እስክንድር ነጋ ዛሬ በአንበሳ አውቶቢሶች እየተዘዋወረ ለነዋሪዎች ስለባላደራው ዓላማ አስረዳ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኦዴፓን የበላይነት ተከትሎ በግልጽ እየተንጸባረቀ ያለውን አዲስ አበባን የመጠቅለል እና የፊንፊኔ ኬኛን ፖለቲካ በተደራጀ መልኩ ፊት ለፊት በመቃወም ላይ የሚገኘው የባላደራው ምክር ቤት (ባልደራስ) ይህንን የጽንፈኛ ፖለቲከኞችን ፍላጎት ለማክሸፍ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ቀጥሏል::
በኦዴፓ እና በከንቲባ ታከለ ኡማ ቀጥተኛና ስውር ትዕዛዞች እንቅስቃሴውን በተደጋጋሚ ለመግታት የተሞከረው ባላደራው ብዙዎች “ብርቱ ሠው” እያሉ በሚያሞካሹት ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ እስክንድር ነጋ እየተመራ ትግሉን ገፍቶበታል::
የኢሬቻ በዓልን ተከትሎ ከታየው ግልጽ የሆነ የተረኝነት ፖለቲካ በኋላ ብዙ የደጋፊዎቹ ቁጥር እየጨመረ የመጣውና የብዙኃኑን ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር ባገኘው የባላደራው ሊቀመንበር እስክንድር ነጋ ላይ ከኦሮሚያ ፖሊስና ከአዴፓና ከቄሮዎች የተውጣጡ አካላት ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ስብሰባዎችን ከማስተጓጎል እስከ ጥቃት ማድረስ የዘለቀ ሙከራ ቢደረግበትም ያለፍርሃት የአዲስ አበባን ነዋሪ በማንቃት ላይ ይገኛል::
በዚህ መሠረት እስክንድር ነጋ እና ስንታየሁ ቸኮልን ጨምሮ የባላደራው ምክር ቤት ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዮ አውቶቢሶች ላይ በመሳፈር አብረው እየተጓዙ ኅብረተሰቡ አዲስ አበባ የሁሉም ሕዝብ ናት በሚል መርህ በመንቀሳቀስ ላይ ስለሚገኘው የባላደራው ምክር ቤት ዓላማ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል::
ከምክር ቤቱ አባላት ጋር አብሮ ተሳፍሮ ውይይቱን የተከታተለው የኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር እነእስክንድር ነጋ ከልጅ እስከ አዋቂ እንዲሁም እስከ ዕድሜ ጠገብ አዛውንቶች ድረስ ከፍተኛ ደጋፊና ተቀባይነት እንዳላቸው ማስተዋሉን አድርሶናል:: ኀብረተሰቡ ላቀረባቸው ጥያቄዎች እስክንድር ነጋ በቂ ማብራሪያ የሰጠ ሲሆን በሚያደርገው የአዲስ አበባ እንቅስቃሴ እናቶችና አባቶች በጸሎት እንደሚያግዙት የገለጹ ሲሆን በርካቶች ከተሳፈሩበት አውቶቢስ ሲወርዱ ከክፉ እንዲጠብቀው ሲመርቁት መዋላቸውን የአዲስ አበባው የኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር ካደረሰን ዜና መረዳት ችለናል::
ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባ የተቀመጠው ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የጥላቻ ንግግር አዋጅን አፀደቀ
የመውሊድ አን’ ነቢ በዓል በተከበረበት በዛሬው የሚኒስትሮች ም/ቤት ባካሄደው አስቸኳይ 75ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉ ተሰምቷል::
ምክር ቤቱ የሃገሪቱን ወቅታዊ ጉዳዮች ተንተርሶ በመደበኛ ስብሰባው በተለያዩ ነጥቦች ላይ ሰፊ ውይይት አድርጎ በአምስት ነጥቦች ላይ ውሳኔ አሳልፏል::
ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ዝርዝርእንደሚከተለው ቀርቧል፦
1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የመከላከያ ሠራዊት መተዳደሪያ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ በአገራአችን የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሰራዊ አገራዊ ተልዕኮውን እንዲወጣ ለማደውረግ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የሪፎርም ሥራዎችን ለማከናወን እንዲቻል አዲስ አዋጅ ጸድቆ ሥራ ላይ መዋሉ ይታወሳል፡፡ በአዲሱ አዋጅ ከተካተቱ አዳዲስ አደረጃጀትና መዋቅሮች ጋር ለማጣጣም፣ በስራ ላይ ባለው ደንብ የታዩ የአፈጻጸም ችግሮችን ለማስተካከል፣ የመከላከያ ሰራዊቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማቃለል የሚረዱ አዳዲስ ድንጋጌዎችን ለማካተት በሚያስችልና የመከላከያ ሰራዊቱን የግዳጅ አፈጻጸምና ሞራላዊ ዝግጁነት ለማጠናከር ሲባል የመከላከያ ሰራዊት ደንብ ቁጥር 385/2008ን ማሻሻል አስፈላጊ በመሆኑ የመከላከያ ሚኒስቴር ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡ ም/ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማከል ደንቡ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል።
2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን በአሁኑ ወቅት በተግባር ስራዎችን እያከናወነ ያለበት ሁኔታ ከተጣለበት ሃላፊነት እና አላማውን ከመፈጸም አኳያ የደንቡ አንዳንድ ክፍሎች ግልጸኝነትን ባለው መንገድ ያልተመላከቱ ስለሆነ የማቋቋሚያ ደንቡን ማሻሻል አስፈላጊ በመሆኑ የመከላከያ ሚኒስቴር ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡ ም/ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማከል ደንቡ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል።
3. ሌላው ም/ቤቱ የተመለከተው የፌዴራል የአስተዳደር ስነ-ስርዓትን ለመደንገግ በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት መንግስታዊ አስራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበትና ማናቸውም የመንግስት ባለስልጣን ሃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን የተመለከተ በመሆኑ፤ የአስተዳደር ተቋማት በሰዎች መብቶችና ጥቅሞች ላይ የሚያስከትሉትን ጣልቃገብነት በሕግ የሚመራና ለህግ የሚገዛ መሆኑን ለማረጋገጥ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የፌዴራል የአስተዳደር ስነ-ስርዓትን ለመደንገግ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።
