ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ሁለት በዓላት እየተከበሩ ነው። አንዱ በአገዛዝ ሥርዓቱ እድሜ ልክ በየዓመቱ በእየስቴዲዮሙ እና በየአዳራሹ ከክልክል እንደ ጽዋ ማህበር እየተሽከረከረ፣ ዳጎስ ያለ የመንግስት በጀት ተበጅቶለት፣ በአልባሳት አጊጦ፣ በዳንኪራ እና በሙዚቃ ታጅቦ፣ በመገናኛ ብዙሃን የሙሉ ቀን አይር ሽፋን ተሰጥቶት፣ በከፍተኛ የመንግስት አመራር የሚመራው የብሔረሰቦች ቀን ነው። ሁለተኛው ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በአገራችን የሚገኙ የሲቪክ እና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች፤ እንዲሁም ከመንግስት ወገን በዶ/ር ዳንኤል በቀለ የሚመራው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የተሳተፈበት የሰብአዊ መብቶች ቀን ነው (እኔ የሰዎች ቀን ያልኩት)።
አዎ ሰውነታችንን የምናከብርበት ቀን ይናፍቀኝ ነበር። አዎ በብሔሮች ዳንኪራ ተሸፍኖ የነበርው ሰውነታችን ክብር ጎልቶ የሚታይበት እና ትኩረት የሚያገኝበት ቀን ይናፍቀኝ ነበር። ብሔሮችን ለማግነን እና እነሱን ሉአላዊ ለማድረግ ሲባል ሰውነትን ማዋረድ የግድ መስሎ የታያቸው እኩይ አክራሪ ብሔረተኞች ሰውነት እንዲረክስ፣ እንዲዋረድ እና እንደ አልባሌ ነገር እንዲታይ ለሃያ ሰባት አመት ያልሰሩት ሥራ የለም። ሰውነታችን በደም ቆጠራና በዘር ተመንዞር የብሔረሰቦች ማሻቀጫ ተደርጎ ቆይቷል። ብሔረሰቦችን ለማግነን ሰውነታችን በቤሳ ተሽጦ እና በጎሳ ተመንዝሮ ሰዋዊ ክብራችንን ተነፍገን ቆይተናል።
ጥቂቶች ሰውነቴን አልጥልም፣ የሰውነት ክብሬን አፈር አላስነካm፣ በጎሳም አልመነዘርም፣ በቤሳም አልሸጥም፣ የብሔረሰቦች ጫማም አልሆንም፣ የሰውነቴን ክብር ግራ ለገባቸው መንጋ ካድሬዎች አሳልፌም አልሰጥም ያሉ ‘እኔ ሰው ነኝ’ እያሉ ሰው ሆነው ሆነው ኖረዋል፣ ሰው ሆነው ሞተዋል፣ ሰው ሆነው አልፈዋል፣ ሰው ሆነው እስር እና እንግልት ሳይፈትናቸው ባሳሪዎቻቸው ፊት የተዋረዱ ቢመስሉም በክብር ኖረዋል። አዎ ሰው መሆን የተፈተነበት ክፉ ሃያ ሰባት አመታትን አሳልፈናል። ሰው መሆን እራስን ችሎ መቆምን ይጠይቃል። ሰው መሆን እራስን ችሎ ማሰብን ይጠይቃል፣ ሰው መሆን ከመንጋዎች ይነጥላል፣ ሰው መሆን የህሊና ተገዢ ያደርጋል፣ ሰው መሆን ለሰው ልጆች ሁሉ የማሰብ ዘጋን ያጎናጽፋል። ከሰውነትህ ስትላቀቅ የምትሸሸግበት ጥግ ትፈልጋለህ። ከሰውነትህ ስትርቅ በመንጋ እሳቤ ውስጥ እራስህን ታገኘዋለህ። የሰውነት ጸጋ ከላይህ ላይ ሲገፈፍ ስም የተሰጠለት ሰልፍ ውስጥ እራስህን ታገኘዋለህ። ያኔ እንዳንተ ሌላኛው ሰልፍ ውስጥ ያለው ሰው ወይም ብቻውን በሰውነቱ የቆመው ሰው አይመስልህም።
