ኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቄ የቅንጦት ሳይሆን፣ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው አለች
ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያ የሆነችውን ሳተላይት ከቻይና የሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ ዛሬ ማለዳ ወደ ህዋ ልካለች። ሳተላይቷ ለግብርና፣ ለማዕድን፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለአየር ንብረት ጥበቃና ለመልከዓ ምድር ጥናት የመረጃ አገልግሎትን ትሰጣለች ነው የተባለው።
Ethiopian Remote Sensing Satellite – 01 (ETRSS – 01) የተሰኘችው ሳተላይት ሙሉ ወጪዋ በቻይና መንግሥት ተሸፍኖ የተገነባች ሲሆን ፤ በግንባታው ሂደትም በርካታ ኢትዮጵያውያን ባለሞያዎች ከቻይና አጋሮቻቸው ጎን ተሰልፈው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ተነግሯል፡፡
ከቻይና 6 ሚሊየን ዶላር ተለግሶ የተሠራችው ይህቺ ሳተላይት በአጠቃላይ 210 ሚሊየን እንደፈጀች ተነግሯል።የሳተላይቷ የመረጃ መቀበያ እንጦጦ ላይ ተሠርቷል:: ከማምጠቅ ሥራው ጀምሮ ቁጥጥሩ ሙሉ ለሙሉ እንጦጦ ላይ በኢትዮጵያውያን የህዋ ዘርፍ ባለሞያዎች ይከናወናል። ይህ ሳተላየት የማምጠቅ ሥራ ከተለያዩ አካላት 10 ሚሊየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማግኘቱ የተነገረ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥትም ተጨማሪ በጀት መመደቡ ታውቋል።
ቻይናውያን ኢንጂነሮች ኢትጵያውያንን እያሰለጠኑ ፣ሳተላይቱ ቻይና ውስጥ እንዲሁም በከፊል ኢትዮጵያ ውስጥ ተገነብቷል።70 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ሳተላይት ዛሬ ታኅሣሥ 10 ቀን 2012 ዓ. ም. ማለዳ ከቻይና መምጠቁ በቀጥታ በተላለፈ ፕሮግራም ታይቷል።
ሳተላይቱ በቻይና መንግሥት እገዛ ከቻይና ምድር ይምጠቅ እንጂ፤ “ተቆጣጣሪዋም፣ አዛዧም ኢትዮጵያ ናት” መሆኗንየኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሰለሞን በላይ ተናግረዋል።
ባለሙያዎች ሳተላይቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ይላሉ። የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር፣ የተፈጥሮ አደጋዎች ከመድረሳቸው አስቀድሞ ለመተንበይ፣ ደህንነትን ለመጠበቅ ወዘተርፈ ይውላል ብለውም ያምናሉ። በእርግጥ ብዙዎች በታዳጊ ሀገር የህዋ ጥናት አስፈላጊነቱ ላይ ጥያቄ ቢያነሱም፤ ዶ/ር ሰለሞን “ህዋ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገሮች የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ነው፤ ቅንጦት አይደለም” ሲሉ ያስረዳሉ።
የአየር ንብረት ለውጥ የመላው ዓለም ስጋት በሆነበት ዘመን፤ አንዳች ተፈጥሯዊ አደጋ ከመድረሱ በፊት አስቀድሞ መረጃ ማግኘት ብልህነት ነው። የዛፍ ቁጥር፣ የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎችም መረጃዎች ከተሰበቡ በኋላ እንደ ጎርፍ ያሉ አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት መተንበይ ይቻላል – በህዋ ምርምር::
ግብርና ቀዳሚ መተዳደሪያ በሆነባት ሀገር የቱ አካባቢ ምርታማ ነው? የአየር ንብረት ለውጥ ይኖር ይሆን? የሚሉ ጥያቄዎች በቀላሉ እንዲመለሱ የሳተላይቱ መረጃ አስፈላጊ እንደሆነም ታምኖበታል::
