ሰዎች ትክክለኛውን መንገድ ያሳዩናል፣ ቅዱሱን የእግዚአብሔር ቃል ያስተምሩናል፣ በትክክለኛውም መንገድ ይመሩናል ባሏቸው እና ራሳቸውን ‹‹ነብያት›› ብለው በሚጠሩ ግለሰቦች ግፍ ሲፈጸምባቸው እና እንባቸውም በአደባባይ ሲፈስ መታዘብ ከጀመርን ዋል አደር ብለናል።
በዚህም ረገድ በእነዚህ ራሳቸውን ከፈጣሪ የተላኩ ‹‹መልዕክተኞች›› ወይም ‹‹ነብያቶች›› ብለው በሚጠሩ ሰዎች ምክንያት ምዕመናን ተሰድደዋል፣ ተደብድበዋል፣ ታስረዋል ከፍ ሲልም ውድ ሕይወታቸውን እንዲያጡ ሆነዋል። ‹‹ሃይ›› ባይ አለመገኘቱ ደግሞ ችግሮች ከቀን ወደ ቀን እንዲጨምሩ እና ጉዳቱም እንዲከፋ አድርጓል።
የአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ በእነዚህ ግለሰቦች ጉዳት ደርሶብናል ያሉ አካላትን አናግሮ፣ የተወሰኑ የአምልኮ ስፍራዎችንም ጎብኝቶ እንዲሁም ባለ ድርሻ አካላትን ከባለሙያዎች አስተያየት ጋር አካቶ የሐተታ ዘ ማለዳ ጉዳይ አድርጎታል።
የ34 ዓመት ወጣት የሆነው አቤል አዲሱ የአራት ልጆች አባት ነው። ከሦስት ዓመታት በፊት ከአዲስ አበባ የተለያዩ የቀለም ምርቶችን በመጫን ወደ ደቡብ ክልል መናገሻ ሐዋሳ በመውሰድና በማከፋፈል ደኅና ገቢ የሚያገኝ፣ ቤተሰቦቹን የሚደግፍ በራሱ አንደበት እንደሚገልጸው ‹‹መለኛ›› ነበር።
የንግድ ሕይወት ገና ከማለዳው ዘልቆት ነበርና ከቀለም ማከፋፈል በተጨማሪም የትራንስፖርት መኪኖችም ስለነበሩት የንግድ እንቅስቃሴው ዘርፈ ብዙ እንደነበር አቤል ለአዲስ ማለዳ ይናገራል። በተደጋጋሚ ከአዲስ አበባ ሐዋሳ በንግድ ሰበብ የሚመላለሰው አቤል፣ ረጅሙን ጉዞ ብቻውን ለመጓዝ ካለመፈለግ የተነሳ የተለያዩ አይነት ሰዎችን አብረውት እንዲጓዙና የጉዞ አጋሩ እንዲሆኑ ማድረግ የዘወትር ልማዱ ነበር።
በርካታ ጊዜያት ትራንስፖርት ከሚሰጣቸው ሰዎች አብዛኞቹ የፕሮቴስታንት እምነት አገልጋዮች መሆናቸው፣ አብዛኛው የጉዞ ላይ ወሬያቸው በመንፈሳዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያጠነጠነ እንዲሆን አድርጓል። የጨዋታቸው ርዕስ ታዲያ በወንጌላውያን አማኞች ቤተሰብ ውስጥ ተወልዶ ላደገው አቤል፣ አዲስ ካለመሆኑም በላይ ምቾት የሚሰጠው የጨዋታ ርዕስ ነውና በርካታ ጉዞዎችን በዚህ መልኩ ያሳልፋል። ሲደርስም ተመራርቆ ከፍ ካለም አንዱ ለአንዱ ጸልዮ ጉዞው ያበቃል፤ ሌላ አዲስ ቀን።
በዚህ የአዲስ አበባ ሐዋሳ ጉዞ ታዲያ አንድ ቀን ኪቦርድ ሙዚቃ መሣሪያ የያዙ እና ወደ ሐዋሳ ጉዞ ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች ከአቤል ጋር ይገናኛሉ። የአቤል የጉዞ አጋሮች ታዲያ የወንጌላዊያን አማኞች መሆናቸውን ተናግረው በሐዋሳ የሚገኝ ‹‹የእግዚአብሔር ኃለወት ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስትያን›› አባላት እንደሆኑና የቤተ ክርስትያኒቱ መሥራችና ባለ ራዕይም ነብይ ሱራፌል ደምሴ እንደሚባል ነግረውት ወደ ቤተ ክርስቲያኗ በመምጣት እንዲገለገል ይወተውቱታል።
‹‹ሱራፌል ሲባል በሥም አውቀዋለሁ እንጂ በአካል አይቼው አላውቅም።›› ይላል አቤል ወደ ኋላ መለስ ብሎ የሆነውን ሲያስታውስ። ውትወታቸው ከፍ ብሎ የዛኑ ቀን ማታ የአዳር ጸሎት መርሃ ግብር መኖሩን ነግረውት አልጋ ይዞ ከሚያድር እዛው ነብይ ሱራፌል ቤት ውስጥ ማደር እንደሚችል ነግረው አግባብተውት ወደ ተባለው ሰው ቤት ይዘውት ይሄዳሉ።
‹‹ጸሎት ተጀምሮ ነብይ ሱራፌል ትንቢታዊ መልዕክቶችን ለእኔ ማምጣት ጀመረ። እኔም ብዙ የማልቀበላቸውን እና ጥቂት ደግሞ የምቀበላቸውን ጉዳዮች በትንቢታዊ አካሔድ ነገረኝ›› ሲል አቤል ይናገራል። ከዛም ከጥቂት ቀናት በኋላ ይኸው ነብይ አፈላልጎ አግኝቶት አብሮት ማገልገል እንደሚኖርበትና በቤተክርስትያኒቷ ውስጥ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ በመሆን እንዲሠራ በ‹‹ትህትና እና በመንፈሳዊነት›› እንደጠየቀው ይናገራል።
