በሃገራችን የብሄረሰቦች ጭቆና ነበር ብሎ የሚያስበው የዘውግ ፖለቲካ ሰልፈኛ የየራሱን ዘውግ ተጨቋኝ አድርጎ ሲያስብ ጨቋኝ ብሎ የሚወስደው ደግሞ የአማራ ዘውግን ነው፡፡ ይህ አማራን ጨቋኝ አድርጎ የመውሰድ እሳቤ የዘውግ ፖለቲከኛን ሁሉ አንድ የሚያደርግ ብያኔ ነው፡፡ ይህ ብያኔ አማራ የተባለን ሰው ሁሉ በበጎ እንዳያዩ ያደርጋቸዋል፡፡በርግጥ ለአፋቸው “ጨቋኝ ዘውግ የለም፤ የነፍጠኛው ስርዓትም ማንንም ህዝብ የሚወክል አይደለም” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
በተግባር የሚታየው ግን “ነፍጠኛ” የሚለው ቃል አማራ ለተባለ ሁሉ እንደሚሰራ እና አማራ ሁሉ ጨቋኝ እንደሆነ የማሰብ ዝንባሌ ነው፡፡ ይህን በተግባር ለማየት ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖር ማንኛውም አማራ ከመፈናቀል፣ ከመገደል፣ በስነ-ልቦና ከመዋከብ፣በአደባባይ ከመንጓጠጥ የሚያስቀረው አንዳች ነገር አለመኖሩ ነው፡፡ ይህ ከህወሃት የበላይነት ዘመን ጀምሮ ያለ አሁንም የቀጠለ ልማድ ሆኖ የህወሃት የበላይነት ካከተመበት ዘመን ወዲህም ቢሆን የዘውግ በፖለቲከኞች አማራውን የሚያዩበት እይታ የወዳጅነት እንዳልሆነ ማሳያው ብዙ ነው፡፡
አማራው በዘውግ ፖለቲከኞች የሚታይበት በጎ ያልሆነ እይታ ከዚህ ቀደም የሚገለፀው ከክልሉ ውጭ ያሉ አማሮችን መግደል፣ በማዋከብ፣ በማፈናቀል እና በማዋረድ ነበር፡፡ አሁን ግን ሌላ ተጨማሪ መልክ እየያዘ መጥቷል፡፡ ይህ አዲስ ተግዳሮት በአማራ ክልል ላይ ፈተናዎች በመደቀን ክልሉን በውስጥ ፈተናዎች ባተሌ (Busy) በማድረግ በማዕከላዊው የሃገራችን ፖለቲካ ሊኖረው የሚችለውን ንቁ ተሳትፎ ማዳከም ነው፡፡
እንደሚታወቀው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በአክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ዘንድ ትልቅ ችግር ተደርጎ እየቀረበ ያለው ዶ/ር አብይ በሚመሩት የፌደራል መንግስት መዋቅር ውስጥ አማሮች በርከት ብለው ታዩ የሚለው አቤቱታ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን “በነፍጠኛ ጉዳይ አስፈፃሚነት” እያስከሰሳቸው ያለውም ይሄው ተረክ ነው፡፡ ሆኖም ሃገራችን አሁን ለተያያዘችው ለውጥ የብአዴን ባለስልጣናት ያደረጉትን አስተዋፅኦ ጠንቅቀው የሚያውቁት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አማራውን አግልሎ የመሄዱ ጉዞ ብዙ እንደማያስኬድ አያጡትም፡፡ በመሆኑንም የለዘብተኛ ኦሮሞ እና አማራ ልሂቃንን ክንድ አጣምረው በሚያመጡት ብርቱ ድጋፍ ላይ ቆመው ሃገር የማረጋጋቱን ስራ ለመስራት እየሞከሩ ይገኛሉ፡፡
ይህ የማይዋጥላቸው አማራ አከራካሪው ተሰብሮ፣እንደወትሮው አንገቱን ደፍቶ፣በአደባባይ እየተሰደበ እንዲኖር የሚሹቱ በጃዋር መሃመድ የሚመሩት አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ደግሞ በህወሃት ዘመን በነበረው የአማራ ህዝብ ፈተና ላይ ሌላ አዲስ ፈተና ጨምረው አማራውን የማዳከም ስልታቸውን እያፋፋሙ ይገኛሉ፡፡ የሚያሳዝነው ይህን አስጊ ፈተና አማራ ክልልን የሚመሩ መሪዎችም ሆኑ ለክልሉ ህዝብ እንታገላለን የሚሉ የአማራ ፓርቲዎች በቅጡ ተረድተው የስጋቱን ያህል እየሰሩ አለመሆኑ ነው፡፡