4.የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ሌላው በም/ቤቱ የታዬ ጉዳይ ነው፡፡ የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት ለማህበራዊ ስምረት፣ ለፖለቲካ መረጋጋት፣ ለሀገራዊ አንድነት ፣ ለሰብአዊ ክብር፣ ለብዝሃነት ጠንቅ መሆኑን በመገንዘብ በተለይም በአሁኑ ወቅት በአገራችን በህብረተሰቡ መካከል ያሉ የመልካም እሴቶች በጥላቻ ንግግሮችና በሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ እየተሸረሸሩና ለሀገርም ስጋት የደቀኑ በመሆናቸው እንዲሁም እነዚህን ችግሮች አሁን ባሉት ህጎች መፍታት የማይቻል በመሆኑ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።
5. በመጨረሻም ም/ቤቱ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ እና በጅቡቲ ሪፐብሊክ መንግሥት መካከል የተፈጥሮ ጋዝ ቧንቧ መስመር ለማስተላለፍ የተደረገውን ስምምነት ለማጽደቅ የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ተቀብሎ አዋጁ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።
በሃዋሳ የምርጫ ጣቢያዎች የኢጄቶ አባላት ከፍተኛ ብጥብጥ ለመፍጠር ሞከሩ
በተጀመረው ለሲዳማ ህዝበ ውሳኔ እስከ ዛሬ ጥቅምት 29 ምሽት ድረስ 1 ሚሊየን 394 ሺህ 922 ድምጽ ሰጪዎች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ፡፡
የምርጫ ቦርዱ ሥራ ሓላፊዎች እና የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ አባላት፣ በተለያዩ ወረዳዎች በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው የምዝገባ ሂደቱን በዛሬው ዕለት በየቦታዎቹ ተገኝተው ተከታትለዋል፡፡
በ1 ሺህ 692 የምዝገባ ጣቢያዎች በተሰበሰበው መረጃ መሠረት እስከ አሁን 1 ሚሊየን 394 ሺህ 922 ድምጽ ሰጪዎች መመዝገባቸው ታውቋል:: በሃዋሳ ከተማ ምስራቅ ክፍለ ከተማ ምርጫ ጣቢያ አካባቢ ቀላል ያለኹከት ተከስቶ እንደነበርም የከተማዋን ነዋሪዎች በስልክ ያነጋገረው የኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባ ዘጋቢያችን ጠቁሞናል፡
የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ውስጥ የሃዋሳ ከተማ አለመካተቷን ምርጫ ቦርድ ያወጣው መግለጫ ያልተዋጠላቸው ኢጄቶዎች በሃዋሳ አካባቢ ሰሞኑን ግጭት ለመቀስቀስ ሃሳብና ሙከራው የነበራቸው ቢሆንም ይህ ዕቅድ በተጠናከረው የጸጥታ ኃይል አማካይነት መክሸፉን እነዚሁ ምንጮች ተናግረዋል::
በዚህን መሰሉ እንቅስቃሴ ዛሬ ምሽት ላይ ወደ ምርጫ ጣቢያው ለረብሻ ተጠግተው የነበሩ የኢጄቶ አካላት በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆኑን የኢትዮጵያ ነገ ታማኝ ምንጮች ለሪፖርተራችን ገልጸዋል:: የኢጄቶን የአመጽ ትንኮሳ በተመለከተ ከተለያዮ መንግሥታዊ የጸጥታ አካላት ከተዋቀረው ቡድን መረጃ ለማግኘት በስልክ ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው በዚህ ላይ ምላሽ አንሰጥም በሚል ድፍን ያለ መልስ ውድቅ ሆኖብናል::
የሃዋሳ ከተማ ፖሊስ ግን ነገሩን ለመሸፋፈን በሚመስል መልኩ በሥፍራው የተካሄደው የዝፊያ ሙከራ ነው ሲል አስቂኝ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ “ሲዳማ ያለ ሃዋሳ የማይታሰብ ነው” የሚሉ የተቃውሞ ድምጽ ሲያሰሙ የነበሩ ኢጄቶዎች ግን አሁንም ዛሬ ያደረጉትን የግጭት ትንኮሳ በቀጣዮች ቀናት ወይም ከምርጫው በኋላ ሊቀሰቀሱ ይችላሉ የሚል ስጋት በነዋሪዎች ዘንድ በስፋት መኖሩን ሪፖርተራችን ያነጋገራቸው ግለሰቦች ይናገራሉ::