‹‹ጥያቄውን ሲያቀርብልኝ አልዋሽህም በጣም ደስታ ተሰምቶኝ ነበር፣ ምክንያቱም እኔ እግዚአብሔርን ማገልገል ፍላጎት ነበረኝ›› የሚለው አቤል፣ ሥራውን ጎን ለጎን እያስኬደ ሙሉ ጊዜውን ግን በመንፈሳዊ ሥራ ላይ ያተኩራል። ‹‹በሞኝነት ነበር ጥያቄውን ተቀብዬ ወደ ቤተ ክርስትያን የሔድኩት። ነገር ግን ከዛ በኋላ እታዘበው የነበረው ነገር እኔ ካደኩበት የክርስትና ሕይወት ፍጹም የማይገናኝ እና ክርስትናን ወይም ወንጌልን መነገጃ ሲያደርጉት ማየት እጅግ የሚያሳቅቅ ጉዳይ ነበር።››
አቤል እንደሚለው በዋናነት ከፍተኛ ገቢ ሲያስገኝለት የነበረውን የቀለም ውጤቶች ማከፋፈል ሥራ ከኮንትሮባንድ ጋር በተያያዘ የቀለም ዋጋ በመውረዱ ሙሉ ትኩረት ባለመስጠቱ ኪሳራ በማስመዝገብ ለመዝጋት ተገደደ። የአቤል የንግድ ጉዞ በዚህ ብቻ አላበቃም፤ ከአዲስ አበባ ሐዋሳ ሲመላለስባት የነበረችውን በተለምዶ ‹‹ዶልፊን›› የተሰኘችው ቶዮታ ሚኒባስ ተሽከርካሪ ነብይ ሱራፌል ፎቶውን በመለጠፍ ማስታወቂያ ሲያሠራባት እንደሚውልና ቀሪዎቹንም አቫንዛ መኪኖች ወደ ራሱ እንዳስገባቸው አቤል ለአዲስ ማለዳ ቁጭት በቀላቀለ አንደበት ይተርካል።
ስምንት ወራትን ‹‹በእግዚአብሔር ኃለወት ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስትያን›› ያገለገለው አቤል፣ ‹‹መጀመሪያ ላይ ሚኒባስ መኪናዋን እከፍልሃለሁ በሚል ነበር ሲጠቀምባት የነበረው። በኋላ ግን በጉባዔ መሐል ‹ይኸው ለጌታ ቤት የተሰጠ ስጦታ› እያለ ቁልፉን ጭራሽ ሌሎችን ማነሳሻ አድርጎት ነበር›› ይላል አቤል። ከዚሁ በተጨማሪ የተለያዩ ዓይነት የድምጽ ስርዓቶችን (sound system) በተደጋጋሚ እሱ እንደሚያቀርብና እከፍልሃለሁ ከማለት ውጪ ያወጣውን ገንዘብ መልሶለት እንደማያውቅ ያስረዳል።
‹‹የእኔ ገንዘብ ምንም ማለት አይደለም። ጤና ካለኝ ሠርቼ አገኘዋለሁ። ነገር ግን ሕዝብ ይህን ነገር ማወቅ ይኖርበታል፤ ሲጀመር የእግዚአብሔር ቤት መነገጃ አይደለም። ለዓለም አቀፍ ምዕመኖች ተብሎ የሚዘጋጅ መርሃ ግብር አለ። በዚህ መርሃ ግብር ላይ ታዲያ አንድ ደረጃውን ያልጠበቀ ቲሸርት በ100 ዶላር በመግዛት ነው የሚጸልዩት እንጂ ያልገዛ ሰው መጸለይ አይችልም›› ይላል አቤል ያለፈውን አስታውሶ ሲያወራ።
ከውጭ አገር ለሚመጡ እንግዶች ማረፊያ ተብሎ የተዘጋጀ ትልቅ የዕንግዳ ማረፊያ ያለው ሱራፌል፣ በእርግጥ ግብር ለመክፈሉ እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል አቤል ጥቆማ ቢጤም ጣል ያደርጋል። ‹‹ከኹሉም የሚከፋው ግን ሱራፌል በተለያዩ የውጭ ዜጎች አማካኝነት ከአገር የሚያሸሸው የውጭ አገር ገንዘብ ነው›› ሲል አቤል ለአዲስ ማለዳ ይናገራል።
አሁን አቤል ከስምንት ወራት አገልግሎት ቆይታ በኋላ ከቤተ ክርስትያኒቱ መሥራችና ባለ ራዕይ ‹‹ነብይ ሱራፌል›› ጋር የሂሳብ እንተሳሰብ ጥያቄ ማንሳት ጀምሯል። ይሁን እንጂ እከፍልሃለሁ ከማለት ውጪ ጠብ የሚል ነገር ባለማየቱ ተጠርቼበታለሁ ያለውን የአገልግሎት ጥሪ ችላ እስከማለት ደረሰ። ይባስ ብሎ ባልታሰበ ቀን ከቤተ ክርስትያኒቱ መታገዱን የሚገልጽ መልዕክት ደረሰው። እንዲታገድ የተደረገው ደግሞ በራሱ በነብይ ሱራፌል አማካኝነት መሆኑን አወቀ።
‹‹በጊዜው ምን እንደማደርግ አላውቅም ነበር። እውነት ለመናገር የመሸወድ፣ የመበለጥ እና የቁጭት ስሜቶች ተደበላለቁብኝ ። በተለይ ደግሞ በየዋህነት እንዳገለግል ጠርቶ እንዴት እንዲህ ያደርገኛል ብዬ እየደጋገምኩ ባሰብኩ ቁጥር ወደ ማበድ እየቀረብኩ እንደሆነ እየተሰማኝ መጣ።››
አቤል ከዚህ በኋላ በተረጋጋ መንፈስ ምን ያህል ገንዘብ እንደተበላ ማሰብ ነበረበትና ቁጭ ብሎ በሚያስብበት ወቀት፣ በየጊዜው ከኪሱ አውጥቶ ይሰጠው ከነበረው 850 ሽሕ ብር በተጨማሪ ሌሎች ሥራዎች ተሠርተው ያልተከፈለው በጠቅላላው ከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ተገለጸለት። ይሄኔ ከነበረበት የመንፈሳዊ ሕይወት ጋር ፍቺ ፈጸመ።