ከላይ እንደጠቀስኩት አዲሱ የአማራ ክልል/ህዝብ ፈተና ከቀድሞው ለየት የሚያደርገው ፈተናውን የሚሰጡ አካላት ከቀድሞው የተለዩ እና የበረከቱ መሆናቸው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የአማራን ህዝብ በጅምላ የመጥላቱ እና የመርገሙ አካሄድ የሚመራው በህወሃት ነበር፡፡ አሁን ግን የህወሃት “አማራውን አይቼ ልጥፋ” የሚያሰኝ መሪር ጥላቻ በባሰ ሁኔታ የቀጠለ ሲሆን ተጨማሪው አዲስ ነገር ህወሃትን ሽሽተው ከሃገር ተሰደው የነበሩ፣ ግን ደግሞ በያሉበት ቦታ ሆነው አማራውን ደመኛ አድርገው በማሰቡ ረገድ አንድ ቀን ተዘናግተው የማያውቁ እንደ ጃዋር መሃመድ ያሉ የኦሮሞ ልሂቃን ሃገር ቤት ገብተው አማራውን እንዳይነሳ አድርጎ ለማድቀቅ ሲሆን ከአሳዳጃቸው ህወሃት ጋር ሳይቀር ገጥመው እየሰሩ መሆኑ ነው፡፡
እነዚህ ቡድኖች በአማራ ህዝብ ላይ የደቀኑት አዲሱ ፈተና ከዚህ ቀደም ህወሃት ከክልላቸው ውጭ ባሉ አማሮች ላይ ሲያደርገው ከነበረው ግፍ በተጨማሪ በርካታ ፈተናዎችን ወደ ራሱ ወደ አማራ ክልል ይዞ የመሄድ እጅግ መሰሪና አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ ይህ አዲሱ የነጃዋር ዕቅድ በጊዜ ካልከሸፈ በክልሉ ያለውም ሆነ ከክልሉ ውጭ ያለው አማራ ታይቶ በማይታወቅ ውስብስብ ፈተና ውስጥ ይወድቃል ማለት ነው፡፡
አዲሱን የአማራ ህዝብ ፈተና ህወሃት ሲያደርግበት ከነበረው ፈተና የከፋ የሚያደርገው በህወሃት ዘመን ከክልሉ ውጭ ያለው አማራ ሲሳደድ እንኳን ወደ ክልሉ ሄዶ የመኖር ተስፋ የነበረው ሲሆን አሁን በነ ጃዋር መሪነት ወደ በክልሉ ላይ የተደቀነው ፈተና የአማራን ህዝብ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያማርር፣ አገር የሚያሳጣ እና ተስፋ ቢስ የሚያደርግ ነው፡፡ የእኔ ስጋት ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ የአማራ ህዝብ በየምክንያቱ በሚደቀንበት አደጋ፣ ሰበብ ተፈልጎ በሚደርስበት ውግዝ፣ተንቀሳቅሶ በመስራት መብቱ ላይ የተደቀነው አደጋ፣ በክልሉ በሰላም የመኖር መብቱ ላይ የሚደረገው ደባ ተጠራቅሞ የሚፈጥርበት የባይትዋርነት ስሜት የሃገሪቱ መንግስት ለሚሰብከው ለውጥ፣ ብሩህ ተስፋ ጆሮው ዝግ እንዲሆን ጭራሽም ለአመፅ እንዲነሳሳ ሊያደርግ ይችላል፡፡
ይህ ከየአቅጣጫው የመዋከብ ስሜት የሚወልደው የአመፅ ዝንባሌ ደግሞ ከዚህ ቀደም አማራው የሚታወቅበትን ኢትዮጵያን የማለት ስሜት ሸርሽሮ ክልሉን የሚመራው ብልፅግና ፓርቲ ከሚቆጣጠር ውጭ የሆነ፣ ቅርፅ የለሽ አመፅ ሊፈጥር ይችላል፡፡ ይህ የአማራ ህዝብ ካለው የታጣቂነት ባህል ጋር ተደማምሮ ሃገራችንን ወደማትወጣው ማጥ እንዳይከታት መስጋት ምክንታዊ ነው፡፡ ሕዝቡ እንዲህ ባለው የተበድየ ስሜት ወለድ አመፅ ውስጥ ከገባ የአማራ ክልልን መልካም የማትወደዋ ህወሃት እሳቷን ለኩሳ ከተፍ ማለቷ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡
እነዚህን አዳዲስ ፈተናዎች ተረድቶ በበሰለ እና በተረጋጋ መንገድ ከፈተናዎች የማለፍ ዘዴን መተለም በቅድሚያ በብልፅግና ፓርቲ ስም ክልሉን የሚመሩ ባለስልጣናት የቤት ስራ ነው፡፡ በመቀጠል ለአማራ ህዝብ እታገላለሁ የሚል ማንኛውም አካል ጉዳይ ሊሆን ይገባል፡፡ በበኩሌ እነዚህን አዳዲስ ፈተናዎች ክልሉን የሚመሩ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮችም ሆኑ ሌሎች ለአማራ ህዝብ እንታገላለን የሚሉ እንደ አብን ያሉ ፓርቲዎች የተረዱት አልመሰለኝምና ፈተናዎቹን በታየኝ መንገድ ወደማሳየት ልለፍ፡፡
ፈተና አንድ፡ የአማራ ክልልን የውስጥ ሰላም ማወክ
የአማራ ክልል ውስጣዊ መረጋጋት እንዳይኖረው ታጥቆ የመስራቱ ዝንባሌ ቀዳሚ ተዋናይ ህወሃት ስትሆን የህዋትን ሰላም የማወክ ፊሽካ ተከትሎ ማንኛውም የዘውግ ፖለቲከኛ የአማራ ክልልን ጥፋተኛ አድርጎ በመቆም ጉዳዩን የማራገብ ስራ ይሰራል፡፡ ለዚህ የህወሃት እና ጋሻጃግሬዎቹ ሴራ አይነተኛ እርካቡ “የቅማንት ጥያቄ” የሚለው ፈሊጥ ነው፡፡
በቅማንት ጥያቄ ሰበብ ከባድ መሳሪያ አስታጥቃ ክልሉን የምታምሰው ህወሃት የጠባጫሪነቱን ሚና ቀድማ ወስዳ፣የልቧን ስትሰራ የአማራ ልዩ ሃይል ለዚህ ደባ የሚመልሰው መልስ “የአማራ ልዩ ሃይል በቅማንት ህዝብ ላይ የሚያደርገው ዘር ማጥፋት” ተደርጎ በነጃዋር ሚዲያ ይራገባል፡፡ አቶ ጃዋር (ምናልባትም የአማራ ክልል አስተዳዳሪዎች ስለጉዳዩ ከመስማታቸው ቀድሞ ተሸቀዳድሞ) በማህበራዊ ገፁ ብቅ ብሎ “ከታማኝ ምንጮች ደረሰኝ” ሲል የሆነውንም ያልሆነውንም አጠናቅሮ ያቀርባል፡፡ በአማራ ክልል እንዲህ ያለ የፀጥታ ችግር የተነሳ በመሰለው ሰሞን ይህንኑ ያለማራገብ ስራ የለውም፡፡
ደርሶ ለቅማንት ህዝብ አዛኝ ቅቤ አንጓች የሆነው ጃዋር እና ሚዲያው በትግራይ ክልል መንግስት ስር ለሚሰቃዩት የራያ እና የወልቃይት የማንነት ጥያቄ አቅራቢዎች ተመሳሳዩን “ርህራሄውን” ሲያሳይ አይታይም፡፡ “ለምን?” ቢባል የነዚህ አካላት የማንነት ጥያቄ ከተመለሰ የአማራን ክልል ይበልጥ የሚያገዝፍ ነገር ይዞ ሊመጣ ነው፡፡ ስለዚህ ጃዋር “ጠላቱን” ለሚያደልብ ነገር የሚያዋጣው ታጋይነት የለውምና ለራያ እና ወልቃይት የማንነት ጥያቄዎች የሚሆን አንጀት የለውም፤ ስማቸውን ሲያነሳ፣ጥያቄያቸውን ሲያስተጋባም ታይቶ አይታወቅም፡፡ እሱ የሚያውቀው አማራው “የሚበድለውን” የቅማንት ህዝብ ጥያቄ እንጅ “አማራ ነኝ” በማለቱ የሚገደለውን ወልቃይቴ ወይም “ወደ አማራ ክልል መካለል እፈልጋልሁ” የሚለውን የራያን ህዝብ በደል አይደለም፡፡
ሌላው የአማራን ክልል የማወኪያ ፈተና የሚደቀነው የኦሮሚያ ልዩ ዞን በሆነው በከሚሴ አካባቢ ነው፡፡በዚህ አቅጣጫ በሚመጣው የክልሉን ሰላም የማወክ ደባ ውስጥ ቁጥር አንድ ተዋናይዋ ህወሃት ልትሆን አትችልም፡፡ ህወሃት የአማራን ክልል ለማወክ ተራራ የማይጋርዳት፣እንቅልፍ የማይይዛት ጠላት ብትሆንም ከሚሴ ከትግራይ ክልል ካለው ርቀት አንፃር የሚኖራት ሚና ጉልህ ሊሆን አይችልም፡፡ስለዚህ ከወደ ከሚሴ የሚመጣው የአማራ ክልል ተግዳሮት ዋነኛ ተዋናዮች ሊሆኑ የሚችሉት የጃዋር ሰልፈኛ የሆኑ ኦሮሞ ብሄርተኞች ናቸው፡፡ የጃዋር ሰልፈኛ የሆኑ የኦሮሞ ብሄረተኞች የት ቦታ እንደሚገኙ ግልፅ አድርጎ ማወቅ አለመቻሉ ነው ትልቁ ፈተና፡፡
እነዚህ ሰልፈኞች በታጣቂው ኦነግም ሆነ ስልጣን በያዘው የኦህዴድ ቤት አይጠፉም፡፡ ከወራት በፊት አጣየ ላይ በታየው የአዳፍኔ ጥቃት አጥቂዎቹ በአምቡላንስ ሳይቀር ስንቅ እና ትጥቅ ሲመጣላቸው ያዩ የአገሬው አርሶ አደሮች ምስክርነት ሲጤን ነገሩ ውስጥ ሃገር የሚመራው ኦህዴድ ጭምር ሊኖርበት እንደሚችል መጠርጠር ጥፋት አይደለም፡፡ ኦህዴድ ውስጥ ያሉ ባለስልጣናት ጊዜና ቦታ እንኳን መምረጥ ያላስቻላቸው “ነፍጠኛን እንሰብራለን” የሚለውን ቁጭት ያዘለ ድንፋታቸውን ለተመለከተ በዚህ ደባ ውስጥ መጠርጠራቸው ላያስገርም ይቻላል፡፡