ባለፉት አሥርት አመታት ውስጥ ሰው ነኝ ብሎ በአደባባይ ከነሙሉ ክብር መቆም፣ ሰው ነኝ ብሎ ለሰው ልጆች መብት መቆም፣ ሰው ነኝ ብሎ እንደ ሰው ማሰብ ያስገድል፣ ያሳስር፣ ያስገርፍና ከሃግር ያስባርር ነበር። ብሔረሰቦችን እንደ ጭንብል ያጠለአቁ ብሔረተኞች ሰው ሆኖ ብቻውን የሚቆምን ሰው እንደ አንድ ባታሊዮን ጦር ይፈሩ ነበር። የኢትዮጵያን ሕዝብ ከሰውነት ተራ ለማውጣት ያልተሰራ ሥራ፣ ያልተቆፈረ ጉድጓድ፣ ያልባከነ የአገር ሃብት፣ ያልተሰራ ወንጀል የለም። የኢትዮጵያን እስር ቤቶች ሞልተው ሲማቅቁ ከነበሩ፣ በማዕከላዊ እና በሌሎች የማሰቃያ ሥፍራዎች የግፍ እንቆቆ ሲጋቱ ከነበሩ፣ በስደት ሲንከራተቱ ከነበሩ ብዙ ሺዎች መካከል አብዛኛዎቹ ሰውነትን ለማጥፋት በተከፈተው ዘመቻ አንበረከክም ያሉ ሰዎች ነበሩ።
ለሃያ ሰባት አመት በብሔረሰቦች ጫማ ስር ተጨፍልቆ እንዲቆይ የተደረገው ሰውነታችን ኮስሶና መንምኖ ቢታይም ዛሬም ኢትዮጵያ በሰውነታቸው ሳይሸማቀቁ አንገታቸውን ቀና አድርገው ‘እኔ ሰው ነኝ፤ አልመነዘርም በጎሳ፤ አልሸጥም በቤሳ’ የሚሉ ብዙ ልጆች አሏት። ሰውነት እንዲዋረድ እና እንዲላሽቅ ያደረገው ክፉ ሥርዓት የዘራውን ፍሬ ዛሬ እያስቃመን ቢሆንም ሰውነታችንን ግን ሊያስጥለን አልቻለም። ሰዎች በዘር እና በጎሳ ጥላቻ ታውረው ሌላውን የሰው ዘር፤ ሊያውም የገዛ ወገናቸውን፣ ሊያውም እንቅብ የሚዋዋሳቸውን የገዛ ጎረቤታቸውን፣ ሊያውም አብሯቸው አፈር እየፈጨ ያደገ የገዛ ጓደኛቸውን፣ ሊያውም በአንድ የትምህርት ገበታ ቁጭ ብሎ አብሯቸው የሚማር ወገናቸውን፣ የአገራቸውን ልጅ አንተ ምንትሴ እያሉ የጎሳ እና የኃይማኖት ስም እየለጠፉ ሲገሉ፣ አካል ሲቆራርጡ፣ ከፎቅ ሲወረውሩ፣ ከነ ነፍሱ ሲያቃጥሉ እያየን ነው።
እነዚህ በዘር እና በጎሳ ጭፍን ጥላቻ የታወሩና ከሰው ተራ የወጡ ሰዎች የሚገድሉት ሰው ለእነሱ ሰው መስሎ እንደማይታያቸው አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ። እነሱ አንድ ሰው ሲገድሉ የሚታያቸው ያ በአዕምሯቸው ውስጥ አውሬ ተደርጎ እንዲቀረጽ የተደረገውን ኃይማኖት ወይም ብሔር እንጂ ሰው አይደለም። ጓደኛቸውን፣ ጎረቤታቸውን፣ ወንድም እህታቸውን ሳይሆን እየገደሉ እንደሆነ የሚታያቸው በጭካኔ የሚገድሉት እና በድንጋይ የሚወቅሩት የጠሉትን ብሔርን ወይም ኃይማኖትን ነው። አንድ ሰው ሲገድሉ ለእኛ ሰው ነው የሚጎድልብን። ለእነሱ ደሞ የጠሉትን ብሄር ወይም ኃማኖት ነው የሚቀንሱት። ሰው እየገደሉ፣ ሰው እየደበደቡ እንደሆነ የሚያውቁ አይመስለኝም።
ዛሬ ሰውነት ገና ብዙ ፈተናዎች የሚጋፈጥ ቢሆንም ቀን እየወጣላት ይመስላል። ትላንት በብሔረሰቦች ቀን ስም ታፍኖ የነበረው የሰዎች ቀን ዛሬ ሰው ሆነው በቆዩት ጽኑዎች በየአዳራሹ እየተከበረ ነው። ነገ ልክ እንደ ብሄረሰቦች ቀን ከፍ ያለ የመንግስት በጀት ተበጅቶለት በየእስታዲዮሙ እና በአደባባዮች የሚከበርበት ቀን ይመጣል የሚል ተስፋ አለኝ።
ሰው ሆኖ ተፈጥሮ፣ እንደ ሰው ኖሮ፣ ሰው ሆኖ የማለፍን ታላቅ ጸጋ ያህል ምን መልካምና አስደሳች ነገር አለ? ሰው ሆነን ኖረን ሰው ሆነን እንሙት!
እንኳን ለሰዎች ቀን አደረሳችው!!!!