አቤል ገንዘቤን ተበልቻለሁ ብሎ እጅ እና እግሩን አጣጥፎ ከመቀመጥ የተለያዩ ሽማግሌዎችን በመላክ ገንዘብ ወስዶብኛል ወደሚለው ሱራፌል እንዲያደራድሩት ጠይቋል። ምላሹ ግን ከነብዩ እንደተላኩ በሚናገሩት ሰማይ ስባሪ በሚያክሉ ወጠምሻዎች መደብደብ እና የጥቃት ሰለባ መሆን ነው።
‹‹መጀመሪያ ጊዜ በተደጋጋሚ የእጅ ስልኬ ላይ እየተደወለ ከጀመርኩት ሽማግሌዎችን የመላክ ድርጊት እንድታቀብ ማስጠንቀቂያዎች ይደርሱኝ ነበር። እኔ ግን የልጆች አባት ነኝ። በዛ ላይ ባለቤቴ ያማታል። ስለዚህ ገንዘብ ያስፈልገኝ ስለነበር ማቆም አልቻልኩም። ከዛ በኋላ ግን ከዚህ ቀደም በስልክ የነበረው ማስፈራሪያ ስጋ ለብሶ ወደ ቡጢ ዞረ። አንድ ቀን ምሽት ላይ ጠብቀው ከፍተኛ ጉዳት አድርሰውብኝ ተሰወሩ። በዚህም ሳቢያ አፍንጫዬ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብኛል›› ይላል አቤል።
አቤል በተደጋጋሚ ጉዳት ስለደረሰበት እና ሰዎችን ማመን ስለተቸገረ፣ ከማን ወገን ተልከው ይሆን በሚል እርግጠኛ ስላልሆነ ከአዲስ ማለዳ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ ሰዋራ ቦታ ላይ እንዲደረግ መርጦ ነበር።
ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ባደረገበት ወቅትም፣ ፊቱ ላይ ጠባሳ መኖሩን ተከትሎ ስለጠባሳው ምክንያት መልስ መስጠት ጀመረ።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ‹‹ምን ጥስ ኢንተርናሺናል›› የሚል የፌስቡክ ገፅ በመክፈት በአጠቃላይ ተመሳሳይ ነገሮችን ይፈፅማሉ ያላቸውን ሰዎች ጉዳይ ይፋ በማውጣት እና በመተቸት አንድ ዓመት አለፈው። ይህንንም ማንነቱን ደብቆ ባለማድረጉ እና ፎቶውም ጭምር ስለሚታወቅ አደጋ እንደሚደርስበት ይናገራል። ከኹለት ሳምንት በፊት ማንነታቸውን ባላወቃቸው እና ከአንድ ነብይ እንደተላኩ በመናገር ፌስ ቡክ ላይ የሚጽፋቸውን ነገሮች ካላቆመ እንደሚገድሉት ነግረውት ደብድበውት እንደሄዱ ለአዲስ ማለዳ በፍርሃት አጫውቷታል።
‹‹ምን ጥስ›› በሚል ፌስ ቡክ ገጽ ነብያቶችን በመሞገት የሚጽፋቸው ጽሑፎች በከተማዋ እውቅ ከተባሉ ‹አገልጋዮች› ስልክ እየተደወለ ማስፈራሪያዎች እንደሚደርሱበትም ይናገራል። ወደ ሕግ ዘንድ ሔደህ አመልክተህ ታውቃለህ ወይ ስትል አዲስ ማለዳ ላቀረበችለት ጥያቄ ‹‹ኹሉም በእጃቸው ነው፣ በፖሊስ ቤታቸውን እያስጠበቁ እኔ ሔጄ ባመለክት የባሰ ራሴን ጥርስ ውስጥ ማስገባት ነው›› ሲል መልሷል።
አራት ልጆቹን ለመመገብ እስኪቸገር ድረስ የገቢ ምንጩ የደረቀው ወጣቱ፣ የሥራ በሮች ተዘግተውበት የራይድ አገልግሎት በመስጠት ልጆቹን እና ሚስቱን ያስተዳድራል። ‹‹እንደዛ መንፈሳዊ የነበርኩኝ ልጅ ከክርስትያን ቤተሰብ የተወለድኩኝ፣ በእግዚአብሔር ቤት ያደኩኝ ሰው ይሔው አሁን የአልኮል ሱሰኛ ሆኛለሁ›› ሲል አቤል አራተኛው ብርጭቆ ጂን ላይ ደርሶ ነበር።
ሞት
ስሟ እንዲገለፅ የማትፈልገው እና ከአንድ ዓመት በፊት አብሮ አደግ ጓደኛዋን በሞት ያጣችው ወጣት ከእንባዋ ጋር በመታገል ነበር ታሪኳን የምታካፍለው። ሟች በጠና ትታመምና ወደ ተለያዩ የሕክምና ተቋማት ብትሔድም ነገሩ በመድኃኒት የሚድን አልነበረም። እናም ‹‹ነብይ›› ታምራት ታረቀኝ ጋር ብትሔድና ቢጸለይላት ልትድን ትችላለች በሚል ወደዛው ይሄዳሉ። በወቅቱ ይቺ ባለታሪካችን በሌላ ቤተ ክርስትያን ውስጥ በዘማሪነት ነበርና የምታገለግለው፣ ቦታ ለማግኘት የሚደረገውን ትግል እዛው በምታውቃቸው ሰዎች ተይዞላት ጓደኛዋን ይዛ ታምራት ታረቀኝ ፊት ትቀርባለች።
‹‹ከብዙ ጥበቃ በኋላ አገልጋዩ ወደ ሕዝብ መጣ›› የምትለው ወጣት፣ ይህችን ታማሚ ልጅ እጁን ጭኖ ከጸለየላት በኋላ የታሸገ ውሃ ‹‹የተፀለየበት ስለሆነ ሙሉውን ጠጪው›› በሚል እንድትጠጣ ከተደረገ በኋላ ‹‹አሁን ተፈውሰሻል የምትወስጅውን መድኃኒት አቁሚ›› በሚል መዳኗን ይነግራታል። ሟች እንደተባለችው ፈፀመች፤ የሆነው ግን ከዚህ የተለየ ነበር። ከቀን ወደ ቀን የጤናዋ ሁኔታ እንኳን መሻሻል አላሳየም። እንደውም ተባብሶ ብዙም ሳትዘልቅ በወጣትነት ዕድሜዋ ይህን ዓለም መሰናበቷን ወዳጇ በሃዘን እና በእንባ ቃላቷን እያቆራረጠች ትናገራለች።
