ባይ ባይ ደሞዝ! || ምሕረት ዘገዬ

ባይ ባይ ደሞዝ! || ምሕረት ዘገዬ

Ethiopia's Prime Minister Abiy Ahmed (C) arrives at Khartoum international airport on June 7, 2019. - Ethiopia's prime minister arrived in Khartoum today seeking to broker talks between the ruling generals and protesters as heavily armed paramilitaries remained deployed in some squares of the Sudanese capital after a deadly crackdown, leaving residents in 'terror'. (Photo by ASHRAF SHAZLY / AFP) (Photo credit should read ASHRAF SHAZLY/AFP/Getty Images)

ከገዛ ሕዝቡ ጋር ጦርነት የገጠመ መንግሥት እንደ አሁኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለ አይቼም ሆነ ሰምቼ አላውቅም፡፡ “የበላችው ያስገሳታል፤ በላይ በላዩ ያጎርሳታል” አሉ፡፡ የኑሮ ጫና አገር ምድሩን እያስለቀሰ ባለበት በአሁኑ ቅጽበት ግፍ አይፈሬውና ነውር ልብሱ መንግሥታችን በመጠጦችና በአሮጌ መኪኖች ላይ ኤክሳይዝ ቀረጥ ጭማሪ ሊያወጅ እንደሆነ ከሚዲያዎች እየሰማን ነው – ሀፍረትን ከሸጡ፣ ሕዝብንም ከናቁ አይቀር እንዲህ ነው፡፡

ይህ ፓርላማ ተብዬ የግዑዝ ማይማን ስብስብ የቀረበለትን ሁሉ ከእንቅልፍ በባነነ ጭብጨባው ከማጽደቅ ውጭ ለምን ብሎ የማይጠይቅ እንደመሆኑ ለሕዝብ የሚራራ የመንግሥት አካል ይኖራል ተብሎ አይገምትም፡፡ አንድ ዐዋጅ የሕዝብን ኑሮ ያገናዘበ መሆን ሲገባው የእነአዳነች አቤቤ መንግሥት ግን ኑሮውን ይበልጥ የሚሰቅል እየሆነ ነው፡፡ ዐዋጅ ሲታወጅ ሁለንተናዊ አንድምታው መጤን ይገባዋል እንጂ ገና ለገና “ከዚህ ዕቅድ ይህ ገንዘብ ይገኛል” ከሚል ጉጉትና ፍቅረ ንዋይ ዝም ብለው ቢያውጁ ከትርፉ ኪሣራው ይበልጣል፡፡ ለምሣሌ ይቺው አቤቤ በሠራተኛው ገቢ ላይ የጣለችው የ30 ፐርሰንት ግብር ዘረፋ እንጂ ግብር ሊባል እንኳን አይችልም፡፡

ሀገሪቱ ለሀገርና ለወገን የሚቆረቆር የተማረ ሰው ስለሌላት የዕውቀት ዘመን እስኪብት ድረስ ለጥቂት ጊዜ መቸገራችን አይቀርም፡፡ አንድ ተሞዳሟጅ ጉቦ አቀባይ ነጋዴ በዓመት ለሚያገኘው በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዓመታዊ ገቢ ጥቂት አሥር ሽዎችን ብቻ ሲከፍል እኔን መሰሉ ምሥኪን ተቀጣሪ ከመሥሪያ ቤቴ ውጪ ትንሽ ሥራ ባገኝ የሚቆረጥብኝ ገንዘብ ከመቶ 30 ነው፡፡ ከደሞዝ ላይ የሚከፈለው ግብር ራሱ የትም የሌለ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የግብር ማዕቀፉና (መነሻና መድረሻው) የየማዕቀፉ መጠን መስተካከል ሲገባው የመንግሥት ባለሥልጣናት በደሞዛቸው ባለመኖራቸው ምክንያት ችግሩ ስለማይገባቸው ችግራችን ተሰምቷቸው ይህን ሸፋፋ አሠራር ሊያተስካክሉ አልቻሉም፡፡ የጠገበ ደግሞ ዐይንም ጆሮም የለውም፡፡ ይህንን ግፋቸውን ፈጣሪ ይየው፡፡ አይቶም ይህን ህግ በደነገጉ ሰዎች ላይ መብረቁን ያውርድባቸው፤ እንደነገሩ እንኳን እንዳንኖር ዋና ምክንያት ሆነዋልና፡፡

