የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም

ዶክተር ዐቢይ የኖቤል ሽልማታቸውን በኦስሎ ተቀብለዋል፤ የቀረቡት ንግግሮች ትኩረት ስበዋል 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ  ከወራት በፊት ያሸነፉትን የኖቤል ሽልማት ዛሬ ኖርዌይ ኦስሎ ተገኝተው ተቀብለዋል። ዶክተር ዐቢይ ይህንን ሽልማት በብቸኝነት በማግኘት በታሪክ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊም አፍሪካዊም ሆነዋል::

የኖቤል የሰላም ኮሚቴ ሊቀመንበር ቤሪት ሬይሳ አንደርሰን በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባስመዘገቧቸው ሦስት ዋና ዋና ውጤቶች የ2019 የኖቤል ሰላም ተሸላሚ እንዲሆኑ መመረጣቸውን አስታውሰዋል።

በተለይ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለዓመታት የዘለቀውን ውዝግብ በሰላም ለመፍታት ባሳዩት ተነሳሽነት፣ በኢትዮጵያ በዲሞክራሲ ግንባታ ለተጫወቱት ሚና እንዲሁም በኢትዮጵያ፣ በምስራቅና በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ሰላምና እርቅ እንዲመጣ ያደረጉት አስተዋፅኦ  ዋነኞቹ የሽልማቱ መገኛዎች እንደሆኑም አስረድተዋል።

“እንደ ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነትዎ በአገር ውስጥ በርካታ ተግዳሮቶችን እየተጋፈጡ ነው፤ የክልል እና የብሔር ክፍፍል ዜጎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል። እነዚህ ሰዎች በራሳቸው ሃገር ቤት አልባ ሆነዋል። ሰዎቹ ወደ ቀያቸው መመለስ አለባቸው። የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ሥራ አጥነት፣ ትምህርት እና ጤና ላይም መሠራት ይኖርባቸዋል” ሲሉ ሊቀመንበሯ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ሽልማታቸውን ከተቀበሉ በኋላ፣ የኖሮዌይ ኖቤል ኮሚቴ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሰላም ለማስፈን የወሰዱትን እርምጃ ከግምት በማስገባት ሽልማቱን ስላበረከተላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ታሪካዊውን ሽልማትም በኢትዮጵያ ሕዝብና በፕሬዝዳንት ኢሳያስ ስም፣ በተለይም ሰላምን ለማምጣት የማይተካ ዋጋ በከፈሉ ግለሰቦች ስም እንደሚቀበሉ ነው ያስታወቁት። “ዛሬ ከፊት ለፊታችሁ ቆሜ ስለ ሰላም ለማውራት የቻልኩት በእድል ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኢትዮ-ኤርትራ ጦር ከፊት ተሰልፈው የጦርነትን አስከፊነት ማየታቸውን በምስጋና ንግግራቸው ላይ አስታውሰዋል።

በጦርነቱ ወቅት ባድመ  ላይ የሬዲዮ ኦፕሬተር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩበት ጦር፣ ለጥቂት ዞር ብለው ሲመለሱ በደረሰበት ጥቃት አባላቱ ሙሉ በሙሉ መሞታቸውን አመላክተው፤ ጦርነት ለክፉዎች፣ ለልበ ደንዳኖችና ለጨካኞች ነው ካሉ በኋላ በዛን ዕለት በጦርነት አውደ ግንባር ያጧቸውን ጓደኞቻቸውም ዛሬም ድረስ እንደሚያስታውሷቸው አስረድተዋል። 100 ሺህ ወታደሮችና ንጹኀን ሕይወታቸውን በዚህ ጦርነት ማጣታቸውን በመጠቆም በኢትዮጵያም በኤርትራም ወገን ያደረሰውን ቀውስ ለማሳየት ሞክረዋል።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ለሁለት አስርታት ያለ ሰላምም ያለጦርነትም በቆዮበት ዓመታት ቤተሰቦች ተቆራርጠው መቅረታቸውን የገለፁት ዶክተር ዐቢይ፤ ከ18 ወር በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር በሆኑበት ወቅት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሰላም ለማምጣት እንደሚችል ጠንካራ እምነት እንደነበራቸው፣ ፕሬዝዳንት ኢሳያስም ይህ እምነት እንደነበራቸው ለታዳሚዎች መስክረዋል።

