ተከታታይ የኢትዮጵያ መንግስታት በኤርትራ ላይ የእሽሩሩ ፖሊሲ (appeasement policy) እንደነበራቸው ይታወቃል።
ለምሳሌ ጃንሆይ ኤርትራውያንን በኢትዮጵያ የቅንጡ መደብ (privileged class) አባላት ሆነው እንዲኖሩ አስችለዋቸው ነበር። ለናሙና ያክል፣ እነ በረከት ሀ/ስላሴ በ28 እድሜው የኢትዮጵያ ጠቅላይ አቃቤ ህግ (attorney general) ነበር። ሻቢያን ተቀላቅሎ የኢትዮጵያ ጠላት ከመሆን ግን አልቀረም።
የ 90 አመት አዛውንቱ ፕሮፌሰር ለገሠ አስመሮምም ጣልያን እስከ 4ኛ ክፍል አስተምሮ አስመራ ውስጥ በዘበኛነት ሊያሰቀረው ሲል፣ ጃንሆይ ወደ አዲስ አበባ አስመጥተው በኢትዮጵያ ሀብት በሀገረ አሜሪካ ተምሮ ፕሮፌሰር ከተባለ ብዙ ትውልድ አልፏል።
ይህ የኢሳያስ አፈወርቂ አምላኪ ካድሬ የሆነው ፕሮፌሰር፣ እድሜ ልኩን ለኦሮሞ መብት ተቆርቋሪ መስሎ በኢትዮጵያ ላይ መርዝ ሲረጭ ከኖረ በኋላ፣ በቅርቡ በሰጠው ቃለ-ምልልስ ከመሞቴ በፊት በኢትዮጵያ መቃብር ላይ “በኩሽ ህዝብ አንድነት የምትመሰረት ሀገር እንዳይ የጀመርኩትን ፕሮጀክት ያስጨርሰኝ!” እያለ ሲፀልይ ተደምጧል።
የኦሮሞ ልሂቃንም “የገዳ ሥርዓት ቀደምት ምሁር” እያሉ የሚያሞካሹት አስመሮምን የ “አባ ገዳ” ማዕረግ ሲሰጡት፣ ለማ መገርሳም የክብር ዶክትሬት ጀባ ብሎታል።
አብይ ደግሞ ፈርዶበት ኖቤል ከተሸለመ በኋላ በአምስት ዓለም አቀፍ መድረክ “የሰላም ጓዴ” እያለ ኢሳያስ አፈወርቂን ሲክብ ሰንብቷል። ኢሳያስ ግን ለተለመደው የኢትዮጵያውያን “የእሽሩሩ ፖሊሲ” እንግዳ ስላልሆነ፣ እንደሚያተርፍበትም ስለሚያውቅ፣ አብይን አንድም ጊዜ “እንኳን ደስ ያለህ” ሳይል፣ በኩራት ለሌላ ዙር ጉብኝት አዲስ አበባ ገብቷል።
አብይ ኢትዮጵያን ሊያናጋ የተቃረበው የአገር ውስጥ ችግር ችላ ብሎ ተስፋው ኢሳያስ ጋር የጣለ ይመስላል። ተወዳጁ አብይ አህመድ እጥፍ ዘርጋ እያለ ኢሳያስን ሲያስተናግድ ላየ ሰው፣ ኢሳያስ አፈወርቂ “አሰብ ወደብን ለኢትዮጵያ መለሰ እንዴ?” ያሰኛል።
በታሪክ የእሽሩሩ ፖሊሲ የሚከተሉ ሀገሮች ሲጎዱ እንጂ ሲያተርፉ አይታወቁም።
በነገራችን ላይ፣ ማን ነበር እንዲህ ብሎ ያዜመው?
“ያዋከቡት ነገር፣ ምዕራፍ አያገኝም፤
ፍቅሬ፣ ፍቅሬ በዛ እኔ አላማረኝም!”