ልጅ አይውጣላቸው፡፡ ምላሴ ጥቁር ነው፤ ልጅ ቀርቶ እነሱ ራሳቸውም በያዙት ሥልጣን ብዙ አይቆዩም፡፡ ዕንባና ሀዘን ምን እንደሚያስከትል ዕድሜ ለዕድሜየ ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ ችግሩ ግፈኛ ግፈኛን እየተካው አሣራችን መቀጠሉ ነው፡፡ መንግሥቱንና መለስን ማየት ይበቃል፡፡

በኑሮ ሁኔታ ከጓደኞቼ ጋር ስንጫወት አንዱ ምርር ብሎት እንዲህ አለኝ፡፡

“ስማ ምሕረቴ፣ መቼም አንተ ስሜትህንና ቁጣህን በመጫጫር እንደምትወጣ አውቃለሁ፡፡ እኔ ግን ብርጭቆ ውስጥ ቀብሬያት እሄዳለሁ፡፡ ከአሁን በኋላ ግን ከብርጭቆም ጋር አልገናኝም፡፡ መጠጡ ሁሉ ሊጨምር ነው አሉ፡፡ የአሁኑን ወር ወጪየን ብቻ ልንገርህ፡፡ ከዚያ በፊት ግን ‹የወር ደሞዙ 200 የቀን ወጪው 500፤ ይህን ሰው ማን እንበለው?› የሚል የደርግ ዘመን ፖስተር ታስታውሳላህ?” አለና ፈገግታየን ካረጋገጠ በኋላ የርሱን ስንክሳር ቀጠለልኝ፡፡

“ይሄውልህ፡- በቀደምለት አሥር ሽህ ብር የሚጠጋ ደሞዝ ወሰድኩ፡፡ ወሰድኩናም ቤቴ ገብቼ ለየወጪው ሁሉ ሳከፋፍል በኪሴ የሚቀር ነገር ሊኖር ይቅርና ከዚያም ከዚህም ብዬ በምሥጢር ኪሴ የቆጠብኳትን ጥቂት ሣንቲም ሳይቀር ባልተለመደ ሁኔታ ለማውጣት ተገደድኩ፡፡ በዚህ መልክ ከአንድ ግፋ ቢል ከሁለት ወር በላይ ላልኖር ነው፡፡ ደሞዝና ሠራተኛ ተለያየን፡፡ ተመልከት … ለወር ወጪ ብር 4000 ለማንጠግቦሽ ሰጠሁ – ያም ስለማይበቃት ገና ብዙ መደጎም አለብኝ፡፡ የቀን አማካይ ወጪየ ብር 150 ነው፡፡ መብራትና ውኃ እንዲሁም ስልክ በአማካይ ብር 1200 ስለሆነ ያን ገንዘብ መደብኩ፡፡ ለመቃብር ፉካ የመግቢያ ክፍያው እስኪያልቅ በየወሩ ብር 1500 ስለምከፍል ያንንም መደብኩ፡፡ ዩኒቨርስቲ ለሚማር አንድ ልጄ ብር 800 ላክሁ – ያም እንደማይበቃው አውቃለሁ – ግን የድሃ ልጅ ነውና ምንም ማድረግ አልችልም፡፡