በመካሄድ ላይ ባለው የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ምዝገባ ላይ ከፍተኛ ተመዝጋቢ የታየባቸው አካባቢዎች መሀል አርቤጎና፣ ሁላ፣ ወንሾ እና ቦና ዙሪያ ሲሆኑ ፣ ዝቅተኛ ተመዝጋቢ የታየባቸው አካባቢዎች ደግሞ ሃዋሳ ከተማ፣ አለታ ወንዶ እና ዳራ የተሰኙት አካባቢዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
አብን ከመወነጃጀል ወጥቶ ከአዴፓ ጋር ለአማራ ሕዝብ እንደሚሠራ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ አረጋገጡ
ከቀናት በፊት የአማራን ህዝብ ማዕከል አድርገው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል:: የጋራ መድረክበመፍጠር በሚያስሟሟቸው አጀንዳዎች ላይ አብረው ለመስራት የተስማሙት ፓርቲዎች አዴፓ፣ አብን፣ አዴኃን፣ መአህድ፣ መላው አማራ ህዝብ ፓርቲና ነፀብራቅ አማራ ናቸው።
ፖለቲካ ፓርቲዎቹ የተለያዩ ፕሮግራሞች፣ ርዕዮተ ዓለም ከመከተላቸው አንፃር ፣ እንዲሁም የአማራን ህዝብ ጥቅም አልወከሉም በሚል ከመወነጃጀላቸው ጋር ተያይዞ ፣ በምን አይነት ጉዳዮች ላይ አብረው ለመሥራት ስምምነት ላይ ደረሱ የሚለው ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን አስነስቷል::
በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ለተመሳሳይ ህዝብ እንደመሥራታቸው መጠን ምንም እንኳን ፕሮግራማቸውም ሆነ ሌሎች የሚለያዩዋቸው ጉዳዮች ቢኖርም አብሮ ለመስራት ዋነኛው መሰረቱ እንወክለዋለን የሚሉት ህዝብ ልማትና ብልፅግና እንደሆነ የአብን ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ገልጸዋል።
በዚህ መሰረት በማድረግ በዋነኝነት የአማራን ህዝብ ጥቅም እንዲሁም ደህነነት ማስጠበቅ አጀንዳዎች ላይ ስምምነት መደረሱን ፣ ይህም መሰረታዊ ለውጥ ለመሆኑ ሳይታለም የተፈታ እንደሆነና በተለይም ሲወነጃጀሉ ለነበሩ ፓርቲዎች አዙሪቱን የሰበረ አጋጣሚ መሆኑን የአብን ሊቀመንበር ይናገራሉ:: “ከመጠላለፍ ወጥተን ወደ መተባበሩ እንድናተኩር፤ የምናደርጋቸውም ውድድሮች በሰለጠነና በሰከነ መንገድ እንዲሆን ስምምነት ላይ ደርሰናል” በማለትም ስምምነቱን አብራርተዋል::
የአዴፓ ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተተካ በቀለ “መድረኩ የሚለየው ከመጠላለፍ ወጥቶ በሰከነ ፖለቲካዊ ትግል ውስጥ ለማለፍ እና በአማራ ህዝብ ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች የሚያደርጉት ሥራ በትብብር ላይ የተመሰረተ ሆኖ ህዝቡ በላቀ ደረጃ የሚጠቀምበት እና በአማራ የጋራ አጀንዳዎች ላይ በጋራ መስራት ነው። በዚህም ሁሉንም በአማራ ዙሪያ የሚሠሩ ድርጅቶች የተሰባሰቡበት እና ልብ ለልብ የተግባባንበት ነው ማለት ይቻላል” ሲሉ የድርጅታቸውን ሃሳብ አንጸባርቀዋል።