‹‹የሚገርምህ ነገር በጓደኛዬ የደረሰው ነገር እጅግ ስላሳዘነኝ እንዲህ ዓይነት ተፈውሳችኋል የተባሉ ሰዎችን ሁኔታ በቅርበት ለመከታተል እሞክራለሁ። እናም ምናልባትም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ፈውሱ ትክክል አይደለም። እግዚአብሔር አዳኝ መሆኑን አልጠራጠርም፤ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ቀልድ ነው የያዙት። ምናልባት ጸጋ ቢኖራቸው እንኳን ሰጪውን ከማክበር ይልቅ ራሳቸውን ማግነን እና ኑሯቸውን ማደላደያ ነው ያደረጉት›› ስትል በኻያዎቹ መጨረሻ ላይ የምትገኘው ወጣት ትናገራለች።
ከወዳጇ ሞት አልፎ የሌሎችን ጉዳት በመመልከት የምትንገበገው ወጣት ‹‹በተደጋጋሚ ለምን እንደዚህ ይሆናል እያልኩ የምብሰለሰልበት ነገር ነው። የሰዎችን የግል ታሪክ በጉባዔ ፊት ማስወራታቸው ሳያንስ በካሜራ ፊት እያስደገሙ ለራሳቸው ማስታወቂያ መሥራታቸው አሳዛኝ ነው›› ትላለች።
ከባለ ታሪካችን ጋር አንድ ሳቅ የሚያጭር ገጠመኟን አጫውታን ተሰነባብተናል። ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ በአንድ የጸሎት መርሃ ግብር ላይ ሥሙን መጥራት ያልፈለገችው ነብይ ነኝ የሚል ሰው እጁን ጭኖ ሲጸልይላት ‹‹ትዳርሽ ከዚህ አገር አይደለም። ከውጪ አገር ነው ሲለኝ እኔ ሳቄን መቆጣጠር አቅቶኝ በሩጫ ወጣሁ። ምክንያቱ ደግሞ እሱ ያገባሁ አልመሰለውም እንጂ እኔ አኮ በጊዜው ባለ ትዳር እና የአንዲት ልጅ እናት ነበርኩ። የተሸወደው ደግሞ ቀለበት ጣቴ ላይ አለማየቱ ነው›› ስትል ቃለ ምልልሳችንን ቋጨን።
የአዲስ ማለዳ ትዝብት
ይህ ጽሑፍ በተዘጋጀበት ጊዜ የነብያት አገልግሎት በስፋት በሚስተዋልባቸው የአዲስ አበባ ቤተ ክርስትያኖች በሌሊትና በቀን አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ ለመታዘብ ችላለች። ይቅርና ማዋራት አጠገባቸው መድረስም የማይቻል ሆነ እንጂ፣ የተወቀሱትንም ሆነ አዲስ ማለዳ ጥያቄዋን መሰንዘር የፈለገቻቸውን ነብዮች ቀጠሮ ለመያዝ እና ለማናገር ሙከራ አድርጋላች።
በተለይም ደግሞ በየካ ክፍለ ከተማ ልዩ ሥሙ ኮተቤ 32 ቁጥር ማዞሪያ አካባቢ በሚገኘው ‹‹ክርስቶስ ኢየሱስ ቤተ ክርስትያን›› እንዲሁም በየካ ክፍለ ከተማ ልዩ ሥሙ ቤላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ‹‹የመንግሥቱ ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስትያን›› ተዘዋውራ ታዝባለች።
ኮተቤ በሚገኘው ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በርካቶች በቀጣዩ ቀን በሚካሔደው የአምልኮ፤ እነሱ እንደሚሉት ‹‹ነጻ የመውጣት፣ የትንቢት፣ የታምራት›› ቀን ቀድመው ቦታ ለመያዝ እና እንዲጸለይላቸው ሌሊቱን ሙሉ አጥንት ድረስ ዘልቆ በሚቆረጥመው ብርድ ማደር ይኖርባቸዋል። አዲስ ማለዳ በደረሰችበት ወቅት የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች ሞልተው ብርዱም እጅግ ጠንክሮ ነበር። ከዚህ የሚብሰው ግን ያን ኹሉ ብርድ ተቋቁመው በሚያድሩ ምዕመኖች ላይ የቤተ ክርስትያኒቱ ጥበቃዎች የሚያደርሱባቸው ዱላ ነው።
