የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ የታገቱ ተማሪዎችን በተመለከተ ሰሞኑን በሩን ያላንኳኳነው የፌደራልና የክልል መንግስት ባለስልጣን የለም። ጉዳዩን ከሰማን ጊዜ ጀምሮ በተለይም ባለፉት ጥቂት ቀናት ”የመረጃ ያለህ” ጩኸታችንን ሳይቋረጥ አሰምተናል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ እስከ ኦሮሚያና አማራ ክልሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸውንም የማይመለከታቸውንም ቁጥራቸው ባለን ባለስጣናት ስልክ ላይ አብዝተን ደውለናል። ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጄይላን አብዲ በቀር ማናቸውም መልስ አልሰጡንም። አቶ ጄይላን ስልክ በማንሳት ትብብራቸውን ማሳየታቸው የሚመሰገን ቢሆንም ከጉዳዩ አንጻር ምንም ዓይነት መረጃ የሚሰጡ አልሆኑም። ለአስራት ቴሌቪዥን ተናገሩ የተባለውንና በድምጽ ተቀንጭቦ የሰማነውን እንኳን ለማስተባበል ከመሞከር ያለፈ ፍንጭ ያለው መረጃ ሊሰጡን አልቻሉም።
ከደቂቃዎች በፊት ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከተው የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን ጋር የጽሁፍ መልዕክት ተለዋውጬ ነበር። ከበርካታ የስልክ ሙከራዎችና የጽሁፍ መልዕክቶች በኋላ አጭር መልስ የሰጡኝ እኚህ ባለስልጣን ሰሞኑን ምናልባትም ከሰኞ በኋላ በመንግስት በኩል ያለውን መረጃ የሚገለጽ መሆኑን ጠቆሙኝ። ይህንን እንዲያረጋግጡልኝ ላቀረብኩት ጥያቄ መልስ እየጠበቅኩ ነው ወደዚህ መንደር የመጣሁት። ጉዳዩ አሳሳቢ፡ አስጨናቂ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የመንግስት ዝምታ ያስፈራል። የሆነው ምንድን ነው? ከአፈናው ጀርባ የማን እጅ አለበት? አሁን እህት ወንድሞቻችን የት ነው ያሉት? በምን ሁኔታ ነው የሚገኙት? ለሁለት ወራት መረጃው እንዳይወጣ የተፈለገበት ምክንያት ምንድን ነው? ጥያቄዎቹ ብዙ ናቸው። መልስ የሚሰጥ አካል የለም እንጂ!!
ባለስልጣኑ እንደጠቆሙኝ ያለውን ወቅታዊ መረጃ ከሰሞኑ የሚታወቅ ከሆነ አንድ ነገር ነው። የሆነ ነገር መባል አለበት። የእናቶች ስቃይ፡ የአባቶች እንግልት፡ የቤተሰብ ስጋት በአጠቃላይ የኢትዮጵያውያን የሰሞኑ ጭንቀት ከዚህ በላይ መዝለቅ የለበትም። ይበቃል። የወገኖቻችን ጫንቃ ደክሞታል። እምባም ደርቋል። ለሀዘን የሚሆን አቅም የለም። እየተደራረቡና እየተፈራረቁ በተከሰቱ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ህዝባችን ትከሻው ጎብጧል። በመከራ ተወልዶ ፣በመከራ ኖሮ፣ በመከራ የሚሞተው ኢትዮጵያዊ ለውጥ ይፈልጋል። አንድ ቀን ደስታን አጣጥሞ ይህቺን ምድር የሚሰናበትበት እድል ሊሰጠው ይገባል። ከትላንት እስከዛሬ ባለው መከራና ስቃይ ውስጥ እያለፈ ላለው መላው ኢትዮጵያዊ የጨለማ ዘመኑ እንዲያበቃለት፡ የብርሃን አመቱ እንዲጀምርለት ማድረግ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም።
