በመንጋዎች የምትናጠው ድሬደዋን ወደ ቀደመ ሰላሟ መመለስ ከባድ ሆኗል
ተደጋጋሚ ኹከት የነገሰባት የድሬዳዋ ከተማን የቀደመ ሠላም ለመመለስ ሁሉም አካላት ርብርብ በማድረግ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ተባለ። በድሬዳዋ ሰላምና ፀጥታ ዙሪያ ያተኮረ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ዛሬ በከተማዋ ተጀምሯል።
የድሬዳዋ አስተዳደር የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ሓላፊ ወይዘሮ ከሪማ አሊ፥ ድሬዳዋ ከዚህ በፊት የምትታወቅበት የሰላምና አብሮ የመኖር እሴት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ተማጽነው ፤ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህግ ኮሌጅ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር እንዳወቅ ፀጋ፥ ሠላም የሁሉም ነገር መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።
አሁን ለሚታየው የድሬዳዋ የሰላም መደፍረስ የሥራ አጥነት መስፋፋት፣ የፖለቲካ የስልጣን ሽኩቻ፣ መደበኛ ያልሆኑ አደረጃጀቶች መበራከትና የወጣቱ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ምክንያት መሆኑን ከማንሳት ባሻገር፤ የከተማዋን የቀደመ ሠላም ለመመለስ የቋንቋና የባህል ልዩነትን በማክበር፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር በማድረግ ጽንፈኛና ዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦችን ማስወገድ እንደሚገባም መክረዋል።
የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ረዳት ኢንስፔክተር ባንታለም ግርማ፥ ፖሊስ የአካባቢ ፀጥታን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን የድሬዳዋ የቀደመ ሰላም እንዲመለስ የማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አደጃጀቶችን በማጠናከር ድርሻውን ይወጣል ካሉ በኋላ፤ ኅብረተሰቡም ትናንሽ ግጭቶች እንዳይስፋፉ ማድረግና ቤተሰቦችም ልጆቻቸውን መምከር እንደሚኖርባቸውም ተናግረዋል።
ተሳታፊዎችም የዜጎች ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ በአግባቡ አለመመለሱ፣ የወጣቶች የስብዕና ማዕከላት በአግባቡ አለመስፋፋት እንዲሁም የፖለቲካ አደረጃጀቱና የስልጣን ሽኩቻ ለሰላም እጦት ምክንያት መሆኑን በውይይቱ ላይ ከመግለጻቸው በተጨማሪ ፤ የአስተዳደሩ አመራሮችም ከህዝቡ ጋር በመነጋገር የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት የድሬዳዋ የቀደመ ሰላም እንዲመለስ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
በተለይም የለውጡ ቡድን ሥልጣኑን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ ስርዓት አልበኝነት እና የተደራጁ የታጠቁ ኃይሎች በስፋት የሚንቀሳቀሱባት ድሬደዋ ከተማ ላይ የሃገራዊ ስሜትን የሚያደፈርሱ እንቅስቃሴዎች በተደጋጋሚ ሲፈጸሙ የከተማ አስተዳደሩም ሆነ ፌደራል መንግሥቱ ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰዳቸውን ለኢትዮጵያ ነገ ዘጋቢ የገለፁ የከተማዋ ነዋሪዎች በተለይም የኦነግን እና የጃዋር መሐመድን ፖለቲካ የሚደግፉ የመንጋ ቡድን አባላት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጽንፈኛ ብሔርተኝነትን እና ሃይማኖታዊ ግጭቶችን በመቀስቀስ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል:: የመንጋ ቡድን በከፍተኛ ሁኔታ እየናጣት የምትገኘው ድሬደዋ በአሁኑ ሰዐት መረጋጋት ቢታይባትም ወደ ቀድሞ አስተማማኝ የረጋ ሰላሟ መመለሷ አሁንም ርግጠኛ መሆን አልተቻለም::
