የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥር 4 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥር 4 ቀን 2011 ዓ.ም

የታከለ ኡማ አዲስ አበባ መስተዳደር 50 ቢሊዮን ብር ዕዳ አለበት ተባለ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከቤቶች ልማት ጋር በተያያዘ 50 ቢሊየን ብር የባንክ እዳ እንዳለበት ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ አስታወቁ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራ የምክር ቤቱ አባል፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ እና ካቢኔያቸው ጋር ዛሬ ተወያይተዋል። በውይይቱ ወቅት ኢንጅነር ታከለ ኡማ የከተማዋን ፀጥታ ለማስጠበቅ ኅብረተሰቡን እና ወጣቶችን በማደራጀት በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

የከተማውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስም የተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸው፤ ለአብነትም በቀጣይ ወር ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው የሸገር የዳቦ ፍብሪካ እና ወደ ግንባታ የገባው የዘይት ማምረቻ ፋብሪካ የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል። በተጨማሪም ወደ ከተማዋ በ5 በሮች የሚገቡ የአርሶ አደር ምርቶችን ቀጥታ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ የሚሆኑበትን አሠራርን እየሠራን ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው።

ለከተማዋ ነዋሪ የዲጂታል መታወቂያ ለመስጠትም በከተማዋ ካሉት 116 ወረዳዎች ውስጥ 100 ወረዳዎች ላይ ሥራቸው መጠናቀቁን እና ቀሪዎቹ ወረዳዎችም በቅርቡ እንደሚጠናቀቁ አመላክተው ፤ በተያዘው የበጀት ዓመት ለ250 ሺህ ወጣቶች ቋሚ የስራ እድል ለመፍጠር እየተሠራ ሲሆን ፣ እስካሁን ለ150 ሺህ ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩንም ገልፀዋል።

ከቋሚ ኮሚቴዎቹ አባላትም ከመኖሪያ ቤት ግንባታ መዘግየት፣ ከመሬት ወረራና ሰነድ አልባ ይዞታዎች ጋር ተያይዞ ለተነሱት ጥያቄዎች ምክትል ከንቲባው ምላሽ ሰጥተዋል። ከቤቶች ልማት ጋር በተያያዘ ለሚነሱት ቅሬታዎች አስተዳደሩ በለውጥ ስራው ያለቁትን የማስተላለፍና የተጀመሩትን በፍጥነት የመጨረስ ሥራመሠራቱን ኢንጅነር ታከለ አስረድተዋል።

በከተማው በስምንት ወራት ብቻ ስምንት ሕንጻዎች ያሉት 1 ሺህ 700 ቤቶችን ሠርቶ መጠናቀቁን የተናገሩት ታከለ ኡበቀጣይም በመሃል ከተማዋ ግንባታቸው የተጠናቀቁ 38 ሺህ ቤቶችም ለነዋሪዎች ይተላለፋሉ ብለዋል።

ኢንጂነር ታከለ የቤት ባለዕድለኞች ከባንክ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥማቸውን ችግሮች ማቃለል እንደተቻለ ጠቁመው፤ አሁንም ችግሮች መኖራቸውን እንዲሁም ቤቶች በፍጥነት ተገንብተው ለባለዕድለኞች ባለመተላለፋቸው የከተማ አስተዳደሩ 50 ቢሊየን ብር የባንክ እዳ እንዳለበትም ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ይፋ አድርገዋል።

40/60 እና 20/80 የቤት ልማት መርሃ ግብር የተገነቡ መሆናቸውን ገልጸው፤ ይህ የሆነው ቤቱን የወሰዱ ሰዎች በትክክል ወለድና ኢንሹራንስ መክፈል ባለመጀመራቸው መሆኑን ተናግረዋል። አያይዘውም 130 ሺህ ቤቶች ተገንብተው በወቅቱ ለባለዕድለኞች ባለመተላለፋቸው እንዲሁም በአጋጣሚ የተላለፉትንም ግለሰቦች ገብተው ኑሮ ባለመጀመራቸው እንደሆነም ጠቁመዋል።

ይህ መሆኑ ደግሞ የመንግስት ተቀማጭ ገንዘብ ላይ የራሱን ጫና እያሳደረ በመሆኑ ከባንክ ጋር እየተነጋገርን ነው ያሉት የሥልጣን ጊዜያቸው ያለፈው ከንቲባ ታከለ ኡማ ፤ ዘንድሮ በከተማው 500 ሺህ ቤቶች ለመገንባት የታቀደ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ 175 ሺህ ቤቶች በመንግስት ቀሪዎቹ ደግሞ በባለሀብቶች የሚገነቡ መሆናቸውን አስረድተዋል::