በፖለቲካው ዘርፍ ስምምነት ላይ ከደረሱባቸው መካከል የተወሰኑትን ደሳለኝ (ዶ/ር) እንደጠቀሱት ፓርቲዎቹ በማንኛውም እንቅሴያቸው ላይ ስም ከማጠልሸት፣ ከመወነጃጀልና ከመጠላለፍ መታቀብ፤ ወጣቱን በጋራ አቅጣጫ ማስያዝ፤ ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን አብሮ መስራት ግንባር ቀደሞቹናቸው።
“ለዘመናት የነበረውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የመጠላለፍና የመገዳደል ባህልንም የሚያስቀር ነው። አሁን ባለው ሁኔታ አማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ይህ ነው የሚባል ልዩነት የለንም” ያሉት አቶ ተተካ በበኩላቸው ፤የአማራን ህዝብና ፍላጎት በዘላቂነት ለማረጋገጥ፤ ከጥቃት ለመከላከል እና ከችግር ለመጠበቅ በአማራ ህዝብ ስም የተደራጁ ኃይሎች ማዶ ለማዶ ሆነው ከሚጠላለፉ ተቀራርበው መስራት በሚችሉበት ላይ አብረው ህዝቡን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ መጣር አለባቸው የሚል ጽኑ እምነት አዴፓ እንደያዘ አብራርተዋል።
በክልሉ ብቻ ሳይሆን ከክልሉ ውጭ ለሚኖሩ ሚሊዮን አማሮችም ድምፃቸው የሚሰማበትን መንገድ መቀየስ፣ ህዝቡ በቋንቋው የመጠቀም፣ ባህሉን የማዳበር እንዲሁም የፖለቲካ ውክልና የሚያገኙበት መንገድ ላይ ለመስራት የተስማሙት ፓርቲዎቹ፤ በተጨማሪ የህይወት ደህንነቱ፣ የንብረት ዋስትና የማግኘት እሱንም የማስጠበቅም ሥራ ለመሥራት ማቀዳቸውንም ገልጸዋል። በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊና የወጣቱንም የፖለቲካ ተሳትፎ በመጨመር ረገድም አብረው ለመሥራት ከተስማሙባቸው ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች መካከል ለአብነት ተቀምጠዋል።
ምንም እንኳን የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ስምምነት በአንዳንድ አካላት ዘንድ እንደ ውህደት ወይም ግንባር የመፍጠር አድርገው የተመለከቱት ቢኖሩም ደሳለኝም (ዶ/ር) ሆነ አቶ ተተካ ይህ እንዳልሆነ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል:: “በሚያስማሙን እና በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ አብረን እንሥራ፤ በማያግባቡን ደግሞ እንተባበር ነው። በጋራ የመሥራት ፍላጎት ሰነድ እንጂ አስገዳጅ ህግም ሰነድም አይደለም ” ሲሉ የገለጹት አቶ ተተካ፤ ወደፊት በግንባር ደረጃ ወይንም በመዋሃድ ዕቅድ ይኖር ይሆን ወይ? በሚል ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ዓላማ እና አጀንዳ እየጠበበ ከሄደ በሁለት ወይም ከዚያ በላይ ድርጅቶች መካከል እስከ ውህደት ልናመራበት የምንችልበት አጋጣሚ ዝግ ላይሆን ይችላል” ሲሉ ተደምጠዋል::
በትብብር መድረኩ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆኑ ምሁራን የሃይማኖት አባቶች እና ታዋቂ ሰዎች መኖራቸውን ጠቅሰው በየጊዜው በመገናኘት ሥራዎች እየተገመገሙ አቅጣጫ በማስያዝ በቀጣይነት እንደሚሰራም ያስረዳሉ።
“ለዓመታት የጨቋኝና ተጨቋኝ ታሪክ በመፍጠር የአማራን ህዝብ የባይተዋርነት ስሜት እንዲሰማው ለረዥም ጊዜ ተሰርቷል፤ ይሄ በጥናትና በዕውቀት ተመስርቶ መቀልበስ አለበት የሚል ፅኑ እምነት አዴፓ አለው፤ ይህንን ከሞላ ጎደል ሌሎች ፓርቲዎችም ይስማሙበታል” የሚሉት ከፍተኛ አመራር ፤ ለረዥም ጊዜያት አብን፤ አዴፓን ወይም የቀድሞውን ብአዴን ለአማራ ህዝብ ጥቅም እየሰራ አልነበረም፤ የአማራ ህዝብ ውክልና የለውም ሲሉ በተደጋጋሚ ይሰማ ነበር፤ ይህንን ሃሳባቸውን ያስቀየራቸው ጉዳይም አዴፓ ካደረገው የአመራር ለውጥ ጋር እንደሚገናኝም ጠቁመዋል።
