የለውጡ መሐንዲሶች ለማና ዐቢይ በብልፅግና ምሥረታ ላይ መስማማታቸውን ኢሕአዴግ ገለፀ
ከሳምንታት በፊት በገዢው ፓርቲ ውህደትና እየተከተለ ባለው አካሄድ ላይ እንደማይስማሙ በመግለጽ ልዩነታቸውን ይፋ ያደረጉት የለውጡ ፊታውራሪ ኦቦ ለማ መገርሳ የተፈጠረውን ክፍተት በማጥበብ ፣ ከአዲሱ ፓርቲ (ብልፅግና) ጋር አብረው ለውጡን ለማስቀጠል ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ተነገረ።
በመከላከያ ሚኒስትሩ በአቶ ለማና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መካከል ጉልህ ልዩነት እንደተፈጠረ ተደርጎ የተነገረው ትክክል አይደለም ያለው የኢሕአዴግ ይፋዊ ድህረ ገፅ ፤ “ልዩነቱ የግል ሐሳብን በነፃነት ማራመድን የሚያመላክት ዴሞክራሲያዊ መብት የተንፀባረቀበት እንጂ የተካረረ የግለሰቦች ፀብ አልነበረም” ካለ በኋላ ፣ የተከሰተው ለውጡ ዘላቂነት እንዲኖረው ለማድረግ በሚመራበት መንገድ ላይ የተወሰነ “የአካሄድ ልዩነት” እንጂ ሲነገር እንደነበረው የጎላ ችግር አይደለም ሲል አስነብቧል።
ጉዳዮን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ የሆኑት ኢንጂነር ታከለ ኡማ በትዊተር ገጻቸው ላይ አጭር መልዕክት አስፍረዋል::በተመሳሳይ ትናንት አመሻሽ ላይም የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን) ዝርዝር የሌለው አጭር ዜና አውጥቶ እንደነበርም ታዝበናል።
ሁለቱ ከፍተኛ የመንግሥትና ፓርቲው አመራሮች በተፈጠረው ልዩነት ላይ ቁጭ ብለው መወያየታቸውንና ተፈጥሮ የነበረውን የሐሳብ ልዩነት ላይ መግባባት እንደቻሉና አብረው ለመሥራት መስማማታቸው እየተነገረ ነው። መሪዎቹ የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ በጋራ በመሥራት እውን ለማድረግ ከመግባባት ላይ መድረሳቸውን ፓርቲው በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ አስታውቋል።
የመደመር እሳቤን መሠረት አድርጎ ከህወሓት በስተቀር ቀሪዎቹን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችንና አጋር የተባሉትን ፓርቲዎች በማቀፍ ፣ የተመሰረተውን የብልጽግና ፓርቲ ይፋ መሆን ተከትሎ አቶ ለማ መገርሳ ልዩነት እንዳላቸው በተናገሩበት ጊዜ ግራ መጋባት በብዙዎች ዘንድ መፈጠሩ አይዘነጋም።
አቶ ለማ በፓርቲዎቹ ውህደት ላይ ያላቸውን ጥያቄና የተሄደበት መንገድን በማንሳት የተለየ አቋም ከማንጸባረቃቸው ባሻገር ተሰሚነት እንዳልነበራቸው መግለጻቸውን ተከትሎ ፤ ከተለያዩ ወገኖች በፓርቲው ውስጥ ስለሚኖራቸው ቀጣይ ዕጣ ፈንታና ይህ ልዩነትም የሚያስከትለውን ውጤት በተመለከተ መላምቶች ሲሰነዘሩም ታይቷል።
አሁን ከፓርቲው በኩል የሚወጣ መረጃ የሚያመለክተው ግን ፣ አቶ ለማ በልዩነታቸው ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተወያይተው መግባባት ላይ እንደደረሱና የተጀመረውን ለውጥ በጋራ ለማስቀጠል እንደተስማሙ ያረጋግጣል።
በሞጣ ከተማ የቤተ እምነቶች ጥቃት የተጠረጠሩ ሰዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ
በምሥራቅ ጎጃም ፣ ሞጣ ከተማ ቤተ እምነቶች ላይ ጥቃት አድርሰዋል የተባሉ 22 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑ ታወቀ።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ ሓላፊ የሆኑት ዋና ኢንስፔክተር አያልነህ ተስፋዬ በጥቃቱ የተጠረጠሩ እስካሁን ድረስ 22 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ፣ ማኅበረሰቡ ጥፋተኞችን እየጠቆመ በመሆኑ ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ገልፀው ፤ በፖሊስ የተያዙት ተጠርጣሪዎችም እንደተያዙበት ቅደም ተከተል ወደ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መደረጉንም አስታውቀዋል።
