ለቀጣዮ ምርጫ የምዝገባ ሰነዶች፣ ህትመትና ቁሳቁስ ግዢ መጀመሩ የምርጫውን አይቀሬነት ያረጋግጣል ተባለ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ የሚውል የመራጮች ምዝገባ ሰነዶች ህትመትና የቁሳቁሶች ግዥ መጀመሩን ገልጿል ።
ምርጫ ቦርድ ለቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ከሚያደርጋቸው ዝግጅቶች መካከል አንዱ የሆነውን የመራጮችን ምዝገባ ዘመናዊ እና ተዓማኒ የሚያደርግ የህትመት ሥራ እንዲጀመር የሚያስችለውን ስምምነት በዱባይ ተፈራርሟል።የተፈረመው የህትመት ውል አላማም የምርጫው ሂደት ዓለም ዐቀፍ ደረጃን የጠበቀ እና አዲሱ የምርጫ ህግ ላይ የተቀመጡትን መስፈርቶች ያሟላ እንዲሆን የሚያስችል ነው ተብሏል።
በተጨማሪም በምርጫ ሂደቱ ሊፈጠሩ የሚችሉ ስህተቶችን ለመቀነስና እና ማጭበርበርን ለማስወገድ የሚረዳ እንዲሆን ፣ ለምርጫ አስፈጻሚዎች ለመረዳትና ለማስፈጸም ቀላል እንዲሆን ለማድረግ ያስችላል መባሉንም ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
የህትመት ሥራው ከዚህ በፊት ከነበሩትና ሀገር ውስጥ ከሚደረጉ ህትመቶች የተለየ መሆኑም ተገልጿል። በመሆኑም ህትመቱ የመራጮች መመዝገቢያ መዝገቡም ሆነ ፣ የምዝገባ ማረጋገጫ ካርድ የራሳቸው የደህንነት ማረጋገጫ ያላቸውና ሊጭበረበሩ እና ሊባዙ የማይችሉ መሆናቸውም ታውቋል።
የመራጮች ካርድ ቀሪ ያለው ሆኖ የሚዘጋጅና መራጮች ጋር ያለው ካርድ ቀሪ ደግሞ የምርጫ አስፈጻሚዎች ጋር የሚቀር መሆኑ ፤ በምዝገባ ወቅት ሊፈጠር የሚችል ማጭበርበርን ማስቀረት እንደሚያስችልም ተገልጿል።
በተጨማሪም እያንዳንዱ መራጭ በመራጮች ካርር አማካኝነት የራሱ የሆነ ልዩ መለያ ቁጥር ያለው ሲሆን፤ ሁሉም ሰነዶች በአምስት ቋንቋ ማለትም፣ በአማርኛ፣ በአማርኛ/ትግርኛ፣ በአማርኛ/አፋን ኦሮሞ፣ በአማርኛ/ሶማሊኛ እንዲሁም በአማርኛ/ አፋርኛ ቋንቋዎች ይታተማሉ።
ህገ ወጥ የሆነ የምርጫ ዕቃዎች አግባብ ባልሆነ እጅ እንዳይወድቁ ዕቃዎቹ የሚታሸጉበት ልዩ ቁሳቁስ ለመራጮች ምዝገባም ሆነ ለድምጽ መስጫ ይውላል።ከህትመት ሂደቱ ጋር አብሮ የሚከናወነው ግዥ ጥቅል የሆነ ለመራጮች ምዝገባ የሚያስፈልግ ቁሳቁስ፣ የማጭበርበር ሙከራ ካለ ሊያጋልጥ የሚችል የፕላስቲክ ቦርሳ እና የአጠቃቀም ስልጠናን እንደሚያካትት ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የደረሰን መረጃ ያሳያል።
የህትመት ሥራውን የሚያከናውነው ድርጅት ለኬንያ ፣ ለኡጋንዳ፣ ለማላዊና ለዛምቢያ የምርጫ ሰነዶችን በማተም የሚታወቅና የምርጫ ሥራዎችን በልዩ ሁኔታ የሚሠራ ተቋም መሆኑም ተገልጿል።
ከሀገር የሸሸ ገንዘብን ለማስመለስ ከተወሰኑ ሀገራት ጋር ስምምነት ተደረሰ
ከሀገር በተለያዩ መንገዶች የሸሸን ሃብት ለማስመለስ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ገለጸ፡፡ ባለፉት ዓመታት ከሀገሪቱ በተለያየ መንገድ በርካታ ሃብት ተመዝብሮ ወደ ውጭ ሃገራት መሸሹ ይታወቃል።
ሃብቱ ሊሸሽ የቻለው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በነበሩና ከእነሱ ጋር ጥብቅ ቁርኝት በነበራቸው ባለሃብቶች ትብብር እንደነበረም ተገልጿል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ብርሁኑ ጸጋዬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2011 ዓ.ም የ11 ወራት የሥራ አፈጻጸምን ሪፖርትን ሲያቀርቡ ፤የሸሸውን ሃብት ለማስመለስ ከተወሰኑ ሀገራት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ጠቁመው ፤ ከሌሎች ሀገራት ጋርም ሃብቱን ለማስመለስ በጥንካሬ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል::
ሃብቱ የተደበቀው በእነማን እና የት እንደሆነ ተለይቷል ያሉት በጠቅላይ ዓቃቢ ህግ የህዝብ ግንኙነት ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱሉ ፤ በወንጀል የተገኘ ሃብትን የማስተዳደር ሥርዓት አለመኖሩ በሂደቱ ችግር መፍጠሩን አስታውቀዋል፡፡
አሁን ላይ ሃብት የማስመለስ ዳይሬክቶሬት መቋቋሙን በመግለፅ፤ በዚህ የተሳተፉ ወንጀለኞች በህግ እንዲጠየቁ ማድረጉ በትኩረት እየተሠራበት ነውም ብለዋል።
