የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን በክብር ከሓላፊነታቸው ተሰናበቱ
ኢትዮጵያ ካገኘቻቸው መሪዎች ለየት ባለ መልኩ ለሕዝብ ቅርብ ለመሆን እየጣሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ በአዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ አካባቢ የሚገኘውን ብራይት ስታር የበጎ አድራጎት ድርጅትን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተጨማሪ ሌሎች የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላትም ተሳታፊ መሆናቸውን ለመመልከት ችለናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጉብኝቱን አስመልክተው በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ “ዛሬ ከሰዓት በኋላ ብራይት ስታር ኢትዮጵያ የተሰኘውን ጉብኝት ያዘጋጀው የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትርን ለማመስገን እወዳለሁ” ብለዋል።
200 የሚደርሱ በጎዳና ላይ የሚኖሩና ለችግር የተጋለጡ ህፃናት ቀጣይ ህይወት ለመደገፍ የተደራጀውን የማዕከሉን እንቅስቃሴዎች ከሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት ጋር በመሆን መጎብኘታቸውንም አረጋግጠዋል።
በዚያውም ትርፍ ጊዜያቸውን በበጎ አድራጎትና በተመሳሳይ ሰብኣዊ ሥራዎች ለሚያሳልፋት ዶክተር አሚር አማን ሽኝት መደረጉንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት።
በዚሁ ፕሮግራም ላይ ዶክተር አሚር አማን የተዘጋጀላቸውን ስጦታም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እጅተቀብለዋል።
“ነፃ ጊዜያችንን ተጋላጭ ማኅበረሰቦችን ለመደገፍ እና ለእድገታቸው አስተዋፅኦ ለማድረግ ማዋል ክቡር ብቻ ሳይሆን የመልካም ዜግነት ምልክትም ነው” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መልዕክት አስተላልፈዋል::
በአ/አ ለሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ቅድመ ዝግጅት ተጀመረ
ቀጣዩ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ እንደከዚህ ቀደሙ በስኬት እንዲጠናቀቅ የዝግጅት ፣ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ሓላፊ አቶ ነብያት ጌታቸው ፣ የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እ.ኤ.አ ከየካቲት 6 እሰከ 10 ባለው ጊዜ ውስጥ በኅብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ ይካሄዳል።
ለጉባኤው ዝግጅትም የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላትን ያካተተ ብሄራዊ የዝግጅት ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ እንደሆነ ያመላከቱት ቃል አቀባዮ ፤ ኮሚቴው ከጸጥታ፣ ትራፊክ ፍሰት፣ ከሆቴሎች መስተንግዶና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶች መካሄድ ጀምረዋል።
በአዲሱ የፈረንጆች አመት የመጀመሪያ ወቅት ላይ የሚካሄደው ጉባኤ ዋና ትኩረት የሰላም ጉዳይ እንደሆነ እየተነገረ ነው:: በአጀንዳ 2063 እንደተቀመጠው የአፍሪካ አህጉር የሰላም ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው እንደሆነም ይታወቃል።