የተጠርጣሪዎቹ ቁጥርም ሊጨምር ስለሚችል ፣ አዳዲስ ሰዎች በቁጥጥር ስር የሚውሉ ከሆነም ምርመራ በማድረግና ሕጉ በሚያዘው መሠረት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ይደረጋልም ብለዋል። በሞጣ ከተማ ሁኔታዎች መረጋጋታቸውን የተናገሩት ዋና ኢንስፔክተር አያልነህ፤ በከተማዋም ያለው ጥበቃም መጠናከሩን ተናግረዋል።
የክልሉ ፖሊስ ከልዩ ኃይል ጋር በመሆን የሞጣ ከተማን ወደነበረችበት መረጋጋት ለመመለስ እየተሠራ ነው ያሉት ኢንስፔክተሩ፤ በተፈጸመው ወንጀል ዙሪያ የምርመራ ሥራውም፣ የማረጋጋት ሥራውም ሆነ ሕዝብ ለሕዝብ የማገናኘት ሥራውን ጎን ለጎን እየተካሄዱ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ትምህርት ቤቶች፣ የመንግሥት ቢሮዎች ተከፍተዋል በማለት ፣ ምናልባት የተቃጠሉ ሱቆች አካባቢ ያሉት ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ወደ መደበኛው ሕይወቱ ተመልሷል በማለትም በከተማዋ ያለውን መረጋጋት ጠቁመዋል።
ችግሩ ከመከሰቱ ቀደም ብሎ አንዳንድ ግለሰቦች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በከተማዋ ግጭት ሊቀሰቀስ እንደሚችል ለከተማው ፖሊስ ጥቆማ ቢያቀርቡም ፖሊስ ጥቆማውን ቸል በማለቱ ጥፋት መድረሱን በተመለከተ ለቀረበው ወቀሳም፤ ዋና ኢንስፔክተር አያልነህ “ይህንን በማኅበራዊ ሚዲያ የሚመላለሱ መረጃዎችን እኛም አይተናቸዋል፤ ነገር ግን ምንም በጽሑፍም ሆነ በቃል ተደራጅቶ የቀረበ ጥቆማና መረጃ አልነበረም” ሲሉ አጣጥለዋል።
በፈረንጆቹ 2020 መታየት ከሚገባቸው የዓለም ከተሞች አዲስ አበባ በቀዳሚነት ተመረጠች
ዓለም ላይ ታዋቂ የጉዞ መረጃ አውጪ ድረ ገፅ የሆነው ትራቭል ኤንድ ሌይዠር የተሰኘው ድረ ገፅ በፈረንጆቹ 2020 ሊጎበኙ ከሚገባቸው 50 የዓለማችን ስፍራዎች ውስጥ አዲስ አበባን አንደኛ አድርጎ አስቀምጧታል::
ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ በቀደመው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ሲሰጠው የቆየውን ብሔራዊ ቤተ መንግሥት አሳድሰው በቅርቡ ለሕዝብ ክፍት ያደረጉት አንድነት ፓርክ የከተማዋ አዲስ ገፅታ መሆኑን ድረ ገፁ አስነብቧል::
በተጨማሪም ጎብኚዎች የማስፋፊያ ግንባታ የተደረገለት ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የዓለም ዐቀፍ ተጓዦችን በመልካም ሁኔታ አንዲስተናገዱ ከማድረጉ ባሻገር ፤ በከተማዋ ስላለው ለውጥ መመልከት የሚያስችል አቅም እንዳለው ድረ ገፁ ጠቁሟል::
ድረ ገፁ እነዚህን የዓለማችን ሊጎበኙ የሚገባቸው ስፍራዎች ብሎ የዘረዘራቸውን አካባቢዎቼ ሲመርጥ የተለያዮ ጽሑፎችን የቱሪዝም ስታስቲክሶችን ዋና ዋና ክስተቶችን አዳዲስ የበረራ መንገድ ሰንጠረዦችን እና የሆቴል አገልግሎትን በማጥናት መሆኑን ጠቁሟል::
በአዲስ አበባ ደብዛው የጠፋው ኤርትራዊ ምርመራ እንዲጠናቀቅ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አዘዘ
ከሁለት ዓመታት በፊት ከስዊድን አዲስ አበባ በገባ በሁለት ሳምንቱ ደብዛው ጠፋ የተባለው ኤርትራዊ ስዊድናዊው ኤርሚያስ ተክኤን አስመልክቶ ፣ የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የምርመራው ጉዳይ በተቻለ ፍጥነት እንዲጠናቀቅ መመሪያ መስጠቱን በስዊድን የኤርሚያስ ጠበቃ የሆኑት አቶ ሙሴ ኤፍሬም አስታወቁ።
ጠቅላይ ዐቃቤ መመሪያውን ያስተላለፈው ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ምክትል ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት በላከው ደብዳቤ መሆኑም ታውቋል።
ሕዳር 3/2012 ዓ.ም የተፃፈውን ደብዳቤ ዋቢ ያደረገውና የኤርትራዊውን ጠበቃ ያነጋገረው ቢቢሲ ፤ ምርመራው ተመዝግቦ በሂደት ላይ የሚገኝ ከሆነ ከሚመለከታቸው የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች በጋራ በመሆን የተጀመረው ምርመራ በተቻለ ፍጥነት የሚጠናቀቅበትን እንዲሁም ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች ተጠያቂ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲከናወን መታዘዙን ዘግቧል።
አቶ ሙሴ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ የሰጠው መመሪያ አርብ ዕለት፣ ታህሳስ 10/2012 ዓ.ም እንደደረሳቸው ገልጸው፤ ይህም ሁኔታ ትልቅ ተስፋ እንደሰጣቸው ገልፀዋል:: “እስካሁን ባለው የአገሪቷን ህግ ተከትለን ስንሄድ ነበር ፤ ይሁን እንጂ ከአሁን በኋላ የምናየው ለውጥ ከሌለ ትዕግስታችን በማለቁ ወደ አፍሪካ ህብረት የሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን አቤቱታ እናቀርባለን” ሲሉም ቀጣይ ዕቅዳቸውን ተናግረዋል።
የኤርሚያስ ተኪኤ ቤተሰቦችና ጠበቆች፤ የኢትዮጵያ ፖሊስ ለዚህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት በመስጠት የተሻለ የምርመራ እውቀትና ክህሎት ያላቸው የመርማሪዎች ቡድን በማደራጀት ምርመራውን በጥልቀትና በፍጥነት እንዲካሄድ የሥራ መመሪያ ይሰጥልን ብለው በጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም አመልክተው እንደነበር ይታወሳል።
ኤርሚያስ አዲስ አበባ የገባው ሚያዝያ 26፣ 2010 ዓ.ም ሲሆን፤ አዲስ አበባ በሚገኘው “አርክ ሆቴል” እስከ ግንቦት 13 ቀን 2010 ዓ.ም መቆየቱ ተረጋግጧል:: ግንቦት 13 ቀን 2010 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ አራት ሰዓት ሲሆን ፣ ዳህላክ (ኤፍሬም) የተባለ ግለሰብ ጠርቶት በመኪና ከወሰደው በኋላ ፣ ደብዛው መጥፋቱን ቤተሰቡና ጠበቆቹ ማሳወቃቸውን የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ደብዳቤ በግልፅ ያሳያል።
ጉዳዩንም ለማጣራት ወዳረፈበት ሆቴል መሄዳቸውን ጠቅሰው ፣ ከሆቴሉ ያገኙትንም መረጃ ይዘው ሰኔ 22፣ 2010 ዓ.ም፤ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ክፍል ምርመራ እንዲጣራላቸው አመልክተው፣ ምስክርነት ሰጥተው ቢመለሱም እስካሁን ድረስ ያለበትን እንደማያውቁና ደብዛው እንደጠፋ፣ ባቀረቡት አቤቱታ መግለፃቸውን የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ደብዳቤ አብራርቷል።
አስመራ ተወልዶ ያደገው ኤርሚያስ ባለትዳር ከመሆኑ ባሻገር በስዊድን አገር በስደት ከ12 ዓመታት በላይ ኖሯል።በተጠቀሰው ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦቹን ለመጠየቅ ፣ ስዊድን ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቪዛ ጠይቆ፤ ኤምባሲው በሰጠው ፍቃድ መሰረት ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ እስካሁን ድረስ የጠፋበት ደብዛ ሊገኝ አልቻለም::
በከፍተኛ ዶላር ከውጭ የሚገባው ስንዴን ለማስቀረት ታስቧል ተባለ
በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከባህር ማዶ የሚገባውን ስንዴ ለማስቀረት እየተሠራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ከ14 ሺህ ሄክታር በላይ የቆላ ስንዴ በመስኖ እየለማ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በቆላማ አካባቢዎች ስንዴን በስፋት ለማልማት በ3 ሺህ ሄክታር የዘር ብዜት እየተሠራ ነው ያሉት ሓላፊው ፤ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገባውን ስንዴ ለማስቀረት ለቆላ ስንዴ ልማት ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራልም ብለዋል።
ሚኒስትሩ በበርሃ አንበጣና ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ በምርት ብክነት ላይ የደረሰው ጉዳት የዳሰሳ ጥናት እየተሠራ እንደሆነና የጥናቱ ውጤትም ወደፊት እንደሚገለጽ አመላክተዋል።
መንግሥት የሜካናይዜሽን መሳሪያዎችን ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ፣ መወሰኑ የምርት ብክነትን ለመቀነስና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ መነሳሳትን እየፈጠረ መሆኑን እንዲሁም ፤ ዘንድሮ በዘር ከተሸፈነው 12 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ውስጥ 9 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታሩ መሰብሰቡንም ተናግረዋል።
ቀሪው ምርት በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት እንዲሰበሰብ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ መቅረቡን ግብርና ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል::
የኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ ቡድን በአስመራ ዝግጅቱን አቀረበ
በባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሠረት የተመራ የኢትዮጵያ የባህል የልዑካን ቡድን የማጠቃለያ ዝግጅቱን ትናንት በአስመራ ሲኒማ ሮማ ማቅረቡ ተነገረ።
የኤርትራ የባህል እና ስፖርት ኮሚሽነር አምባሳደር ዘመዴ ተክለ ፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሰላም እንዲሰፍን የወሰዱትን እርምጃ ተከትሎ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን በዝግጅቱ መክፈቻ ላይ መስክረዋል።
ዝግጅቱ እውን እንዲሆን የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ፣ እንዲሁም በኤርትራ በኩል ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውንም አቅርበዋል። የኢፌዴሪ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት በበኩላቸው፣ የኤርትራ የባህል ቡድን በኢትዮጵያ አራት ከተሞች የሙዚቃ ዝግጅት ማቅረቡን አስታውሰው፤የኢትዮጵያ የባህል ቡድን በኤርትራ በነበረው ቆይታ በከረን እና ምጽዋ ደማቅ ዝግጅት ያቀረበ ከማቅረቡ በተጨማሪ የተለያዩ የመስህብ ስፍራዎችን መጎብኘቱንም ገልጰዋል:: የልዑካን ቡድኑ ተልዕኮ እንዲሳካ የኤርትራ ህዝብ እና መንግስት ላደረጉት ትብብርም ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።