የመንግስትን ተአማኒነት ለፈተና ያቀረበው የደምቢዶሎው እገታ ተሸፋፍኖና ተደበስብሶ፡ አሊያም ለአንዳች ፖለቲካዊ ትርፍ ተብሎ በዝምታ እንዳይታለፍ የሁላችንንም ድምጽ ወደቤተመንግስት ማድረግ ያስፈልጋል። የሰነበቱትን ትተን የቅርብ ጊዜያቱን ብንመለከት በኦሮሚያ ክልል በሁለት ቀናት ውስጥ 86 ወገኖቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉበት ትራጄዲ አሁን ድረስ አጥንት ዘልቆ በሚያም ሀዘን እየተወጋን እንገኛለን። በአማራ ክልል አፍቅሮተ ነዋይ ባናወዛቸው አጋቾች ጥይት ህይወታቸውን ያጡት ሰባት ታዳጊ ህጻናት ጉዳይ በብርቱ እንዳንገበገበን አለን። የቡራዩ ሰማዕታት ድምጽ ከጆሮአችን ያቃጭላል። በደቦ ፍርድ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በዘግናኝ ሁኔታ የተገደሉ ወገኖቻችን ነገር ከአእምሮ ጓዳ መቼም የሚጠፋ አይደለም። በእነዚህ ሁሉ ክስተቶች መሀል የመንግስት መረጃዎችና እርምጃዎች ግልጽነት የጎደላቸው፡ አጥፊዎችን ለፍርድ ለማቅረብ ቁርጠኝነት ያልታየባቸው መሆናቸው በመንግስት ላይ ህዝብ ያለው አመኔታን የመሸርሸር አዝማሚያ ተንጸባርቋል። የሰሞኑ የደምቢዶሎው እገታ ጉዳይ ላይ የመንግስት አካሄድ በዚሁ ከቀጠለ ከፍተኛ የተአማኒነት ቀውስ ሊገጥም እንደሚችል ጥርጥር የለውም።
መንግስት ለምን ዝምታን መረጠ? እህትወንድሞቻችን ምን ቢገጥማቸው ነው በመንግስት በኩል የመረጃ በሩ የተቆለፈው? በእርግጥ ወለጋ የትኛውም የግንኙነት መስመር ለጊዜው ተቋርጧል። ስልክም ሆነ የኢንተርኔት አገልግሎቶች እንደሌሉ የሚመለከተው አካልም በይፋ ገልጿል። ይህ መሆኑ ግን ለመንግስት መረጃ እንዳያቀርብ የሚከለክለው አይሆንም። ሀገሪቱን የሚመራ መንግስት እሰከሆነ ድረስ በየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢሆን እንኳን ለህዝብ መነገር ያለበትን ከመናገር ወደኋላ ማፈግፈግ አደጋው ከባድ ነው። ይህን የመንግስት ሃላፊዎች አይረዱትም ማለት አይቻልም። እሳቱን በጊዜ ማጥፋት ካልተቻለ በሂደት እንደሰደድ ተቀጣጥሎ ከቤመንግስት ደጃፍ የሚደርስ ለመሆኑ ታሪካችን ይነግረናል። ሳይቃጠል በቅጠል የሚለው ብሂል መዘንጋት የለበትም። እንቆቅልሽ የሆነውን እገታና የመንግስትን ረጅም ዝምታ ተከትሎ በህዝብ ላይ የተፈጠረውን መከፋት በቀላሉ ማየት ዋጋ ያስከፍላል።
የመንግስት ዝምታ ሁለት አደጋዎችን እየጋበዘ መሆኑን ታዝቤአለሁ። አንደኛው ከወላጆች ያለፈ፡ ከቤተሰብ የተሻገር አጠቃላይ ጭንቀትና ስጋት እንዲፈጠር አድርጓል። ሁለተኛው አደጋ ደግሞ ለግጭት ነጋዴዎች በር የሚከፍት አጋጣሚን ፈጥሯል። ሰሞኑን የሴራ ፖለቲካ አፍቃሪያን ከኪሳቸው ከሚያመርቱት መረጃ ጋር በየቦታው ድምጻቸው ጎልቶ እየተሰማ ነው። ጉዳዩ ሰርግና ምላሽ ሆኖላቸዋል። በመንግስት ዝምታ ነጥብ እያስቆጠሩ ነው። እንዲህ ዓይነት አዱኛ ከደጃፋቸው መጥቶላቸው ይቅርና ቀድሞኑ በካፊያ የሚርሱ፡ በጸጉር አየር የሚመትሩ ናቸው። የመንግስት ዝምታ ቀውስ ጠማቂዎችን ከየቦታው አነቃቅቷል። ህወሀትም ከመቀሌ አይኑን ገልጧል። ባህርማዶ ተጎልተው ወሬ እያንቃረሩ፡ በሪሞት ኮንትሮል ሀገር ቤት ማዕበል ለመፍጠር የሚንገታገቱ የማህበራዊ ሚዲያ አርበኞችና የህወሀት ሰራዊት ከሰሞኑ የደምቢዶሎው ትራጄዲ ጋር ሰልፋቸውን አንድ ላይ አድርገው ተነስተዋል። ዶ/ር አብይን ጎዳን ብለው ሀገር ሊያፈራርስ በሚችል መስመር ላይ ወጥተው አካኪ ዘራፉን ተያይዘውታል።
