ህወሓት “ህልውናዬን” እወስንበታለሁ ያለውን ጉባዔ እያካሄደ ነው
ህወሓት ከዛሬ ታህሳስ 25/2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ አስቸኳይ ድርጅታዊ ጉባኤ በመቀሌ ከተማ ሰማዕታት ሐውልት አዳራሽ እያካሄደ መሆኑ ታውቋል።
እስካሁን 13 ድርጅታዊ ጉባዔዎችን ያካሄደው ህወሓት አስቸኳይ ጉባዔ ሲጠራ ይህ የመጀመሪያው ሆኗል።በጉባዔው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል ፤ ጉባዔውን ቀጣይ የህወሓትን ህልውና የሚወስን ልዩና ታሪካዊ ጉባዔ ነው በማለት ገልፀውታል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ፤ ጉባኤው በህወሓት ፍላጎት የተጠራ ሳይሆን፤ በአገሪቷ ያለው ሁኔታ አስገድዶ የተጠራ አስቸኳይ ጉባዔ መሆኑንም ተናግረዋል።
የፓርቲው ጽ/ቤት ሓላፊና ከጉባዔው አስተባባሪ ኮሚቴዎች አንዱ የሆኑት አቶ አለም ገ/ዋህድ የጉባዔውን ሦስት አጀንዳዎች አስተዋውቀዋል። ከኢህአዴግ መፍረስና እና ከአዲሱ ብልፅግና ፓርቲ መመስረት ጋር በተያያዘ የማዕከላዊ ኮሚቴውን በጥልቀት መገምገም፣ በምርጫ አዋጅ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ሥነ ምግባር ጋር እንዲሁም ከኢህአዴግ ጋር ስላላቸው ግንኙነት የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ ላይ ለውጥ ለማድረግ እና የፓርቲው ፕሮግራም ከኢህአዴግ ጋር ከነበረው ግንኙነት እና ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ ጉዳዮችን ለማሻሻል እንደሆነም አብራርተዋል።
በጉባዔው ላይ ከፓርቲው አባላት ውጭ እስከ 150 የሚሆኑ ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የተለያዩ ብሔረሰብ ተወካዮች እና ሌሎች እንግዶች በመክፈቻውና እና በመዝጊያው ላይ ብቻ እንዲሳተፉ ተፈቅዶላቸዋል። ዛሬ ጠዋት የተጀመረው ጉባኤ በአጀንዳዎቹ ላይ ውሳኔ በማሳለፍ ነገ ይጠናቀቃል።
በሌላ በኩል የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመጀመሪያውን ስብሰባ ትናንት አካሂዷል። ፓርቲው ከግንባር ወደ ውህደት ከተሸጋገረ በኋላ የመጀመሪያውን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ነው ያካሄደው። በስብሰባው ላይ ውይይት ከተደረገባቸው አጀንዳዎች መካከል ምርጫ 2012 አንዱ መሆኑ ታውቋል።
የዶ/ር ዐቢይ ብልፅግና ፓርቲ ምርጫው እንዲራዘም አልፈልግም አለ
ከኢህአዴግ የተፋታውና 29 ዓመት የዘለቀውን ድርጅት ያፈራረሰው አዲሱ የብልፅግና ፓርቲ የ2012 ብሄራዊ ምርጫ በያዝነው ዓመት እንዲካሄድ ጠንካራ አቋም መያዙን ገልጿል።
የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ትናንት በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ እና በቀጣዮ አገራዊ ምርጫ ዙሪያ ተወያይቶ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉን የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይ አረጋግጠዋል።
ብልፅግና ፓርቲ በምርጫው ዙሪያ የአቋም ለውጥ አላደረገም ያሉት አመራሩ፤ ፓርቲው ምርጫው በዚህ ዓመት መካሄድ አለበት የሚል እምነት እንዳለው አመላክተው ፤ ይህ ማለት ግን ፈታኝ ነገሮች የሉም ማለት አለመሆኑን እና ከዚህም በመነሳት ሥራ አስፈፃሚው በስብሰባው የምርጫው ስጋቶች እና መልካም እድሎች ዙሪያ በስፋት መክሮ የመፍትሄ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ገልጸዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ ኅብረተሰቡ ከምርጫው መካሄድ ጋር ተያይዞ የሚያነሷቸው ስጋቶችን እንደተወያየባቸው ፣ የምርጫው መካሄድ አልያም መራዘም የሚያስገኛቸው ጥቅሞች እና ጉዳቶች ላይ በስፋት መምከሩን ጭምር አስረድተዋል።