በዚሁ መሰረት አፍሪካ ውስጥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተኩስ ድምጽ የማይሰማበት እንዲሆን ለማስቻል የኅብረቱ አባል አገሮች እየሠሩ ይገኛሉ የሚሉት አቶ ነቢያት ፤ ጉባኤው በአፍሪካ ኅብረት ከተቀመጡ አጀንዳዎች ጋር ተያይዞ ሰላም ለማስፈን የሚያጋጥሙ ችግሮችንና መፍትሄዎችን በጥልቀት የሚመረምርበት መድረክ ነው ሲሉ ቅድመ ግምት አስቀምጠዋል።
በቀጠናው ሰላም ለማስፈን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በኖቤል ሽልማት ዕውቅና የተሰጣቸው በመሆኑም ጉባኤው ኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን የሚከናወኑ ሥራዎችን የምታሳይበት መድረክ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የለውጥ እንቅስቃሴዎችን በስፋት እያከናወነ ሲሆን የለውጡ ዋነኛ ትኩረት ተቋሙ ሓላፊነቱን መወጣት የሚችልበት መንገድና የተጠያቂነትን ባህል የማዳበር ሥራዎች ቀዳሚዎቹ ናቸው።
የአህጉሩ ህዝቦችን ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚቻልባቸው መንገዶች ላይም በትኩረት እየተሠራ መሆኑም በመነገር ላይ ነው።
ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ የኅብረቱን ጉባኤ ስታካሂድ ለ57ኛ ጊዜ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በአክራሪ ብሔርተኞች ተሞልቷል የሚባለው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ልዮ ኃይሎችን አስመረቀ
የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዩ የማሰልጠኛ ማዕከላት የተለያዩ ሥልጠናዎችን የወሰዱ አባላቶቹን በይፋአስመርቋል።
ኮሚሽኑ ለስድስት ወራት በሁርሶ፣ አላጌ፣ አዋሽ ቢሾላና በሰንቀሌ ማዕከላት ያሰለጠናቸውን የፖሊስ ልዩ ኃይል አባላቱን ነው በአዋሽ ቢሾላ ወታደራዊ ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከል በዛሬው እለት ያስመረቀው። በምረቃው ላይየኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ሌሎች የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
በአክራሪ ብሔርተኛ ትርክት የአማራን ሕዝብ “ነፍጠኛውን ሰበርነው” ሲሉ በአደባባይ የኢሬቻ በዓል ላይ የተናገሩትና ብዙኃኑን ኢትዮጵያዊ ክፉኛ ያሳዘኑት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በምረቃ ሥነ ሥርዐቱ ላይህግና ስርዓት መሬት ወርዶ እንዲተገበርና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ፣ በስነ ምግባር የታነፀ የፀጥታ ኃይል ድርሻው ከፍተኛ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
መንግሥት የክልሉን ህዝብ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅና የለውጡ ጉዞ ከዳር ለማድረስ የፀጥታ ኃይሉን በአዲስ መልክ እያደራጀ መሆኑን የጠቆሙት አወዛጋቢው የኦሮሚያ ክልል ም /ርዕሰ መስተዳደር ፣ የፖሊስ ሠራዊቱ የሚጠበቅበትን ግዴታ እንዲወጣ በየደረጃው የሚገኘው የኅብረተሰብ ክፍል ተገቢውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግለት ጠይቀዋል። የፖሊስ ልዩ ኃይል አባላት ሙያው የሚጠይቀውን ስነ- ምግባር በመጠቀምና በብቃት በመወጣት አገራዊ ለውጡን ወደ ቀጣይ ምዕራፍ የማሸጋገር ተልዕኳቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ከፍያለው