<<ስለ ላልይበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ሥራዎች ብዙ ብጽፍ የሚያምነኝ ሰው መኖሩ በጣም ያሳስበኛል፤ ያስጨንቀኛልም፡፡ እስካሁን ያልኩትንም እንኳን ቢሆን “ውሸት ነው” ነው የሚሉኝ፡፡ ነገር ግን የጻፍሑት በሙሉ እውነት ለመሆኑ በኃያሉ እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፡፡ እንዲያውም ከዚህ በላይ ማለት ይቻል ነበር፡፡ ሆኖም ባልሁትም እንኳን በቀጣፊነት ስሜ እንደማይነሳ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡>>
ይህን ያለው 1512 ዓ.ም ኢትዮጵያን ለመጎብኘት መጥቶና ተመስጦባት እስከ 1518 ዓ.ም ያየውን ሁሉ እያደነቀ የቆየው ፖርቹጋላዊው ቄስ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ ነው። በጽሑፍ በተቀመጡልን መረጃዎች መሠረት ላሊበላን ጎብኝቶ ስላየው ድንቅ ጥበብ ጽፎ ያስቀመጠ የመጀመሪያው አውሮፓዊ ነው ቄስ ፍራንሲስኮ።
…
<<የዓለም ሕዝቦች ሆይ! ላልይበላን ሳታዩ ካለፋችሁ በሕይወታችሁ ትልቅ ነገር ጎድሏችሁ እንደሞታችሁ ቁጥሩት። የሰው ልጅ ሁሉ ሊያየውና የኢትዮጵያን ታላቅነት የነገሥታቶቿንም ጠቢብነት ሊመሠክር ይገባል ስል በሙሉ ልቤ ነው።>> ያለው ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ዳይሬክተር የነበረው ሙስሊሙ ዶ/ር ታሌብ ራፋይ ነው። ይህን ተጽፎልኝ ያነበብሁት ሳይሆን በጆሮዬ የሰማሁት ምስክርነት ነው።
…
ከሀገራችን ቅርሶች በዩኔስኮ በመመዝገብ ቀዳሚ ነው – ላልይበላ። ከዓለም 8 እጅግ አስደናቂ ቅርሶች አንዱ ነው። ያዩት ሁሉ ለመግለጽ ቃል አጥሯቸዋል። ቅርሶች ከምድር ሆድ ከተኘ አለት ነው በጥበበኛው ቅዱስ ንጉሥ እጅ የተፈለፈሉት። በሰው እጅ ተሠሩ ብሎ ለማመን የሚያስቸግሩና “የመላእክት ሥራዎች መሆን አለባቸው” የተባለላቸው ያልተፈቱ እንቆቅልሾች ናቸው። ረቂቅ መንፈሳዊና ሥጋዊ ምስጢራትን አለት ላይ አትመው እንደያዙ ዘመናትን የተሻገሩ ትንግርቶች።
…
ቤዛ ከሉ ዓለም ልዩ የዝማሬ ሥርዓት ነው። ላልይበላ ብቻ የሚገኝ። በየዓመቱ ታኅሣሥ 29 በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ደግሞ በ28 የሚከበር አስደማሚ መንፈሳዊ ትእይንት። ከላልይበላ አስደማሚ ቅርሶች ላይ ልዩ ውበት ሆኖ የተደረበ የውበት ካባና የዜማ ጌጥ፣ የጥበብ ውጤትና የመንፈስ ልእልና ማሳያ – ቤዛ ኩሉ ዓለም። ዘንድሮም በልዩ በልዩ ድምቀት ይከበራል። እዛው እንገናኝ።
…
.
(((የእኔ ትውልድ ብዙ የሚያፍርበት ነገር ቢኖርም… ላልይበላ እየፈረሰ ቆሞ ከማየት በላይ ግን አንገት ሚያስደፋው ነገር የለም። ምን ልባትም በታሪክ ፊት ቆሞ የሚወቀስበት ይሆናል – ተረባርቦ ካላዳንነው። እንዴት ታሪክ መሥራት ቢያቅተን ቅርስ መጠበቅ ይሳነናል?
… መገፋፋትና መወቃቀስ አቁመን እንተጋገዝ። ላልይበላን ብቻ ሳይሆን ብዙ ሺህ አደጋ ውስጥ ያሉ ቅርሶችን የማዳን፣ የመጠበቅና ለቀጣይ ትውልድ የማሻገር ዕዳ አለብን። መንግሥትም ሕዝብም እኩል ዕዳ አለበት። በተናጠል እንደማይሳካ ማመንና በጋራ መሥራት ብቻ ያሻግረናል። የችግሩን ውስብስብነት መረዳትና ለመፍትሔው የድርሻን ማዋጣት የሁሉም እንጅ የአንዱ ብቻ ሊሆን አይችልምና።
… ይህን ስል የአንበሳው ድርሻ የመንግሥት መሆኑን በመዘንጋት አይደለም። በተለይ በክልሉ መንግሥት ባህልና ቱሪዝም በኩል ከዚህ የሚበልጥ ሥራ የለንም። አሁን ላይ ከቁጭት ባለፈ ጥሩ መነሳሳት አለ። ቅርሶችን ለማዳን ብዙ ጅምር እንቅስቃሴዎች አሉ። ከረጅ ድርጅቶች ብቻ በመጠበቅ ወይም ውስን የመንግሥት በጀትን ብቻ በማሰብ የሚሠራ ሥራ ግን የትም እንደማያደርስ ታምኖበታል። እናም ሌላ አማራጮችን ለመተግበር ሕጋዊ አካሄድ ተጀምሯል። ለምሳሌ በባህልና ቱሪዝም ቢሮ ውስጥ የቅርስ ፈንድ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል። ይህን በቱሪዝም ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሀብቶችና ኩሁሉም ዜጋ የሚጠበቀውን እገዛ በሕጋዊና እውቅና ባለው አግባብ አደራጅቶ ለመምራት ነው። ይህም አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያስኬድ ነው። ለዚህ በጎ ዓላማ ከሁሉም ቀና ትብብር እንጠብቃለን። ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተጀምሯል። እስካሁን ተስፋ ሰጭ ነገር አለ። ግን…. ያው የበለጠ እንሄድበታለን። በእኛ በኩል ከዚህ በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ የለንም። ቁርጠኝነቱ አለን።
(ስለዚህ የቅርስ ፈንድ ጉዳይ በቅርቡ በስፋት እመለስበታለሁ።)
…
ቅርስ ሲፈርስና ይዘቱን ሲያጣ እንደማየት የሚያም ነገር የለም። ብዙ ያበግናል። ያናድዳል። ብዙም ያስብላል። ግን ከመብገን ባሻገር የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን። ቅርሶች የሁላችንም ውድ ሀብቶች ናቸው። ለማንም በተለየ የምንተዋቸው አይደሉም። የቅርሶቻችን ጉዳት የምር የሚያመን ከሆነ ለመፍትሔውም የምር ልንሠራ እንጅ ባዶ ቁጭት ብቻ እየገለጽን የምንቀመጥ አንሁን። ሁላችንም የምንፈተንበት ታሪካዊ ዘመን ላይ ነን። የማንነታችን መገለጫዎችን ረስተን የምንኮፈስበት ማንነት አይኖርም።