ስለሚኖሩባት ሃገር መፈራረስ ሟርት… || ሙሼ ሰሙ

ስለሚኖሩባት ሃገር መፈራረስ ሟርት… || ሙሼ ሰሙ

ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ የተፈጠሩ እድሎችን ተጠቅሞ ወደ ጠረጴዛ በመምጣት ከመወያየትና መፍትሔ ከመሻት ይልቅ፣ በድርጅታዊ መካረርና እንካ-ሰላንታ በመጠመድ፣ ኢትዮጵያ ከአሸዋ የተሰራች ቤት ይመስል ትፈርሳለች የሚሉ ሟርቶችን መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡

አብዛኛዎቹ የፓለቲካ ልሂቃን ከጠላት በማይጠበቅ ደረጃ፣ ስለሚኖሩባት ሃገር መፈራረስ ሟረት ሲያሟርቱ መስማት እጅጉን የሚያሳዝን ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ማርተኞቹ እነሱ ሳይነኩ ሃገር እንዴት እንደምትፈርስ ቢያስረዱን መልካም ነበር፡፡

ከንግግርና ከድርድር ውጭ በግብዝነትና በእልህ ወይም በሟርት ድርጅት ይፈርስ ይሆናል እንጂ፤ እንቅልፍ ነስቶ የሚያሻኩታቸው ስልጣን ብቸኛ ባለቤት የሆነው ኢትዮጵያዊና ሊገዟት የሚቋምጡላት ኢትዮጵያ ግን አንደማትፈርስ መገንዘብ ቢችሉ መልካም ነበር፡፡ ይህ ሃቅ ማንነትና ድንበር ሳያግደው ለሁሉም ሟርተኛ የሚሰራ ጥሪ ሀቅ ነው፡፡

አሁንም ተጨባጭ የሆነ አማራጭ ሃሳብ አፍልቆ ሕዝብን ከማታገል ይልቅ መረጃ እናወጣለንና እናጋልጣለን የሚል መደራደርያ አጀንዳ እያዳመጥን ነው። ይህ ደግሞ ሌላው የኃልዮሽ ጉዞ መገለጫ መሆኑን ከወዲሁ መገመት ይቻላል፡፡ ወንጀለኛና ከሃዲ ካለ ማንም ይሁን ማን ማጋለጥ የዜግነት ግደታችን ነው፡፡ መረጃው ሲቀርብ ያኔ ተጠያቂው በሰራው ወንጀልና በክህደቱ የሚያፍርበትና የሚዳኝበት ጉዳይ ይሆናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ “ማጋለጥ” አማራጭ የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ ሃሳብ ሆኖ ለስልጣን አንደማያበቃ መገንዘብ ይጠቅማል።

ይህም ሆኖ፣ ለማጋለጥ በበር መጣሁ በመስኮት ማለት ለምን እንዳስፈለገ ግልጽ አይደለም፡፡ በስልጣን ላይ የሚገኝ ሹመኛ የሰራው ወንጀልና በሃገር ላይ የፈጽመው ክህደት ካለ ጉዳዩ የግለሰብ፣ የቡድን ወይም የድርጅት እጅ መጠምዘዣና አጀንዳ ማስቀየሻ መሳርያ ሊሆን አይገባም፡፡

በሕዝብና በሃገር ላይ የተፈጸመ የወንጀልንና የክህደት ተግባር በተጨባጭና በመረጃ እስከተረጋገጠ ድረስ የቡድን፣ የግለሰብ ወይም የድርጀት ንብረት ወይም መጠቀሚያ መሆን የለበትም፡፡ መረጃው ሳይውል ሳያድር መቅረብ ነበረበት፡፡ በሕዝብ ላይ የተፈፀመ ወንጀልን መደበቅም ሆነ በማስፈራሪያነት መጠቅም ወይም አስቦና አቅዶ መረጃውን ማዘግየት እራሱን ችሎ የሚያስጠይቅ ተግባር ነው፡፡

LEAVE A REPLY