በጠና የታመመ ዘመዳቸውን ይዘው ፈውስ ይቀበላል ብለው ስጋቸውን ለብርድ ነብሳቸውን ለጭንቀት የሰጡ ሰዎችን የአምልኮ ስፍራውን ሞልተውታል ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ሥሜ ይቆይ በሚል አስተያየቱን ለአዲስ ማለዳ የሰጠው ወጣት ‹‹የሚገርምህ ነገር እንዲህ ተጠብቆም ነብዩ ላይመጣ ይችላል።›› ይላል። የጓደኛውን ወንድም ይዞ መምጣቱን የሚናገረው ወጣቱ ‹‹እኔ እምነቴ ፕሮቴስታንት ቢሆንም እንዲህ አይነት ልምምድ ስለሌለኝ የነብያት አገልግሎትን እምብዛም አልቀበልም›› ይላል። አያይዞም ‹‹የዛሬ ሳምንት አንዱ ዘበኛ እንደዚህ የሚያድሩትን በዱላ ሲደበድብ አይቼ እኔም ተጣልቼ ነበር። መንግሥት ግን ምን ሲያደርጉ እንደሆነ ወደ ሕግ የሚያቀርባቸው ባላውቅም፤ እነዚህ ሰዎች ግን መቅረብ ይኖርባቸዋል›› ሲል ጥያቄ አዘል ጉዳዮችን ይናገራል።
ኮተቤ አካባቢ የሚገኘው በ ነብይ ታምራት ታረቀኝ ከሚመራው የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ከርስትያን ለመታዘብ እንደቻልነውም፣ በቀጣይ ቀን ለሚካሄደው ፀሎት ቀድመው ቦታ ለመያዝ በአዳራሽ እና በግቢው ከሚያድረው የሚበልጠው ከግቢው ውጪ የሚያድር በመሆኑ ሌቦች ጥቃት ያደርሳሉ። አዲስ ማለዳም በቦታው ተገኝታ እንዳየችው ምእመኑ ተሽከርካሪውንም ሆነ የያዘውን እቃ መጠበቅ ዋና ተግባሩ ነው።
አዲስ ማለዳ አሁንም ቅኝቷን እንደቀጠለች ነው። በነብይ ኤርሚያስ ሁሴን መሥራችና ባለራዕይነት ወደሚመራው የ‹‹መንግሥቱ ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስትያን›› ሔደናል። ፈረንሳይ ለጋሲዮንን የማለዳ ምናልባትም የሌሊት ብርድ ለሚያውቀው እንዴት ፈታኝ እንደሆነ ይረዳል። አዲስ ማለዳ ወደ ቤተ ክርስትያኒቱ ስትደርስ ከእኩለ ሌሊት ጥቂት ደቂቃዎች አልፎ ነበር። ኮተቤ ከሚገኘው ቤተ ክርስትያን እምብዛም የማይለይ የምዕመን እና ፈውስ ፈላጊ ሰዎች ብዛት፣ እዚህም ለቁጥር የሚያዳግት ነው። ጥበቃዎች በአንጻራዊነት ትህትና የሚነበብባቸው ነበሩ።
ብርዱን ለመቋቋም ከባባድ ጃኬቶችን አድርገው እዚህ እና እዛ የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን ግቢውን ሞልተዋል። በዚህ ወቅት ታዲያ ዓለማየሁ አበበ (ሥም የተቀየረ) ስለ ሁኔታው እና ስላጋጠመው ነገር እንዲህ ሲል ለአዲስ ማለዳ ያጫውታል። ‹‹በተደጋጋሚ መጥቻለሁ። አንድም ቀን ግን ‹ነብይ ኤርሚያስ› አጋጥሞኝ አያውቅም። አገልጋዮችም ሰውየው እንደሌለ እያወቁ አይነግሩንም። ከውጪ ለሚመጡ ሰዎች ገና ከአውሮፕላን ማረፊያ በሰርቪስ ተቀብሎ ወደ እንግዳ ማረፊያ ከወሰዳቸው በኋላ እዛው በግል ስለሚጸልይላቸው እና ብዙ ብር ስለሚከፍሉት ደክሞኛል ብሎ ሰውን ያጉላላል›› ሲል ይናገራል።
‹‹እኔ በተደጋጋሚ ስመጣ ማግኘት አልቻልኩም። በዛ ላይ ደግሞ የማውቃቸው ሰዎች የተለያዩ ነገሮችን ስለ ሰውየው ነግረውኛል። በመሆኑም ማረጋገጥ ይኖርብኛል ብዬ ነው የመጣሁት›› በማለት የመጣበትን ዓላማ ያስረዳል።
ነብይ ኤርሚያስ በሚመሩት ቤተ ክርስትያን የነበረን የሌሊት ቆይታ በማግስቱ ለመምጣት እና በአዳራሽ ውስጥ ገብተን ለመታደም ማረጋገጫ በማግኘት ተጠናቋል። በጠዋት አዳራሽ ውስጥ በመግባት የፊት ወንበሮች ላይ በመቀመጥ ሁኔታወን እየቃኘን ነው።
ሌሊት ጀምረው ለዛሬ ቦታ የያዙት ምዕመናን እስከ ምሳ ሰዓት ድረስ የሚጠብቁት ሰው አልመጣም። ምሳ ሰዓት አልፎ ለመክሰስ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ተጠባቂው ነብይ ወደ አዳራሹ ሲገቡ የተደረገላቸው አቀባበል የተለያዩ ቅሬታዎችን ሲያሰሙ ከቆዩ ምእመናን የተደረገ አይመስልም።
‹‹የእግዚአብሔር ሰው ወደ አዳራሹ እየገቡ ስለሆነ ጭብጨባ እልልታ ያስፈልጋል›› በማለት ከመድረክ በተደረገው ግበዣ የተሰበሰበው ሰው በሙሉ እንደተባለው አድርጓል። የሰማይ ስባሪ በሚያካክሉ የግል ጠባቂዎቻቸው ታጅበው ወደ አዳራሽ የገቡት ኤርሚያስ፣ ሊነኳቸው እጃቸውን በሚዘረጉ ሰዎች ላይ የግልምጫ ይሁን የቁጣ ባለየ ሁኔታ እየተመለከቱ ሲያልፉ ጠባቂዎቻቸው ደግሞ ሰውን ገፍትረው ሲያሽቀነጥሩ ተመልክተናል። በዚህ ወቅት ፎቶ ለማንሳት የተደረገው ሙከራ አዲስ ማለዳን ከግዙፉ የነብዩ የግል ጠባቂ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ከቷታል።
‹አምላክ› ወይስ ሰው?