ሶስተኛው የአማራን ክልል ሰላም ማወኪያ መቼት በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው፡፡ በአዲሱ አመት በሃገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ሰላም መደፍረስ ሲጀመር በአማራ ክልል ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ መጀመሩ የተማሪዎች ብቻ ድርጊት ነው ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ይልቅስ ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ከዚሁ ከኦሮሚያ ልዩ ዞን አቅራቢያ የሚገኝ መሆኑ ለጃዋራዊያን የሁከት ፕሮግራም የሚያበረክተው አስተዋፅኦ አይጠፋም፡፡ ከሁሉም በላይ በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የተከሰተው ሞት ከመቅፅበት በኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሳይቀር በተለያዩ አካላት ቅብብል በከፍተኛ ሁኔታ እንዲራገብ የተደረገበት መንገድ ብዙ የሚያሳየው ነገር አለ፡፡
ከላይ በተጠቀሱት ዋና ዋና ሁኔታዎችም ሆነ ባልተጠቀሱ መንገዶች የአማራን ክልል ሰላም የማወኩ ፍላጎት በጃዋር መር የኦሮሞ ፖለቲከኞች እና በህወሃቶች ለነገ ሳይባል የሚሰራበት ምክንያት ምንድን ነው የሚለውን መጠየቅ አስፈላጊ ነው፡፡የአማራ ክልልን የማወኩ ተግባር በነዚህ አካላት በህብረትም ሆነ በተናጠል እየተሰራበት ያለው ዋናው ምክንያት የአማራን ክልል በውስጥ የፀጥታ ፈተና በመጥመድ የአማራ ፖለቲከኞች ወደ ፌደራል ስልጣን የሚያደርጉትን ጉዞ ባያስቀሩም መቀነስ ነው፡፡ ሌላው እና ዋነኛው ምክንያት ግን በአሁኑ ወቅት ክልሉን እያስተዳደሩ ያሉ አመራሮች የክልሉን ሰላም እንኳን ማስጠበቅ የማይችሉ ተብለው በክልሉ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ማድረግ ነው፡፡
ይህ ሲሆን ህወሃትም ሆነች የጃዋር ሰልፈኛ የኦሮሞ ብሄርተኞች የሚያገኙት ጥቅም አለ፡፡ ህወሃት ከአዲስ አበባው መንበረ ስልጣኗ ያሽቀነጠሯትን የብአዴን ባለስልጣናት ከህዝባቸው በመለየቷ፣ አለመቻላቸውን በማስመስከሯ የበቀል ስሜቷን ታስተነፍሳለች፡፡ የህወሃት ባለስልጣናት በየጊዜው ብቅ እያሉ “እኛ ከፌደራል ስልጣን ብንነሳም ክልላችንን በደምብ እያስተዳደርን ነው” የሚሉት የአማራ ክልል ባለስልጣናትን ህወሃት የሚደቅንበትን ፈተና ተቋቁሞ ህዝብን የማስተዳደር ብቃት እንደሚጎድላቸው በአግድም እየተናገሩ ነው፡፡
እነጃዋር ደግሞ የአማራ ክልል ላይ የፀጥታ ፈተናዎች በመደቀን በፌደራል ስልጣን ላይ በርከት ብለው የሚታዩዋቸው የአማራ ባለስልጣናት በራሳቸው ህዝብ ዘንድ ተአማኒነት እንዲያጡ በማድረግ አንድም ወደ ፌደራል ስልጣን የሚከጅሉበት ጉልበት እንዳይኖራቸው ያደርጋሉ ሁለትም የአማራ ክልል ህዝብ ከብልፅግና ፓርቲ ላይ ተስፋው ተሟጦ ክልሉን ወደሚያምስ አመፀኝነት ሊነጉድ ይችላል፡፡ሁለቱም ለጃዋራዊያን ሰርግ እና ምላሽ ነው!