ህወሀት ተስፋ የቆረጠ ቡድን ነው። ከንግስና የወረደ፡ ከቤተመንግስት የተፈናቀለ ቡድን በመሆኑ ኢትዮጵያን በአፍጢሟ ብትደፋ ጉዳዩም አይደለም። አጥፍቶ ለመጥፋት እጁን እያሟሸ ነው። የቀረችውን ቅንጣቢ አቅም ሀገር ሊያፈርስ በሚችል ማንኛውም እንቅስቃሴ ላይ ለመጠቀም ወስኗል። እንደደምቢዶሎው ዓይነት ህዝብ የሚያስቆጣ ክስተት ሲፈጠር አዛኝ አንጓች ሆኖ፡ የፍየሏን ለቅሶ እያሰማ ብቅ ብሏል። የህወሀትስ የታወቀ ነው። ተስፋ ከቆረጠ ቡድን የሚጠበቅ ነገር ነው። በኢትዮጵያ ስም ለሚምሉ፡ የምንዋደቀው ስለኢትዮጵያ ነው ብለው አብዝተው ለሚጮሁ፡ ከእስር ቤት እስከባህር ማዶ ስደት የምንገላታው ስለሀገራችን ነው እያሉ ለራሳቸው ምስክርነት በመስጠት በየመድረኩና በየመስኮቱ ለሚነግሩን የደምቢዶሎው ጉዳይ ዋና ተቆርቋሪ ነን ባዮች ግን ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢ ነው። ለመሆኑ ዶ/ር አብይ ላይ አብዝታችሁ የምትወረውሩት ድንጋይ እንደምኞታችሁ ይሁንና መንግስትን የሚያፈርስ ቢሆን ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያ ሁኔታ ምን እንደሚሆን አስባችኋል?
ያልተሞከረ የለም። በተገኘው አጀንዳ ኢትዮጵያ ላይ ቀውስ እንዲፈጠር ያልተፈነቀለ ድንጋይ አላየሁም። ከኪስ ከምትፈበረክ መረጃ ጋር ጫፍ እየያዙ ሰማይ ጥግ አድርሰው በማጋነን ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የተደረገውን የሞት ሽረት ትንቅንቅ በቅርበት የምንከታተለው አሳዛኝ ክስተት ነው። የደምቢዶሎውን አስጨናቂ አጋጣሚን በራሳቸው ወርድና ቁመት ሰፍተው፡ በውጤቱም የዶ/ር አብይ መንግስት በህዝብ ነውጥ የሚፈርስበትን ምኞት በልባቸው አኑረው ሰማይ ምድሩን በለቅሶና ኋይታ እያናወጡ መሆናቸውን የሰሞኑ ግርግር ለሁላችንም ግልጽ ሆኖ ይመሰክራል። እውነት ነው ጉዳዩ ያስጨንቃል። የእህቶቻችን ደብዛ መጥፋት በእጅጉን ያሳስባል። የወንድሞቻችን ዱካ አለመገኘቱ ልብን በሀዘን ክፉኛ ይመታል። የመንግስት ዝምታ ደግሞ ይበልጥ በፍርሃት የሚያርድ ይሆናል። ታዲያ ምን ይደረግ? መንግስት መረጃ እንዲሰጥ፡ የታገቱትን በአስቸኳይ አስለቅቆ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ በሰላማዊ መንገድ ጫና መፍጠር የሁሉም ኢትዮጵያዊ የወቅቱ ግንባር ቀደም ጉዳይ መሆኑም እርግጥ ነው። ከዚያ ባለፈ ሀገር እንዲናወጥ፡ እሳት እንዲቀጣጠል የሚደረገው ርብርብ ምን ይፈይዳል? ማንን ይጠቅማል? ከጀርባው የትኛው ሃይል የሚገፋው እንቅስቃሴ ነው? አፋኝ ኦሮሞ፡ ታፋኝ አማራ፡ የእገታውን መረጃ የደበቁት አራት የኦሮሞ መሪዎች፡ መረጃው የተነፈጋቸው የአዴፓ ሰዎች ናቸው የሚል ልብወለድ እየፈጠሩ፡ ለአማራ ድርጅቶች ”ተነሱ” የሚል ጥሪ ማቅረብ ምን የሚሉት እብደት ነው?
