ታላቅ ዋጋ ተከፍሎበታል…!!! || ታምሩ ገዳ

ታላቅ ዋጋ ተከፍሎበታል…!!! || ታምሩ ገዳ

ያለመታደል ሆኖ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ነገር ከአስማሚነት ይልቅ በተቃርኖ አዚም የተጠመቀ ይመስላል። የተሻለ ዘመን መጣ ሲባል፣ የመንግስት ጋሻ ጃግሬዎች ጉልበታቸውን በምስኪን ዜጌች ላይ የሚያፈረጠሙበት፣ የተወሰኑ ወገኖችን ደግሞ በይታለፍ ሒሳብ የሚያልፉበት አጋጣሚዎች የተበራከቱበት፣ የአብዛኛው ሰው ትእግስት የተሟጠጠበት ፣አብረን ኖረን የማናውቅ ፣ሰው መሆናችን የተዘነጋበት ክስተቶች ተበራክተዋል።

በተለይ ደግሞ ሰሞኑን ከባንዲራ (ሰንደቅ አላማ)ጋር በተያያዘ የሚታየው ፍጥጫ፣በዜጎች ላይ የሚደርሰው የህይወት፣ የአካል እና የስነልቦና ጉዳትን ለተመለከተ የኢትዮጵያ እና የልጆቿ መከራዎች ገና ተጀመረ እንጂ ምኑ ተነካና ያሰኛል።

ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ወክሎ ለዘመናት የኖረ፣በጨለማ እና በቀኝ ግዛት ቀንበር ለነበሩ በርካታ አገራት ቀና ብለው እንዲሄዱ ምሳሌ እና የሞራል ስንቅ የሆናቸው ባለአረንጓዴ፣ቢጫ ፣ቀዩ ቀለም ባንዲራን ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር ትርጉም የለሽ አድርጎ ለማቅረብ የሚሰጡት ምክንያቶች እና የአገራቸውን ታሪክ በቅጡ ጠንቅቀው ያለወቁ ፣ያልተማሩ፣ በእድሜ ይሁን በአኗኗር ስሜታቸው ያልተገራ ወጣቶችን እያሰማሩ ባንዲራን እያወረዱ መቅደድ እና ማስቀደድ እኛ ኢትዮጵያኖች ለጥላቻ ፓለቲካ እንጂ ፣ ለመቻቻል ፓለቲካ የቱን ያህል እሩቆች እንደሆንን ያመላክታል።

አባቶቻቸው፣ ቅድመ አያቶቻቸው በአደዋ፣ በማይጨው፣ በመተማ፣ በኦጋዴን..፣ በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምእራብ፣ በምስራቅ ጋራ ሸንተረሩን ወንዙን፣ በረሀውን፣ ብርዱን፣ ሀሩሩን፣ ክረምት፣ ድርቁ፣ ረሀቡን፣ ጥማቱን፣ እርዛቱን፣ በሽታው ሳይበግራቸው ይህንን ባንዲራን በመሸከም፣ ድል ሲያደርጉ ከፍ አድርገው በማውለብለብ፣ ሲወድቁም በሰንደቁ በመሸፈን በክብር ሲሸኙበት በኖረ አገር የበቀሉ የዘመኑ የውጥንቅጥ ፓለቲካ አራጋቢዎች ይህ ትላንትና ትልቅ ዋጋ የተከፈለበት ሰንደቅ አላማን ከአንድ ብሔር እና ከአንድ ሐይማኖት ጋር ለማጣመር መሞከራቸው ባንዲራውን ያለአንዳች ሀፍረት ሲቀዱ፣ ሲያስቀድዱ እና ባንዲራውን በማንኛውም መልኩ ይዞ የተገኘ/ች ወገን ላይ ኢ -ሰብአዊ እርምጃ ሲወስዱ እና ሲያስወስዱ ለተመለከተ አገር ወዳድ በእጅጉ ልብን ይሰብራል፣የኢትዮጵያዊነት እሴቱም በቀላሉ እየጠፋ ነው ለማለት ያስደፍራል ።

ከዚህ እና መሰል የጥቃት እርምጃዎች አኳያ ብዙዎች ትላንትን መተኪያ የሌለው ህይወታቸውን የገበሩለት፣ ትልቅ ዋጋ የከፈሉበት፣ብዙዎች ዛሬም ቢሆን የማያፍሩበት ታሪካቸውን እና ገድላቸውን ያላከበረ ፣የመቻቻልን እና የአብሮነት ጠቀሜታን በቃላት ክሸና ሳይሆን ዋልታ እና ማገሩን በተግባር ያለጸና ባለተራ አገዛዝ ስለ ነገው ራዕያችን እና ብልጽግናችን ቢሰብከን እነዚያ ለአገራቸው እና ለሰንደቃቸው ክብር ትልቅ ዋጋ የከፈሉ የሰማእታት ልጆች እንዴት ያምኑት ይሆን?፣ዛሬስ ይህንን ብቻ አውለብልቡ የሚባለው ባንድራስ ነገ ተመሳሳይ እጣ ይገጠመው ወይም አይግጠመው ምን ዋስትና አለን?።

LEAVE A REPLY