ፈተና ሁለት፡ ክልሉ ለብሄረሰቦች/ሃይማኖቶች ብዝሃነት የማይመች አድርጎ ማቅረብ
በሃገራችን ካሉ ክልሎች ውስጥ በውስጡ ለያዛቸው ብሄረሰቦች ልዩ የአስተዳደር ሁኔታ በማመቻቸት የአማራ ክልል ከሚገባው በላይ የሚሄድበት ሁኔታም አለ፡፡ ክልሉ በህወሃቶች እና ጃዋራዊያን የሚብጠለጠልበት የቅማንት ህዝብ ጉዳይ ስክነት ያለበት ሃገር ውስጥ ብንሆን ኖሮ የአማራ ክልል ከሚገባው በላይ ሄዶ የሰራበት፣ እንደውም ሊያስመሰግነው የሚገባው እርምጃ ነበር፡፡
እንደሚታወቀው የአማራ ክልል የቅማንት ማንነት ጥያቄን ተቀብሎ ወደ አርባ ሁለት ለሚጠጉ ቀበሌዎች ሪፈረንደም አስደርጎ ለቅማንት ልዩ የአስተዳደር መብት ሰጥቷል፡፡ የአማራ ክልል ይህን ሲያደርግ ግን ይመስገንበት ይወቀስበት ግራ የሚያጋባ አንድ ነገር ፈፅሟል፡፡ ይኽውም በሃገራችን ህገ-መንግስት አንቀፅ 39 ቁጥር 5 ላይ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት የተፈቀደላቸው ብሄር ብሄረሰብ እና ህዝብ መባል የሚችሉ አካላት ሊያሟሏቸው የሚገባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጧል፡፡
ከነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደርም ሆነ ለመገንጠል የሚጠይቁ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ሊግባቡበት የሚገባ የጋራ ቋንቋ ያላቸው መሆን እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ በዚህ መሰረት ሲታይ ለአማራ ክልል ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ያቀረበው የቅማንት ህዝብ የሚግባባበት ቋንቋ አማርኛ እንጅ ቅማንትኛ እንዳልሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ ሆኖም የአማራ ክልል በአማርኛ ቋንቋ እየተግባቡ፣ ልዩ ቋንቋ ሳይኖራቸው፣ ህገ-መንግስቱ የሚጠይቀውን ከአማራ ህዝብ ልዩ ብሄር ብሄረሰብ የመሆን መስፈርት ሳያሟሉ፣ በአማራ ክልል ልዩ የሆነ አስተዳደር ያስፈልገናል ላሉ ወረዳዎች የክልሉ መስተዳድር የፖለቲካ ውሳኔ አድርጎ የቅማንት ልዩ አስተዳደርነት መብት ሰጥቷል፡፡
ሆኖም ማንም ይህን እላፊ እርምጃውን ቆጥሮ የአማራ ክልል መስተዳድርን ሲያመሰግነው አልታየም፤ ጭራሽ የአማራ ክልል የቅማንትን ህዝብ ዘር በማጥፋት የፈጠራ ወሬ ነው መስተዳድሩ የሚብጠለጠለው፡፡ ይህን ነገር ነጥቃ የምታቀጣጥለው ህወሃትም ስልጣን እንደያዘች ትቂት ቆይታ በ1987 ባደረገችው የህዝብ ቆጠራ ቅማንት የሚለውን ስም ያላካተተች፣ ብሄረሰቡ መኖሩንም እውቅና ያልሰጠች ነበረች፡፡ ህወሃት ቆይታ ይህን የቅማንትን ጉዳይ ማንሳት የጀመረችው የወልቃይትን ለም መሬቶች ዘርፋ መውሰዷን የመቃወም ዝንባሌ በአማራ ክልል መታየት ሲጀምር ነው፡፡