የቀደመ የአዴፓ ታሪክ “የአማራን ህዝብ አጀንዳ አሳልፎ የሚሰጥ ነበር” ያሉት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ካለፈው ዓመት ጀምሮ ግን ድርጅቱ ውስጥ “ለአማራ ጥቅም አልታመኑም” የተባሉ አመራሮችን ያጠራበት፤ የተሻለ የአማራ ወገንተኝነት የሚያሳይና ለአማራ ህዝብ የሚቆረቆሩ አመራሮችን ወደፊት ያመጣበት ሁኔታ ተፈጥሯል ይሄ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም አብሮ በመስራት ደረጃ የሚያስችለውን ማስተካከል አምጥቷል”ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አዴፓ ደግሞ ሕገ መንግሥቱን ካረቀቁት ድርጅቶች አንዱ ከመሆኑ አንፃር ተቃርኖ የለውም ወይ? ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) አብን ሕገ መንግሥቱ የአማራ ህዝብ ስላልተወከለበት ሊሻሻል ይገባል ብሎ ከማመኑ አንፃር አዴፓም ይህንን መቀበሉ አብሮ ለመስራት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።
ከአዴፓ ጋር ከነበራቸው ቅራኔ በተጨማሪ ህወሓትን ጋር ያላቸውን የከፋ ቅሬታም በተደጋጋሚ ከመናገራቸው አንፃር፤ አብረው ሊሰሩት ያቀዱት አዴፓ ደግሞ ከህወሓት ጋር በአንድ ግንባር ስር ነው፤ ይህ እንዴት ይታያል?ለሚለውም፤ምንም እንኳን ህወሓትና አዴፓ ከአስርት ዓመታት በላይ በእህትማማችነት በኢህአዴግ ውስጥ ሲሰሩ የቆዩ ቢሆንም በቅርብ ጊዜያት ግን በግልፅ ተቃርኗቸው እየታየ ነው ያሉት የአብን ሊቀመንበር በቅርብ ጊዜያት ፓርቲዎቹ ባወጧቸው መግለጫዎችም ያላቸውን የሻከረ ግንኙነት ያሳየ ሲሆን፤ ይህንንም በማየት በአሁኑ ሰዓት ያላቸው ግንኙነት የይምሰል አይነት እንደሆነ ጠቁመው ፣ ይህንንም በመታዘብ በቀጣይ ሊፈጠር በሚችለው አዲሱ የውህድ ፓርቲ ህወሓት ሊገባ የማይችልበት እድል ሰፊ መሆኑን ያስረዳሉ።
“አዴፓ ወደ አማራ ህዝብ ጥያቄ እየቀረበ መሔዱን የሚያሳይ ነው፤ እሱንም የሚያረጋግጥልን ነው። ከአዴፓም ጋር እያደረግናቸው ያሉ ግንኙነቶች ወደፊት የሚያስኬደን መሆኑን የሚያሳይ ነው። ከህወሓት ጋር በአንድ ግንባር ውስጥ ስላለ አማራዊ የሆነውን አዴፓን ገፍተን አብረን አንሰራም የምንልበት ምክንያት ሊኖር አይችልም” በማለት ከላይ ያነሱትን ሃሳብ እንደምታ በግልጽ ካስቀመጡ በኋላምንም እንኳን ህወሓት ላይ ከፍተኛ ቅሬታ ቢኖራቸውም ህወሓትም ቢሆን ሥርዓት ወዳለው የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲገባ አብን ፍላጎቱ መሆኑን ይፋ አድርገዋል::
የድሬደዋ ዮንቨርስቲ ሴት ተማሪዎች የእርግዝና ምርመራ ጉዳይ እያነጋገረ ነው
በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ፤ ሴት ተማሪዎች በመንግሥት ሆስፒታል የእርግዝና ምርመራ አድርገው በ48 ሰዓት ውስጥ ለፕሮክተራቸው (ለተቆጣጣሪዎች) እንዲያስገቡ የሚያሳስብ ማስታወቂያ መውጣቱ በርካቶችን እያነጋገረ ይገኛል::