አገልጋዩ ኤርሚያስ ለሳቸው ብቻ ተብሎ በተለየ እና ሰማይ ዝቅ ምድር ከፍ ቢልም ማንም በማይቀመጥባት ወንበራቸው (ዙፋናቸው ቢባል ይቀላል) ላይ ተቀመጡ። የሚደረግላቸው እንክብካቤ ለጉድ ነው። በዚህ ወቅት ግን አንድ አስደንጋጭ እና እንግዳ ነገር ተከሰተ።
በየሰከንድ ሽቶ በእግራቸው ስር ሲረጭ ቆይቶ ከአፍታ በኋላ ግን አንዲት ልጅ እግር ሴት በጉልበቷ ተንበርካካ ወደ ኤርሚያስ በመቅረብ መጽሐፍ ቅዱስ ስታቀብላቸው አዲስ ማለዳ ታዝባለች። እዚህ ላይ ‹‹የመንግሥቱ ኃይለማርያም ትዝታዎች›› በሚለው መጽሐፍ ላይ ቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ ኮሎኔል መንግሥቱ ከገነት አየለ ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለ ሊቢያው የቀድሞ መሪ መሐመድ ጋዳፊ ተጠይቀው ሲመልሱ፣ ጋዳፊ በምሥራቅ አውሮፓ ሴቶችን በማስመጣት በጉልበታቸው ተንበርክከው ያስተናግዱት እንደነበር የመለሱትን ምላሽ ወደ እዝነ ሕሊና ያመጣል።
ንጥቂያ
በዚሁ ግለሰብ በደል እንደደረሰበት የሚናገረው ያሬድ አበራ ከአራት ዓመታት በፊት የተለያዩ ድምጽ ማጉያዎችን በማከራየት ነበር ሕይወቱን መምራት የጀመረው። ይሁን እና ከቀናት በአንዱ ‹‹የነብይ ኤርሚያስ ቤተ ክርስትያን›› ድምጽ ማጉያ መከራየት እንደሚፈልግ ተነግሮት በዋጋ ተስማምቶ ለሦስት ወራት ያከራያል። የኪራዩን ገንዘብ ከሳምንታት ውትወታ በኋላ ያውም ግማሽ ያህሉ ቢሰጠውም፣ ቀሪው ግን የውሃ ሽታ ሆኖ ይቀራል።
ውትወታውም ቀጥሎ ኪራዩም ኹለተኛው ወር አጋምሷል። ‹‹ኮንትራቱ ሲያልቅ ይሰጥሃል›› የተባለው ያሬድ፣ ሦስት ወሩ ደርሶ ሲጠይቅ ዕቃውንም ሆነ ገንዘቡን መጠየቅ እንደማይችል ተነግሮት በጥበቃ ከጊቢው እንዲወጣ እንደተደረገ ይናገራል። ‹‹በጊዜው ሰውየው ቀይ መለዮ ባላቸው ሰዎች የሚታጀብ እና ራሱን የቻለ መንግሥት ነበር›› ሲል ይናገራል። ሕይወቱን የሚመራበት የገቢ ምንጭ እንዲህ በአንድ ጀምበር ሲነጠቅ አርፎ መቀመጥ ያልቻለው ያሬድ፣ በተደጋጋሚ ዕቃውን ለማስመለስ ባደረገው ጥረት ድብደባ፣ ዛቻ እንዲሁም እስር አጋጥሞታል።
‹‹አንድ ምሽት ቤት ውስጥ ከተቀመጥኩበት በሐይማኖት ተቋም ላይ ጥቃት ልትሰነዝር ነበር በሚል አስረው ከወሰዱኝ በኋላ ሲደበድቡኝ አደሩ›› የሚለው ያሬድ፣ ዛሬም እንደዛ በደል ያደረሰበት ሰው ጭራሽ በአንድ መርሃ ግብር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ታድሞ ሲመለከት እጅግ ተስፋ እንደቆረጠ እና አሁንም ወደ ሕግ ማቅረብ እንደማይቻል ደምድሟል።
‹‹አንድ ሰሞን እንዲህ ማድረግ በነብይ ነን ባዮች በጣም እንደ ፋሽን ይታይ ነበር›› የሚለው ያሬድ ጓደኛውም 60 ሺሕ ብር የሚያወጣ ተመሳሳይ የድምጽ መሣሪያ ‹‹የሆሌ ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስትያን›› እና ‹‹ባለ ራዕይ በላይ ሽፈራው›› አማካኝነት ተነጥቆ የመንግሥት እና የሕዝብ ብሎም የአገር ኃላፊነት በተጣለባቸው እና ለሆዳቸው ባደሩ የደኅንነት አባላት ታፍኖ ወደ ሰንዳፋ ተወስዶ እንደነበር ለአዲስ ማለዳ ይናገራል። ‹‹ጓደኛዬ ብዙ ጉዳት ቢደርስበትም ቤተሰቦቹ ደኅና ደረጃ ላይ ስለሚገኙ ከአገር እንዲወጣ አድርገውታል›› ሲልም ይተርካል።
ስደት
አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው መካከል የመጨረሻው ግለሰብ የትውልድ ቀየውን ለቆ ወደ አዲስ አበባ እስከመሰደድ ያበቃውን ታሪክ እንዲህ ይተርካል።
‹‹ሥሜን ከምነግርህ ኹሉም ነገር ቢቀር እመርጣለሁ። ከዚህ በኋላ ከእነዚህ ሰዎች (ነብያቶች) መሰወር ነው የምፈልገው። አንተም በሰው ስለመጣህብኝ እንጂ ባልናገር እወዳለሁ›› ሲል የሚጀምረው ባለ ታሪካችን፣ በዚህ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ወደ ‹‹ነብይ እዩ ጩፋ›› ወደ አርባ ምንጭ ከተማ ለአገልግሎት እንደሚገኝ ተነግሮት እንደማንኛውም ምዕመን ፀጋን ለመካፈል እንደተገኘ ያስረዳል።
በጊዜው አገልግሎት ላይ የነበረው እዩ ጩፋ ወደዚህ ባለታሪካችን ይቀርብና ፣ትንቢታዊ መልዕክት ያመጣል። ታዲያ ይህ ባለታሪክ በአደባባይ ውሸት ነው እንዲህ አይነት ነገር የለኝም ሲል ትንቢቱን ሐሰት እንደሆነ በሕዝብ ፊት ይናገራል።
‹‹መጀመሪያ እንደመደንገጥ ብሎ ዝም ብሎ ካለፈኝ በኋላ ተመልሶ በመምጣት ስወጣ አናግረኝ እጸልይልሃለሁ አለኝ። ከዛም ፕሮግራሙ እስኪያልቅ ጠበኩ፤ በብዙ ሰዎች ታጅቦ ስለሚሔድ እንደምንም ብዬ አገኘሁት። ለጠባቂዎቹም ወደ አንድ ክፍል እንዲያስገቡኝ ከነገራቸው በኋላ እንዴት በአደባባይ ትቃወመኛለህ እያለ ቆሞ አስደበደበኝ። ይህም ሳይበቃው ለአንድ ወር በአንድ ሰፊ ጊቢ ውስጥ አስሮ ሲያስጠብቀኝ ከቆየ በኋላ ኹለተኛ ባገኝህ አገድልሃለሁ በማለት አገር ጥዬ እንድሰደድ አድርጎኛል›› ሲል ያስረዳል።
‹‹እኔም ምርጫ የለኝም፤ ፖሊሶች፣ ወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ እንዲሁም ሌሎች የመንግሥት ሰዎች ወዳጆቹ ስለሆኑ ወደ ሕግ ብሔድ እኔ ነኝ ተጠቂ የምሆነው። በዛ ላይ እጅግ አስፈሪ ነው፤ እገድልሃለሁ ብሎኛል›› በማለት አገር ጥሎ እንዴት እንደሸሸ ይናገራል።
ለዚህ ጽሑፍ እንዲመጥን አድርገን አቀረብን እንጂ፣ በርካታ ጉዳዮችን ለማጣራት ችለናል። በተለይ ደግሞ ከተበዳዮች ቁጥር መብዛት የተነሳ ማቅረብ ያልቻልናቸው እልፍ ናቸው።
የአብያተ ክርስትያናት ኅብረት ምን አለ?