አሁን ለቅማንት ህዝብ “የሚቆረቆረው” ብዙ ነው፡፡ኦ.ኤም.ኤን የተባለውን ቴሌቭዥን ለአፍታ የከፈተ ሰው ስለ ቅማንት ህዝብ “በደል” የሚያለቅስ የዘውግ ፖለቲከኛ መስማቱ የተለመደ ነው፡፡ በዚሁ ቴሌቭዝን በቅርቡ የሰማሁት የዘውግ ፖለቲኛ “እኛ የምንታገለው ለራሳችን ብሄረሰብ ብቻ ሳይሆን ለቅማንት ህዝብም ጭምር ነው” ሲል ፈርጠም ብሎ ይናገራል፡፡ ይህ ሰው በማንነት ጥያቄ ትግል ውስጥ የቅማንትን ህዝብ ያህል ድምፃቸው ያልተሰማ የራያ እና የወልቃይት ህዝቦች መኖራቸውን ይወቅ አይወቅ አላውቅም- እንዲህ ያለውን ሰው ጠርቶ የሚያናግረው ቴሌቭዥን ባቤት ግን ጉዳዩን አሳምሮ እንደሚያውቅ፣አውቆ እንዲሚያደናቁርም እሙን ነው፡፡
አማራ ክልልን በማንነት ጥያቄ ጨፍላቂነት የሚያብጠለጥሉ የዘውግ ፖለቲከኞች በትግራይ ክልል ተካለው ግን ደግሞ “አማራነን” ወይም “ወደ አማራ ክልል እንካለል” የማለት ትግል ከጀመሩ የህወሃትን የስልጣን እድሜ ያህል ያስቆጠሩትን የወልቃይት እና የራያ የማንነት ጥያቄ አቀንቃኞች ጉዳይ አንስተው አያውቁም፡፡ የዚህ ምክንያቱ እነዚህ ቦታዎች ወደ አማራ ክልል ከተካለሉ የአማራ ክልል ግዝፈት ጨምሮ፣ የፓርላማ ወንበርም ሆነ በመሪ ፓርቲዎች ውስጥ ያለው የውክልና መጠን ሊያድግ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የአማራ ክልል ሁለተኛ ትልቅነት እጅግ ለሚያስጨንቃቸው ንዑሳኑ ህወሃታዊያን እና የጃዋር ሰልፈኛ የኦሮሞ ለፖለቲኞች ሆኖ ሊያዩት የማይፈልጉት ነገር ነው፡፡
ሌላው የአማራን ክልል የብሃነት ጨፍላቂ አድርጎ ለማቅረብ የሚነሳው ሃሳብ የሃይማኖት ጉዳይ ነው፡፡ይህን ነገር ለማራገብ እንዲመች ከመነሻው አማራነትን ከኦርቶዶክስ ክርስቲያንነት ጋር ብቻ የመፍተል አውቆ የማደናቆር ፕሮፖጋንዳ ተደልቋል፡፡ እነዚህ እኩይ ፈራጆች በአንፃሩ ኦሮሞነትን ከሙስሊምነት ጋር ፈትለው በግልፅ በአደባባይ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በእስልምና እና ክርስትና በኩል የአማራ እና የኦሮሞ ህዝቦች መካከል እንዲኖር የሚፈልጉትን የአይጥ እና ድመትነት ፖለቲካ ያራግባሉ፡፡
ከዚህ ፕሮፖጋንዳ በመቀጠል የሚመጣው በአማራ ክልል ያሉ ሙስሊሞች በመገለል እንደሚኖሩ፣ መብታቸው እንደማይጠበቅ፣ በአማራነታቸው የማይታወቁ ባይተዋሮች እንደሆኑ አድርገው በማቅረብ አማራ ክልል ላለው ሙስሊም ኦሮሚያ ክልል ሆነው አጋርነት ለማሳየት ይንጠራራሉ፡፡ የሚገርመው ነገር ግን “አባቢዩማ” ለሚሉት ኦሮሞ ያልሆነን ሰው ከኦሮሚያ የመጥረግ ፕሮጀክታቸው ሙስሊም አማሮችን የመሳፈሪያ እንኳን ሳይተርፋቸው ተዘርፈው ከኦሮሚያ ምድር ሲባረሩ ሙስሊምነታቸው ከአማራነታቸው በልጦ ያልታያቸው መሆኑ ነው፡፡
የአማራ ክልልን ለብዝሃነት የማይመች ክልል አድርጎ የፈጠራ ወሬ የማራገቡ አካሄድ ዋነኛ አላማ አማራውን ጨፍላቂ፣ ለፌደራል አስተዳደር የማይመች፣በእነሱ ቋንቋ “አሃዳዊ” አድርጎ በማቅረብ የክልሉን ፖለቲከኞች ከዋነኛ የስልጣን እርከኖች በዘዴ ለማግለል የሚደረግ ስር ሰደድ የፖለቲካ አሻጥር ነው፡
ፈተና ሶስት፡ ክልሉን የመሸንሸን ዕቅድ