“ምርጫው ወቅቱን ጠብቆ የአገሪቱን የዲሞክራሲ ሥርዓትግንባታ እውን ለማድረግ ያግዛል፤ ኅብረተሰቡ የመረጥኩት መንግሥት ነው የሚያስተዳድረኝ የሚል እምነት እንዲኖረውም ያደርጋል” ያሉት አቶ ብናልፍ አንዷለም ፤ በብዙ መለኪያዎች ምርጫው ቢካሄድ የተሻለ መሆኑን በሥራ አስፈፃሚው ስብሰባ እንደተገመገመ እና በአገሪቱ አሁን ላይ የሚታዩ ችግሮችን ግን በቀላሉ እንደማይታዮም ገልጸዋል ።
የፀጥታ ችግሮቹን ለመፍታት የፀጥታ እና የፍትህ ተቋማት ሓላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ያሉት ሓላፊው፤ኅብረተሰቡም አጥፊዎችን በማጋለጥ የሰላም ቀናኢነቱን አሁንም አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ፣ እንዲሁም ተፎካካሪ ፓርቲዎችም አባላት እና ደጋፊዎቻቸውን ሰላምን ከሚያውኩ ተግባራት እንዲያርቁ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አድርገዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በትናንትናስብሰባው የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ አገሪቱን ወደ ተሟላ መረጋጋት ለመመለስ በየደረጃው ያሉ የፀጥታ መዋቅሮች ፀጥታ የማስከበር ሓላፊነታቸውን በሚገባ እንዲወጡ አቅጣጫ ከማስቀመጡ ባሻገርዓ በብልፅግና ፓርቲ የ10 መት እቅድ ላይም ዝርዝር ውይይት አካሂዶ ማፅደቁ አይዘነጋም።
ጎንደር ዮንቨርስቲ ግጭቶች ላይ ተሳትፈዋል ባላቸው ተማሪዎችና መምህራን ላይ እርምጃ ወሰደ
በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በሚከሰቱ ግጭቶች የሰዎች ሕይወት አልፏል፣ የአካል ጉዳት አጋጥሟል፣ በንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል። ከእነዚህም ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ችግሮቹን ለመፍታት “አንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ” የሚለውን ጨምሮ የተለያዩ መፍትሄ ይሆናሉ ያላቸውን ተግባራዊ እያደረግኹ ነው ብሏል።
በዚህም ታህሳስ 22/2012 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ፤ በግጭቶቹ በተለያየ ደረጃ ተሳትፈዋል ባላቸው ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና የጤና ባለሙያ ላይ እርምጃ መወሰዱን የዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ይዳኝ ማንደፍሮ ተናግረዋል።
እርምጃው የተወሰደው ከኅዳር 4 ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው ከተፈጠሩ ግጭቶች ጋር በተያያዘ ሲሆን በወቅታዊ ጉዳይ ላይ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩት ግለሰቦች በተለያዩ ማስረጃዎች፣ የዐይን ምስክሮች እና እጅ ከፍንጅ የተያዙ በመሆኑ እንደየ ተሳትፏቸው ቅጣቱ መተላለፉን ሓላፊዋ አስረድተዋል።
ሰላማዊ የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዳይቀጥል ለማደናቀፍ በተቀናጀ መልኩ በውጭም ካሉ ኃይሎች ግፊት በድርጊቱ ላይ የተሳተፉም ይገኙበታልም መባሉን ሰምተናል። በዚህም መሠረት 2 ተማሪዎች ለአንድ ዓመት፣ 39 ተማሪዎች ደግሞ ለሁለት ዓመት ከትምህርታቸው እንዲታገዱ፣ እንዲሁም 11 ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ከትምህርታቸው እንዲሰናበቱ ውሳኔ ተላልፏል።
