በኢትዮጵያ “ሙስሊም ጠልነት” ስለመኖሩ || መሐመድ አሊ መሐመድ

በኢትዮጵያ “ሙስሊም ጠልነት” ስለመኖሩ || መሐመድ አሊ መሐመድ

|| በኢትዮጵያ "ሙስሊም ጠልነት"(Islamo-phobia) ስለመኖሩ፣ 
መሐመድ አሊ መሐመድ-ጠበቃና የሕግ አማካሪ||

በእኔ እይታና ግምገማ በኢትዮጵያ ሙስሊም ጠልነት (Islamo-phobia) ሰፊ ማህበራዊ መሠረት ያለው አይመስለኝም፡፡ ምናልባትም በአንዳንድ አካባቢዎችና ወገኖች ዘንድ ሙስሊሙን በአጉል ጥርጣሬና ሥጋት የማዬት ችግር፣ ብሎም በጠላትነት የመፈረጅ አዝማሚያ መኖሩን መካድ አይቻል ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን ይህ የተዛባ አመለካከትና የተሳሳተ ዝንባሌ አብዛኛውን (የሌሎች እምነቶች ተከታይ የሆነውን) ህዝብ ሊወክልና፣ መገለጫው ተደርጎም ሊወሰድ አይችልም፡፡

በመሬት ላይ ያለውን ሐቅ በጥሞና ካየነው፣ አብዛኛው ህዝብ (የእምነት ልዩነቶቹ እንደተጠበቁ ሆነው) በፈርጀ-ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች የተሳሰረ ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ በጋብቻና በዝምድናም ጭምር የተሳሰረ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በጥቅሉ ሲታይ (almost exclusively) የአንድ እምነት ተከታይ ናቸው የሚባሉ ማህበረሰቦችም ቢሆኑ እንኳ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር በጋብቻና በዝምድና የተሳሰሩ ስለመሆናቸው በርካታ አብነቶችን ጠቅሶ መናገር ይቻላል፡፡

መሬት ላይ ያለው ሐቅ በተጨባጭ የሚያሳዬን፣ አብዛኛው ህዝብ በመኖሪያ አካባቢ በሚቋቋሙ ዕድሮች፣ በዕቁብ፣ በንግድና በሌሎች ሥራዎች/አገልግሎቶች የተሳሳረ መሆኑን ነው፡፡ ጉዳዩን በቅርበትና በጥልቀት ከመረመርነው፣ አንዱ ያለሌላው መኖር የሚችልበት ተጨባጭ ሁኔታ የለም፡፡ በዚህ ሁኔታ፣ አብዛኛው ህዝብ የእምነት ልዩነት ሳይከልለው ደስታና ሀዘኑን በጋራ የሚካፈልበትን እውነታ መዘንጋት አያስፈልግም፡፡ በየትኛውም አካባቢ ቢሆን የአንዱ እምነት ተከታይ ሠርግ ሲደግስ ወይም ሌላ ማህበራዊ ጉዳይ ሲኖረው የሌላውን እምነት ተከታይ ታሳቢ ሳያደርግ አይቀርም፡፡ በሞት፣ በቀብር ሥነ-ሥርዓት፣ በሀዘንና ሌሎች ችግሮች ላይም ህዝቡ (የእምነት ልዩነቶቹ እንደተጠበቁ ሆነው) በጋራ የሚረባረብበትንና አብሮነቱን የሚያረጋግጥበትን ሁኔታና/እውነት በአንክሮ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

ዳሩ ግን “በጥባጭ ሳለ ማን ጥሩ ይጠጣል” እንዲሉ አንዳንድ ኃላፊነት የማይሰማቸው “አጉል ብልጣብልጥ” ግለሰቦችና በተሳሳተ ትርክት የተቃኙ ቡድኖች ራሳቸውን የሃይማኖት ተቆርቋሪ በማድረግ፣ የራሳቸውን ሥምና ዝና ለመገንባት፣ በአቋራጭ ከፍ ያለ ማህበራዊ ማማ፣ ወይም ሥልጣን ላይ ለመንጠላጠልና/ለመውጣት፣ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ሀብት ለማፍራት … ሲሉ ለዘመናት በሰላምና በመደጋገፍ አብሮ፣ ተጋብቶ፣ ተዋልዶና ተዛምዶ የኖረውን ህዝብ የእምነት ልዩነቱን መሠረት በማድረግ በጥርጣሬና በሥጋት እንዲተያይ፣ ብሎም ያላስፈላጊ ግጭት ውስጥ እንዲገባ ሌት ከቀን ሲባዝኑ ማዬት የተለመደ ሆኗል፡፡ አልፎ አልፎም በአንዳንድ አካባቢዎችና አጋጣሚዎች የጥረታቸውን ፍሬ መሰብሰብ ስለመቻላቸው “ድንዙዝ” እማኝ ለመሆን ተገድደናል፡፡