ጉዳዩ ውስብስብና ጊዜ ይጠይቃል ያሉት አቶ ዝናቡየምራመራ ሂደቱ ሲጠናቀቅ በእነማን እና የት ሀገር ሃብት ሸሸ የሚለው ወደ ፊት ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በሀገሪቱ በወንጀልና በሙስና የተዘረፈን የሀገርና የህዝብ ሃብት የማስመለሱ ሥራ መጠናከሩን አቶ ዝናቡ ገልጸዋል:: በ2011 ዓ.ም ያለአግባብ የህዝብ ሃብትን ለራሳቸው አድርገው ያከማቹትን በማጣራትና በመለየት ከ95 ሚሊየን ብር በላይ ማስመለስ እንደተቻለ እና ባለፉት ሦስት ወራትም ከ35 ሚሊየን ብር በላይ ማስመለስ ተችሏል ሲሉ ተደምጠዋል።
በርካታ የቀድሞ የህወሀት/ኢህአዴግ ባለስልጣናት በልጆቻቸው፣ በሚስቶቻቸውና በቅርብ ዘመዶች ስም በተለያዩ ሃገራት ቤት ንብረትና ድርጅቶችን በመክፈት ገንዘብ ሲያሸሹ እንደነበር በተለይ በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሲወተውቱ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። አሁንም በተለይ በካናዳና አሜሪካ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ከሞርጌጅ ነፃ የሆኑ ቤቶች ጥሬ ገንዘብ ከፍለው የገዙ የህወሀት ኢህአዴግ የቅርብ ሰዎች እንዳሉ ይታወቃል።
2 ዓመት የዘለቀው የነልደቱ አያሌው (ኢዴፓ) አመራር ውዝግብ ውሳኔ ተሰጠበት
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢዴፓ/ አመራር ውዝግብ ዙሪያ ሲቀርብለት ለቆየው አቤቱታ ውሳኔ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/ ኢዴፓ/ ውስጥ ላለፉት ሁለት አመታት የቆየውን የፓርቲውን አመራር ምርጫ እና ተያያዥ ውዝግብ መርምሮ ነው ውሳኔውን ያስተላለፈው።
ኢዴፓ ( እነ አቶ አዳነ ታደሰ ) በ25/02/2012 በተጻፈ ደብዳቤ ፣የኢዴፓ አመራር ምርጫ እና የፓርቲው ምክር ቤት ስብሰባን አስመልክቶ ለቦርዱ ዝርዝር አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን አቤቱታውም ፤ ፓርቲው ሐምሌ 06 ቀን 2011 ዓ.ም አስቸኳይ ፓርቲው ምክር ቤት ስብሰባ ማድረጉን በዚህ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎች ማሳለፉን እና ያሳለፈው ውሳኔ በቦርዱ እውቅና እንዲያገኝ ቢጠይቅም በቦርዱ እውቅና እንዳላገኘ፣በዚህም መሰረት የእርምት እርምጃ ወስዶ ጥቅምት 23 ቀን 2012 ዓ.ም በድጋሚ ልዩ አስቸኳይ ስብሰባ ማድረጉን ገልጿል::
ስብሰባው የተጠራው በምክር ቤቱ አባላት ፒቲሽን መሆኑን፣ የስብሰባው ቀንና ሰአት ሥራ አስፈጻሚው በወሰነው መሰረት ማካሄዱን፣ በዚህ ምክር ቤቱ ሁለተኛ ጉባኤ የኦዲትና ኢንስፔክሽን አባላት ተገኝተው ስብሰባውን መታዘባቸውን ከዚሁ ጋር በማያያዝም በቦርዱ በተሰጠው መመሪያ መሰረት በዚሁ አስቸኳይ ስብሰባ ይህንን የእርምት እርምጃ መውሰዱን በመግለፅ ፣ በጉባኤው የተሰጡ ውሳኔዎች እውቅና አግኝተው ተፈጻሚ እንዲሆኑ ተገቢውን ሁሉ እንዲደረግለትም ጠይቆ ነበር።
ቦርዱም ከላይ የተጠቀሱትን ሰነዶች፣ መተዳደሪያ ደንቡን እንዲሁም ቃለጉባኤዎቹን ከመረመረ በኋላ ህዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም ከፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን፥ ይህ አስቸኳይ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ በፓርቲው ህገ ደንብ መሰረት የተከናወነ ስብሰባ መሆኑን ቦርዱ መገንዘቡን ገልጿል ።
በመሆኑም ቦርዱ ጥቅምት 23 ቀን 2012 ዓ.ም በተደረገው የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ የተወሰኑት ማለትም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ፣ የጠቅላላ ጉባኤ ቀን እና የጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ ምርጫ ፣ አራት አባላቱን ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እና ከብሔራዊ ምክር ቤት ማሰናበቱ እና ሌሎች ቃለ ጉባኤው ላይ የሚገኙ ውሳኔዎች ህጋዊ ናቸው ብሎ በመወሰን ለሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን የትብብር ደብዳቤ በመጻፍ ማሳወቁንምአረጋግጧል::
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የእናቶችና የሕጻናት ማዕከል ሥራ ሊጀምር ነው