ዩኒቨርሲቲው “ማስታወቂያው የወጣው በስህተት ነው” ሲል ማስተባበያ ቢያወጣም፤ ማስታወቂያው ለምን እና እንዴት ወጣ? ተማሪዎች እንዲመረመሩ ማስገደድ ሕጋዊ አግባብ አለው? በዩኒቨርስቲው ተማሪዎች በተደጋጋሚ ስለመውለዳቸው እና ህጻናት ተጥለው ስለመገኘታቸው የሚናፈሰው እውነት ነው? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች በመቅረብ ላይ ናቸው።
ትናንትና ጥር 28 ቀን ማስታወቂያው የወጣው በተማሪዎች ኅብረት እንደሆነ የሚገልጸው የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዘዳንት ዳንኤል ጌታቸው፤ “ጠዋት ላይ ሕዳር 28 ቀን 2012 ዓ. ም ውይይት ሳይኖር በተማሪዎች ኅብረትና በዩኒቨርስቲው መካከል በስሜታዊነት የተደረገ ነው፤ ስህተት መሆኑን አምነን ይቅርታ ጠይቀናል” ሲል ማስተባበያ ሰጥቷል።
በዕለቱ ጠዋት ላይ ልጅ ወልዳ መንገድ ዳር ጥላ የሄደች ተማሪ እንደነበረች የሚናገረው ዳንኤል፤ ክስተቱ ስሜታዊ እንዳደረጋቸው ገልጾ፤ ይህን ተከትሎ ማስታወቂያው የወጣው ነገሩ ስላሳሰባቸው መሆኑንም አስታውቋል::
የተባለው ችግር በዩኒቨርስቲው አለ ቢባል እንኳን፤ የእርግዝና ምርመራ ይደረግ ብሎ ማስገደድ እንዴት መፍትሔ ይሆናል? በሚል ለቀረበው ጥያቄ፤ “ሌሎች ሴቶች ላይ እንዳይከሰት አስበን ነው፤ ባለማስተዋል የተደረገ ነው” ሲል መልሷል።
በዩኒቨርስቲው ተማሪዎች በተደጋጋሚ ይወልዳሉ? ህጻናት ተጥለው ስለመገኘታቸው የሚናፈሰው ወሬስ እውነት ነው? የሚል ጥያቄ የቀረቀላቸው የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ወ/ት መቅደስ ካሳሁን “ምን ያህል አለ? እስከዛሬ ምን ተሠራ? የሚለው መረጃ ተሰብስቦ እየተሠራ ነው። ሠርተን ይፋ እናደርጋለን” ካሉ በኋላ ፤ የተማሪዎች ኅብረት፣ የተማሪዎች ዲን እና ፕሮክተሮች፤ ዩኒቨርስቲው ላይ እውን ይሄ ነገር ይደጋገማል ወይ? ከሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ምን የተለየ ነገር አለ? የሚለውን መረጃ በመሰብሰብ እየሠሩ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ትላንት የወጣውን ማስታወቂያ በተመለከተም “ማስታወቂያ ወጥቷል። ግን የወጣው ኦፊሻል አይደለም። እኛ አስተባብበለን በኦፊሻል ገጻችን ላይ አውጥተናል” ብለዋል ወ/ት መቅደስ። የሕግ ባለሙያዋ ወ/ሮ ሰብለ አሰፋ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርስቲው ማስታወቂያው ኦፊሻል አይደለም ሲል ቢያስተባብልም፤ የተማሪዎች ኅብረት የአስተዳደሩ አካል በመሆኑ ይህን ማለት አይችልም ይላሉ።
“አስተዳደሩ በሥሩ ያሉ ተማሪዎችን ያለ ፍቀዳቸው አገድዶ የህክምና ምርመራ እንዲያደርጉ የማድርግ ሥልጣን የለውም። ተማሪዎቹ በአንድ ማስታወቂያ ይህን እንዲያድረጉ በማዘዝ ያወጣው ነገር ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀም ነው” ሲሉ ተችተውታል::
በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሕግም፤ አንድ ግለሰብ ያለፈቃዱ የህክምና ምርመራ እንዲያደርግ እንዳይገደድ በሕግ ጥበቃ የማግኘት መብት እንዳለው ጠቁመው ፤ “አስተዳደሩ ተማሪዎች ምርመራውን እንዲያደርጉ ያወጣው ማስታወቂያ ግልጽ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው። ግልጽ የሆነ የሕግ ድንጋጌዎችን የሚጻረርም ነው” ሲሉ ገልጸዋል::