ዛሬ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተለያዩ ቤተሰቦች ተገናኝተዋል፣ የአየርና የስልክ ግንኙነት እንዲሁም ዲፕሎማቲክ ግንኙነት ተጀምሯል በማለት ለሰላም ያላቸው ቁርጠኝነት ብርቱ እንደሆነ ገልፀዋል። የሰላም ያላቸው ግንዛቤ በመደመር እሳቤ ላይ የተመሠረተ እንደሆነም አስረድተዋል።

የዓለም ኃያላን ሀገራት በቀጠናው ወታደራዊ ኃይላቸውን ለማስፈር አሸባሪዎችና ጽንፈኛ ኃይሎች ደግሞ በቀጠናው ጠንካራ መሰረት ለመጣል እየጣሩ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቀጠናው የኃያላን ሀገራት ጦርነት ሜዳ እንዲሆን፣ የሽብር ነጋዴዎችና ደላሎችም መደበቂያ እንዲሆን እንደማይሹ አረጋግጠዋል።

በኖሮዌይና ስውዲን የሚኖሩ 200 ስደተኛ ኤርትራውያን የዶ/ር ዐቢይን ሽልማት ተቃወሙ

የዶክተር  ዐቢይ አህመድን የሰላም የኖቤል ሽልማት በመቃመወም ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ሰልፈኞች በኖርዌይ መዲና ኦስሎ መፈክራቸውን አንግበው  ታይተዋል።

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሽልማት ለሰጠው የኖቤል ኮሚቴ “የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰላም በሚገባ አልተረጋገጠም፤ የኖቤል ሽልማት ሊሰጣቸው አይገባም” የሚልተቃውሟቸውን በትናንትናው ዕለት እነዚህ በኖርዌይ የሚገኙ ኤርትራውያን አቅርበው እንደነበርም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ከተለያዩ የኖርዌይና የስዊድን ከተሞች የመጡ 250 የሚጠጉ ኤርትራውያን “በሰላም ስም ሳይታሰብበት ሽልማት ሊሰጥ አይገባም፤ በተግባር እንጂ የወሬ ሰላም አንቀበልም” የሚሉ የታቃውሞ ድምፆችን በማሰማት ወደ መንግሥታዊ ተቋማትም ተጉዘዋል።

የኤርትራ መንግሥትን በተመለከተ የተለያዩ ስር ነቀል ለውጦች ሊመጡ ይገባል በሚል የሚንቀሳቀሰው በኖርዌይና አካባቢው የሚገኝ የ ‘ይበቃል’ (ይአክል) ኮሚቴ ለሦስት የተለያዮ መንግሥታዊ ተቋማት ደብዳቤ እንደፃፈ የኮሚቴው ሊቀ መንበር ቲቲ ኃይለ አስታውቃለች።ለኖርዌይ መንግሥት በአካል፣ ለኖቤል ኮሚቴ በአድራሻቸው እንዲሁም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ደግሞ በኢሜይል ያላቸውን ተቃውሞ ማድረሳቸውንም ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ ላይ ገልጻለች።

“ይበቃል” የተሰኘው የኤርትራዊያኑ የእንቅስቃሴ ኮሚቴ ጸሐፊ ይብራህ ዘውደ፤ ምንም እንኳ ኤርትራና ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ቢፈራረሙም “መሬት ላይ ያለውን እውነታ ስናይ ወደ ተግባር የተሸጋገረ ነገር እንደሌለ” የለም ብሎ ያምናል። የኤርትራ ሕዝብ የጠበቀውና የተመኘው ለውጥ እንዳልመጣ በመጠቆም፤ በሁለቱም አገራት የሰላም ስምምነት አማካኝነት የተሰጠው የኖቤል ሽልማት ፍትሃዊ እንዳልሆነም ይናገራል።