የኦዴፓና የዞን አመራሮች በአዳማው የብልጽግና ውይይት ለሁለት ተከፈሉ
የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የክልል አመራሮች በብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራም እና መተዳደሪያ ህገ ደንብ ዙሪያ በመምከር ላይ ናቸው።በአዳማ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ ውይይት በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የኦዲፒ የዞን አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።
በመድረኩ በውህድ ፓርቲው ፕሮግራም፣ በመተዳደሪያ ህገ ደንብና የድርጅቱ አወቃቀር ዙሪያ ውይይት እየተደረገ ይገኛል። በፓርቲው ዙሪያ በሚነሱ የተለያዩ የግልጸኝነት ጥያቄዎች ዙሪያ ውይይት ተደርጎ በከፍተኛ ሁኔታ ያለመግባባቶች መከሰታቸውን የኢትዮጵያ ነገ ምንጮች ይናገራሉ::
ዶ/ር ዐቢይ እና ለማ መገርሳ በሌሉበት እየተካሄደ የሚገኘው የኦዴፓ ከፍተኛ አመራሮችና የዞን ሓላፊዎች የብልፅግና ፓርቲ ምስረታና የኢህአዴግ ውህደት ከጅምሩ ሁለት ሊጋጩና ሊጣጣሙ የማይችሉ አቋሞችን ይዘው በመጡ ተሰብሳቢውች በመደረግ ላይ መሆኑን በአዳማ የሚገኙ ተሰብሳቢዎችን ዋቢ ያደረጉ ምንጮቻችን ያስረዳሉ::
በተለይም የለማ መገርሳ ማፈንገጥና የነሽመልስ አብዲሳ ጽንፈኝነትን የሚደግፉ እንዲሁም የጃዋርን ሃገር የማፈራረስ መንገድ የሚከተሉ ከባሌ እና አሩሲ አካባቢ የመጡ የዞን አመራሮች እና የኦዴፓ አባላት ውህደቱን ከመተቸት ባሻገር የኦሮሞ ሕዝብን መብት ትግል የደፈጠጠ ነው በሚል በሁለተኛው ረድፍ ከተቀመጠው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቡድን ጋር ከረፋዱ ጀምሮ ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል ነው የተባለው::
የወሰንና ማንነት ኮሚሽን ከአማራ ክልል ባለሥልጣናት ጋር እየተወያየ ነው
የኢፌዴሪ የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ኮሚሽን አባላት ከአማራ ክልል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎች ጋር እየተወያዩ ናቸው።
በውይይቱ ላይ የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ኮሚሽን አባላት፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህና እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎች መገኘታቸው ታውቋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፥ የክልሉ መንግስት ለኮሚሽኑ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠው ፤ ኮሚሽኑ ሥራውን በከፍተኛ ጥንቃቄ እና በተቻለ ፍጥነት እንዲያካሂድም አሳስበዋል።
የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ጣሰው ገብሬ በበኩላቸው ፤ በኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም የተከናወኑ ተግባራትን ለተወያዮቹ ያብራሩ ሲሆን፤ ከዚህ በፊት ከሐረሪ ክልል መንግሥት ጋር መሠል ውይይት ማካሄዳቸውን አስታውሰው በቀጣይም ከሁሉም ክልሎች ጋር ውይይ ይደረጋል ብለዋል።