የእኔ ጭንቀት የዶ/ር አብይ ወንበር እንዳይነካ ከሚል ስሜት የመነጨ አይደለም። የዶ/ር አብይ መንግስት ያሉበትን ክፍተቶች እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከሚረዳው በላይ በቅርበትም አውቀዋለሁ። የሰሞኑ ጭልጥ ያለው ዝምታው ግራ ቢገባኝም ኢትዮጵያው ውስጥ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተፈጠሩት ቀውሶች አንጻር የመንግስት አቅም የደከመበት፡ እርምጃ ከመውሰድ እጁ የተሰበሰበት፡ ሀገሪቱም የጽንፈኞች መፈንጪያ፡ የኢትዮጵያ ጠል አክራሪ ብሄርተኞች መቦረቂያ እስክትሆን የታገሰበትን ምክንያት ግን በሚገባ እረዳዋለሁ። ስለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ የሚለው የመንግስት ስትራቴጂ አያሌ ቀውሶችን፡ እዚያም እዚህም የተፈለፈሉ ጽንፈኞችን ቢጋብዝም ኢትዮጵያን ለማዳን ለጊዜው ያለው ብቸኛ አማራጭ ነው የሚል እምነት አለኝ። ይህ የዶ/ር አብይ ጉዳይ አይደለም። ምርጫ የማጣት እንጂ። አይኑን ገልጦ፡ የኢትዮጵያን ሁኔታ በሚገባ ተረድቶ ነገን ለሚጠብቅ፡ ከጀርባው የዘርና የሃይማኖት ኮተት የሌለበት ቅን ዜጋ የዶ/ር አብይን መንግስት የሚመለከተው ኢትዮጵያን ከጨካኝ የጅብ መንጋጋ ውስጥ ለማላቀቅ የሚፍጨረጨር ሃይል አድርጎ ሰለመሆኑ ከግምት በላይ መናገር እችላለሁ።
ከዚህ ውጪ ምን ምርጫ አለ? የዶ/ር አብይ መንግስት ላይ ሰይፋችሁን የመዘዛችሁ፡ ባገኛችሁት ጠጠርና ድንጋይ ወርውራችሁ እንዲወድቅ ቀን ከሌሊት የምትጣጣሩ ወገኖች እስቲ ከዶ/ር አብይ በኋላ ስለምትኖረው ኢትዮጵያ ንገሩን? ምርጫችሁን አሳዩን። ምርጫ የሌለው የ”በለው፡ ፍለጠው ቁረጠው” እልህ አስጨራሽ ግብግባችሁ መጨረሻው ምንድን ነው? ጽንፈኞች ሀገሪቱን ሰልቅጠው ለመዋጥ ባሰፈሰፉበት በዚህን ወቅት ኢትዮጵያን ለማዳን የሚቻልበት መንገድ የትኛው እንደሆነ ሳታሳዩን መንግስትን እንድንጥለው የምትሰብኩን ለምንድን ነው? ፌርማታችሁ ከየት ያደርሰናል?
አዎን! ጉዳዩ የዶ/ር አብይ ስልጣን መቆየት አይደለም። የብልጽግና ፓርቲ ምርጫውን እንዲያሸንፍ የመመኘትም ነገር አይደለም። ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ባላት ቁመና ከጅቦቹ መንጋጋ እንዴት ታመልጣለች የሚለው እንጂ። ከእነጉድፎቹ፡ ከነድክመቶቹ የዶ/ር አብይን መንግስት ለግዜው እንዲቆይ ከማድረግ ያለፈ ምርጫ አለን? ሰሞኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባቀረበው ሪፖርት የኢትዮጵያ ቀውሶች ምንጭ ከመንግስት ውጪ ያሉ ቡድኖች (non-state actors) እንደሆኑ በሰፊው ተገልጿል። የኢትዮጵያ ታሪክ ተገልብጦ የአፈናና የቀውስ ምንጭ መንግስት መሆኑ ቀርቶ ከመንግስት ውጪ የሆኑ ሃይሎች እንደሆኑ ተነግሮናል። ባይነገረንም የምናውቀው፡ ዓለም የተረዳው መራር እውነታ ነው። ታዲያ እንደቀድሞ ዘመን መንግስትን ለመጣል ያነጣጠረ ትግል አስፈላጊ ነውን? ከዚህ ትግል ኢትዮጵያ ምን ታተርፋለች? የዶ/ር አብይ መንግስት ባይኖር እንደጽንፈኞች አሰላለፍና የህወሀት የማያባራ ጸረ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ጋር ