የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 19 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 19 ቀን 2011 ዓ.ም

ኦቦ ለማ መገርሳ የመደመርንም ሆነ ውህደቱን አላምንበትም ማለት እያወዛገበ ነው 

የለውጡ ቡድን መሪ፣ የኢፌዲሪ መከላከያ ሚኒስትርና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ፤ የኢሕአዴግን ውህደት እንደማያምኑበት መናገራቸው እያወዛገበ ነው።

ወሳኙ ሰው “መዋሀዱ ትክክል አይደለም። ከሆነም በችኮላ መሆን የለበትም፤ ወቅቱም አይደለም” ሲሉ ኢሕአዴግ ወደ ውህደትና የብልፅግና ፓርቲነት የሚያደርገውን ጉዞ አስመልክቶ ከቪኦኤ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል:: አቶ ለማ፤ በመደመር ፍልስፍናም እንደማይስማሙ ከራድዮ ጣቢያው ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ በግልፅ አስቀምጠዋል።

የኢሕአዴግ ምክር ቤት የፓርቲዎችን ውህደት ባፀደቀ ጊዜ የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ተገኝተው እንደነበር ያልካዱት የቲም ለማ፤ በዕለቱ ውህደቱን አስመልክቶ ግልፅ ባለ መልኩ እጃቸውን ሲያወጡ ያልታዮትና በተለያዮ ማህበራዊ ሚዲያዎች በተለቀቁ ፎቶዎች ላይ እጃቸውን በማውጣትና ባለማውጣት ሃሳብ ውስጥ ሲዋልሉ የተስተዋሉት ኦቦ ለማ ስለ ሂደቱ ለቪኦኤ ዝርዝር ማብራሪያ መስጠትን አልፈለጉም።

በአጠቃላይ ከመጀመሪያ ጀምሮ እስከ መጨረሻ ድረስ የፓርቲዎች ውህደትን በተመለከተ የተለየ ሀሳብ እንዳላቸው እና ይህንንም ለሥራ አስፈጻሚውና ለሁሉም መናገራቸውንም በመጥቀስ ውህደቱን ያልተቀበሉ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ ታየ ደንደኣ ስለ ብልፅግና ፓርቲ አመሠራረት ሂደት፣ ፋይዳዎቹና የአቶ ለማ በውህደቱ አላምንም ማለትን አስመልክተው ከኤስቢኤስ አማርኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ማድረጋቸውን በፌስቡክ ገፁ ላይ አስነብበዋል።

“አቶ ለማ በኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ውህደቱ አስፈላጊ እንደሆነና የመደመር ዕሳቤ ከኢትዮጵያ ዐልፎ ለምሥራቅ አፍሪካም ጠቃሚ ሃሳብ እንደሆነ ተስማምተው ነው ያጸደቁት፤ የልዩነት ሃሳብ አልሰማንም። ከዚያም አልፎ በኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴና ጉባኤ፣ በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎች ላይ ሁሉ የተለየ አቋም አላንጸባረቁም። በዚህ መሄድ አለብን የሚል የተለየ አማራጭ ሃሳብም አላቀረቡም” ሲሉም ታዬ ደንደአ ተከራክረዋል።

የኦቦ ለማ አቋም በይፋ ከተገለፀበት ከትላንትና ጀምሮ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተለዬ አቅጣጫ ይይዛል የሚል ምልከታ በተለያዩ ወገኖች ዘንድ እየተሰማ ሲሆን የፖለቲካው ሂደት ላይ ምንም አይነት ተፅዕኖ ሳያሳድር ያልፋል የሚል አስተያየት የሚሰጡ ወገኖችም ዶክተር አብይ ቀድመው አቶ ለማንና አቶ ገዱን ወደ ፌዴራል አምጥተው ድምጻቸውን ከህዝብ በማራቃቸው የአቶ ለማ መነጠል በፖለቲካው ጉዞ ላይ እምብዛም ጉዳት አይደርስም ሲሉ ይከራከራሉ።

