የኢትዮጵያ የውይይትና መፍትሄ መድረክ (EDF)አስተያየትና መግለጫ

የኢትዮጵያ የውይይትና መፍትሄ መድረክ (EDF)አስተያየትና መግለጫ

ትምህርት የእውቀት ምንጭ ሲሆን ት/ቤቶች ደግሞ የእውቀት ማሰራጫ ተቋማት ናቸው። የሰው ልጅ ተፈጥሮ ከሚያደርስበት አሉታዊ ተጸዕኖ እራሱን ጠብቆ የተፈጥሮን ፀጋ መቋደስና ለጥቅሙ ለማዋል የሚችለው የህይወት ምርጫውና ጉዞው በእውቀትና በጥበብ የታነጹ ከሆነ ብቻ ነው። አልያ ግን በየጊዜው የሚፈራረቁበት ፖሊቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ነውጦች ወደ ግቡ ሳይደርስ፣ መልካም ምኞቱና ራዕዩ እውን ሳይሆን፣ በከንቱ ሲባክን ምንም ሳያፍስ ያለችውንም አፍስሶ እራሱንና አገሩን ጭምር ያጣል።

አለመታደል ሆኖ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ወደ አገራችን የገባው በአስርተ ዓመታት ውስጥ ቢሆንም ኢትዮጵያውያኖች ለጥበቡና ለስልጣኔ በዓለም ዙርያ ከሚገኙ ህዝቦች ከቀዳሚዎቹ ተርታ ያለን ቀዳሚዎች መሆናችን አይዘነጋም። በአፄ ሚኒሊክ ዘመን ዘመናዊ ትምህርት ሲጀመር የነበረው የተማሪው ቁጥር ትንሽ ነበር፣ ዛሬ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የተማረና በትምህርት ቤት ያለፈ ትውልድ ላይ ደርሰናል።

ለትምህርት መስፋፋት ህብረተሰባችን በጥቅሉ፣ መንግስት ደግሞ (ባለአደራ ነውና) በተለይ ሃላፊነት በትከሻው ላይ ያርፋል። ህብረተሰባችን ከእለት ጉርሱ አብዛኛው ደግሞ ከእጦቱ ቀንሶ የሚከፍለውን ግብር(ታክስ) መንግስት መልሶ ለህዝባችን፣ ለትውልዳችንና ለአገራችን እድገትና ብልጽግና በተለይ ለትምህርት ልዩ ቦታ በመስጠት ከፍተኛ ባጀት ሊመድብለት ይገባዋል። አገርን የሚያንጸው የመሳርያ ጋጋታ ሳይሆን እውቀት ነውና።

ባለፉት ሃያ ሰባት የኢህአዴጋውያን አገዛዝ የትምህርት ቤቶች ቁጥር በተለይም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት  ቀድሞ ከነበረው በቁጥር መጨመሩ አይካድም። መልካምም ነው ። ከዚህ ጋር በንጽጽር መስተዋል ያለበት ግን  ከህንፃዎቹ በስተጀርባ ያለው የትምህርቱ ጥራትና ተልዕኮ ትውልድን የሚቀርፅ፣ አገርንና የህዝቡን አንድነት ይበልጥ የሚያስተሳስስር፣ ወደ ላቀ የምርምርና የፈጠራ ሥራ በመሸጋገር በአጠቃላይ ትውልድን የሚያኮሩ ወጣቶችን የምናፈራበት ነውን? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። ይህንን ጥያቄ እንድናነሳ የሚያስገድደን ሁኔታ ከቅርብ ዓመታት ወዲህና በሰሞኑም በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የተከሰቱት ጎጂ ሁኔታዎች መከሰታቸው ነው። ትምህርት ቤቶችን እስከመዝጋት ያደረሱ፣ የወጣቶችን ህይወት በለጋነታቸው የቀጠፉ ሁኔታዎች መከሰታቸውም ነው።

ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ኢትዮጵያ አገራችንና አንድነታችን ወዴት እያመሩ ነው? የነበረው አብሮነታችንና ሰላማችን በነውጥ ውስጥ እንዲወድቅ ሆን ተብሎ የሚሰራው ፀረ ወጣት፣ ፀረ ኢትዮጵያ ሴራ ብዙዎቻችንን አሳዝኖናል።

ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር እየዶለቱና የልመና በጀት እየተመጸወቱ አባቶቻችን አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደማቸውን አፍስሰው ያቆይዋትን እናት ሃገር በእምነትና በፅናት ከፈጣሪ የተሰጠችንን ፀጋ በትውልድ ጉዞ ውስጥ በመዋለድ፣ በመባዛት፣ በመደባለቅ፣ አንዱ ከሁሉ ሁሉም ከአንዱ ጋር የደም የጋራ እሴቶችና የመንፈሳዊ ቁርኝት ያለውን ህዝብ በውሸት የተረት ተረት ትረካ አስጨንቀውታል። በዘርና በጎሳ ትውልዱን ከፋፍለው፣ አጥብበው፣ ወጣቱን ያውም ታዳጊውን፣ አገር ተረካቢውን አገሩን እንዲያጣ ብቻ ሳይሆን አገሩን የሚያፈርስ እንዲሆን እንደአውዳሚ ፈንጂ ሲጠቀሙበት ይስተዋላሉ። የጭካኔ ሁሉ ጭካኔ የታዳጊዎችን ተስፋ ማጨለም ነው።

የኢዲኤፍ (Ethiopian Dialogue Forum) አመራር በከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ባሉ ወጣቶች ላይ ከሰሞኑ የተፈጠረውን ሁኔታ ላይ በጥልቅ ተወያይቶ የሚከተለውን መልዕክት ለወጣቱ ትውልድ፣ ለአባቶችና እናቶች እንዲሁም ለመንግስትና የፖሊቲካ ድርጅቶች ነን ለሚሉ የሚከተለውን መልዕክት ያስተላልፋል።

ለኢትዮጵያ ወጣቶች!!!

የኢትዮጵያ ወጣቶች ከቋንቋና ከዘር በላይ ኢትዮጵያዊ ናችሁ። ድንበራችሁ ሆነ ወሰናችሁ ዛሬ ገዢዎቻችን ቆራርጠው የሰጧችሁ ኩርማን መሬት ሳይሆን፣ በስፋቱ ከሰሜን ጫፍ እስከደቡብ፣ ከምዕራብ ጫፍ እስከ ምስራቅ ድረስ በጥልቀቱ በምድራችን (ኢትዮጵያ) ከርሰምድር ፣ በወንዞቻችን ሃይቆቻችን ውስጥ ያሉት ሁሉ፣ በምጥቀቱ ከባለግርማ ሞገስ ተራሮቻችን ጫፍ እስከ ወዲያኛው የአየር ክልል ያለው ሁሉ የሁላችሁም የሆነ በታሪክና በህግም የፀና እናት መንደራችሁ እናት አገራችሁ ነው። የኢትዮጵያ ወጣቶች አንድ ወጥ የሆነው፣ ባለብዙ ባህል፣ ቋንቋና ልምድ ያለው በጋራ ኢትዮጵያዊ እሴት የተባበረ የሠመረ ህዝብ ውጤት ናችሁ እንጂ ነጠላ አይደላችሁም። የአንድ አገር ልጅ መሆናችሁን ተረድታችሁ ዘረኞችና ከፋፋዮች በዘረጉላችሁ ፀረ ህዝብና ፀረ አንድነት ደባ ሳትሸነፉ ከእንግዲህ ይበቃል ብላችሁ በወንድማማችነት ፈጥናችሁ ካልተነሳችሁ በስተቀር ይህቺን ባለታሪክ አገር ወደ ጥፋት በመምራት ትውልድ ሁሉ ይቅር የማይላችሁ ስህተት ውስጥ እየገባችሁ መሆኑን መዘንጋት የለባችሁም።

ስለሆነም በቃ ብላችሁ በደም የተሳሰረውን ወንድምና እህትማማችነታችሁን አድሳችሁ በኢትዮጵያዊ ትምክህትና ኩራት በጋራ በመቆም እናት ኢትዮጵያን እንድትክሷትና እንድትጠብቋት ኢዲኤፍ (EDF) ምክሩን ይለግሳል።

የኢትዮጵያ እናቶች፣ አባቶችና ወላጆች፣

ከቅድመ አያቶቻችሁ ሲወርድ ሲወራረድ ፀንታ የኖረችው እናት አገራችሁ ኢትዮጵያ ዛሬ በዘረኞችና ለስልጣን በቋመጡ ከሃዲዎች (ፖሊቲከኛ ነን ባዮች) እየታነጠች ትገኛለች ። የአድዋ ድል ባለቤት፣ የጥቁር ህዝብ ተምሳሌት፣ ባለገድል አገር ዛሬ የአንድነትና የአርበኝነት ታሪኳ ተክዶ በውጪም ሆነ በውስጥ ጠላቶቿ ተቀስፋ ተይዛለች ።