” አንድ የግብርና አካባቢን የሚያሳይ ፎቶግራፍ ስለ እርሻ መሬቱ፣ ስለ ውሀው፣ ስለ አፈሩ ዝርዘር መረጃ ይሰጣል። መረጃዎቹን በመጠቀም ምርታማ የሆኑ አካባቢዎችን መለየት፣ የምርት መጠንን በትክክል ማወቅም ይቻላል።ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ በመጡባት ኢትዮጵያ፤ ፋብሪካዎች የት መገንባት አለባቸው? ለሚለው ጥያቄ የሳተላይቱ መረጃ መልስ ሊሰጥ ይችላል።” ሲሉም ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ሳተላይት ወደ ህዋ በማምጠቋ የምታገኘውን ጥቅም ያስረዳሉ::
ሕዝብ መቁጠር ሲያስፈልግ ከዘልማዳዊው መንገድ ሳተላይቱን መጠቀም ይመረጣል። ትክክለኛ መረጃ ከማግኘት፣ ገንዘብና የሰው ሀይል ከማዳን አንጻርም የተሻለው አማራጭ ነው።ሳተላይቱን ደህንነትን ከመጠበቅ ጋር የሚያስተሳስሩት ባለሙያዎችም በርካታ ናቸው።
ዶ/ር ሰለሞን በበኩላቸው “በመርህ ደረጃ ህዋ የሚውለው ለሰላማዊ እንቅስቃሴ ነው” ካሉ በኋላ፤ ለጦርነት፣ ለጦር መሳሪያ ማሳለጫነት እንደማይውልም ያስረዳሉ። የ’ኢንተርናሽናል የአውተር ስፔስ’ ተቋም አባል መሆን፤ ኢትዮጵያን ከመሰል ድርጊቶች እንደሚያግዳት ይታወቃል::
ኢትዮጵያ እነዚህን መረጃዎች ሳተላይት አምጥቀው ፎቶ ከሚያስነሱ ሀገሮች ትሸምት ነበር። ዶ/ር ሰለሞን እንደሚሉት ፣ ከአምስት ዓመት በፊት በተሰራ ጥናት መሰረት ኢትዮጵያ የሳተላይት መረጃን ለመግዛት በዓመት 250 ሚሊዮን ብር ታወጣለች:: ጥናቱ ለደህንነት የሚወጣውንና ዩኒቨርስቲዎች የሚከፍሉትን አያካትትም ተብሏል። ወጪው ከዓመት ወደ ዓመት እንደሚጨምርም ያስረዳሉ። የከተሞች መስፋፋት፣ ኢንቨስትመንቶች እየጨመሩ ሲሄዱም በዛው መጠን የመረጃው አስፈላጊነት ይንራል። የሚወጣው ገንዘብም እንዲሁ። ሳተላይት ማምጠቅ እነዚህን ወጪዎች እንደሚቀንስ ነው እየተነገረ ያለው።
አፍሪካ ውስጥ መሰል ሳተላይት ለሌላቸው ሀገሮች መረጃ መሸጥም ይቻላል። የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተሩ “ትልቅ ቢዝነስ ነው” በማለትም ጅምር እንቅስቃሴውን ይገልጹታል። “ሲያስፈልግ መረጃ እንሸጣለን። ከኛ የላቀ ቴክኖሎጂ ካላቸው ሀገሮች ጋር መረጃ መለዋወጥም ይቻላል፤ ዓለም በህዋ ጥናት ቴክኖሎጂ እየመጠቀ ሄዷል። ኢትዮጵያ ከተቀረው ዓለም አንጻር ጀማሪ ናት። አፍሪካ ውስጥ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አልጄሪያና ግብጽ ጥሩ ስም አላቸው። ” ይላሉ ::
ኢትዮጵያ “ህዋ ለልማት” የሚል የምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች ትብብር ቢሮ አቋቁማ አበረታች እንቅስቃሴ ማድረጓ ተጠቃሽ ስኬት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ2030 ይደረስባቸዋል ብሎ ካስቀመጣው ግቦች አብዛኞቹ የህዋ ቴክኖሎጂን ያማከሉ መሆናቸው፤ ዘርፉን ችላ ማለት እንደማያዋጣ ያሳያል።
ዶ/ር ሰለሞንም የመሬት ምልከታ ሳተላይት ማምጠቅ ኢትዮጵያ በህዋ ሳይንስ ዘርፍ እንቅስቃሴ እያደረገች ስለመሆኑ ለዓለም መልዕክት ማስተላለፊያ መንገድ እንደሚሆን ዕምነታቸው ነው።።
ዛሬ በወላይታ ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ፤ የዎብን አመራሮችም ታስረዋል
የወላይታ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄን ካቀረበበት አንደኛ ዓመት ጋር በተያያዘ በነበረ እንቅስቃሴ ምክንያት በወላይታ ሶዶ ከተማ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ግለሰቦች መለቀቃቸው ታወቀ።
ከተከሰተው ችግርና አደጋ አዘል እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በጸጥታ ኃይሎች ተይዘው ከነበሩት ሰዎች መካከልም የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ወብን) ጽሕፈት ቤት ሓላፊ ከሆኑት ከአቶ አንዱለም ታደሰ በስተቀር ሁሉም መለቀቃቸው ተረጋግጧል።