የተጠቀሱትን ጉዳዮች በመያዝ አዲስ ማለዳ ወደ ወንጌላዊያን የአብያተ ክርስትያናት ኅብረት በማቅናት ፕሬዘዳንቱን ፓስተር ጻዲቁ አብዶን አነጋግራለች። ፕሬዘዳንቱ እንደሚሉት፣ ከሦስት ዓመት በፊት ባካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔ እንደዚህ ዓይነት አስተምህሮ ያላቸውን ግለሰቦች ነቅሰው ማውጣት እንደቻሉ ገልጸዋል። አያይዘውም ‹‹የብልጽግና ወንጌል›› እንሰብካለን የሚሉ ነገር ግን ያልሆነውን የስህተት ትምህርት እያስተማሩ ምዕመኑን ወዳልሆነ ልምምድ ውስጥ የሚከቱ ግለሰቦችን በመለየት የኅብረቱ አካል አለመሆናቸውን እንዳወጁ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በይፋ ከታገዱት ውስጥም እስራኤል ዳንሳ እና እዩ ጩፋ ዋነኞቹ መሆናቸውንም ጻድቁ አብዶ ተናግረዋል።
ሙሉ ወንጌል፣ ቃለ ሕይወት እና መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስትያኖች ዋነኞቹ የኅብረቱ አባላት ሲሆኑ ሌሎችም አስተምህሮታቸው ተገምግሞ አባል እንዲሆኑ እንደተደረገም ፕሬዘዳንቱ ገልጸዋል። ‹‹ገስት ሐውስ ቢኖር መልካም ነው። ነገር ግን በታላላቅ ሆቴሎች የማይከፈለውን ገንዘብ እያስከፈሉ ከጸሎት ጋር እንዲያያዝ ማድረግ ከአስተምህሮትም ባሻገር በሞራልም ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ ነው›› ሲሉ ጻድቁ ገልጸዋል።
በቀደሙት ዓመታትም ወደ ተለያዩ የመንግሥት ቢሮዎች በመሄድ መንግሥት እነዚህን ሰዎች ስርዓት እንዲያሲዝ ጠይቀው የነበረና የተሠሩ ሥራዎች ቢኖሩም፣ እምብዛም አመርቂ እንዳልነበሩ ይጠቁማሉ። ‹‹እኛ በትክክለኛው መንገድ ኦዲት የሚደረጉ ቤተ ክርስትያኖችንም ነው የምንቀበለው›› የሚሉት ፕሬዘዳንቱ፣ አሁን እየታዩ ያሉት ግን እንኳን ኦዲት ሊደረጉ በአንድ ሰው አድራጊ ፈጣሪነት የሚመሩ በመሆናቸው ለሰላም ሚኒስቴር አስታውቀን ፈቃድ ለምን እንደሚሰጣቸው ግልጽ እንዲያደርጉልን ጠይቀናል›› ብለዋል።
ምንም እንኳን ከኅብረቱ የተገለሉ እንደሆኑ ለሕዝብ ቢነገርም፤ አሁንም ድረስ ግን ጉዳት ደረሰብኝ ብሎ ወደ ቢሯቸው እንደሚመጣ አልሸሸጉም። ‹‹ሕዝቡም መገንዘብ የሚኖርበት አብረን ከማዘን ውጪ የምንፈይደው ነገር አለመኖሩን ነው›› ሲሉም ተናግረዋል። ‹‹አሁን በቅርቡ አንዲት ሴት 500 ሺሕ ብር ተበላሁ ብላ ወደ እኔ ቢሮ መጥታ ነበር›› ሲሉም ገጠመኛቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
በቅርቡ ከሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሐት ካሚል እና ሚኒስትር ዲኤታዎች ጋር በመሆን በዚህ ጉዳይ ላይ እንደመከሩ የሚናገሩት ፕሬዘዳንቱ፣ በቅርቡ አንድ ውሳኔ ላይ ይደረሳል ብለው እንደሚጠብቁም ተስፋቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
መፍትሔው ምንድነው?