የናንተ አባቶችና እናቶች ያስረከቧችሁን የአደራ አገርና ህዝብ ቢቻል አበልፅጋችሁ ለተተኪው ትውልድ ማውረስ የሚገባ ሲሆን ካልተቻላችሁ እንኳን አንድነቷን፣ ስሟን፣ የወላጆቻችሁ አፅም ያረፈበት የክብር ቦታ ሳይናወጥ ረግቶ በኢትዮጵያዊነቱ በኢትዮጵያ ሆድ ውስጥ እንዲኖር ማድረግ ይኖርባችኋል።

ዛሬ ግን የምናየው ኢትዮጵያን የማጥፋት አሳዛኝ ተግባር ታሪኳን የመቀየር፣ የነበረውን ያለውን የፀናውን ማህተም በጥሰው አዲስ ቃል ኪዳን እያሉ በነርሱ አምሳል ጠፍጥፈው ሊሰሯት ሲቅበዘበዙ ይታያሉ።

ስለሆነም እናት አገር ያለችበትን ጭንቅና ሰቆቃ አዳምጣችሁ እርስ በእርስ ምን እያደረኩኝ ነው? ወዴት እየሄድን ነው? መንግስታችንና አስመሳይ ፖሊቲከኞች ወዴት እየገፉን ነው ብላችሁ መጠያየቅ ይኖርባችኋል። ለልጆቻችሁ እውነተኛውን የኢትዮጵያን ታሪክ አስተምሩ፤ የዚህች አንዲት አገር የጋራ ፍሬዎች መሆናቸውንና የህይወት ጉዞአቸውም በልጆቿ ታፍራና ተከብራ በልፅጋ የምትኖር፣ በዲሞክራሲ ጎዳና የምትራመድ ኢትዮጵያን መገንባት እንደሆነ ምከሩ።

በቃ ለዘረኝነት በሉ። በእናት አገርና በልጆቻችሁ ህይወት ላይ የሚደረግ መደራደርን አውግዙ ሲል ኢዲኤፍ ይማጸናል።

ለመንግስት ባለስልጣናትና የፖሊቲካ ኅይሎች፦

መንግስት ህዝብን ከስጋት የሚጠብቅ የልማት፣ የሰላም፣ የብልጽግና፣ የአንድነትና ነፃነት ምልክትና ፈር ቀዳጅ መሆን ሲገባው ያለመታደል ሆኖ የኢህአዴግ መንግስት የራሱን ህዝብ በጎሳ እየከፋፈለ የሚያራርቅ፣ የሚያፈናቅል፣ የሚያጋጭ፣ በክልል ለያይቶ በትምህርት ቤት ሳይቀር ወጣቱንና ትውልድን የሚያፋጅ (ከውጪ ወራሪዎች ባልተናነሰ)፣ የዘር ፖሊቲካ አራማጅ በመሆኑ ዛሬም የኢትዮጵያውያኖች ሃዘንና እንባ አልቆመም። በዚህ ጨለማ ውስጥ ንጋት መከሰቱ አይቀሬ ነውና ይህ ትውልድ ሁልጊዜም ተሸናፊ ሆኖ፣ ሃሞተ ቢስ ሆኖ፣ ለጥቂቶች የስልጣን ዘመን መወጣጫ ርካብ ሆኖ እንደማይቀር ታሪክ ደጋግሞ አስተምሮናል። ቅዱሳን መጻህፍትም ይህንን ያስተምሩናል።

ስለሆነም መንግስት በተለይ ወጣቱና ታዳጊው ትውልድ ከጨለማ እንዳይወጣ በዘረኞች አነሳሽነት በተለይ በትምህርት ተቋማት ውስጥ ከሚደርስበት የሽብር ስራ እጁን እንዲያወጣና ሃላፊነቱን እንዲወጣ ኢዲኤፍ (EDF) በአፅንኦት ያሳስባል።

የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ መንግስትም ሆነ አሸባሪዎች በህዝብ የሚዳኙበት ወቅት መምጣቱ የማይቀር ነው። ጆሮ ያለው ይስማ ግን በአእምሮው ያስብ ያሰላስል እንላለን።

LEAVE A REPLY