ተፈራ በበኩላቸው፤ በክልሉም ሆነ በአገር ደረጃ አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣና የህግ የበላይነት እንዲከበር የክልሉን ፖሊስ ልዩ ኃይል በአዲስ መልክ ማደራጀት ማስፈለጉን ተናግረው “የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ ካልተቻለ አገሪቱ ሰላም ልትሆን አትችልም” ካሉ በኋላ ተመራቂዎች በስልጠና ቆይታቸው ያገኙትን ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ በብቃት ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
አቶ ሽመልስ አብዲሳም ሆነ የፖሊስ ኮሚሽነሩ ይህን ይበሉ እንጂ የኦሮሚያ ፖሊስ ህግ የማስከበር ጉዳይን በተመለከተ መሬት ላይ ያለው እውነታ ፈጽሞ ከዚህ የራቀ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ::
በተሳሳተ የታሪክ ትርክት እና የጥላቻ ፖለቲካን እየተሰበኩ በኖሩ የኦሮሞ ወጣቶች የተዋቀረው የኦሮሚያ ፖሊስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተጠመቁበት የጽንፈኛ ብሔርተኝነት ልክፍት በመታገዝ “የኬኛ” እና የተረኝነት ፖለቲካን የሚያንጸባርቁ ድርጊቶችን በተደጋጋሚ ሲፈጽሙ መታየታቸውን ጥቂት የማይባሉ ኢትይጵያውያን ይጠቁማሉ::
በቅርቡ ጃዋር መሐመድ የቀሰቀሰውን ጥቃት ላይም ሆነ በተለያዮ አጋጣሚዎች ከሀውጡ ማግስት ጀምሮ በተፈጠሩ አመጾች ላይ የኦሮሚያ ፖሊስ ህግ ከማስከበር ይልቅ ጥቃቶች እንዲበዙ ግልጽ የሆነ ቸልተኝነትን ከማሳየቱ ባሻገር በእነዚህ አመጾች ላይ ብሔራቸው እየተለየ ንጹሃን ዜጎች ሲገደሉ አንዳችም የማዳን እርምጃ አለመውሰደንም በማስረጃነት ያቀርባሉ::
እውነተኛውን “ፋኖ” ን ያገለለ፣ የአማራ ወጣቶች ማኅበር ጉባዔ በባህር ዳር ተጀመረ
የአማራ ወጣቶች በር ለሁለት ተከታይ ቀናት የሚቆይ ጠቅላላ ጉባኤውን ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ማካሄድ መጀመሩን ከደረሰን ዜና መረዳት ችለናል።
የአማራ ወጣቶች ማኅበር 5ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ “አንደነት ለአማራ ወጣቶች ውበት፤ ለኢትዮጵያ ድምቀት” በሚል መሪ ቃል ነው እየተካሄደ ያለው።
በጉባዔው ከአማራ ክልል እና ከሁሉም አካባቢ የተወጣጡ ወጣቶች፣ የሌሎች ክልል ወጣት ማኅበራት ተወካዩች በዋናነት እንዲሁም የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ተወካዮች በተጋባዥነት ተሳትፈዋል ተብሏል።
በውይይት መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ርዕስ መስተዳደድ ልዩ አማካሪ አቶ ጎሹ እንዳላማው፥ ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ ለነበረው ለውጥ የወጣቶች ንቅናቄ ከፍተኛ መሆኑን ፣ አሁን ለመጣው ለውጥም የወጣቶች ትግል ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ጠቁመው፤ ይሁን እንጂ ለውጡ አሁንም ፈተናዎች ስላሉበት ፣ የሚፈለገው ለውጥ እንዲመጣ የአገራችን መፃኢ እድል በወጣቶች እጅ ላይ ነው ሲሉ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ወጣቶች ማኅበር ሊቀ መንበር ወጣት አባይነህ መላኩ በበኩሉ፣ የአማራ ወጣቶች ማኅበር ከተመሠረተበት 1995ዓ.ም ጀምሮ ከመንግሥትና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የአባላትንና የሌሎች ወጣቶችን የማኅበራዊ ኢኮኖማያዊና ፓለቲካዊ ችግሮች ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎችን እያካሄደ ነው ብሏል፡፡