በሁለቱ አገራት መካከል በተጨባጭ የመጣ ሰላም አለመኖሩን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊገነዘብ እንደሚገባው ተቃዋሚዎቹ  ገልፀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም እንኳን ጅምሮቻቸው መበረታት ቢገባቸውም፤ ሽልማቱ የሁለቱን አገራት መሬት ላይ ያለ እውነታ የሚያንፀባርቅ እንዳልሆነ ከተቃዋሚዎቹ መካከል ለይላ ካሊድ ታስረዳለች።

“በሌላ በኩል የኤርትራ ሁኔታ እየባሰ እንጂ እየተሻሻለ የመጣ ነገር የለም፤ የተከፈቱ ድንበሮች ተዘግተዋል፤ ሕገ መንግሥቱ አሁንም ቢሆን ሥራ ላይ አልዋለም፤ ለተወሰነ ጊዜ መሆን የነበረበት ብሔራዊ አገልግሎት አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን  ነው ፣የተቃውሞ ሰልፍ ማካሄድ ክልክል ነው” ትላለች።

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ኖርዌይን ጨምሮ የተለያዩ የአውሮፓ አገራት ለኤርትራ እያደረጉት ካለው ድጋፍ ባሻገር በአገሪቷ ውስጥ እየተፈፀመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና በደል እንዲወገድ ከሕዝቡ ጎን ሊቆሙ እንደሚገባ ለይላ ጠቁማ ፤ “የኤርትራ ሕዝብ ሰላምና ፍቅርን ይፈልጋል ይሁን እንጂ የናፈቀውንና ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለበትን ሰላም ሊያገኝ አልቻለም ፤ በተግባር የሚጨበጥ ሰላም እንጂ የወሬ ሰላም አንቀበልም” በማለት መረር ያለ መልእክቷን አድርሳለች።

የሸፈቱ 130  የቅማንት ተወላጆች በድርድር መመለሳቸው ተነገረ

ከአስተዳደር እና ማንነት ጉዳዮች ጋር የሚነሱ ጥያቄዎች በሠላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥረት እንደሚያደርግ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ገለፀ ። ከሠላም እና ደኅንነት፤ ወቅታዊ የግብርና ተግባር እና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት  ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል::

የጽሕፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይርሳው “የአማራ ህዝብ ከወሰን እና ማንነት ጋር ተያይዞ ጥያቄዎችን ያነሳው ዛሬ ብቻ አይደለም። ለዘመናት የነበሩ ጥያቄዎች ናቸው። የክልሉ መንግሥትም ጥያቄዎች ናቸው” ብለዋል::

በዚህም የክልሉ መንግሥት ከአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ጋር በመሆን በእውነት ላይ ተመስርቶ የኅብረተሰቡን ጥያቄ እስከ መጨረሻው ለመፍታት ጥረት ያደርጋል ያሉት ሓላፊ “ክልሉ ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለባቸው የሚል ጽኑ እምነት አለው ፤ ጥያቄዎቹን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ከኀብረተሰቡ ጋር በመሆን ተሳትፎ  እንሠራለን” ሲሉ ገልጸዋል::

130 የቅማንት የማንነት ኮሚቴ አባላት የተደረገላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው መግባታቸውን በመግለፅ፤ በአካባቢዎቹ እንቅስቃሴዎች በተለመደው ሠላም እንዲቀጥሉ በመደበኛነት እንደሚሠራም ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት። በክልሉ በሚገኙ 10 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ተማሪዎች በሠላማዊ መንገድ እንዲማሩ ጥረቶች እየተካሄዱ መሆኑንም አስታውቀዋል። በተያያዘም በኦሮሚያ ክልለዊ መንግሥት የሚማሩ የክልሉ ተማሪዎች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ በጋራ እየሠራን ነው ሲሉ ተደምጠዋል::

በዋሽንግተን ዲሲ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ሲያካሂዱት የነበረው ስብሰባ ተጠናቀቀ