ጥምቀትን በጎንደር በልዮ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው

የጥምቀት በዓልን በጎንደር ለማክበር ዝግጅት መደረጉን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ገለፀ። የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ማስተዋል ስዩም ለክርስትና እምነት ተከታዮች ትልቅ በዓል የሆነው ይህንን ክብረ በዓል አስመልክቶ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ዛሬ ይፋ አድርገዋል።

በዓሉ በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ ሲከበር እንደከዚህ ቀደሙ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ አገር እንግዶች እንዲታደሙ እየተሠራ መሆኑን እና ከ2 ሚሊየን በላይ ሰዎች ይሳተፉበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው ያስረዱት።አያይዘውም እንግዶችን በብቃት ለማስተናገድ ዐቢይ እና ንዑሳን ኮሚቴዎች በየዘርፉ ተዋቅረው ሰፊ ሥራ ተሰርቷል ነውያሉት። የጥምቀት በዓል ያለው ሃይማኖታዊና ባህላዊ ገፅታው ሳይበረዝ እንዲከበር በጥንቃቄ እየተሠራበት እንደሚገኝም አክለዋል።

በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅም የጎንደር ከተማና የአካባቢው ሕዝብ እንግዶችን ተቀብሎ በማስተናገድ በኩል የድርሻውን እንዲወጣም ከንቲባው መልእክት አስተላልፈዋል። የጥምቀት በዓል በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት ከተመዘገበ ወዲህ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚከበር አይዘነጋም።


የስፖርት አወራራጆች (Beting) በከፍተኛ የበጎ አድራጎት ተግባር ላይ ልንሰማራ ነው አሉ

በሀገሪቱ እየተስፋፋ ለመጣው የስፖርት ውርርድ ጨዋታ አዲስ ፈቃድ መስጠት ማቆሙን የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር አስታወቀ። የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶቹ በበኩላቸው ውድድሩን አስመልክቶ በአንዳንድ ሚዲያዎች በኩል ሰሞኑን እየተካሄደ ያለው ቅስቀሳ በኅብረተሰቡ ዘንድ የተሳሳተ ግንዛቤ እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል::

ጨዋታው ላይ የተግባር ቁጥጥርን አጥብቆ ለመስራት የሚያስችለውን የአሰራር ስርዓት እስከሚዘረጋ ድረስ አዲስ ፈቃድ መስጠት ማቆሙን የገለጹት የብሔራዊ ሎተሪ አመራሮች የስፖርት ውድድሩ ኢትዮጵያ ውስጥ በሕግ ማዕቀፍ ስር ሆኖ መተግበር የጀመረው ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ የነበረ ቢሆንም በከፍተኛ ሁኔታ የተስፋፋው ግን ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ እንደሆነ አረጋግጠዋል::

የውርርድ ተቋማት ተብለው ህጋዊ ፈቃድና እውቅና የተሰጣቸው ድርጅቶች፣ የዳበሩ ድረገፆች ያሏቸው፣ አማራጭ የአንድሮይድ መተግበሪያን መጠቀማቸው እና አለፍ ሲልም ይህ ላልገባቸው በአዲስ አበባ እና በክልሎች የተለያዩ ቦታዎች የመወራረጃ ትኬትን መሸጣቸው ወጣቶች እና ታዳጊዎችን በቀላሉ እንዲይዙ አድርጓል ቢባልም አወራራጅ ድርጅቶቹ ዕድሜያቸው 18 ዓመት ያልሞላቸው ልጆችን ፈጽሞ በአሠራራቸው እንደማያስቆርጡ ፣ ይህንን ላለማድረግም ቅድመ ግዴታ ተቀብለው ወደ ሥራ መግባታቸውን አብራርተዋል::

ሁለቱ ወገኖች ጉዳዮን አስመልክቶ ዛሬ በአዲስ አበባ ጎልደን ቱሊፕ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በአሁኑ ሰዐት በአገሪቱ 22 የሚሆኑ ድርጅቶች በስፖርታዊ ውርርድ ጨዋታ ላይ ፍቃድ አውጥተው እየሠሩ ሲሆን ሌሎች 13 ድርጅቶች ፍቃድ ወስደው ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችላቸውን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶቹ (ቤቲንግ) ከሚያገኙት ትርፍ ላይ አስቀድመው በገቡት የውዴታ ግዴታ ውል መሠረት እያንዳንዳቸው 20 ፐርሰንት ለበጎ አድራጎት ተግባር እያዋሉ መሆናቸውን አስታውሰው በቀጣይ ለዘለቄታው ተጨማሪ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ለመሥራት ፣ በተለይም ወጣቶችና ሴቶችን በሚደግፉ ፕሮጀክቶችን ለማገዝ እቅድ ነድፈው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን እንደገለጹ ጋዜጣዊ መግለጫውን የተከታተለው የአዲስ አበባ ዘጋቢያችን አድርሶናል::