ዩኒቨርስቲ ጨርሶ ሥራ ለማግኘት ለሚንከራተት አንደኛው ልጄ ለትራንስፖርት ብር 600 ሰጠሁ – ይህም እንደሚያንሰው አውቃለሁ – ምን ላድርግ፤ ብር እንደቅጠል ከዛፍ አይሸመጠጥ! ያ ልጄ በዘር ሐረጉና በተመራቂዎች ብዛት የተነሣ በቅርብ ሥራ እንደማያገኝም እሱም እኔም ከተረዳን ቆይተናል፡፡ ትንሹ ልጅ ጫማ ግዙልኝ ብሎ እሪታውን ማቅለጥ ከጀመረና እኔም በይደር ካቆየሁት ሦስት ወራትን ስላስቆጠረ ያበጠው ይፈንዳ ብዬ ለሱም ብር 500 መድቤያለሁ – አንዲት ሸራ ጫማ እንኳን ቢገዛ፡፡ የሴት ዕድር፣ የወንድ ዕድር፣ የጽዋ ማኅበር መዋጮ፣ … ስላሉብን ለነዚህም በትንሹ ብር 500 መድቤያለሁ፡፡ የፍርድ ቤት ክርክር ስለነበረብኝና ያም ስላለቀ የጠበቃ ቀሪ ክፍያ ብር 4000 አፍጥጦ እየጠበቀኝ ነው – በአንድ ሣምንት ውስጥ መከፈል ያለበት፡፡ ማንጠግቦሽ ለዓመት የሚሆን በርበሬ አዘጋጃለሁ ብላኝ ከነቅመሙ ብር 3500 ተጠይቄ እሱንም መድቤያለሁ፡፡

ሲያቀብጠኝ በሰው ግፊት የገባሁት የብር 3000 ዕቁብም የሚዘለል አይደለም፡፡ ደምርልኛ – ምነው ፈዘህ ታየኛለህ? ደግሞም ይህንንም ጻፈው አሉ – እንዳትጽፈው አደራ! እናሳ ሥንት ሆነ? አዎ፣ ካልተሳሳትኩ ድምሩ ብር 24400 ነው – ሁለት ሽህ አራት መቶ ዐርባ አላልኩህም – ሃያ አራት ሽህ አራት መቶ ዐርባ ብር ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ብዙ ያልታዩ የክፍያ ሰነዶችን  ያላገናዘበ ግርድፍ ወጪ ነው፡፡ በዚያ ላይ ልብስ፣ ጫማ፣ መቼም ወግ አይቀርምና የሴትና የወንድ የውበት ዕቃዎች፣ ህክምና፣ …. ሁሉ ከሂሣብ ውጪ መሆናቸውን ልብ በል – ባይገርምህ አንዱን ልጄን በቀደምለት ወደአንዱ የግል ክሊኒክ ወስጄው ነበር፤ ቀደም ሲል 30 ብር በቅርቡ ደግሞ 70 ብር የነበረው የካርድ ክፍያ 200 ብር ሆኖ ጠበቀኝ – በጥቂት ወራት ውስጥ ነው ይህ ሁሉ የሆነው፡፡

አትታመም – ከታመምክ ወደጠበል እንጂ ሀኪም ቤቶች ከቄራ ብሰዋል – ኪስህን ቆራርጠው ባዶ ያስቀሩሃል – ኅሊና ብሎ ነገር የለም፤ ከሀገር ሸፍቷል፡፡ የቤት ኪራይ ቢኖርብኝማ… ኧሯ!… የሚገርም ዘመን፤ የሚገርም ተዓምራዊ ማኅበረሰብ፡፡ ካልኩህ ሁሉ አንድም ሀሰት የለበትም ወንድማለም፡፡ ለካንስ ያ ወላጅ እንዲህ ያለው ወዶ አልነበረም – እንዲህ፡- ልጅ፡- ‹አባዬ ሦስት ብር ስጠኝ›፤ አባት፡- ‹ለምንህ?›፤  ልጅ፡- ‹ት/ቤት ውስጥ ምትሃት ልናይ ነውና ለመግቢያ›፤ አባት፡- ‹አየ ልጄ፤ በ300 ብር ቤተሰቤን ቀጥ አድርጌ ከማኖር የበለጠ ምትሃት አለ ብለህ ነው? በል እዚሁ አሳይሃለሁ፡፡› ቀደም ባለ ዘመን የተወራ ቀልድ ነው፡፡”