የዐቢይና የለማ ልዩነት የኦሮሞን ሕዝብና ፓርቲውን አደጋ ላይ ጥሏል ተባለ 

አቶ ለማ መገርሳ የኢሕአዴግን ውህደት አለመቀበላቸውና የመደመር ፍልስፍናን የማያምኑበት መሆናቸውን ተከትሎ የተለያዮ የፖለቲካ ሰዎች ስጋታቸውንና አስተያየታቸውን በመግለፅ ላይ ናቸው:: በዋሺንግተን ናሊ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር የሆኑት ዶኬተር ሔኖክ ገቢሳ “አሁን እየሆነ ያለውን ውህደት ብለን የምንናገር ከሆነ ለዚች አገር ከፍተኛ ውለታ የዋሉት እንደ አቶ ለማ መገርሳ ያሉትን ሰዎች እየቀነስን ውህደቱን እውን ማድረግ አስቸጋሪ ነው ” ይላሉ።

በአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰዎችን፣ ሀሳባቸውንና እምነታቸውን ሳያካትቱ ውህደቱን ማካሄድ ከባድ ነው ሲሉም የጠቅላይ ሚኒስትሩንና የደጋፊ አባሎቻቸውን አካሄድ ይተቻሉ።

በሌላ በኩል የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር የሆኑት ፕሮፌሰር መረራ፣ ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት ‘ለዐቢይ ትልቁ ተግዳሮት የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝቦችን መርቶ ማሻገር ሳይሆን ኢሕአዴግን እንደ ኢሕአዴግ መርቶ መሻገር መቻልና አለመቻል ላይ ይመሰረታል’ ማለታቸውን በማስታወስ፣ በአሁኑ ሰዓትም በግንባሩ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች መጠላለፍ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ትልቁ ተግዳሮት ሆኖበታል ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል። “ከዚህም የተነሳ እንደሚፈለገው አብሮ ወደፊት መሄድ አልቻሉም” በማለት የእርሳቸው ፓርቲ ኢሕአዴግ ተዋሀደም አልተዋሀደም የሚጠብቅበት ነገር እንዳለ አጽንኦት በተሞላበት ሁኔታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በውህደቱ ላይ አቶ ለማ እንደማይስማሙ በተባራሪ ወሬ ሲሰሙ መቆየታቸውን የሚናገሩት ዶ/ር ሔኖክ በበኩላቸው፤ እንዲህ ዓይነት መከፋፈል በአሁኑ ሰዓት መፈጠር አልነበረበትም ብለው እንደሚያምኑም ይጠቁማሉ። “በእነርሱ መካከል በሚፈጠር አለመግባባት የኦሮሞ ትግል መከፋፈል የለበትም ብዬ ስለማምን ነው” ሲሉም ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

“አቶ ለማም ሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ትልቅ ውለታ የዋሉ ሰዎች ስለሆኑ ሃሳባቸውን ወደ አንድ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል፤ የኦሮሞን ሕዝብ ጥያቄ እንመልሳለን ብለው ካመኑ፤ የኦሮሞ ሕዝብ መሪዎች ነን ብለው ካሉ፤ መደማመጥ አስፈላጊ ነው” ሲሉ መነጋገር አስፈላጊ መሆኑን አስረግጠው ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ መሪዎች ዲሞክራሲን አንገነባለን ሲሉ ተቃራኒ ሀሳቦችንም ማስታገድ አለባቸው ብዬ አምናለሁ የሚሉት ዶ/ር ሔኖክ፤ አሁንም ያለመግባባት መንስዔ የሆነው የውህደት ውሳኔ እንደገና መታየት አለበት ብለው እንደሚያምኑ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ላይ አሳስበዋል።