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ውስጥ የተገነባው የእናቶችና የሕጻናት ማዕከል በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተባለ።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ውስጥ የተገነባውን የእናቶችና የህጻናት ማዕከል እንዲሁም በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ዋና መሥሪያ ቤት የተገነባውን የሕክምና ግብዓቶች ማከማቻ ማዕከል ያሉበትን ሁኔታ ጎብኝተዋል።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ውስጥ የተሠራው ባለ 8 ፎቅ እና 450 አልጋ የሚይዝ ምቹ የእናቶችና የህጻናት ማዕከል ግንባታ የተጠናቀቀ መሆኑን እና በቅርቡ ተመርቆ ሥራ የሚጀመር መሆኑን ዶከተር አሚር ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ዋና መሥሪያ ቤትም ከ 2 እስከ 8 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ቅዝቃዜ ለሚያስፈልጋቸው የሕክምና ግብዓቶች ማከማቻ የሚሆኑ 6 ቀዝቃዛ ክፍሎች መገንባታቸውን ነው አስረድተዋል። በተመሳሳይም ከ-25 እስከ -15 ድግሪ ሴንቲግሬድ ቅዝቃዜ ለሚያስፈልጋቸው የሕክምና ግብዓቶችን ማከማቻ የሚሆኑ ሁለት የከፍተኛ ቀዝቃዛ ክፍሎች ግንባታ መጠናቀቁንና ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጁ መሆናቸው ተገልጿል::
የፖለቲካ ፓርቲዎች ካለፉ ታሪኮች በመማር ለሀገር ሰላም ሊሠሩ ይገባል ተባለ
የፖለቲካ ፓርቲዎች ካለፉ ታሪኮች በመማር ለሀገር ሰላም ሊሠሩ እንደሚገባ የታሪክ ምሁራንና ፖለቲከኞች ገለጹ::
በሃረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የታሪክ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለፉ ታሪኮችንና ትርክቶችን የርዕዮት ዓለም አካል አድርገዉ መንቀሳቀሳቸውን በማቆም የፖለቲካ ትኩሳት የሚያደርሰዉን አሉታዊ ተጽዕኖ መከላከል እንደሚገባቸው ጠቁመው ፤ ፓርቲዎች ካለፉ ታሪኮች ሊማሩ ይገባል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ፣ለሰላም እና ሀገራዊ አንድነት የሚጠበቅባቸውን ሓላፊነት በተገቢው ሁኔታ መወጣት እንዳለባቸው አስጠንቅቀዋል።
የአማራ ማኅበራዊ ራዕይ ግንባር ሊቀመንበር አቶ ስዩም መንገሻ እና የመድረክ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በበኩላቸው ፤ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሃሳብ ልዕልና ላይ የተመሰረተ ፖሊሲና ስትራቴጂን በመንደፍ የሕዝብን ችግሮች መፍታት ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በመነጋገርና ተቀራርቦ በመሥራት መርህ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲ ለሰላም ካለው አበርክቶ አንጻር የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ ሥራ ሊሠሩ እንደሚገባም እና ሰላምን በሀገሪቱ በማስፈን ረገድ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለባቸውም አስረድተዋል::
የብልጽግና ፓርቲ ውይይት ወደ ዝቅተኛ የድርጅቱ አባላት ወረደ
የኢህአዴግ ውህደትን ተከትሎ እውን የሆነው ብልጽግና ፓርቲን አስመልክቶ በከፍተኛ አመራሮች ዘንድ ሲካሄድ የቆየው ውይይት ወደ ታች አባላት ወርዷል:: በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኙ ዝቅተኛ አመራሮች በብልጽግና ፓርቲ ዙሪያ ውይይት እያካሄዱ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡
ውይይቱ የብልፅግና ፓርቲ ያለፉ መልካም ተሞክሮዎችን በማጠናከር፣ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ እና አሳታፊ ዴሞክራሲ መገንባት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል። በውህደቱ አስፈላጊነት፣ ሂደት እና በፓርቲው ህገ ደንብ ዙሪያ ያተኮረ መሆኑን ሰምተናል፡፡
የበታች አባላትን ባሳተፈው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከክፍለ ከተማው አስር ወረዳዎች የተውጣጡ 1 ሺህ 500 ዝቅተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ነው፡፡