ህወሃት እና የአክራሪ ኦሮሞ ብሄርተኞች የሚጠሉት ሃቅ አማራ የሚባለው ህዝብ ብዙ መሆን እና ክልሉም ግዙፍ መሆኑ ነው፡፡ ይህ የማይጋፉት ሃቅ መሆኑን ባያጡትም የሚወዱት ሃቅ ግን አይደለም፡፡ የማይወዱትን ሃቅ መግፋት በሚችሉበት አቅም መግፋቱን ግን አልተውም፡፡ ስለሆነም በተቻለ መጠን የአማራ ክልል ከኦሮሚያ ክልል ግዝፈት እየራቀ ወደ ትግራይ ክልል ንዑስነት የሚጠጋበትን ቅዠት መሰል ምኞት ያውጠነጥናሉ፡፡ ህወሃቶች ይህን ምኞታቸውን በአቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ አፍ ሳይቀር “በአማራ ክልል የሚኖረው አማራ ብቻ አይደለም” ሲሉ የልባቸውን በገደምዳሜ ይገልፁ ነበር፡፡ ይህን የሚሉት አቶ ኃ/ማርያም ግን በትግራይ ክልል የሚኖረውም ትግሬ ብቻ ሳይሆን ኢሮብ፣ኩናማ፣ራያ ወዘተ እንደሆነ ተመሳሳዩን ሲናገሩ ተሰምተው አይውቁም፡፡ እንደ አጠቃላይ ሃቅም አንድ ህዝብ ብቻ የሚኖርበት ክልል የለም፡፡
ያም ሆነ ይህ የአማራን ክልል ግዝፈት ለመሸርሸር በኦሮሞ እና ትግሬ ብሄርተኞች የሚውጠነጠው አንድ እቅድ አማራን እና አገውን ሆድ እና ጀርባ ማድረግ፣ ከዛም የአገው ህዝብ የክልልነት ጥያቄ አንስቶ ከአማራ ክልል ግዝፈት ላይ የተወሰነ ኪሎ መቀነስ ነው፡፡ ይህ ህወሃቶች ቀርተው ከህዋት እንለያለን የሚሉት አረናዎች ሳይቀሩ ሲሞካከሩት የሚያጋጥም ነገር ነው፡፡
ቀጣዩ በኦሮሞ ብሄርተኞች በግልፅ እየተነገረ ያለው ወሎን ሰሜን ኦሮሚያ የማድረግ ህልም ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተቀሩትን የአማራ ክልል ግዛቶች በጎጃም በጎንደር በሸዋ የተከፋፈሉ ማድረግ ነው፡፡ የአማራ ብሄረተኝነት ከሰኔው ግድያ ወዲህ እየተጓዘበት ያለው መንገድ ደግሞ ለዚህ ደባ ጥሩ ግብዓት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ በስተመጨሻው አማራ የሚባል አካል የለም በማለት የሚጠሉትን ክልል ከመኖር ወደ አለመኖር የመቀየር የምኞት ስንቅ ተሰንቋል፡፡
ፈተና አራት፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ክልሉን ማሳጣት
ሃገራችን በአሁኑ ወቅት ያለችበት የሰላም እና ፀጥታ ችግር የሚታወቅ ነው፡፡ ሆኖም በአማራ ክልል የሚነሳው የፀጥታም ሆነ የደህንነት ችግር የተለየ ትርጉም ተሰጥቶት በተጋነነ ሁኔታ እንዲቀርብ ማድረግ ከመንግስት ባለስልጣናት እስከ ተቃዋሚ ነን ባይ ፓርቲዎች ድረስ በሃገራችን ያሉ የፖለቲካ ሃይሎች ሁሉ የተያያዙት አካሄድ ነው፡፡ ለዚሀ አይነተኛ ማሳያው በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የተከሰተውን የተማሪ ሞት ተከትሎ የተደረገው ጤነኛ የማይመስል ማራገብ እና በሞጣ የተከሰተውን የመስጊድ ቃጠሎ ስንት ቤተ-ክርስቲያን ሲቃጠል በኖረባት ሃገር ያልተደረገ አዲስ ክስተት ለማድረግ የተኬደበት አስተዛዛቢ ግነት ነው፡፡ በሃገራችን የሃይማኖቶች መከባበር መኖር እንዳለበት፣ የሙስሊሙም ሆነ የክርስቲያኑ የእምነት ቦታ በክብር መታየት መቻሉ ብቻ በሰላም የሚያኖረተን እሳቤ እንደሆነ አጥብቄ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ለእምነት እኩልነት መምጣት የሁሉም ሃይማኖቶች የእምነት ቦታዎች በእኩል ሁኔታ መጠበቅም ሆነ በየትኛውም የሃገራችን ክፍል እክል ሲገጥማቸው እኩል ሊጠበቁ፣ ድርጊቱም እኩል ሊወገዝ ይገባል፡፡