አቶ ለማ ኦዲፒን ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር በማስታረቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን በማንሳት፤ የእርሳቸው አቋም የደጋፊዎቻቸውንም አቋም እንደሚለውጠው ያመላከቱት ዶክተር ሄኖክ ፤ ከዚህም በመነሳት የአቶ ለማ አስተያየት ወደኋላ ከተተወ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው እና “ለማ መገርሳን የቀነሰ መደመር፣ መደመር አይሆንም” በማለት አዲሱን የኢሕአዴግ ጉዞ አጣጥለዋል።

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ዶ/ር ዐቢይ ይህንን የሚቀበሉ አይመስሉም የሚሉት የሕግ ባለሙያው፤ የኦሮሞና ሌሎች የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ እንዲመለስ የሚፈልጉ ከሆነ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይና አቶ ለማ የግድ በትብብር መሥራት አለባቸው ብለዋል። “ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይና አቶ ለማ አንድ ባህል እና አንድ ቋንቋ ኖሯቸው፣ ለተመሳሳይ ሕዝብ እየታገሉ፣ በመግባባት አብሮ መሥራት ካቃታቸው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ አስቸጋሪ ነው ብዬ አምናለሁ” ሲሉም ተደምጠዋል።

ይህ ትግል እዚህ የደረሰው በኦሮሞ ልጆች ደምና በሕዝቦች መስዋዕትነት ነው ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፣ ፓርቲው ዋጋ የተከፈለባቸውን ጥያቄዎችን ወደ ጎን መተው አይገባውም ፤ ፖለቲካ በራሱ የሰጥቶ መቀበል ጥበብ ፣ በፖለቲካ አካሄድ ውስጥ መደማመጥና ሚዛን ለሚደፋ ተፎካካሪ ሀሳብ መሸነፍ ወሳኝ እንደሆነም ይገልፃሉ።

ውህደት የኦሮሞ ሕዝብን ጥያቄ የሚመልስ እስከሆነ ድረስ ምንም ችግር የለበትም የሚሉት ዶ/ር ሔኖክ፤ ይሁን እንጂ አዲሱ መዋቅር እንደ ሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ይሰጣል መባሉ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው በማስታወስጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በዚህ ጉዳይ ላይ መግባባትን ለማምጣት፣ ቆም ብለው ግልፅና ፍትሀዊ የሆነ ምክክር ከአቶ ለማ ጋር ቢያደርጉ የበለጠ ጠቀሜታ አለው ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና በመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መካከል በተከሰተው አለመግባባት፣ ስለወደፊቱ የሀገሪቱ ሁኔታ ፓርቲያቸው ስጋት እንዳለው የተጠየቁት ፕሮፌሰር መረራ፣ “እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም ሰፍኖ፣ ሕዝቦች በቀያቸው እኩል ባለቤትነት ኖሯቸው ትግላችንን ግብ እስኪመታ ድረስ መስጋታችን አይቀርም” ብለዋል።

የአገሪቱን ፖለቲካ በሚፈለገው ፍጥነት ወደፊት ለማስኬድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና በመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ መካከል ያለው መግባባት ወሳኝ ነው የሚሉት ዶ/ር ሔኖክ፤ ይህንንም መግባባት ለማምጣት ትልቁ ሚና የሚጠበቀው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑን ጠቁመው ፤በመካከላቸው መግባባት ባይፈጠር ግን የአገሪቱ ፖለቲካ ወዳልተፈለገ ጎዳና ሊሄድ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው አብራርተዋል።

“ምናልባትም አቶ ለማ ሥልጣን ወደ መልቀቅ እርምጃ ሊያመሩ ይችላሉ ፤ ይህ ሆነ ማለት ደግሞ የመከላከያ ሚኒስትሩ ወደ ተቃዋሚነት ተሸጋገሩ ማለት ነው” የሚሉት ዶክተር ሄኖክ ፤ከዚህም በተጨማሪ አቶ ለማ የተቃዋሚነትን አቋም የሚከተሉ ከሆነ በእርሳቸው አመራር የሚያምኑ አካላት ስላሉ ትልቅ የፖለቲካ ክፍፍል ይፈጥራል ሲሉ ከወዲሁ ቅድመ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከችግሮቻቸው በፍጥነት ሊላቀቁ ይገባል ተባለ