በአማራ ክልል በተለይ የቅማንትና የራያ ሕዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ በማንሳት ለ28 ዓመታት የዘለቀ ጥያቄ እንደነበር ይታወሳል። በርካቶች አሁን ላለው የለውጥ ሂደት ምጣት ይህ የወሰንና የማንነት ጥያቄ ወሳኝ ሚና እንደተጫወተ ይስማማሉ።
የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የ170 ሚሊዮን ዮሮ ድጋፍ አደረገ
የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የ170 ሚሊየን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ታወቀ። የድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ እና በዓለም አቀፍ ትብብር የአውሮፓውያን ኮሚሽነር ዩታ ኧርፒላይነን ተፈራርመውታል።
ህብረቱ ለኢትዮጵያ ጤና፣ ምርጫ ቦርድ ማጠናከሪያ፣ የሥራ እድል ፈጠራ እና ኢንቨስትመንት የሚውል የ170 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ማድረጉ ነው የተነገረው።
ከተለገሰው ገንዘብ ውስጥ 50 ሚሊየን ዩሮ ለጤና የሚውል ሲሆን ፤ 10 ሚሊየን ዩሮው ደግሞ ለሥራ እድል ፈጠራና ኢንቨስትመንት እንዲሁም 10 ሚሊየን ዩሮ ለምርጫ ቦርድ ማጠናከሪያ ይውላል። በተጨማሪም 100 ሚሊየን ዩሮው በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ህብረት ማዕቀፍ ስምምነት መሰረት ሃገር በቀል ማሻሻያውን በቀጥታ ለማገዝ እንደሚዌል ነው የተነገረው። ድጋፉ የቀጠናውን መሰረተ ልማት ትስስር ለማሳደግ ይውላል።
የደፈሯት ሰዎች ላይ ለመመስከር ወደ ፍርድ ቤት ስትሄድ የነበረችው ሴት በእሳት ተቃጥላ ሞተች
አስገድደው በደፈሯትና ክስ በመሠረትችባቸው በ ግለሰቦች ላይ ምስክርነት ለመስጠት ወደ ፍርድ ቤት እየሄደች የነበረችው ሴት በእሳት ተቃጥላ ሕይወቷ እንዲያልፍ መደረጉ ተሰማ። የ23 ዓመቷ ሕንዳዊት፤ ወደ ፍርድ ቤት እየሄደች ሳለ በእሳት መቃጠሏ ዓለምን እያነጋገረ ይገኛል።
በሰሜናዊቷ ኡናዎ የተባለች ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ወንዶችን በአስገድዶ መድፈር የከሰሰችው ሕንዳዊት፤ የእሳት ቃጠሎ ከደረሰባት በኋላ በደልሂ ሆስፒታል ህክምና እየተከታተለች ነበር። ፖሊስ ተከሳሾቹን ጨምሮ አምስት ወንዶች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል።
የሟቿ እህት፤ ቤተሰባቸው ክሱን እንደሚገፋበት እና ተጠርጣሪዎቹ በሞት እንዲቀጡ እንደምትፈልግም ገልጻለች። ከሰባት ዓመት በፊት፤ በሕንዷ መዲና ደልሂ፤ አንዲት ወጣት አውቶብስ ውስጥ በቡድን ተደፍራ ከተገደለች ወዲህ በአገሪቱ ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት የበርካቶች መነጋገሪያ ቢሆንም፤ የተጠቂዎችን ቁጥር መቀነስ ካለመቻሉ ባሻገር ድርጊቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2017 ብቻ 33,658 ሴቶች መደፈራቸውን የሕንድ መንግሥት አረጋግጧል:: በዚህ አሀዝ መሰረት በቀን በአማካይ 92 ሴቶች ይደፈራሉ ነው የተባለው። ከዚህ ቀደም፤ የሕንድ ገዢ ፓርቲ አባልን በአስገድዶ መድፈር የከሰሰች ሴት በመኪና አደጋ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባት መግለጿን ተከትል ሁለት አክስቶቿ የተገደሉ ሲሆን፤ ጠበቃዋም ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ባለፈው ሳምንት በደቡባዊ ሕንድ በምትገኘው ሀይደርባድ ግዛት፤ አንዲት የእንስሳት ሀኪምን ደፍሮ በመግደል የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች በፖሊስ ቢገደሉምየተጠርጣሪዎቹ መገደል በአካባቢው ከፍተኛ ቁጣ መቀስቀሱን ተከትሎ የአገሪቱ ሴቶች በህግ ሊተማመኑ ባለመቻላቸው ከፍተኛ ስጋት ላይ ወድቀዋል::