የዋሽንግተን ዲሲ ከንቲባ 50 አሜሪካውያን የቢዝነስ ሰዎችን ይዘው ሸገር ደረሱ
የአሜሪካዋ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ከንቲባ ሙሪየል ቦውሰር ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ መግባታቸው ተነገረ::
ከንቲባ ሙሪየል ዛሬ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲድርሱ አቻቸው ምክትል ከንቲባ ኢነጂነር ታከለ ኡማና የተለያዩ የከተማ መስተዳደሩና የፌዴራል መንግሥቱክፍተኛ የሥራ ሓላፊዎች አቀባበል እንዳደረጉላቸው ለማወቅ ችለናል::
ከዋሽንግተን ከንቲባዋ ጋር ከ50 በላይ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት አዲስ አበባ መግባታቸውን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል::
ከንቲባዋ ወደ አዲስ አበባ የመጡበት ዋነኛ ምክንያትከዚህ ቀደም ምክትል ከንቲባ ኢንጂነርር ታከለ ኡማ በዋሽንግተን ዲሲ ባደረጉት ጉብኝት ወቅት ባቀረቡላቸው ግብዣ መሰረት እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ::
ከንቲባ ሙሪየል ቦውሰር በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታየተለያዩ ጉብኝቶችን የሚያደርጉ ከማድረግ ባሻገርአዲስ አበባና ዋሽንግተን ዲሲም የእህትማማች ከተማነት ስምምነታቸውን የሚያጠናክር ስምምነት ይፈራረማሉ የሚል ቅድመ ግምት ከወዲሁ እየተሰማ ነው።
የትዊተር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጃክ ፓትሪክ ዶርሴይ በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደርጋሉ
የትዊተር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጃክ ፓትሪክ ዶርሴይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአራት የአፍሪካ ሀገራት ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተገለጸ:: ሥራ አስፈጻሚው ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀሪያ እና ጋና የሚደርጉትን ጉብኝት መጀመራቸው ታውቋል::
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለአንድ ወር የሚቆየውን የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በትናትናው ዕለት በናይጀሪያ ሌጎስ እንደጀመሩ መረጃዎች ጠቁመዋል::
ጃክ ፓትሪክ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከቴክኖሎጂ ንግስቷ ቤተልሄም ደሴ እና የአፍሪካ ቴክ ኔክስት አንደኛውመስራች ከሆነው ኖኤል ዳንኤል ጋር ሠፊ ውይይት ያካሂዳሉ ተብሎ ከወዲሁ ተገምቷል:: ዋና ስራ አስፈፃሚው በተጨማሪም ከሌሎቸ በርካታ ሥራ ፈጣሪዎች ጋር ተጨማሪ የውይይት ጊዜን እንደሚያሳልፉ ነው የታወቀው::
የትዊተር ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ጃክ ፓትሪክ ዶርሴይ አሜሪካ የኮሙፒውተር ፕሮግራመር እና ኢንተርኔት ሥራ ፈጣሪ እንዲሁም ስኩዌር የተባለው የሞባይል የክፍያ ኩባንያ ሥራ አስፈፃሚ ናቸው፡፡