አፄ ምንሊክ ሐውልት ስር የተሠራው የቆርቆሮ ቤት እንዲፈርስ ባላደራው አሳሰበ

አፄ ምንሊክ ሐውልት ስር የተሠራው የቆርቆሮ ቤት እንዲፈርስ ባላደራው አሳሰበ

የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት በታላቁ ንጉሥ መታሰቢያ  በአፄ ምንሊክ  ሐዉልት አደባባይ ውስጥ ታጥሮ የተቀመጠው የቆርቆሮ ቤት እንዲፈርስ  አሳሰበ፡፡

የታላቁ ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሐዉልት በቅርብ ጊዜ ዕድሳት ተደርጎለት ቢጠናቀቅም ለረጅም ጊዜ ታጥሮ የተሠራዉ የቆርቆሮ ቤት ሳይነሳ እንደተራ ሥፍራ እንዲቀመጥ ተደርጓል:: ከዚህ በተጨማሪ ሐውልቱ ባለበትበግቢዉ ውስጥ የሚታየው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴም አሳፋሪና አሳዛኝ ከሆነ ሰንብቷል:: የኢትዮጵያውያን ባለውለታና ታላቁ ንጉሥ ሐውልት ያረፈበት የታጠረ ግቢ ውስጥ ልብስ እያጠቡ የሚያሰጡ ግለሰቦች መኖራቸው በተደረገዉ ማጣራትና ከህዝብ በመጣ ጥቆማ ለመታዘብ ተችሏል፡፡

ባለአደራዉ ይህን የህዝብ ጥያቄ ከግምት በማስገባት የሚታዩ ስጋቶችን ለመቅረፍ የተሰራው ቤት በፍጥነት እንዲፈርስ፣ በውስጡ የሚታየዉ የፅዳት መጓደል እንዲስተካከል ለአራዳ ክ/ከተማ ደንብ ማስከበር ዘርፍ በደብዳቤ አሳስቧል፡፡

ይህን ጥያቄ የተቀበሉት የአራዳ ክ/ከተማ ደንብ ማስከበር ዘርፍ ሓላፊ በአጭር ጊዜ ከአመራሩ ጋር በመነጋገር መልሳቸዉን እንደሚያሳውቁ በቃል አስረድተዋል፡፡ ሐውልቱን ማደሱ የሚያስመሰግነው መንግሥታዊ አካል ትልቁን ተግባር ከከወነ በኋላ ቀጣይ ክትትሉን መተው መጀመሪያውኑም  ዕድሳቱ የተካሄደው ለፖለቲካ ፕሮፐጋንዳ ትርፍ ማግኛ ነው የሚል ትችትን ከከተማዋ ነዋሪ እያሰጠ መሆኑን በጉዳዮ ላይ አስተያየታቸውን የሰነዘሩ በርካታ ዜጎች በአዲስ አበባ ለሚገኘው ለኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር ገልጸዋል::

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ማንነቷ ተጠብቆ እንዲቆይ ጣልያንን አሽመድምደው የላኩትና የስልጣኔው ፊታውራሪ የዳግማዊ ምንሊክ ሐውልት ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ፊት ለፊት የሚገኝ መሆኑና ይህ ታሪካዊ ሐውልት ማንም የሚፀዳዳበት ፣ ልብስ ማጠቢያና ማስጫ ሲሆን ዕለት ተዕለት ሲወጡና ሲገቡ የሚያስተውሉት ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ እና የመስተዳድሩ ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚዎች ምንም ዓይነት ማስተካከያ ሳይወስዱ በዝምታ ማለፋቸው እያስተቻቸው ይገኛል::

በአዲስ አበባ የባለቤትነት ዙሪያ የሚንቀሳቀሰውን የባላደራ ምክር ቤት እንቅስቃሴዎችን በሙሉ ለመግታት ያልቦዘነውና ራሱን የከተማዋ ተቆርቋሪና ብቸኛ ተወካይ ያደረገው የታከለ ኡማ አስተዳደር በህዝብ ተቀባይነት ለማግኘት ከሚያደርጋቸው የተለያዮ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የዳግማዊ ምንሊክ ሐውልት ላይ እየተፈጸመ ያለውን አሳፋሪ ተግባር ለማስቀረት ምንም ሙከራ አለማድረጉ ለከተማዋ ህዝብም ሆነ ለኢትዮጵያዊነት ያለው ስሜት የወረደና የይስሙላ መሆኑን በርካታ ነዋሪዎች ለኢትዮጵያ ነገ ተናግረዋል::

በጋዜጠኛና የሰብኣዊ መብት ተሟጋቹ እስክንድር ነጋ በዳግማዊ አፄ ምንሊክ ሐውልት ዙሪያ የተሠራው ቤት እንዲፈርስና የሚደረገው ተገቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲቆም የጠየቀበትን ሙሉ ደብዳቤ እንደሚከተለው አቅርበነዋል::

ጉዳዩ፡- በምንሊክ አደባባይ ስለተሰራው ቆርቆሮ ቤት

      በምንሊክ አደባባይ የታላቁ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምንሊክ መታሰቢያ  ሀውልት  ቆሞ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ሀውልቱ የአዲስ አበባ መለያ ሆኖ ከመቆየቱም ባሻገር፣ ከአድዋ ድል ጋር በተሳሰረ የመላ አፍሪካዊያንም ኩራት መገለጫ ሆኖል፡፡ በዚህም ሳቢያ፣ በመላ ኢትዮጵያዊያን ዘንድም ሆነ በአፍሪካዊያን ዘንድ በታላቅ ከበሬታ የሚታይ ነው፡፡

  ሆኖም፣ ቀላል ለማይባል ጊዜ ሀውልቱ በሚገኝበት አደባባይ  ህገ ወጥ የቆርቆሮ ቤት ተገንብቶ ይገኛል፡፡ ይህ ህገ ወጥ ቆርቆሮ ቤት የታላቁን ንጉሠ ነገሥት ክብር ለመንካት ሆን ተብሎ ከመቆሙም ባሻገር፣ የከተማዋን መልካም ገጽታ በእጅጉ አበላሽቶታል፡፡

  ይህን አስመልክቶ ህዝቡ ተደጋጋሚ ጥያቄ እያቀረበ የሚገኝ በመሆኑ፣ በህዝቡ ጥያቄ መሠረት ህገ ወጡ ቆርቆሮ ቤት እንዲፈርስና በአደባባዩ ላይ ምንም ዓይነት ህገ ወጥ ግንባታ እንዳይደረግ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ በትህትና እንጠይቃለን፡፡

ከሰላምታ ጋር

እስክንድር ነጋ

የአዲስ አበባ ባለ አደራ ምክር ቤት ሰብሳቢ

አዲስ አበባ

LEAVE A REPLY