“ምሕረቴ! ከሚገርምህ ነገር በቅርብ በጄቲቪ ‹እርስዎም ይሞክሩት› የነፃነት ወርቅነህ አንድ ዝግጅት ላይ ከቀረቡ የአንድ ሥጋ በል ድርጅት ሠራተኞች አንደበት እንደሰማሁት በወር 800 ብርም የሚከፍል ቀጣሪ ድርጅት አለ፡፡ ‹ወገብ ዘላውን ይክፈለው› እንዳልልህ ባለጌ ትለኛለህና ይቅርብኝ፡፡ ብቻ የኔ የትልቅ ደሞዝተኛ ኑሮ እንደዚህ ከእጅ ወደ አፍም መሆን ካቃተው ለትራንስፖርት ብቻ ሽዎችን ለሚፈጅ ሥራ ብር 800 እና  ከዚያ ብዙም የማይሻል ክፍያ የሚያገኝ ወገናችን እንደምን ኑሮን እንደሚገፋ ይታይህ፡፡ በዚህ ሕዝብ መሀል ስትኖር እኮ በየምትሄድበት ቦታ ሁሉ በርሀብ በሞተ ዜጋ ሬሣ ላይ እየተረማመድህ መሆን ነበረበት፡፡ ግን የፈጣሪን ጥበቃና አለኝታነት ማድነቅ እንድንችል ይመስለኛል ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆኖ እንዲያውም ሰው ሲስቅና ከአንገት በላይ ሊሆን ቢችልም ፈገግ ሲል ታያለህ፡፡
ለነገሩ ሬሣም እኮ ይስቃል ይባላል፤ ዋናው ሲሞት የነበረው ገጽታዊ ስሜት ወይም ስሜታዊ ገጽታ ነው፡፡ …” ኢትዮጵያ ግን እንዴት የምትገርም ሀገር ናት! “ሞተው” የሚኖሩባት፤ “እየኖሩ”ም የሚሞቱባት እጅግ ዕጹብ ድንቅ ሀገር! የኛን መሰል “ታጋሽ” ሕዝብና “ሩኅሩኅ” መንግሥት መቼም የትም የለም፡፡

ጓደኛየን ዝም ካልኩት በቀላሉ የሚጨርስ አልመሰለኝም፡፡

ግን ግን በእውኑ መንግሥት አለ? በኔ ዕድሜ በኩንታል ዘጠኝ ብር የነበረ የጎጃም ነጭ ጤፍ ዛሬ ብር 4000 ሲደርስ፣ በሣንቲሞች የነበሩት እነዘይት፣ ላምባ፣ ከሰል፣ ጥራጥሬዎች፣ ስኳር፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣… ዛሬ ሰማየ ሰማያት ተሰቅለው ሕዝብ እዬዬ ሲል መንግሥት ገበያውን እንደማረጋጋት፣ ነጋዴውን በማንቃት ሀገራዊና ወገናዊ ስሜት እንዲኖረውና ተዛዝኖና ተያይቶም እንዲያድግ ከመምከርና እምቢ ካለም ህጋዊ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ከዘራፊዎች ጋር መተባበሩ ማንን እየመራ እንደሆነ ማወቅ ይቸግራል፡፡ በኔ ዘመን የስድስት ብር ሙክት ሌጦው በዘጠኝ ብር እየተሸጠ ለሥጋ በሊታዎች የሦስት ብር ማነቃቂያ እንዳልተከፈለ ዛሬ በኪሎ አራትና አምስት መቶ ብር ሲገባ፣ በሬ 100 ሽህ ብርን ሲታከክ፣ በግና ፍየል 12 ሽህ ብርን ሲያልፍ ምን ዓይነት አዚም እንደተጣለብን ሳስበው ይጨንቀኛል፡፡ ሌላ ቃል ስለሌለ እንደዋዛ “ይጨንቀኛል” ልበል እንጂ፡፡