“ሁሉም የስፖርት አወራራጆች” በሚል በቀጣይ ሁሉንም ድርጅቶች ያቀፈ ማኅበር ለመመስረት ሕጋዊ እንቅስቃሴው መጀመሩን የገለጹት አወራራጆች ዘርፉ በፋይናንስ ረገድ ለመንግሥት ከፍተኛ ገቢ እያስገባ ያለና ለአገር ኢኮኖሚ መጎልበትም የበኩሉን የሚያበረክት አዲስ አማራጭ ሆኖ መምጣቱን ከማመላከታቸው ባሻገር እስካሁን ለ1220 ( (አንድሺኅ ሁለት መቶ ) ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ይፋ አድርገዋል::

ዶ/ር ዐቢይ ስለሽልማታቸው መመዘኛ ፤ ዶናልድ ትራምፕ የኖቤል አዘጋጆችን እንዲጠይቁ ምላሽ ሰጡ

ከቀናት በፊት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በአገራት መካከል ሊከሰት የነበረን ትልቅ ጦርነት ማስቆማቸውን እና እርሳቸው ጦርነት እንዳይከሰት በማድረጋቸው የአገሪቱ መሪ የኖቤል ሽልማትን እንዲያገኙ ስለማስቻላቸው ገልጸው ነበር።

ይህ የትራምፕ ንግግር ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ብዙዎችን አድርሷል:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። ለይፋዊ ጉብኝት በደቡብ አፍሪካዋ ዋና ከተማ ፕሪቶሪያ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተያየት ” እኔ ስለ ሽልማቱ አካሄድ የማውቀው ነገር የለም” ነው ያሉት።

”የኖቤል ሸልማት ኮሚቴው አሸናፊዎችን ለመመርጥ ከግምት ውስጥ ስለሚያስገባቸው መስፈርቶች ምንም የማውቀው ነገር የለም። ፐሬዝዳንት ትራምፕ ቅሬታ ካላቸው ኦስሎ ወደሚገኘው ኮሚቴ ሄደው ቅሬታቸውን ማሰማት ይችላሉ። እኔ ሽልማቱን ለማግኘት ብዬ አይደለም የምሠራው። በቀጠናው በጣም ወሳኝ ነገር ለሆነው ሰላም ነው የምሠራው” ሲሉም ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ንግግር ምላሻቸውን አድርሰዋል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ በንግግራቸው ስለ የትኛው አገር መሪ ወይም በየትኞቹ አገራት መካከል ሊከሰት ስለነበረው ትልቅ ጦርነት በቀጥታ ያሉት ነገር ባይኖረም፤ አብዛኞች ግንከኢትዮጵያው መሪ እና የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ፣ እንዲሁም ከግብጽ እና ኢትዮጵያ ጋር እያገናኙት ነው።

ከግብጽ በተጨማሪ ጉዳዩን ከኤርትራ እና ኢትዮጵያ ጋር ያያዙትም አልጠፉም። ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ”ስለ የኖቤል የሰላም ሽልማት ልነግራችሁ እችላለሁ፤ ከስምምነት ደረስኩኝ፤ አገር አዳንኩኝ፤ እንደሰማሁት የዚያ አገር መሪ አገሩን በመታደጉ የኖቤል ሽልማት ማግኘቱን ሰማሁ። እኔ በዚህ ላይ ተሳትፎ ነበረኝ? አዎ!። ግን እኛ እውነታውን እስካወቅነው ድረስ ምንም አይደለም፤ ትልቅ ጦርነት ነው ያስቀረሁት። ሁለት አገሮችን ነው ያዳንኩት።” ሲሉ ነበር የገለጹት::


የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የጥራት መጎደል አለበት ተባለ

ኢትዮጵያ ረጅም ዕድሜን ካስቀጠሩና ጥንታዊ የግንባታ ታሪክ ካላቸው የዓለም አገሮች መካከል አንዷ ብትሆንም አሁን ላይ የሚታየው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የጥራት መጓደል ችግር ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከብሄራዊ ሥነ ልክ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በክልልና በከተማ አስተዳደሮች ከሚገኙ የኮንስትራክሽን ላብራቶሪ ማዕከላት ለተውጣጡ አመራርና ባለሞያዎች ስልጠና በመስጠት ላይ ነው።