ከዚህ ሃቅ ውጭ በአማራ ክልል ላይ የታየውን የመስጊድ ቃጠሎ ተከትሎ ከሰሞኑ የታየው ግነት ነገሩ የተደረገው አማራ ክልል ስለሆነ የመጣ መሆኑን መካድ ችግር ላይ መተኛት እንጅ ሌላ ስም የለውም፡፡አመት ሙሉ ቤተክርስቲያን ሲቃጠል አንዱም ጋር ሲሄዱ ቀርቶ ጠበቅ አድርገው ሲያወግዙ ያልታዩ ኢዜማ የተባለው ፓርቲ አመራሮች ሞጣ ድረስ ገስግሰው ለጉብኝት ሲገኙ በአማራ ክልል ላይ የተያዘው በልዩ ሁኔታ የማሳጣት አካሄድ ከዘውግ ፖለቲከኞች አልፎ ህብረ-ብሄራዊ ነን የሚሉት ጉያ ውስጥም እንደማይጠፋ አመላካች ነው፡፡
በአማራ ክልል የሚደረጉ ድርጊቶችን አጋኖ የማቅረቡ ማሳያ የሞጣው መስጊድ ቃጠሎ እና የወልዲያ ዩኒቨርሲቲው ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ሌላው እና ዋነኛው ነገር ክልሉ የፀጥታ ፈተናውን ለማቃለል በሚያደርገው የልዩ ሃይል ስልጠና የሚያጠፋው በጀት እጅግ ተጋኖ በክልሉ የተከሰተውን ግድያ ሁሉ ያስከተለ ጦስ ማምጣቱ አይዘነጋም፡፡ በአንፃሩ ከሰሞኑ ኦሮሚያ ክልል ያሰለጠነው የልዩ ሃይል መጠን ሲታይ ክልሉ ከየአቅጣጫው የሚታይበትን እይታ ማስተካከል እጅግ ትኩረት የሚፈልግ ነገር እንደሆነ አመላካች ነው፡፡ ይህን ማስተካከያ ማድረግ ክልሉን የሚመራው ብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ዋነኛ የቤትስራ ነው፡፡
ሆኖም አመራሮቹ የተደቀነባቸውን ውስብስብ ፈተና በእርጋታ እና በብስለት መርምረው፣ ለክልሉም ሆነ ለሃገራችን ሰላም እና አንድነት የሚበጅ የፖለቲካ ጨዋታ መጫወት መቻላቸው አጠያያቂ ነው፡፡ ይህን ያስባለኝ አንድም ክልሉን የሚመሩ መሪዎች ከለውጡ በኋላ የክልሉን ሁኔታ ከመገምገም አንፃር ያላቸው ልዩነት እስከመጋደል ያደረሰ ሰማይ ከምድር እንደሚርቅ የሚራራቅ መሆኑ ሲሆን ሁለትም ከመጋደሉ በኋላም ክልሉ የተደነቀረበትን አዳዲስ ፈተናዎች ቀድሞ አሽትቶ አዋጭ መላ በመዘየዱ በኩል መሪዎቹ ያላቸውን ዝግጁነት ስለምጠራጠር ነው፡፡
ይህን ጉዳይ ቀድሞ በመረዳቱ በኩል ቀዳሚ መሆን ይገባቸው የነበሩት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ በአማራ ክልል የሚከሰቱ ክስተቶች ተጋነው እንደሚተረጎሙ የተገነዘቡት ገና ትናንት ነው፡፡ አበረ ከወራት በፊት በአማራ ክልል ላይ የተከሰተውን ፈተና በመተንተን ረገድ ከእርሳቸው የተለየ እይታ ያላቸውን ሟቹን ጀነራል አሳምነውን በአእምሮ በሽተኝነት ሲከሱ የከረሙ ሰው ናቸው፡፡ የመፍትሄውን መንገድ የሚያርቀው እንዲህ ያለው ክልሉን በሚመሩት መሪዎች መሃከል ያለው እሳቤን ከማቀራረብ ይልቅ የመፈራረጅ ልማድ ነው፡፡
በዚህ ልማዳቸው ላይ ሰከን ብለው ፖለቲካውን የመመርመር ውስንነታቸው ሲደማመር ከክልሉ አልፎ ለሃገር የሚተርፍ ጦስ ሊያመጣ የሚችል አደጋ ከወደ አማራ ክልል ሊነሳ ይችላል፡፡ የዚህ ችግር ዋነኛ ስር እነዚህ አመራሮች ክልሉ የተጋረጠበትን ችግር በሚመጥን ብልሃት፣ ስክነት እና መደማመጥ ህዝቡን መምራት ካልቻሉ የክልሉ ህዝብ በሚመሩት አመራሮች ላይ ያለው እምነት ተሸርሽሮ፣ አጋርነቱን ወደ አክራሪ የአማራ ብሄርተኞች ሊያዞር ይችላል፡፡ይህ ደግሞ ክልሉን ወደ ግልፅ የአመፅ ቀጠና የሚመራ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ ይህን አደጋ ለማስቀረት ክልሉን የሚመሩ አመራሮች ምን ማድረግ አለባቸው የሚለውን በታየኝ መንገድ ለማሳየት ሳምንት ልመለስ፡፡