በዩናይትድ ስቴትስ ዋሽንግተን ዲሲ ሲካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ተጠናቋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ አተኩሮ በተካሄደው ስብሰባ የሀገራቱ የውሃ ሚኒስትሮችም የተካፈሉ ሲሆን፥ የአሜሪካ መንግሥት እና የዓለም ባንክ ተወካዮችም በታዛቢነት መገኘታቸው ታውቋል። ሚኒስትሮቹ በስብሰባቸው በውሃ ሚኒስትሮች ደረጃ የተካሄዱት የባለሙያዎች ስብሰባዎች ያመጡትን አወንታዊ ለውጦች ቃኝተዋል።

በቀጣይ የሚካሄዱ ሁለት ስብሰባዎችም በግደቡ የውሃ አሞላል እና አስተዳደር ላይ ህግና መመሪያ እንዲያዘጋጅ፣ የድርቅ ሁኔታዎች ተብለው የሚወሰዱትን እና ድርቅን ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎችንም ከወዲሁ ለማስቀመጥ በሚያሴችሉ ሁኔታዎች ዙሪያ ከወዲሁ ከስምምነት ላይ ተደርሷል። ሚኒስትሮቹ ህግ እና መመሪያ መዘጋጀቱ በቀጣይ የሚኖር የድርቅ ሁኔታን ለመከላከል ያስችላል ነው ያሉት።

የግድቡን ውሃ አሞላል እና አስተዳደር በተመለከተ የሚዘጋጁት የቴክኒክ ህጎች እና መመሪያዎች በኢትዮጵያ የሚፈፀም ሲሆን፥በወቅቱ ያለው የዓየር ሁኔታ እየታየ ሦስቱ ሀገራት ተነጋግረው ይህን ህግ ሊያሻሽሉ እንደሚችሉም ተቀምጧል።

የሚደረስበትን ስምምነት ለማጠናቀቅ ፣ በካርቱም እና አዲስ አበባ የሚካሄዱት ስብሰባዎች ውጤትንም ለመገምገም ሚኒስትሮቹ በፈረንጆቹ የፊታችን ጥር 13 ቀን 2020 በዋሽንግተን ለመገናኘት ሃገራቱ ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል።

በኢትዮጵያ የእድሜ ጣራ በ14 ነጥብ 3 ዓመት ጨምሯል ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገለፀ

በኢትዮጵያ የሰው ሀብት ልማት በ65 ነጥብ 8 በመቶ ሲያድግ፥ የእድሜ ጣራ ደግሞ በ14 ነጥብ 3 ዓመት ከፍ ማለቱን የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም አጥንቼ ደርሼበታለሁ ሲል ገለፀ።

ድርጅቱ የአውሮፓውያኑ የ2019 የኢትዮጵያ ሰው ሀብት ልማት ሪፖርትን በዛሬው እለት ይፋ አድርጓል። በሪፖርቱእንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2000 ወዲህ በኢትዮጵያ የሰው ሀብት ልማት በ65 ነጥብ 8 በመቶ ማደጉን አሳይቷል።በሀገሪቱ ያለው የሰዎች የእድሜ ጣራም ከዚህ ቀደም ከነበረው በ14 ነጥብ 3 ዓመት ከፍ ብሏል ሲል በርካታ ኢትነፈዮጵያውያን የተገረሙበትንና በጥርጣሬ የተመለከቱትን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።

በኢትዮጵያ የሰው ሀብት ልማት በ65 ነጥብ 8 በመቶ ጭማሪ ቢያሳይም ፣ ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት አንጻር ሲታይ ግን ዝቅተኛ ነው የመንግሥታቱ ድርጅት ፤ የጾታ እኩልነትን ከማስጠበቅ አንጻርም ኢትዮጵያ ከ162 ሀገራት በ123ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧንም አጋልጧል። ኢትዮጵያ በትምህርት ዘፍር ላይ አሁንም የበለጠ መዋእለ ንዋይ ማፍሰስ እንደሚጠበቅባት በመግለፅ ጎታች የሆነው የሃገሪቱ የትምህርት ፖሊሲ በዘርፉ ችግር ሲፈጥር መሰንበቱን አመላክቷሌ።

LEAVE A REPLY