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች እየተንከባለለ የመጣባቸውን ችግሮች መፍታት እንዳለባቸው ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ።በህዘብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ በጀትና ፋይናስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመንግስት ልማት ድርጅቶችን የ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት የ1ኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ገምግሟል::

በሀገሪቱ ከሚገኙ የልማት ድርጅቶች መካከል ስምንቱ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን፣ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ ኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን፣ ልማት ባንክ፣ ብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ሎጅስቲክ አገልግሎት ድርጅት፣ ኮንስትራክሽ ሥራዎች ኮርፖሬሽና ንግድ ኮርፖሬሽን ሥራዎች በሩብ ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ግምገማ ተደርጎበታል።

ቋሚ ኮሚቴው ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ኤጀንሲና ከተጠሪ ተቋማት ተወጣጠው ከመጡ ሓላፊዎች ጋር ባካሄደው ግምገማው በቀረቡት ሪፖርቶች መሰረት አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ እንደሆነ አስታውቋል። በግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የማዳበሪያ ግብይትና ስርጭት የሚመራበት ወጥ የሆነ የአሰራር ስርዓት አለመኖሩ፣ ኮርፖሬሽኑ ለተሰብሳቢ ሂሳብ ክምችት፣ ለገንዘብ ምንጭ እጥረት፣ ለውጭ ምንዛሬ እጥረት ስለሚያጋልጥ ለችግሮች መፍትሄ በኮርፖሬሽኑ የአሰራር መመሪያ መዘጋጀቱ ቢታወቅም፤ መመሪያው በህጋዊ መንገድ መተግበር እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው በግምገማው ላይ አብራርቷል።

ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ከኮንትራት አመራር አኳያ በኮርፖሬሽኑ የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በተለይ የመስኖ መሰረተ ልማቶች እጅግ በጣም ከመጓተታቸው በተያዘው በጀት ዓመት በሩብ ዓመት የተመዘገበው አብዛኛው አፈጻጸም ዝቅተኛ ነው ያለው ቋሚ ኮሚቴው ፤ በተለይ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ፕሮጀክት 31 ነጥብ 1 በመቶ፣ ኦሞ ኩራዝ መስኖ ግንባታ 14 በመቶ እና የውሃ መሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክት 35 ነጥብ 6 በመቶ በመሆኑ እነዚህ ፕሮጀክች ሌላ ተጨማሪ ጊዜና የገንዘብ ወጭ ሳይጠይቁ በጥራትና በፍጥነት ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ልዩ ስልት መዘጋጀት ይኖርበታልም ሲል አስጠንቅቋል።

ከፕሮጀክት አስተዳደር ውጤታማነ ጋር በተያያዘ በስኳር ኮርፖሬሽን ስር የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ኦሞ ቁጥር 1 እና 5፣በለስ 1 እና 2፣ወልቃይት እና ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካዎች የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና በጀት ሊጠናቀቁ ባለመቻላቸው በፍጥነት ተጠናቀው ወደ ሥራ መግባት አለባቸውም ተብሏል።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የመንግሥት ትርፍ ድርሻ ክፍያና የወጭ ሀገር ብድር አመላለስ ከእቅዱ በታች በጣም ዝቅተኛ አፈጻጸም ሆኖ ተመዝግቧል። ኤጀንሲው በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን ሓላፊነት መሰረት በስሩ ተጠሪ በሆኑ በሁሉም የልማት ድርጅቶች ክትትልና ቁጥጥር ማድረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ በዋናነት በፕሮጀክት አመራርም ሆነ በፋይናንስ አስተዳደር ፍተኛ ችግር ውስጥ የገቡ ድርጅቶችን ለይቶ በመደገፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጤት ማብቃት እንዳለበትም ተገልጿል::

ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ጉዳት ሊደርስ ይችላል ተባለ

በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ የተለያዮ ክልልሎች የደረሰው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በመኸር ምርት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የአማራና ኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮዎች አስታውቀዋል።

የኦሮሚያ ክልል ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ሓላፊ አቶ ዳባ ደበሌ በክልሉ በመኸር ወቅት 6 ሚሊየን ሄክታር የሚጠጋ መሬት በዘር መሸፈኑን ጠቁመው ፤ አሁን ላይም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በምርት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የምርት መሰብሰብ ተግባር በመከናወን ላይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

እስካሁን እየጣለ ባለው ዝናብ ጉዳት አልደረሰም የሚሉት ሓላፊው በቀጣይ ስጋቱን ለመቀነስ እንደየአካባቢዎቹ ሁኔታ የኅብረተሰቡን ተሳትፎ የማሳደግ እርምጃ ይወሰዳል ቢሉም ዝናቡ በዚሁ ከቀጠለ በሰብል ላይ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልፀዋል። በክልሉ ከዚህ ቀደም ተከስቶ የነበረውን የአንበጣ መንጋ መቆጣጠር መቻሉን በማያያዝ ያመላከቱት አመራር የመንጋው ስጋት አሁንም ድረስ መኖሩን እና በዘላቂነት የመከላከሉ ሥራም መቀጠሉን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ አለባቸው አሊጋዝ በክልሉ አንዳንድ ስፍራዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ጉዳት ማድረሱን አረጋግጠዋል። በቀጣይም ዝናቡ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ምርትን በፍጥነት የመሰብሰቡ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ሌላኛው ለምርት ስጋት ሆኖ የቆየውን የአንበጣ መንጋ ለመቆጣጠርም በተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ውጤት ታይቷልም ያሉት የግብርና ቢሮ ሓላፊ ሆኖም አሁንም ድረስ ስጋቱ በመኖሩ የክትትልና ቅድመ መከላከል ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በትግራይ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ቦርድ ተቋቋመ

የትግራይ ክልል ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ቦርድ ማቋቋሙን ገለፀ። ክልላዊ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ቦርዱ በትናንትናው እለት ነው የተቋቋመው።

በትግራይ ሁሉን አቀፍ የልማት ሥራዎች ለማከናወን የተማረ የሰው ሀይል ወሳኝ በመሆኑ ቦርዱ ከታህሳስ 1 2012 ዓ.ም ጀምሮ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርትን በተቀናጀ መርሃ ግብር እንደሚሰጥ ነው የተነገረው። የቦርዱ ሊቀመንበር እና በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የትግራይ ክልል ከተማ ልማት፣ ቦርዱ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሓላፊ ዶክተር አብረሃም ተኸስተ፥ ቦርዱ የከተማ ልማት፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ፣ የትምህርት ቢሮ እና የጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊዎችን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ የመንግስት የሥራ ሓላፊዎችን በአባልነት ያቀፈ እንደሆነም አስታውቀዋል።

ያልተማረ አምራች ዜጋ በሚገባ መልኩ ማንበብ እና መጻፍ ከቻለ በገጠሩ የሚከናወኑ የእርሻ ስራዎች እንዲሁም በከተማ የተለያዩ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ዘርፎች በመሰማራት ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ ያለመ መሆኑንም በማያያዝ ጠቁመዋል። በመሆኑም በወረዳ እና ቀበሌዎች አዲስ የተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት የአመራር ቦርድ እንደሚቋቋም የገለጹት ዶክተር አብረሃም፥ በየደረጃው ያለው አመራር በመርሃ ግብሩ መሰረት ስልጠና ይሰጠዋል ሲሉ ተናግረዋል።

LEAVE A REPLY