ማኅበሩ 884 ሺህ ነባር እና 30ሺህ አዲስ አባላት ይዞ እየተንቀሳቀስ እንደሚገኝ እና ማኅበሩ በክልሉ ከማንኛውም የፓለቲካ ጣልቃ ገብነት፣ ከዘር፣ ከሃይማኖትና ፓለቲካ አመለካከት ነፃ መሆኑንም በተያያዥነት ጠቁሟል።
ይሁን እንጂ አሁን ጉባዔውን እያካሄደ ያለው የአማራ ወጣቶች ማኅበር ቀደም ሲል በብአዴን የተመሠረተ ፣ ሥልጣን ላይ ባለው አካል ድጎማ የሚደረገለት እና አሁንም በአዴፓ ቀጥተኛ አዛዥነት የሚዘወር ስብስብ መሆኑን የኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአማራ ወጣቶች ገልጸዋል::
“ማኅበሩ በአማራ ወጣቶች ስም የሚነግድ ፣ ላላፈው ሥርዐት ፖለቲካ ጎንበስ ቀና ሲሉ የነበሩ በተለያዮ የአማራ ክልል የሚገኙ ሆድ አደር ወጣቶችን አቅፎ የያዘ ነው” ያሉት አስተያየት ሰጪ የአማራ ተወላጅ ወጣቶች እየተካሄደ ያለው ጉባአፈዔም ሆነ ማኅበሩ በኢትዮጵያ ውስጥ በጥቂቱም ቢሆን ለታየው የለውጥ ተስፋ ከወያኔ ሥርዐት ጋር እልህ አስጨራሽ ትግል ያደረገውንና ደረቱን ለጥይት ያለፍርሀት ሰጥቶ የነበረውን እውነተኛውን የአማራ ወጣት “ፋኖ” ን ያገለለ ፣ በአዴፓ አምላኪዎች የተወቀረ ነው ሲሉ ለኢትዮጵያ ነገ አስታውቀዋል::
አሜሪካ በታሪኳ ትልቅ የሚባለውን የጅምላ ግድያ አስተናገደች
ሊገባደድ ጥቂት ቀናት ብቻ በቀሩት የፈረንጆቹ 2019 አሜሪካ በታሪኳ እጅግ ከፍተኛ የሚባል የጅምላ ግድያ ማስተናገዷ ተነገረ።
አሶሺየትድ ፕረስ፣ ዩኤስኤ ቱዴይ እና ኖርዝ ኢስተርን ዩኒቨርሲቲ በትብብር ባጠናቀሩት መረጃ መሠረት በዓመቱ 41 ክስተቶች ተመዝግበዋል:: በእነዚህ ጥቃቶች 211 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።
አንድ ጥቃት፣ የጀምላ ግድያ ነው ተብሎ የሚፈረጀው፤ከጥቃት ፈጻሚው በተጨማሪ አራት ወይም ከዚያ በላይ ሰዎች ሲገደሉ መሆኑ ይታወቃል። በአሜሪካ በሚጠናቀቀው ዓመት ለበርካቶች ሞት ምክንያት ከሆኑት የጅምላ ግድያዎች መካከል በወርሀ ግንቦት ቨርጂኒያ ቢች 12 ሰዎች የተገደሉበትና ነሀሴ ላይ ደግሞ በኤል ፓሶ 22 ሰዎች የሞቱበት ጥቃት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው።
በታላላቆቹ ተቋማት ጥናት መረጃ መሠረት በአርባ አንዱ ጥቃቶች 33 የጦር መሳሪያዎች አገልግሎት ላይ የዋሉ ሲሆን፣ ካሊፎርኒያ 8 የጅምላ ግድያዎችን በማስተናገድ ከሁሉም ግዛቶች ከፍተኛውን ቁጥር ያስመዘገበች ሆናለች።
መረጃውን በማጠናቀሩ ሂደት ተሳታፊ የነበሩ ባለሙያዎች እንደገለጹት፣ ከፈረንጆቹ 1970 በፊትም ሆነ በኋላ እንዲህ አይነት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጅምላ ግድያ ቁጥር አልተመዘገበም። በሁለተኝነት የተቀመጠው ዓመት ደግሞ 2006 ሲሆን፤ በወቅቱ 38 ጥቃቶች ተመዝግበዋል።
ምንም እንኳን 2019 ከፍተኛውን የጅምላ ድግያ ክስተቶች ቢያስተናግድም ፣ በ2017 ለ224 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆኑ ጥቃቶችም የማይዘነጉ ናቸው። በዚሁ ዓመት በላስ ቬጋ የሙዚቃ ድግስ በመታደም ላይ የነበሩ ሰዎች ተኩስ ተከፍቶባቸው 59 ሰዎች በቦታው መሞታቸው የሚዘነጋ አይደለም።
በአሜሪካ አሁንም ዜጎች የጦር መሣሪያ እንዳይዙ ሙሉ በሙሉ መከልከል የተሳናት ሲሆን ፤ ይህን ያክል ዜጎች በየዓመቱ ህይወታቸውን እያጡ መንግሥት ለምን ዝምታን መረጠ? የሚሉ በርካቶች ናቸው።
በነሀሴ ወር ኤል ፓሶ ላይ 22 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በጦር መሣሪያ ጉዳይ ተደጋጋሚ ውይይት አድርገው ነበር።