ነሐሴ 16 ቀን 2011 ዓ·ም
ዓለምን ያስደመመ የሥልጣኔ ፋና ወጊ የሆኑ የቁሳዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ባለቤት የሆነችው ሀገራችን የብዙ ሺህ ዓመታት ዝክረ-ታሪክም ለእኛ ለዜጎቿ ታላቅ ኩራት ነው፡፡ በርካታ የታሪክ ቅርሶችዋ የሥልጣኔን የትየሌለነትን አጉልተው የሚዘክሩ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ብሄረሰቦቿ በፈጠሩት ማኅበራዊ መስተጋብር የተዋበች፣ የተለያዩ ሃይማኖች በመቻቻል፣ በመተሳሰብ ተደጋግፈው ኩራት የሆኗት ታሪካዊት ሀገር ናት፡፡ ዜጎቿ የባህል፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ እና የዘር ወዘተ… ልዩነቶቻቸው ለኢትዮጵያዊነታቸው ልዩ ውበት እንጂ ጋሬጣ ሆኖባቸው አያውቅም ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊያን የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ከውጭ ወራሪ ኃይል ለመከላከል የውስጥ ልዩነቶቻቸውን አቻችለው በአንድ ረድፍ ስለመሰለፋቸው በታሪክ ድርሳናት ተከትበው የሚገኙ ናቸው፡፡ ይህ አኩሪ የሆነ ታሪካቸው ሳይሸረሸር ለቀጣዩ ትውልድ ይተላለፍ ዘንድ ዛሬ ላይ እየታዩ ያሉ ችግሮችን ማረቅ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች እርስበእርስ በመደጋገፍ እና በመፈቃቀር የሚኖሩባት ሀገር መሆንዋ እሙን ነው፡፡ ክርስቲያኖች ከሙስሊሞች ሙስሊሞች ከክርስቲያኖች ጎን በመቆም ሃዘንና ደስታን በጋራ የሚጋሩባት ምድር እንጂ እርስ በእርስ የሚቆራቆሱባት አገር አይደለችም፡፡ አንዱ ሃይማኖት ለሌላኛው የቅርብ አጋርና ተቆርቋሪ በመሆን ኢትዮጵያዊነትን ያደምቃሉ እንጂ በጠላትነት አይፈራረጁም፡፡
ይሁን እንጂ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በነበረው የፖለቲካ ትኩሳት ዘርና ቋንቋን ተገን አድርጎ በዜጎች መሀከል የተለኮሰው እሳት ወላፈኑ ተፋቅረውና ተከባብረው ይኖሩ የነበሩ ሃይማኖቶችን ማወኩን ተመልክተናል፡፡ በአዲስ አበባ፣ ሶማሌ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብና በአማራ ክልሎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣ መስጂዶችና ፀሎት ቤቶች ላይ የደረሱ ጥቃቶች የታሪካችን ማፈሪያ መሆናቸውን ልናስተውል ይገባል፡፡ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ የሚፈጠረው ቀውስ መብረጃ አይኖረውም፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ይህንን አገራዊ እየሆነ የመጣውን ችግር ከወዲሁ ማስቆም ይቻል ዘንድ የበኩሉን ያላሰለሰ ጥረት ለማድረግ ቁርጠኘነቱን እየገለፀ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ ያስተላልፋል፡-
1. ከተለያዩ ፖለቲካዊና የማንነት ጥያቄዎች ጋር በተያያዙ ግጭቶች በተነሱ ቁጥር በሃይማኖት ተቋማት ማለትም በቤተክርስቲያን፣ በመስጂድ እና በፀሎት ቤቶች ላይ የሚሰነዘሩትን ጥቃቶች አጥብቀን እያወገዝን መንግሥት የድርጊቱን ፈፃሚዎች እየተከታተለ ለፍርድ እንዲያቀርብ እና የችግሩን ምንጭ እንዲያደርቅ ጥሪ እናስተላፋለን፤
2. ከ95% በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታይ በሆነባትና እነኚህም ተቋማት ፍቅርና ሰላምን በሚሰብኩባት ምድር በብሔር እና በቋንቋ ሰበብ የሚነሱ ግጭቶችን ወደ ሃይማኖት ለማስጠጋት መሞከር ሀገርን ለማፈራረስ የሚደረግ ሙከራ ስለሆነ አጥብቀን እናወግዛለን፤
3. የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎች በመንፈሳዊ ሥርዓት ሰላምን የሚሰብኩ፣ ቅራኔዎችን የሚፈቱ፣ የተጣላን የሚያስታርቁ፣ አጥፊን የሚገስፁ መሆን ሲገባቸው በተለያዩ ጊዜያት የእምነት ተቋሞቹን ከጥቃት በመከላከል አጀንዳ ተጠምደው የቆሙለትን መንፈሳዊ ተግባር ማከናወን አለመቻላቸው ተገቢ አለመሆኑን እንገልፃለን፤
4. በተለያዩ ጊዜያት በተፈጠሩ ግጭቶች ጥቃት የደረሰባቸውን እና የፈረሱ ቤተ-እምነቶችን መልሶ የመገንባት ሥራ ላይ መንግሥት ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርግ፣ በየአካባቢው የሚገኘው ማኅበረሰብም የእምነት ልዩነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ቤተ-እምነቶችን በጋራ ከጥቃት እንዲከላከል መልሶ ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴም የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክትና ተከባብሮ የመኖር ዘመናት እሴቱን እንዲያጠናክር ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
በመጨረሻም የሃይማኖት ተቋማትና መንፈሳዊ አባቶች ከምንም በላይ የሀገርን ሰላምና የሕዝብን መረጋጋት በሚያሰፍኑ ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ተግባራት ላይ ትኩረት በመስጠት ለቀጣይ ትወልድ የምትሻገር የጋራ አገር እንድትኖረን ትኩረት ሰጥተው እንዲንቀሳቀሱ የአክብሮት ጥያችንን እናስተላልፋለን፡፡