የወላይታ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ወሕዴግ) የወጣቶች ክንፍ አመራር አቶ አሸናፊ ከበደ ፤ ዛሬ ማለዳ የወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄው አንድ ዓመት መሙላቱን በማስመልከት ሰልፍ ለማካሄድ ከወጣቶች ጋር ተሰብስበው ባሉበት በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር ገልጸዋል:: ከእርሳቸው በተጨማሪ የወሕዴግ አባል የሆኑት አቶ ወርቅነህ ገበየሁም ሊያካሂዱት የነበረው ሰልፍ ያልተፈቀደ ነው በሚል መያዛቸውን ጠቁመው፤ ከተያዙ በኋላም ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዳልተወሰዱ ይፋ አድርገዋል።
“ምንም ዓይነት የኤሌክትሮኒክስ ግንኙነት እንዳናደርግ ታግደን እንድንቆይ ከተደረግን በኋላ በመነጋገር ተለቀናል” ሲሉም የነበረውን ሂደት በግልጽ አስቀምጠዋል።
የወላይታ ሶዶ ከተማ የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ነጋ አንጎሬ የወላይታ ሕዝብ የክልል ጥያቄ ዛሬ ታኅሣስ 10 ቀን 2012 ዓመት መሙላቱን በማስመልከት ሰልፍ ማድረጋቸውንገልፀዋል። የከተማው አስተዳደርም የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች የሀገር ሸማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ነጋዴዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች በወላይታ ሶዶ ከተማ በሚገኘው ጉተራ አዳራሽ ውይይት ማድረጋቸውን በፌስ ቡክ ገጹ ላይ አስነብቧል።
አቶ አሸናፊ የክልልነት ጥያቄያቸውን ካቀረቡ ዓመት እንደሞላቸው በማስታወስ “በሕጉ መሰረት ከዛሬ ጀምሮ በደቡብ ክልል ስር አይደለንም” ያሉ ሲሆን፣ የወላይታ ሶዶ ከተማ ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ ከማንኛውም እንቅስቃሴ ታቅባ ፀጥ ረጭ ብላ መዋሏን ነዋሪዎች ይናገራሉ። በከተማዋ የትራንስፖርትም ሆነ የማኅበራዊ አገልግሎት አለመኖሩን ያመላከቱት ነዋሪዎች የመከላከያ ሠራዊት አባላት ግን በከፍተኛ ቁጥር ተሰማርተው እንደሚታዩ አረጋግጠዋል::በወላይታ ዞን ስር የሚገኙ የተለያዩ ከተሞች፤ ዞኑ በክልል የመደራጀቱን ጥያቄ በመደገፍ ሰልፍ አድርገዋል። ክንዶ ድዳዬ፣ ቦዲቲ፣ ቦሎሶ ቦምቤ፣ ሆብቻና አበላ አበያ ሰልፉ ከተደረገባቸው ከተሞች መካከል ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው።
ሕወሓትና ፌደራል መንግሥት ወደለየለት ግጭት እያመሩ መሆናቸውን ባለሥልጠኑ አረጋገጡ
የትግራይ ክልል በተደጋጋሚ እያጋጠመኝ ነው ባለው ችግር ሳቢያ ከፌደራል መንግሥት ጋር ያለው ግንኙነት በጣም አሳሳቢ ወደ ሆነ ደረጃ እየደረሰ መምጣቱን የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ዶ/ር አብረሃም ተከስተ ገለፁ ።
ከትናንት በስቲያ ለሥራ ጉብኝት ወደ ትግራይ ክልል ጉዞ ሊያደርጉ የነበሩ የቻይና የሻንሺ ግዛት ልዑካን ‘በፌደራል መንግሥት ትዕዛዝ’ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይጓዙ ተደርጓል ሲል የትግራይ ክልል መንግሥት ቅሬታውን ካሰማ በኋላ ነው ባለሥልጣኑ ከላይ የሰፈረውን አስተያየት ለቢቢሲ የተናገሩት።
በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የትግራይ ክልል የንግድ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሓላፊ የሆኑት ዶ/ር አብረሃም ተከስተ ፤ በቁጥር ስድስት የሆኑት አባላቱ ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ ከመጡባቸው ምክንያቶች አንዱ ከትግራይ ክልል ጋር በልማት እና አቅም ግንባታ ዙሪያ ለመተባባር የሚያስችል ስምምነት ለመፈራረም እና ጉብኝት ለማድረግ ነበረ ካሉ በኋላ ፤ልዑካኑ ከትናንት በስቲያ ከፌደራል መንግሥት ጋር የነበራቸውን የሥራ ቆይታ አጠናቀው አመሻሹን ወደ መቀለ ለመብረርአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ቢገኙም ፣ ወደ ትግራይ መጓዝ እንደማይችሉ ተነግሯቸው ከአውሮፕላኑ እንዲወርዱ ተደርገዋል ሲሉ ገልጸዋል።
“የምቀበላቸው እኔ ነበርኩ፣ አውሮፕላኑ በሰዓቱ ቢያርፍም እንግዶቹን ይዞ አልመጣም” ይህንንም ተከትሎ ባደረኩት ማጣራት ”የሚያስፈልገውን ጨርሰው አውሮፕላን ውስጥ ከገቡ በኋላ መሄድ እንደማይችሉ እንደተነገራቸው ነው የሰማነው” ይላሉ ዶ/ር አብረሃም። እንግዶቹ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይጓዙ የሚከለክል ምንም ምክንያት የለም ያሉት ዶ/ር አብረሃም፤ የግዛቷ አስተዳዳሪዎች ወደ ትግራይ እንዳይሄዱ መደረጋቸውን ”ተቀባይነት የሌለው ነው” ሲሉ አጣጥለዋል። ከዚህ ቀደምም በፌደራል መንግሥት ባለሃብቶች እና የተቋማት ሓላፊዎች ወደ ትግራይ እንዳይጓዙ ጫና እንደሚደረግም ጠቁመዋል የክልሉ ከፍተኛ ባለሤልጣን::
“ወደ ትግራይ ሄዳችሁ ተብለው ማስፈራሪያ የሚደርስባቸው ምሁራን፣ ተቋማት፣ ባለሃብቶች እና የውጪ ሃገር ዜጎች አሉ። ይህንንም የዚያ አካል አድርጌ ነው የማየው” የሚሉት ዶ/ር አብርሃም ፤ “በትግራይ ህዝብ ላይ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ይደረጋሉ። በትግራይ ህዝብ ላይም ውሸትም ጭምር በመጠቀም ሥነ-ልቦናዊ ጫና ለማሳደር ያልተደረገ ነገር የለም” ሲሉ ተደምጠዋል።
ወደ ትግራይ ጉዞ ሊያደርጉ የነበረው የሻንሺ ግዛት ልዑክ በግዛቷ ምክትል አስተዳዳሪ የሚመራ መሆኑን አስታውሰው፤ ልዑካኑ ወደ መቀለ መሄድ ባለመቻላቸው እሳቸው አዲስ አበባ መጥተው በግብርና፣ በኢንቨስትመንት፣ በማዕድን እና ቱሪዝም መስኮች የመግባቢያ ሰነድ አዲስ አበባ ላይ መፈራረማቸውንም አስረድተዋል።
ዶ/ር አብረሃም በትግራይ ክልል እና በፌደራል መንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት “በጣም አሳሳቢ” ሲሉ የገለጹት ሲሆን፤ ግነኙነቱን ለማሻሻል የትግራይ ክልል ለመወያየት ሁልግዜም ቢሆን ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል። “ሁኔታዎች በጣም እየተወሳሰቡ እየሄዱ ነው። የፌደራል መንግሥቱ ይህን ቆም ብሎ ማጤን አለበት። እንደ ሃገር እንድንቆም ያስቻለን ሥርዓት አለ፣ ይህ ሥርዓት መከበር አለበት። ያጎደልነው ነገር ካለ መጠየቅ አለብን። ሌላውም እንደዛው” ሲሉ የልዮነቱን ምንጭ ለማለሳለስ ሞክረዋል
በትግራይ እና በፌደራሉ መንግሥት መካከል የተፈጠረውን ልዩነት በወዳጅነት እና በመቀራረብ ለመፍታት ለምን እንዳልተቻለ ከቢቢሲ ዘጋቢ ለቀረበላቸው ጥያቄም ፤”ከአንዳንዶቹ ጋር ጓደኝነታችን እንዳለ ነው። ስንገናኝ የልብ የልባችንን እናወጋለን ፤ ይሁን እንጂ መሠረታዊ የሆነ የፖለቲካ ልዩነት ተፈጥሯል” የሚል ግንኙነትና ወዳጅነቱ የይስሙላ መሆኑን ያረጋገጠ ምላሽ ሰጥተዋል።
ጀርመናዊው ግለሰብ በአ/አ ልደታ ፍርድ ቤት በ10 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጡ
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት በትውልድ ጋናዊ በዜግነት ጀርመናዊ የሆኑት ግለሰብ ሐሰተኛ ሰነድ ከውጪ አገር በማስገባት እና በመጠቀማቸው ምክንያት በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ናቸው በማለት የዐስር ዓመት ጽኑ እስራት ፈርዶባቸዋል::