ከዚህም በተጨማሪ ለ7 መምህራን የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ ለ3 መምህራን የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠና 3 መምህራን እና 8 የአስተዳደር ሠራተኞች እንዲሁም የጤና ባለሙያ ጭምር ሙሉ ለሙሉ ከሥራ እንዲሰናበቱ ዮንቨርስቲው መወሰኑን ለማወቅ ተችሏል።
“የአምቡላንስ አሽከርካሪ ግጭት ሲከሰት በሥራ ገበታው ላይ ባለመገኘቱ፤ ለአንድ ተማሪ ሞት ምክንያት ሆኗል” በሚልም ሙሉ ለሙሉ ከሥራው ተሰናብቷል። የጦር መሳሪያ አስቀምጠው የተገኙ ፕሮክተሮችም እርምጃው ከተወሰደባቸው የአስተዳደር ሠራተኞች መካከል እንደሚገኙበት የዮንቨርስቲው የኮሚኒዮኬሽን ሓላፊ አስታውቀዋል።
በወቅቱ ከነበረው የተማሪው ግድያ ጋር በተያያዘ የተያዙ ሰዎች ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሆነ ያስታወሱት ሓላፊዋ፤ አሁን ላይ እርምጃ የተወሰደባቸው “ሁከት የፈጠሩ፣ ያባባሱ፣ ተማሪዎችን የሚስፈራሩ መልዕክቶችን ሲለጥፉ የተያዙ” ናቸው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከከተማው አስተዳደር፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የክልል ልዩ ኃይል እና ኮማንድ ፖስት ግብረ ኃይል ጋር በመቀናጀት በተደረገ ማጣራት የተገኙ ማስረጃዎች ላይ ተመስርተው የተጠረጠሩት ግለሰቦች ላይ እርምጃ መወሰዱ እየተገለፀ ነው። ውሳኔውን የፌደራል ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባለሙያዎች ቡድን አባላት ከዩኒቨርሲቲው ሴናተሮች ጋር በመሆን ታህሳስ 22/2012 ዓ.ም ባካሄዱት ስብሰባ ነው ውሳኔውን ያሳለፉት።
ከዚህም በኋላ የዩኒቨርሲቲውንም ሆነ የከተማውን ማኅበረሰብ ሰላም ለማስከበር በመሰል ድርጊቶች ላይ በሚሳተፉ ማንኛውም የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ሴኔቱ አስጠንቅቋል።
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከፌደራል መንግሥትም ጋር በመሆን በግቢው ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ አማራጭ መፍትሔዎችን እያከናወነ እንደሆነ እና “አንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ ” የሚለውን ፕሮጀክት በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን አመራሮቹ ይናገራሉ:: በዚህ ፕሮጀክት በዩኒቨርሲቲ ያሉ ተማሪዎች በችግራቸው ጊዜ የሚያማክሩት፣ የሚከታተላቸው፣ የሚጠይቃቸው ቤተሰብ የሚፈጥሩበት ነው::
በተያያዘ ዜና ታህሳስ 21/2012 ዓ.ም በወሎ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ተከስቶ በነበረው ግጭት ጉዳት ከደረሰባቸው 3 ተማሪዎች መካከል የአንድ ተማሪ ሕይወት ማለፉ ይታወቃል። በተማሪው ግድያ የተጠረጠረ አንድ ተማሪ ከነተባባሪዎቹ ታህሳስ 22 ከምሽቱ 4፡00 አካባቢ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ዩኒቨርሲቲው በፌስቡክ ገፁ አስታውቋል።ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ማዋል የተቻለው በተማሪዎች ጥቆማ በተማሪዎች ማደሪያ (ዶርም) በተደረገ ፍተሻ ነው።
የአማራ ክልል ባለሀብቶች ቀን በባህር ዳር ከተማ ተከበረ
የአማራ ክልል ባለሀብቶች ቀን በባህር ዳር ከተማ በውይይት እየተከበረ ነው ተባለ። በሀብታሞቹ የውይይት ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ በግብርና ንዑስ ዘርፎች በሰብል ልማት፣ በእንስሳት ሃብት ልማት፣ በወተት ላም እርባታ እና በግብርና ማቀነባበር የተሰማሩ ባለሀብቶች መገኘታቸውም ተነግሯል።