ሆኖም ግን በእምነት ልዩነት ሳቢያ ከሚፈጠር አጉል ጥርጣሬ፣ መሠረተ-ቢስ ሥጋትና አላስፈላጊ ግጭት አብዛኛው ህዝብ አትራፊ ሊሆን የሚችልበት አመንክኖና ስሌት ሊኖር አይችልም፡፡ ከዚህ ሊያተርፉ የሚችሉት ብዙሃኑን በስሜት ሸብበው የሚጋልቡ “ጥቂት ብልጣ-ብልጦች” ብቻ ናቸው፡፡ ለሌላው የሚተርፈው ባላስፈላጊ ግጭት ህይወትን ማጣት፣ የአካል መጉደል፣ የንብረት ውድመት፣ ከሌላው ወገኑ ጋር የነበረውን አብሮነት ማጣት፣ አጉል የጠላትነትና የበቀል ስሜትን ማዳበር፣ ብሎም ቀጣዩን ጊዜ/ወደፊቱን የጨለመና አስፈሪ አድርጎ ማዬት ነው፡፡

እንግዲህ አንዳንድ ኃላፊነት የጎደላቸው (የሃይማኖት ጽንፈኛ የሆኑ?) ግለሰቦችና የሚፈጥሯቸው ቡድኖች በቀየሱት የተሳሳተ አቅጣጫና አካሄድ ለወጡበት ማህበረሰብ የሚያመጡለት ትርፍ፣ ከላይ የጠቀስነውና ከዚሁ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ፈርጀ-ብዙ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲዊ ችግሮችንና ምስቅልቅሎችን ነው፡፡ ይህ አደገኛ አዝማሚያ በወቅቱና በእንጭጩ ካልተቀጨ በቀላሉ የማንወጣው ሀገራዊ ቀውስ ውስጥ ሊያስገባን እንደሚችል መናገር “አጉል ሟርት” ቢሆን ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር፡፡ ሆኖም ግን እውነቱና አደጋው አፍጥጦ እየመጣ እያዬነው የሚሆነውን ዝም ብሎ መጠበቅ “ከአደጋ ለማምለጥ ጭንቅላቷን አሸዋ ውስጥ እንደምትቀብረው ሰጎን ብጤ” ከመሆን አይለይም፡፡ በሌላ አነጋገር አሁን በሀገራችን እየተፈፀመና እየሆነ ካለው አስፈሪና/አሳፋሪ አውነት አንፃር እንደ ሀገርና እንደ ህዝብ ዝምታችን እጅግ የበዛ መሆኑም ይበልጥ አስፈሪና አነጋጋሪ ነው፡፡

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ አንዱ፣ በቅርቡ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በአንድ መድረክ ላይ “ወገን በወገኑ በጭካኔ ሲታረድ፣ እንደ አደገኛ አውሬ በድንጋይና በአጣና ተቀጥቅጦ ሲገደል፣ ሆዱ በስለት ተቀድዶ አንጀቱ ሲዘረገፍ፣ ሬሳው መሬት ላይ ሲጎተት የሚያሳዩ ዘግናኝ ቪዲዮችን ምግብ እየበላን ጭምር የምናይበትንና እየሆነ ያለውን ነገር ከምግባችን ጋር ተረጋግተን የምናጣጥምበትን አውነት” አበክሮ መጠየቁ ነው፡፡ የአቡበከርን ንግግር ቃል በቃል ባልወስደውም ይዘቱ ግን ከዚህ የራቀ አይደለም፡፡ ኡስታዝ አቡበከር ይህን አስፈሪና/አሳፋሪ እውነት እንዴት ልንለማመደው እንደቻልን አምርሮና አበክሮ ይጠይቃል፡፡

ሁለተኛው ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር እንድሪስ የነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) ልደት (መውሊድ) ምክንያት በማድረግ ያደረጉት ንግግርና ያቀረቡት ተማፅኖ ነው፡፡ የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር እንድሪስ አቀራረብና ሰብዕና ሙስሊሙን ብቻ ሳይሆን የሌሎች እምነቶች ተከታዮችንም ልብ ማሸነፉ አልቀረም፡፡ በመሆኑም በአንዳንዶች ዘንድ “የእብዶች መናኸሪያ” ተብሎ በሚወሰደው በዚህ በማህበራዊ ሚዲያ ሳይቀር ለሙፍቲ ሐጅ ዑመር እንድሪስ (በአብዛኛው ከሌሎች እምነት ተከታዮች) እጅግ የበዛ አድናቆት ሲጎርፍ አይተናል፡፡ ከዚህም በመነሳት፣ እዚህ ሀገር (ምናልባትም) መሠረተ-ቢስ ሥጋት ካልሆነ በስተቀር ሥር የሰደደ “ሙስሊም ጠልነት” ሊኖር ይችላል ወይ? የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢነት አለው፡፡

