የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 8 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 8 ቀን 2011 ዓ.ም

ሃዋሳና የሲዳማ ዞን ከተሞች በመከላከያና ፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር ሆኑ

የሲዳማ የክልልነት ህዝበ ውሳኔ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የሲዳማ ዞን አስተዳደር ገለፀ።

የሲዳማ የክልልነት ህዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ በነገው እለት ይካሄዳል። የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ሌዳሞ ይህንን አስመልክቶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ ህዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን አረጋግጠዋል።

ሀዋሳ ከተማን ጨምሮ በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ከኀብረተሰቡ ጋር ውይይት ሲደርግ መቆየቱን ጠቁመው ከዚህ አኳያ ምንም አይነት የጸጥታ ስጋት ሊኖር እንደማይችል አስረድተዋል። የፀጥታ አካሉ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከክልሉ ልዩ ኃይል እና ፖሊስ ጋር በጋራ በመሆን ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን ዝግጅት ማድረጋቸውም ተሰምቷል።

የመራጭነት ካርድ የወሰዱ መራጮች ከነገ ህዳር 10 ከማለዳው 12 ሰአት ጀምሮ ወደ ምርጫ ጣቢያ በማምራት ድምጽ እንዲሰጡ መልዕክት ያስተላለፉት አስተዳዳሪው ፤ ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ እንዲሆን የዞኑ አስተዳደር ጽኑ እምነት እንዳለውም ገልፀዋል::

የሲዳማ ዞን ሠላም እና ፀጥታ መምሪያ ሓላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በበኩላቸው በዕለቱ የተለያዩ የመንግስት እና የንግድ ተቋማት አገልግሎት የማይሰጡ መሆኑን በማስታወስ መራጮች ያለምንም ስጋት ሙሉ መብታቸውን እንዲጠቀሙ መክረው፤ ከዛሬ ምሽት 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ዓርብ ማለዳ ድረስ በሃዋሳ ከተማ እና የሲዳማ ዞን የሁለት እግር ሞተር ተሽከርካሪዎችአገልግሎት የተከለከለ መሆኑን አስታውቀዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ ፣ ሶማሊኛና አፋርኛ የፌደራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ ተወሰነ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመላ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውንና ባለፉት ሦስት ቀናት አዲሱን የብልጽግና ፓርቲ ለመመስረት የተከናወነውን የውይይት ጉባዔ ሂደት አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የግንባሩ ሥራ አስፈጻሚ ውሕደቱን በተመለከተ፣ አዲሱ ሕገ ደንብ እና ፕሮግራም ዙሪያ በጥልቀትመወያየታቸውንና ጠቃሚ ውሳኔዎች ማሳለፋቸውን  ጭምር ይፋ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ኢሕአዴግ የስምና የመዋቅር ለውጥ የሚያደርግበትን የአዲሱን ፓርቲ ስያሜ አስመልክተው  ከ27 ዓመት በላይ የዘለቀው ድርጅት መጠሪያውን “የብልጽግና ፓርቲ” በሚል ለመቀየር መወሰኑን ጠቁመው፤ “ብልጽግና በቁስ ብቻ ሳይሆን፣ በክብርም በነጻነትም ማረጋገጥ የሚችል ፓርቲ” እንደሆነ ከወዲሁ አመላክተዋል።

የፌደራል ሥርዓቱ እስካሁን የነበረበትን ስህተቶች ለማረም በሚያስችል መልኩ የሚደራጅ እንዲሆን መስማማታቸውን በመግለጽም፤ ከአማርኛ በተጨማሪ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና አፋርኛ የፌደራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑመወሰኑንም አብስረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ፓርቲያቸው የፌደራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ጠንክሮ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

ሂደቱ ኢትዮጵያውያን አንዳቸው ከአንዳቸው ተምረው፣ በጋራ የጋራ አገራቸውን ለመገንባት ያላቸውን ፍላጎት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እርምጃው “እስካሁን ከነበረው በእጅጉ የላቀ እድገት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል” ሲሉም አቋማቸውን በግልፅ አስቀምጠዋል። እያንዳንዱ ሕዝብ በልኩ የሚሳተፍበትና ሌላውን የሚያከብርበት የዲሞክራሲ አውድ ለመፍጠር መግባባት ላይ መደረሱን በተጨማሪነት አብስረዋል።

