በእስክንድር ነጋ አቀባበል ላይ ባንዲራ የነጠቁ ፖሊሶች ከወጣቶችና ጋዜጠኞች ጋር ተጋጬ
የባላደራው መሥራችና በአዲስ አበባ የባለቤትነት መብት ላይ በኢትዮጵያውያን ዘንድ መልካም መነቃቃትን የፈጠረው ጋዜጠኛና አክቲቪስት እስክንድር ነጋ አዲስ አበባ ሲገባ በአዲስ አበባ ወጣቶች ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።
የፊንፊኔ ኬኛ ፖለቲካን በሚያቀነቅኑ ቄሮዎችና የኦዴፓ (የኦሮሚያ ክልል ጽንፈኛ ባለስልጣናት) ተደጋጋሚ ትችቶችና ትንኮሳዎች ሲደረግበት የቆየው እስክንድር ነጋ በአሜሪካና አውሮፓ ለሚገኙ ዓለም ዐቀፍ ማኅበረሰብ አባላት በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው ቄሮ በማናለብኝነት ብሔር ተኮር ጥቃት ባለፉት 18 ወራት እያደረሰ መሆኑን በአደባባይ ማሳወቁን ተከትሎ በጽንፈኛ የኦሮሞ ብሔርተኞች በኩል ወደ አገር ቤት ሲመለስ ጥቃት ሊደርስበት እንደሚችል የሚጠቁሙ ፍንጮች በስፋት ታይተው ነበር::
ይህንን ተከትሎ ከብሔራቸው ይልቅ ኢትዮጵያዊነትን እና አንድነትን የሚያመልኩት የአዲስ አበባ ልጆች ተደራጅተው አስፈላጊውን ጥበቃ ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል:: በዚህ መሠረት ዛሬ ጠዋት ለአቀባበል በርካታ እንግዶችና ወጣቶች ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቢመጡም ከጅምሩ የተለያዮ ትንኮሳዎች እንደገጠማቸው የአቀባበል ሥነ ሥርዐቱን በኤርፖርት ተገኝቶ የተከታተለው የኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር ለመታዘብ ችሏል::
ወጣቱን ለመተናኮስና ግጭት ለመፍጠር የፈለጉ ኃይሎችን ህግና ሥርዐት አክባሪው የአዲስ አበባ ወጣት በጨዋ መልክ ባይሸኛቸው ኖሮ በቦታው ከፍተኛ ግጭት ሊፈጠር ከመቻሉ ባሻገር የእስክንድር ነጋንና የባላደራውን አካሄድ በእጅጉ የሚቃወመው የታከለ ኡማ አስተዳደርና ፌደራል መንግሥቱ አጋጣሚውን ተከትሎ ለፖለቲካዊ የፕሮፐጋንዳ ትርፍ ሊጠቀምበት ይችል እንደነበርም መገመት ይቻላል። የሚሉ አስተያየቶችም ተሰንዝረዋል።
ለአዲስ አበባ ባለአደራው ም/ቤት ሰብሳቢ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አቀባበል በተዘጋጀ ባነርና ባንዲራ ላይም በቦሌ አየር መንገድ የነበሩ የፌደራል ጥበቃ አካላት ከአዲስ አበባ ወጣቶች ከፍተኛ ውዝግብ ፈጥረው ነበር:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ወደ ፊት ህገ መንግሥታዊ ምላሽ ያገኛል በማለት አሁን ላይ በይፋ እየተውለበለበ ያለውን ንጹሁን ሰንደቅ ዓላማ እንዳይውለበለብ ብለው ባይደነግጉም የፊንፊኔ ኬኛ ልክፍተኛ የፀጥታ አመራሮች ሆን ብለው የመደቧቸው ናቸው የተባሉ የፌደራል ፖሊሶች ወጣቶችን “የያዛችሁት ባንዲራ ህጋዊ አይደለም” በሚል መንጠቃቸውን ተከትሎ አለመግባባት ተከስቷል::
” የያዝነዉ ባንዲራ የኢትዮጵያ ባንዲራ አይደለም በማለት ቀምተዉናል ” ሲሉ ለሪፖርተራችን አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች “ፖሊሶቹ ይኸው እንዳያችሁት እኛን ለማናደድና የግጭት ክስተት ለመፍጠር ሆን ብለው በኦሮሚኛ እያወሩ ናቸው:: እኛን ግራ የገባን አገሪቱን እየጠበቀና ህግ እያስከበረ ያለው የፌደራል ፖሊስ ነው ወይንስ የኦሮሚያ ፖሊስ?” በማለት ጠይቀዋል::
ልቅ የሆነ ሥርዐት አልበኝነትና ሆን ብለው ግጭት የመቀስቀስ ከፍተኛ ርሃብተኝነት የታየባቸው በስፍራው የተገኙ የፌደራል ፖሊስ ልብስ የለበሱ የፀጥታ አካላት ጉዳዩን ለመከታተል የመጡ ጋዜጠኞችንም ለመተናኮስ ከመፈለጋቸው ባሻገር “እናንተን ብሎ ጋዜጠኞች ፣ ለሽብር ሆን ብላችሁ የምትሯሯጡ ጸረ-ሰላም ናችሁ” በማለትም በይፋ ሲዘልፉና ሲያንጓጥጡም ታይተዋል::
ከዚህ በተጨማሪ የእስክንድር ነጋን አቀባበል ለመዘገብ ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከተገኙ የተለያዮ ሚዲያ ጋዜጠኞች መሀል አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ያለው ቲሸርት የለበሰው የኢትዮጵያ ነገ ዘጋቢ “የትም ቦታ ተገኝተን ያየነውን ለህዝብ ማድረስ መብታችንና ሙያዊ ግዴታችን ነው” ማለቱን ተከትሎ ከሌሎች ጋዜጠኞች መሀል ተነጥሎ ተወሶዶ ለ40 ደቂቃ በኤርፖርቱ ፖሊስ ስቴሽን ውስጥ በጥበቃ ስር እንዲቆይ ተደርጎ በስተመጨረሻ በአዛዦች ትእዛዝ ወደ ሥራው እንዲመለስ ተደርጓል።
ብልጽግና ፌደራሊዝሙን እንደሚንከባከብ ንጉሱ ጥላሁን አስታወቁ
ብልጽግና ፓርቲ “የቆመባቸው ምሰሶዎች ፌዴራሊዝሙን የሚጠብቁና የሚንከባከቡ ናቸው” ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬቴሪያት ሓላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተናገሩ።
አቶ ንጉስ ሰሞኑን እንደገለጹት የብልጽግና ፓርቲ ግብ የኢትዮጵያዊያን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም ባህላዊ፣ ስነ አእምሮአዊና ስነ ልቦናዊ ሁኔታን ባካተተ መልኩ ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ ነው።
የብልጽግና እሴቶች ተብለው የሚጠቀሱት ህብረ አገራዊ አንድነት፣ የዜጎች ክብርና ነጻነት መሆናቸውም ተጠቁሟል።“ኢትዮጵያ አሃዳዊነትን ላትመልስ ሸኝታዋለች። ይህ ዓይነቱ ስርዓት ሊታሰብ አይችልም።” ነው ያሉት አቶ ንጉሱ::
አገሪቷ ባለፉት ዓመታት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ቅኝት ስትመራ እንደነበር አስታውሰው፤ በዚህ ወቅት ያጣቻቸውን እሴቶች በመመለስ ያገኘቻቸውን መልካም ጎኖች ለማስቀጠል መስራት አስፈላጊ ነው ካሉ በኋላ ፌዴራላዊ ስርዓቱን በማፍረስ አሃዳዊነትን መገንባት የማይታሰብ መሆኑን እና አሀዳዊነት ህብረ ብሄራዊ አንድነትን የሚንድ መሆኑንም ይፋ አድርገዋል።
አገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥና እውነተኛውን ፌዴራላዊ ስርዓት ለመገንባት ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ፣ ህብረ ብሄራዊ አንድነት ከሰው ልጆች ባህርይ ተነስቶ ወደ አገራዊ ባህርይ ጎልብቶ የሚያድግ መሆኑንም አመላክተዋል።
ብልፅግና በኢትዮጵያ ያሉ በርካታ ቋንቋ ባህልና ማንነትን ተከትለው ለተነሱ ጥያቄዎች ተገቢው ምላሽ ባለመሰጠቱ ጥያቄ ሆኖ የተነሳና ያታገለ አጀንዳ ነው ያሉት አቶ ንጉሱ፤ ብልጽግና የዜጎችን ክብር የሚያረጋገጥ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያውያን የግለሰብና የቡድን መብታቸው የሚከበርበት ግለሰባዊና ተቋማዊ ጭቆናዎች የሚወገዱበት ስርዓት እንደሚያሰፍንም ገልጸዋል።
የዮንቨርስቲ ምሩቃንን በዘመናዊ ሶፍትዌር አሰልጥኖ ወደ ሥራ ለማስገባት ሀሳብ ቀረበ
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችንና ምሩቃንን በዘመናዊ የሶፍትዌር መተግበሪያ አሰልጥኖ ወደ ቴክኖሎጂ ለማስገባት ያቀደ ሃሳብ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ተባለ።