝብነቱን ወገን የወገንነቱን ድርሻ ከተወጣ እንኳን ድንበር ምንስ ቢመጣ ምን ሊያመጣ???

LEAVE A REPLY