ከአንድ ዓመት በፊት የፓን አፍሪካ ካውንስል ተወካይ እንደሆኑና የአፍሪካ ኅብረት ቅርንጫፍ ባንክን በአዲስ አበባ ለመክፈት ነው የመጣሁት በሚል ከዛፍፋርማሲትውካልስ ባለ ሰባት ፎቅ ህንፃ ተከራይተው ነበር:: በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 የሚገኘውን ይህንን ህንፃ በወር 55 ሺኅ ዶላር እከራያለሁ፣ በሚል ወደ ድርጅቱ ባለቤት የቀረቡት ፍራንክሊን “ለ30 ዓመት” የሚል አማላይ ውል መጠቀማቸውን የዐቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል::
በደላላ አማካኝነት ባለ ሰባት ወለል ህንፃቸውን ያከራዮት የዛፍ ፋርማሲቲካልስ ዋና ሥራ አስኪያጅም ለሰባት ወር የኪራይ ገንዘባቸውን ቢጠብቁ የውሃ ሽታ በመሆኑ በጥርጣሬ ለፌደራል ፖሊስ ማመልከት ግድ ሆንባቸዋል:: ፖሊስም ባደረገው ማጣራት ለዛፍ ፋርማሲውቲካልስ ቀርቦ የነበረው 33 ሺኅ ዶላር የሚያወጣ የባንክ ማስተማመኛ በታንዛኒያ ተሠርቶ የመጣ የሐሰት ሰነድ መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል::
ጀርመናዊው ግለሰብ ህንፃውን ከተከራዮና ፍቃድ ካገኙ በኋላ ከኢትዮጵያ ባንኮች ገንዘብ የመዝረፍ ሐሳብ ነበራቸው ሲል ሌሎች በተከሳሽ ቤት የተገኙ ሰነዶችን በመጥቀስ ክስ መሥርቷል:: ተከሳሽን የዋስ መብት የከለከለው ፍርድ ቤቱ የሰጡትን የእምነት ክህደት ቃላቸውንና የቀረበባቸውን ማስረጃ በማረፊያ ቤት በቆዮበት አንድ ዓመት ተከታትሎ ብይን ሰጥቷል::
በዚህም መሠረት ግለሰቡ በዐስር ዓመት ጽኑ እስራትና በአምስት መቶ ብር የገንዘብ መቀጮ ቀጥቷቸዋል:: ተጠርጣሪው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሌላ መዝገብ ተጨማሪ ክስ እየተከታተሉ እንደሆነም ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል::
የአዋሽ- ወልዲያ- የባቡር ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲቀርብለት ከበላይ ትዕዛዝ ተሰጠ
ሙሉ ለሙሉ ሥራው ቢጠናቀቅም የኤሌክትሪክ ኃይል ባለማግኘቱ ምክንያት ሥራ መጀመር ያልቻለው የአዋሽ- ወልዲያ-ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ኃይል እንዲቀርብለት ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አዘዘ::
ሰሞኑን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተሳተፉበትና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በዝግ በተካሄደው የፕሮጀክቱ ስብሰባ ላይ ነው ቀጠን ያለው ውሳኔ የተላለፈው:: ውሳኔው በፍጥነት እንዲፈጸምም ማስጠንቀቂያ አዘል ደብዳቤ ለሚመለከተው ተቋም መጻፉንም ከታማኝ ምንጮቻችን ማረጋገጥ ችለናል::
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሠረተ ልማት አማካሪ ዣንጥራር አባይ የመሩት እና የትራንስፖርት ሚኒስቴር ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የተሳተፉበት ስብሰባ ሲያወዛግብ የቆየውን የገንዘብ ምንጭ የባቡር ኮርፖሬሽን እንዲሸፍን ከስምምነት ላይ ተደርሶበታል::
በውሳኔው የተደሰቱት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ ከስብሰባው በኋላ ” እስከ አሁን ምንም አይነት ውዝግብ አልነበረም ፤ ለዚህ ሥራ የተያዘ በጀት ስላልነበረ ክፍተቱ ተፈጥሯል:: አሁን ግን ወጪው በኮርፖሬሽኑ ተሸፍኖ ኃይል እንዲቀርብ ተወስኗል” ሲሉ ለመገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል::
ይህ ፕሮጀክት ሥራው ቢጠናቀቅም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ባለማግኘቱ አገልግሎት ለመስጠት እንዳልቻለ ኢትዮጵያ ነገ ቀደም ሲል ምንጮቹን በመጥቀስ መረጃውን ለሕዝብ ማድረሱ የሚዘነጋ አይደለም::