እኔ እንደሚመስለኝ መንግሥት ሕዝብን አያውቀውም፡፡ ሕዝብና መንግሥት ዘይትና ውኃ ሆነዋል፡፡ እውነት ለመናገር በተለይ አቢይ ሥልጣን ከያዘ ወዲህ እልህ በሚመስል ሁኔታ ሁሉም ነገር በየቀኑ እየተሰቀለ ነው – እርሱም የአህያ ባል ሆነና ከተደበቀበት ቤተ መንግሥታዊ ዋሻ ወጥቶ ከቀንም ይሁኑ ከሌሊት ጅቦች ሊያስጥለን አልቻለም፤ አልሞከረምም፡፡ ሴትዮዋ “እኔ እምሞት ዛሬ ማታ፣ እህል እሚደርስ በፍልሰታ” ያለችው ወድዳ አልነበረም፡፡ እሱ ስለወደፊቷ የበለፀገች ኢትዮጵያ በሚያማልሉ ቃላት ይደሰኩራል፤ እኛ በርሱ ነጋዴዎችና በርሱ የመቀሌ ቅምጥል ሽፍቶች በየቀኑ እየተገዘገዝን ልናልቅ ነው – ተስፋ ለባዶ መሬት ምን ይሠራል?  ተስፋ ካለሰው ምን ይረባል? ሰው ለሌለበት መሬት ተስፋ አይዘራም፡፡ አቢይ ምን እየሠራ ነው? ጠይቁት፡፡

አቢይ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ሲገባ ዘጌ ገዳም የገባ መስሎታል መሰለኝ ለነፍስ እንጂ ለሥጋ አንዳችም ትኩረት የሰጠ አይመስልም፡፡ በኑሮ ብናር ብንጠበስ የርሱ ፍላጎት እስካልተነካ ድረስ የኛን ችግር ከምንም አልቆጠረውም፡፡ በምድር ሲኖር ቀዳሚው ሆድን ማሸነፍ ነው፡፡ ሆዱን ያላሸነፈ ማኅበረሰብ ከዐውሬ የከፋ እንደሚሆን ኢትዮጵያን ማየት ነው – ጽድቅና ኩነኔ ከሆድ በኋላ የሚመጡ ወይም የሆድን ጣጣ በዕውቀትና በጥበብ ከለወጡ በኋላ ትልቁና አምስተኛው ማስሏዊ የዕድገት ደረጃ ላይ ሲደርሱ የሚከሰት የልዕለ-ራስ (Overself) ውጤት ነው፡፡ ከመኝታህ ተነስተህ ከተሞችን ብትቃኝ ከሞላ ጎደል ሁሉም ሲኳትን የምታየው ለአንዲት እንጀራ እንጂ ወደ ቤተ መጻሕፍት ወይም ወደ አምልኮት ቦታዎች ገብቶ የነፍስ ምግብን ለመሸመት አይደለም – ወደነዚያ ቦታዎች የሚሄደው ሰው ብዛት ቀላል ባይሆንም ይበልጡን ለታይታና ከአንገት በላይ ለመሆኑ ኑሯችን ኅያው ምሥክር ነው – እዚህ ላይ “ለአንዲት እንጀራ” ስልህ በዱሮው አማርኛ መጠቀሜ እንጂ ዛሬ ዛሬ አንዲት ሙዝና አንዲት ዳቦ በልቶ – የሚውለውና የሚያድረው ዜጋ ብዙ እንደሆነ ልንገነዘብ ይገባል – ሊያውም  እኮ “ቆንጆ” ደሞዝ እያለው – ገመናችን እጅግ ብዙና የሚሰቀጥጥም ነው ወንድሜ፡፡ ጥሩ ደሞዝ እያለው ነገር ግን ኑሮው በመሰቀሉና የገንዘባችን የመግዛት አቅም ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዘመን የጀርመን ዳች እየወረደ በመሆኑ በረንዳና ጎዳናዎች ጥጋጥግ የሚኖረው ዜጋ ብዙ ነው እህቴ፡፡