ከዚህ የተለዬ እይታ ያላቸውና “በኢትዮጵያ ሥር የሰደደ ሙስሊም ጠልነት አለ” የሚሉ ወገኖች ካሉም፣ ሁለት ነገሮችን ልብ ማለት ይኖርባቸዋል፡፡ አንደኛው በሀገራችን በአንዳንድ አካባቢዎችና በተወሰኑ ወገኖች ዘንድ “ሙስሊም ጠልነት አለ” ቢባልንኳ፣ በአብዛኛው ከግንዛቤ ዕጥረትና ከተሳሳተ ትርክት የመነጨ፣ የራሱ መነሻና ሀገራዊ ቀለም ያለው እንጅ በሌላው ክፍለ-ዓለም ካለው “ሙስሊም ጠልነት” (islamo-phobia) ጋር የማይገናኝና የማይመሳሰል መሆኑን ነው፡፡ ሁለተኛው “ሙስሊም ጠልነት” መኖሩን ከማመላከት ባለፈ ምንጩን መለዬትና አስተሳሰቡን ማስቀየር የሚቻልበትን ስልትና አቅጣጫ መከተል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር እንድሪስ አቀራረብ በአርኣያነት ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡

በግሌ የእስልምና እምነት በዓላትን ምክንያት በማድረግ ከሌሎች እምነት ተከታይ ወንድሞችና እህቶቼ (የቀድሞ አንጋፋ የፖለቲካ ጓዶቼን ጨምሮ) የሚጎርፉልኝ የደስታና የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቶች የእጅ ስልኬን ብቻ ሳይሆን ልቤንም በፍቅር የሚያጨናንቁ ናቸው፡፡ ከዚህ ከfacebook መንደርም በውስጥ መስመር እጅግ በርካታ ተመሳሳይ መልዕክቶች እንደደረሱኝ ምስክሮቼ ራሳቸው ላኪዎቹና ቅን አሳቢ ወዳጆቼ ናቸው፡፡ ሌሎች ሙስሊም ወንዴምችና እህቶችም ተመሳሳይ ልምድ ሊኖራቸው እንደሚችል እገምታለሁ።። እንዲህ ዓይነት ልምዶች በሁሉም ዘንድ ቢስፋፉና ተጠናክረው ቢቀጥሉ ይበልጥ ኢትዮጵያውያን ይበልጥ እርስ በርስ እንድንቀራረብ በማድረግና አብሮነታችንን በማጠናከር ረገድ የማይናቅ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል፡፡

ይበልጥ መቀራረቡ ደግሞ አብሮነታችንን ከማጠናከር ጎን ለጎን በጥሞና ለመነጋገር፣ ለመደማመጥ፣ አንዳችን በሌላችን ጫማ ውስጥ ሆነን ለማሰብ፣ ባለፈው (የፖለቲካ) ታሪካችን የነበሩ ክፍተቶችን ለመለዬት፣ ስህተቶችን ለማረም፣ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠርና ነጋችንን/ወደፊታችንን በተሻለ መንገድ ለመቃኘት እንደሚረዳ ጥርጥር የለውም፡፡ ከዚህ በተቃራኒው በየራሳችን አሉታዊ ትርክት ተሞልተን፣ ሞዶ ለማዶ ተራርቀን መተያዬትና አላስፈላጊ እንካ ሰላንቲያ ውስጥ መግባት ለማንኛችንም ቢሆን፣ አንዳችም ትርፍ ሊኖረው አይችልም፡፡ ስለሆነም ሁላችንም ይበልጥ አትራፊና ተጠቃሚ መሆን የምንችልበትን ቀና መንገድ አላህ/እግዚአብሔር ያመላክተን ዘንድ በዱኣ/በፀሎት የተደገፈ ቅን ተነሳሽነት መውሰድ እንደሚያስፈልግ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

እባካችሁ፣
ሁላችንም በየፊናችን፣
ለዘላቂ አብሮነትና አንድነታችን በርትተን እንሥራ!!!

* * *
ግን ዛሬ በበዓሉ ምድር እንዴት ይኸን ላስብ ቻልኩ?

ለማንኛውም ለሙስሊም በዓላት ተገቢውን ዕውቅና እና ሽፋን ለሚሰጡ የሚዲያ ተቋማትና (ፋና ቲቪን ጨምሮ) ጋዜጠኞች ልባዊ አድናቆትና ምስጋናዬን ለመግለፅ እወዳለሁ!!!

LEAVE A REPLY