ሀገሩቱን በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ወደ ብልጽግና ለማሻገር የነበረውን ትልም ለማሳካት በእጅጉ የሚረዳን ነው በማለትም የአዲሱን ፓርቲ መፂኢ ተስፋና ዕቅድ አስመልክተው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ግንባሩን በማዋሃድ ወጥ ፓርቲ ለመመስረት በቀረበለት የውህደት ዝርዝር ጥናት ላይ ተወያይቶ በስድስት ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ ከስምምነት ላይ መድረሱ አይዘነጋም።

ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ አደረጃጀትና በጀት የስራ እንቅፋት እንደሆኑባቸው ገለፁ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ህዝቡ የሚጠብቀውን የሰብኣዊ መብት  አያያዝ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችለው የለውጥ ሥራዎች እያካሄደመሆኑን ዋና ኮሚሽነሩ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር የተቋሙን የ2012 ዓ.ም ዕቅድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት ይህንን ከማለታቸው ባሻገር ፣ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ከ15 ዓመታት በላይ ቢሆንም ያለው አደረጃጀት ተልዕኮውን ማስፈፀም እንደማያስችለው በመግለፅ፤ ለዚህ መፍትሔው ተቋሙን መልሶ ማደራጀት መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ለዚህ የሚሆን ጥናት የሀገሪቷን ተጨባጭ ሁኔታ ባገናዘበ፣ የተለያዩ ሀገሮችን ተሞክሮ በቀመረ እና ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።

የለውጥ ሥራው የተቋሙን ማቋቋሚያ አዋጅ ገለልተኛነትና ነፃነት የሚፈትሽ፤ የሰው ሃይል አደረጃጀቱን ተልዕኮ ፈፃሚ የሚያደርግና ወጪ ቆጣቢ ድጋፍ ሰጪ እንዲኖር የሚያስችል፣ የጥቅማ ጥቅም አወሳሰኑ ብቃትና ልምድ ያላቸውን ሠራተኞች ለማቆየት የሚያግዝ፣ እንዲሁም ለሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ተጋላጭ በሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቅድሚያ እንዲሰጥ በሚያስችል መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኙም ከዋና ኮሚሽነሩ ሪፖርት መረዳት ተችሏል፡፡ የተለመዱ የመብት ጥሰቶችን የመመርመር፣ አቤቱታዎችን ተቀብሎ የማጣራትና የማማከር ሥራዎች በኮሚሽኑ በኩል እየተከናወኑ እንደሆነም ታውቋል።

ከሀገራዊ ለውጡ ጋር በተያያዘ በዜጎች ሰብአዊ መብቶች ላይ እየደረሱ ያሉ የመብት ጥሰቶችን ለመከላከል ኮሚሽኑ ዝግጁነት ምን እንደሚመስል የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ጥያቄ አቅርበዋል።

ዋና ኮሚሽነሩና የሥራ ባልደረቦቻቸው ኮሚሽኑ ይህን ለመስራት የሚያስችል ቁመና እንደሌለው በመግለፅ፤ ለዚህ እንደምክንያት ከቀረቡት መካከል አንዱ የበጀት አናሳነት እንደሆነ ጠቁመው፤ ከተመደበው 74.6 ሚሊዮን ብር መደበኛ በጀት 62 በመቶ ለደምወዝና ለቤት ኪራይ፣ ለመብት ጥሰት መከላከያ ስራዎች 9 በመቶ እና ለምርመራ ስራዎች 12 በመቶ መሆኑን እንደማሳያ አቅርበው፤ በዚህ ፈታኝ ሂደትና አሠራር ለብዙኃኑ ጥያቄዎች ተደራሽ መሆን አዳጋች እንደሆነ አብራርተዋል።

ሪፖርቱን ያደመጠው የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ተመስገን ባይሳ፤ የኮሚሽኑ ዕቅድ ገላጭ መነሻ ሁኔታዎችን እንዲይዝ፣ ቁልፍ ተግባራትን ከአፈፃፀም ሂደታቸው ጋር እንዲያካትት፣ ህዝቡ ከተቋሙ የሚጠብቀውን ፍላጎት እንዲያሳይ፣ የአሳታፊነትና የተደራሽነት ጉዳዮችን በሚገባ እንዲመለከቱበት ዕቅዱ ተከልሶ እንዲቀርብ ማሳሰቢያ የሰጡ ሲሆን፤ ቋሚ ኮሚቴው ኮሚሽኑ የጀመረውን የለውጥ ስራ በሙሉ ልብ እንደሚደግፍ ያላቸውን እምነት ለተቋሙ የስራ ሓላፊዎች አረጋግጠዋል::