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ፕሮፈሰር አፈወርቅ ካሱ ከአገርኛ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ቢያግ ሚን ጋር በቀረበው ሃሳብ ላይ መወያየታቸውም ተሰምቷል። የቀረበው ሃሳብ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን እና ሥራ ፈላጊ ምሩቃንን አስፈላጊ የኮምፒውተር ቋንቋዎችን በማሰልጠን ለማብቃት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ፕሮፈሰር አፈወርቅ ካሱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጅ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ በኢትዮጵያ እንደ ጃቫ ባሉ የኮምፒውተር ቋንቋ ዘርፍ በቂ የሰለጠኑ ባለሙያዎች አለመኖራቸውንም አስረድተዋል። ተማሪዎችንና ምሩቃንን በማብቃት በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪው ውስጥ እንዲሠሩ ለማዘጋጀት እቅድ እንዳላ አመላክተዋል።
አገርኛ በኮሪያ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ በነበሩ ኢትዮጵያውያን የዛሬ 10 ዓመት የተሰራ አማርኛ ለመፃፍ የሚያስችል የሞባይል መተግበሪያ ስያሜ መሆኑን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።
የግዙፉ የቻይናው ኑክቴክ ኩባንያ ልዑካን አዲስ አበባ ገቡ
የቻይና ኑክቴክ ኩባንያ ልዑካን ቡድን አባላት አዲስ አበባ መግባታቸው ተሰማ። ልዑካን ቡድኑ በጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ላይ መተከል ባለበት ማሽኖች ዙሪያ ሥራ ለመጀመር አዲስ አበባ መግባቱን የገቢዎች ሚኒስቴር ነው ይፋ ያደረገው።
የቻይና ልዑካን ቡድኑ የጉምሩክ ፍተሻ ጣቢያዎች በዘመናዊ ፍተሻ መሳሪያዎች መተካት በሚቻልበት ሁኔታ ዝርዝር ሥራዎች ላይ ከገቢዎች ሚኒስቴርና ከጉምሩክ ኮሚሽን አመራሮች ጋር ዛሬውኑ ውይይት ማድረግ መጀመሩም ታውቋል።
በውይይቱ ወቅት የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ዝርዝር የጋራ እቅድ በፍጥነት ተጠናቆ ወደ ተግባር መገባት እንዳለበት ገልጸዋል ነው የተባለው።
የቻይና ኑክቴክ ኩባንያ ልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ከዚህ ቀደም በቻይና ጉምሩክ እና በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን መካከል ተደርጎ የነበረውን ስምምነት መሰረት በማድረግ ነው። በገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የተመራ ልኡክ ባሳለፍነው ታህሳስ ወር በቻይና ጉብኝት ማድረጉ አይዘነጋም።
በጉብኝቱ ወቅትም ገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከቻይና የጉሙሩክ አስተዳደር ሚኒስትር ጋር የተወያዮ ሲሆን ፤ በምክክሩም ህገ ወጥ የንግድ ስርዓትን፣ የዕፅ ዝውውርን ለመቆጣጠር እንዲሁም የጉሙሩክ ሥርዐትን ለማዘመንና የጉሙሩክ መረጃዎችን ለመለዋወጥ አንድ የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲዋቀር መደረጉ ይታወቃል።
የቴክኒክ ኮሚቴ ቡድኑ አዲስ አበባ በመምጣት ከኢትዮጵያ ቡድን ጋር የኢትዮጵያን የጉሙሩክ አገልግሎት አሰጣጥ የሚጎበኝ መሆኑ መገለፁም ይታወሳል። ከዚህ ባለፈም የተለያዩ የቴክኖሎጂ አገልግሎት ድጋፎችን ለኢትዮጵያ ጉሙሩክ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፥ ለጉሙሩክ አገልግሎት ሠራተኞች የተለያዩ ስልጠናዎችን እንደሚሰጥም በወቅቱ ተገልጿል።
አሁን ወደ አዲስ አበባ የመጣው ልኡካን ቡድንም በስምምነቱ መሰረት በጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ላይ መተከል ባለበት ማሽኖች ዙሪያ ሥራ ይጀምራል ተብሏል።