ስለጉዳዮ ሙያዊ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ የሰጡት የሥነ መለኮት ተመራማሪው ዘማች ሻሪ ‹‹ሕዝቡ ወደ እነዚህ ሰዎች የሚሳበው በአስተምህሮታቸው ነው›› ሲሉ ይጀምራሉ። ቀጥለውም ለሰው የሚስማማ፣ ሰማያዊውን ነገር እና መንፈሳዊ አሰራርን ባልተከተለ መልኩ እግዚአብሔርን እና የኢየሱስ ክርስቶስን አካሔድ ከመከተል ይልቅ ‹‹እናንተ እንደ እግዚአብሔር ናችሁ›› እያሉ ስለሚያስተምሩ ብዙኃኑን መሰብሰብ እንደቻሉ ያስረዳሉ።
‹‹እነዚህ ሰዎችኮ የማታለል አቅማቸው ከፍተኛ ሆኖ ሳይሆን የሰዎች የመረዳት አቅም መድከም ነው እንዲህ ጉዳዩ ስር እንዲሰድ ያደረገው›› የሚሉት ዘማች፣ በተለይ ደግሞ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በእነ ኬኔት ኮፕላንድ እና ኬኔታገን አማካኝነት የተፈጠረውን ‹‹ብልጽግና ወንጌልን›› በመስበክ የሰውን ሥነ ልቦና በመስለብ ለጥቅማቸው ሲያደርጉት ኖረዋል፤ እያደረጉትም ይገኛሉ ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
ዘማች በዚህ ብቻ ሳያበቁ ይህን ስር ሰደደ ጉዳይ ቤተ ክርስትያን ለተከታዮቿ ተከታታይ ትምህርት በመስጠት በእውቀት ማስታጠቅ እንደሚኖርባትም ይናገራሉ። ‹‹ሕዝቡ እኮ ዕውቀት ከማጣት የተነሳ እየጠፋ ነው›› የሚሉት ዘማች፣ የሰውን ሃብት እየበዘበዙ፣ ትዳር እያፈረሱ ያሉትን እነዚህን ግለሰቦች ከመቼውም በላይ መቃወም ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል። መንግሥትም እንደ ዋና ባለ ድርሻ አካል ሕግን በማስከበር ሰዎቹ በሕግ ሊዳኙበት የሚችሉበት አካሔድ ቢፈጥር መልካም ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ይቋጫሉ።
ሌላው የሥነ መለኮት ተመራማሪ እና አስተያየት ሰጪ ጌዲዮን አግዘው ሲናገሩ፤ ‹‹ሲጀመር እኔ ሲዜሽኒስት ነኝ። ይህም ማለት ደግሞ ከሐዋሪያት ማለፍ በኋላ ትንቢት መናገር እንዲሁም ልሳን መናገር አለ ብዬ አላምንም›› ይላሉ። በእርግጥ በአሁኑ ሰዓት እንዲህ ዓይነት ሰዎች መኖራቸውን እና ሕዝቡንም እያሳቱ እንደሚገኙ ግን አልደበቁም። ከቀደሙት ዓመታት በላይ አሁን ላይ ‹‹ነብያት ነን›› በማለት በርካታ ሰዎችን የሚያስከትሉ ሰዎች በዝተዋል የሚሉት ጌዲዮን፣ በተለይ ደግሞ የሞራል መዛባት እና ስብዕናቸው ላይ በጉልህ የሚታዩ ችግሮች ለመኖራቸው አጠያያቂ እንዳልሆነ ይናገራሉ።
ለእነዚህ ሰዎች መብዛት ደግሞ በእሳቸው ግምት የምዕራብ አፍሪካ የሐይማኖት ጣቢያዎች መበራከት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ይጠቅሳሉ። ‹‹በእርግጥ ነብያት ነን የሚሉት ቋሚ አባላት በቤተ ክርስትያኖቻቸው የላቸውም። በአብዛኛውን ጎብኚ ነው ያላቸው›› የሚሉት ጌዲዮን፣ በተለይ ደግሞ ከሕመምና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ካልሆነ እምብዛም የሚጎበኛቸው እንደሌለ ይናገራሉ።
ጌዲዮን እንደ መፍትሔ የሚያስቀምጡት ደግሞ ኹሉም ቤተ ክርስትያን እውነተኛውን የእግዚአብሔር ቃል ለምዕመኖች ቢያስተምር ችግሩን መቅረፍ ይቻላል ብለው ያምናሉ። ‹‹ነገር ግን መንግሥት በቀጥታ ጣልቃ ገብቶ እርምጃ መውሰድ የሚችልበት አግባብ አለ ብዬ አላምንም። ምክንያቱ ደግሞ ወዶ እና ፈቅዶ በመንግሥት ፈቃድ ለተቋቋመ ቤተ ክርስትያን ብሩን ከሰጠ በኋላ አንድ ሰው ገንዘቤን ተበላሁ ቢል ወንጀል ይሆናል የሚል ግምት የለኝም›› ብለዋል።
ስለ ፈቃድ አሰጣጡ እና ሕግን ከማስከበር አኳያ በሰላም ሚኒስቴር የሐይማኖት እና እምነት ጉዳዮች ዳይሬክተር ሀለፎም አባይ ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ፣ ‹‹እኛ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 31 የተቀመጠውን የመደራጀት መብት ተከትለን ፈቃድ እንሰጣለን›› ብለዋል። ቀጥለውም ፈቃድ የወሰዱት አካላት በየዓመቱ አስተዳደራዊ ሥራቸውን ለሰላም ሚኒስቴር ሪፖርት እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል። በየአምስት ዓመትም ፈቃዳቸውን እንደሚያድሱ ሀለፎም ገልጸዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በብዛት ሕገ ወጥ ተግባር ተብለው እና ተለይተው ወደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚመጡት በመተዳደሪያ ደንብ አለመመራት እና ሥልጣንን ያለ አግባብ መጠቀም ሲሆኑ፣ በዚህም ወቅት ከሳሽን እና ተከሳሽን በማቀራረብ እንዲታረቁ ይደረጋል። ይሁን እንጂ ሌሎች የማታለል ተግባራት ላይ የተሰማሩ ሰዎችን በተመለከተ በየደረጃው ያሉ ሕግ አስከባሪዎች ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስዱ ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓት 1900 በሐይማኖት ተቋማት እና በማኅበራት ሥም ከሰላም ሚኒስቴር ፈቃድ የወሰዱ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 900 የሚሆኑት በቤተ ክርስትያን ሥም ፈቃድ የተሰጣቸው እንደሆነ ሀለፎም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012