በ4 ቢሊዮን ዶላር  የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር ለመዝርጋት የሚያስችለው ረቂቅ ለፓርላማ ቀረበ

ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ በኢትዮጵያና በጅቡቲ መንግሥታት መካከል የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ መስመር ለመዘርጋት የካቲት 2011 ዓ.ም የተደረገውን ስምምነት ለማፀደቅ ረቂቅ አዋጁ የቀረበለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ዙር ውይይት ካደረገ በኋላ ለዝርዝር ዕይታ ወደ ቋሚ ኮሚቴዎች መርቶታል::

ምክር ቤቱ ባካሄደው ስብሰባ የረቂቅ አዋጁን አስፈላጊነት በተመለከተ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስቴር  ዴኤታ መስፍን ቸርነት ለአባላቱ ዝርዝር ማብራሪያ አቅርበዋል:: ከ1970 ዎቹ (እኤአ) ጀምሮ የተፈጥሮ ጋዝ መገኘቱ ቢገርም እስካሁን ድረስ ጥቅም ላይ አለመዋሉን ሚኒስትሩ ተናግረዋል::

ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያና በጅቡቲ የማዕድንና ነዳጅ ባለሥልጣናት ተፈርሞ ለምክር ቤቱ የቀረበው ስምምነት ፀድቆ ተግባራዊ ቢደረግ የተፈጥሮ ጋዙን ወደ ውጪ በመላክ መሸጥ ይቻላል ተብሎ ታምኖበታል:: ይህን ዕቅድ እውን እንዲሆን ይረዳል የተባለውና በድሬደዋ ለመገንባት ለታሰበው የማዳበሪያ ፋብሪካ የተፈጥሮ ጋዝ ግብዓት ማቅረብ እንደሚቻል እንዲሁም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም በማብራሪያቸው ጠቁመዋል::

በአገሪቱ ስድስት የነዳጅ አለኝታ አካባቢዎች ተለይተው ፍለጋ እየተካሄደባቸው መሆኑን፣ ከእነዚህ መካከል በኦጋዴን አካባቢ ወደ አሥር ትሪሊዮን ኪዮብ ጫማ የተፈጥሮ ጋዝና መጠኑ ገና በመለየት ላይ ያለ ፈሳሽ ነዳጅ መገኘቱን ተከትሎ ወደ ልማት ለማስገባት የተለያዮ እንቅስቃሴዎች በመደረግ ላይ ናቸው ተብሏል::

ምክር ቤቱ በዝርዝር የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ ካዳመጠ በኋላ ምንም ዓይነት ጥያቄዎችን ሳያነሳ ለዝርዝር ዕይታ ለተፈጥሮ ሀብት ፣ መስኖና ኢነርጂ ፣ለውጭ ግንኙነትና ለሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች እንዲመራ በሙሉ ድምፅ ወስኗል::

የታከለ ኡማ አስተዳደር የባለሀብቶች ፎረም ሊያቋቁም መሆኑ ታወቀ

ከመሬት ባለቤትነት ከመሠረተ ልማትና ከፋይናንስ ጋር የተቆራኙ ጥያቄዎች ሲነሱ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል  የባለሀብቶች ፎረም የማቋቋሚያ መመሪያን በታከለ ኡማ የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር አፅድቋል::

ባለሀብቶችን ውጤታማ ተግባር እንዲያከናውኑ ይረዳል የተባለው ፎረም የሚነሱ ጥያቄዎችን በተናጠል ከመመለስ በተደራጀ መንገድ ለማስተናገድ እና ፍላጎታቸውን በማሟላት አሠራሩን የተሻለ ለማድረግ ሰፊ ድርሻ እንደሚኖረው ተገልጿል::

የመስተዳደሩ ካቢኔ የፎረሙን ማቋቋሚያ መመሪያ ኅዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም ማፅደቁን አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሰጡት የአስተዳደሩ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የፕሮጀክት ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ብሩክ እስከዚያ በኮሚሽኑ አቅም ብቻ ከመንቀሳቀስ የባለሀብቶች መደራጀት ጠቃሚ እንደሆነ ተናግረዋል::

ሕገ ወጥ ኢንቨስትመንትን በማስቀረት ወደ ሕጋዊ መንገድ ለማምጣት ፎረሚ አጋዥ እንደሆነ ከወዲሁ እየተነገረለት  ነው::

LEAVE A REPLY