በኢትዮጵያ የሚከናወነው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እመርታ የማሳየቱን ያህል በውስጡ እየታየ ባለው የጥራትና የደህንነት ችግር ምክንያት በሰው፣ በአካባቢ፣ በኢኮኖሚ እና በአገር ላይ ፈተናዎች እየተደቀኑ መምጣታቸውን በሚኒስቴሩ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ አሰራር ማሻሻያ ቢሮ ሓላፊ አቶ ቴዎድሮስ ተገኘ ተናግረዋል።

በመሆኑም በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሚታየውን የጥራት መጓደል ችግር ለመቅረፍ እንዲሁም በዘርፉና በአገር ላይ እየታየ ያለውን ውድመት ለመታደግ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ያሉበትን ማነቆዎች ለመፍታት የኮንስትራክሽን ላብራቶሪዎችን አቅም መገንባትና የአሠራር ሥርዐት ቀርፆ ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚያስፈልግም ።

ለአምስት ተከታታይ ቀናት ይቆያል በተባለው ስልጠና ላይ በኮንስትራክሽን ላብራቶሪዎች ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክፍተቶችን በመዳሰስ ፤ የአገልግሎቱን ጥራት ለማስጠበቅ በመሳሪያዎቹ አጠቃቀምና አያያዝ እንዲሁም የካሊብሬሽን (ልኬት) አገልግሎት እና የተበላሹ የላብራቶሪ መሳሪያዎች ጥገና ላይ፣ የላብራቶሪ ሓላፊዎችና ባለሞያዎች በቂ ስልጠና ያገኛሉ መባሉንም የደረሰን መረጃ ያሳያል፡፡

ቻይና የአውሮፓ ኅብረትና አሜሪካ በዙምባቡዌ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ እንዲያነሱ አሳሰበች

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር፤ አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት በዚምባብዌ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ እንዲያነሱ ጠይቀዋል።

ሚንስትር ዋንግ ይ፤ በዚምባብዌ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ምንም ዓይነት ዓለም ዐቀፋዊ አግባብነት የሌለው ነው ብለዋል። ሚንስትሩ ይህንን ያሉት ዚምባብዌን እየጎበኙ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ነው።

“አንዳንድ ተቋማትና አገራት በዚምባብዌ ላይ የጣሉት ማዕቀብ ዓለም ዐቀፋዊ መሰረት የሌለውና የዚምባብዌን የመልማትና የማደግ መብት የሚጻረር ነው” ሲሉ ሚንስትር ይ ከብሉምበርግ ጋር በነበራቸው ቆይታ ላይ አቋማቸውን በይፋ አሰምተዋል::

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ይ ወደ ዚምባብዌ ያመሩት ቅዳሜ ነው:: በአፍሪካ በሚኖራቸው ቆይታም አምስት አገራትን የመጎብኘት መርሐ ግብር ይዘው እየተንቀሳቀሱ ሲሆን ፤ቀደም ብለው ጂቡቲ፣ ኤርትራና ግብጽን ጎብኝተዋል::በቀጣይ ደግሞ ቡሩንዲን ጎብኝተው የአፍሪካ ቆይታቸውን ያጠናቅቃሉ ነው የተባለው።

ዚምባብዌያዊያን የተጣለባቸውን ማዕቀብ ለማስነሳት አንዱ ግፊት የመፍጠሪያ መንገድ በማድረግ ባለፈው ጥቅምት ወር ባለስልጣናቱ ዓመታዊ በዓል እስከማዘጋጀት መድረሳቸው ይታወሳል።

አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት በዚምባብዌ የሚታየው ዴሞክራሲ፣ የሰብኣዊ መብት አያያዝና የሚዲያ ነጻነት ከመጠን በላይ በመንግሥት ጫና ውስጥ የሚገኝ ነው በማለት ነው ማዕቀቡን የጣሉት። በማዕቀቡም ግለሰቦችንና ኩባንያዎችን ኢላማ ተደርገዋል።

አሜሪካ፤ ፕሬዝዳንት ምናንጋግዋን ጨምሮ በ85 ግለሰቦች ላይ የጉዞና የፋይናንስ ማዕቀብ ጥላለች። 56 የዚምባብዌ ኩባንያዎችም ተመሳሳይ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል። የአውሮፓ ኅብረትም በተመሳሳይ በግለሰቦችና በኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጥሏል። ማዕቀቡ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ሙጋቤ ዘመን የተጣለ ቢሆንም አሁን ነባራዊ ሁኔታዎች መቀየራቸውን ለመገምገም በሚቀጥለው የካቲት ወር ቀጠሮ ተይዞለት ውሳኔው ከወዲሁ በጉጉት እየተጠበቀ ነው።

LEAVE A REPLY