ምክክሩ በክልሉ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ሰፊ እና ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያለመ መሆኑን የክልሉ የኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሓላፊ አቶ መላኩ አለበል ተናግረዋል። የክልሉን የኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማሳደግ ፣ በግብርና ኢኮኖሚው የሚስተዋሉ ችግሮችን ከባለሀብቱ ጋር በቅንጅት መፍታት አስፈላጊ መሆኑን ጭምር ጠቁመዋል።
ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና ምርታማነትን ለማሳደግም በግብርናው ዘርፍ ላይ በትኩረት መሠራት እንደሚገባ እና የማሌዥያን ተሞክሮ መውሰድ በቂ ነው ተብሏል::
በትራምፕ ትእዛዝ የተገደሉት ጀነራል አስከሬን ወደ ኢራን ተሸኘ
በፕሬዝደንት ትራምፕ ትእዛዝ የተገደሉት ጀነራል ቃሲም ሱሊይማኒ አስክሬን ከኢራቅ ወደ ኢራን ተሸኝቷል። የጀነራሉን አስክሬን ለመሸኘት በሺዎች የሚቆጠሩ ኢራቃዊያን አደባባይ ወጥተው ”ሞት ለአሜሪካ” ሲሉም ድምጻቸውን አሰምተዋል።
በአሜሪካ የተገደሉት ጀነራሉ አስክሬን ወደ ኢራን ከተሸኘ በኋላ በተወለዱበት ከተማ ገብዓተ መሬታቸው የፊታችን ማክሰኞ ይፈጸማል ተብሏል።
ኢራቃዊያኑ አስክሬኑን ለመሸኘት ከንጋት ጀምሮ ወደ አደባባይ መትመም የጀመሩ ሲሆን ፣ ብዙዎቹም የኢራቅን ሰንደቅ ዓላማ፣ የጀነራል ሱሊማኒን እና የኢራናዊውን የሃይማኖት መሪ አያቶላህ አሊ ካህሜኒን ምስል ይዘው ታይተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ጀነራል ቃሲም ሱሊማኒ የተገደለው ጦርነት ለማስቆም እንጂ ለማስጀመር አይደለም ማለታቸው አይዘነጋም።
በኢራን እና በመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ የነበሩት ጀነራል ቃሲም ሱሊማኒ በፕሬዝደንት ትራምፕ ትዕዛዝ እንዲገደሉ ከተደረገ በኋላ፤ ትራምፕ ‘ሦስተኛውን የዓለም ጦርነት አስጀመሩ’ ያሉ በርካቶች ናቸው። ፕሬዝደንት ትራምፕ ግን የሱሊማኒ ”የዓመታት የሽብር አገዛዝ አብቅቶለታል” በማለት ነው የተናገሩት።
ጉዳዮን አስመልክተው ፕሬዝደንት ትራምፕ ከፍሎሪዳ ግዛት ሆነው በሰጡት መግለጫ፤ “የአሜሪካ ወታደሮች በቅንጅት ባካሄደው ኦፕሬሽን፤ ቁጥር አንድ የዓለማችንን አሸባሪ ገድለዋል” ካሉ በኋላ ፤ “ሱሊማኒ በማንኛውም ሰዓት ሊቃጣ የሚችል የሽብር ሴራ በአሜሪካ ዲፕሎማቶች እና የጦር መኮንኖች ላይ ሲያሴር ነበር። ይህንን ሲፈጽም ያዝነው፤ አስወገድነው” ሲሉም በይፋ ተናግረዋል።
በሌላ ዜና ጀነራሉ ከተገደሉ ከ24 ሰዓታት በኋላ አሜሪካ ዛሬ ጠዋት ሌላ የአየር ጥቃት በኢራቅ ፈጽማ እንደነበር የኢራቅ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል። ምንም እንኳን ይህ ዜና በአሜሪካ በኩል ባይረጋገጥም ፣ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያው ቅዳሜ ንጋት ላይ በተፈጸመው የአየር ጥቃት ተጨማሪ 6 ሰዎች ተገድለዋል ነው ያለው።
ጀነራል ቃሲም ሱሊማኒ፤ የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ኩድስ ኃይል አዛዥ በትራምፕ ትዕዛዝ ከተገደሉ በኋላ በቀጠና አሜሪካ ጠል እንቅስቃሴዎች ተንሰራፍተዋል። ይህንን ተከትሎም የትራምፕ አስተዳደር በቀጠናው ለሚገኙ ዲፕሎማቶች እና አጋሮቿ ደህንነት ሲባል ተጨማሪ 3000 ወታደሮች ወደ መካከለኛው ምስራቅ እንደሚልኩ ማረጋገጫ ሰጥተዋል::
የጀነራሉ መገደል በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ያለውን ውጥረት ከፍ አድርጎታል። የኢራን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ጃቪድ ዛሪፍ በትዊተር ገጻቸው ላይ አይኤስ፣ አል ኑስራህ፣ አል-ቃይዳ የመሳሰሉ የሽብር ቡድኖችን ሲዋጋ የነበረውን ጀነራል የመግደል እርምጃ እጅግ አደገኛ እና የሞኝ ውሳኔ ነው ማለታቸውን ኢትዮጵያ ነገ ትናንት መዘገቡ ይታወሳል።