ይህን የመሰለ ሕዝብ ይዘህ ምንም ዓይነት ዕድገትና ብልፅግና ማስመዝብ አትችልም – በስያሜዎች ማማር ራስን ማሞኘት ግን አይከለከልም፡፡ ከዚህ በላይ እንደጠቀስኩልህ በማስሎው ትወራ ገና አንደኛው ደረጃ ላይ የሚገኝ ሕዝብ ከሆዱ ባለፈ ስለምንም አይጨነቅም፡፡ በዚህ ላይ ወያኔን ምሥጋን ይንሳውና ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ የሞራል ዕሤቶች በመበጣጠሳቸው ሰዎች ወደየለየለት ዐውሬ ተለውጠው እርስ በርስ ሲፋጁ ታያለህ፡፡ ማተቡን የበጠሰ ሰው፣ ሃቂቃውን በክህደትና በዕብለት የቀየረ ጀምኣ …. የጥፋት ሠራዊት አባል እንጂ የዕድገት ትልም ቀያሽ ሊሆን አይችልም፡፡ ሰሞኑን እንኳን በዐረብ ሀገራት በአንደኛው የተገደለውን ዲያቆን ብናይ የመረገማችን አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ዘመድኩን በቀለ እንደጻፈው ይህ ዲያቆን ሲገደል አራተኛ ሰው መሆኑ ይመስለኛል፡፡

በልዩ ዘዴ የሚገድሉትም በቤተ ክርስቲያን የመሸጉ ዘማዊ ሶዶማያውን የቀበሮ ባህታዊዎች በሥውር በሚያጠምዱት የመርዝ ጦር እንደሆነ ዘመድኩን ጠቁሟል፡፡ ዙሪያችን እሳት ሆኗል፡፡ ሰይጣን ሁለ ነገራችንን ተቆጣጥሮታል፡፡ በርትተን እንጸልይ፡፡

ኢትዮጵያን ለማዳን ሳስብ የሚከብደኝ ይህ ከላይ የጠቀስኩት ነገር እፊቴ እየተደቀነ የሚያስጨንቀኝ ነው፡፡ ለመሆኑ በሀገራችን ሰው መፍጠር የምንችለው እንዴትና በምን አግባብ ነው? ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ሳይመለስ አቢይ ቢነሳ ቢፈርጥ፣ አንድ አይደለም አንድ ሽህ የሰላምና የከተማ ጽዳትና ውበት ኖቤል ቢሸለም ዋጋ የለንም፡፡ በቁም ከሞትንበት አዙሪታዊ ወጀብ ካልወጣንና ወደየኅሊናችን ካልተመለስን መና መቅረታችን ነው፡፡ በዚያ ላይ ጥራት ከሀገራችን ኮብልላለች – የትምህርት ጥራት፣ የዕቃ ምርት ጥራት፣ የግንባታ ጥራት፣ የመንገድ ሥራዎች ጥራት፣ የአመራር ጥራት፣ የስብዕና ጥራት…. ድራሻቸው ጠፍቶ በቅርጽ እንጂ በይዘት የለንም፡፡ ይብላኝ ለልጆቻችን፡፡ ይብላኝ ጤናማ አስተሳሰባቸውን ላጡ ወገኖቼ፡፡ ይብላኝ በሰይጣን አገዛዝ ሥር ገብተው ሥጋቸውን በምቾት ነፍሳቸውን ግን በስቃይ ለሚያማቅቁ የዋህ የዚህች ዓለም ፍጡራን ወንድሞቼና እህቶቼ፡፡ ይብላኝ … በቃኝ እባክህን፡፡ ለሥንቱ ይብላኝ ብዬ እዘልቀዋለሁ?

ለማንኛውም ጤናማና አስተማሪ አስተያየት –  ma74085@gmail.com

LEAVE A REPLY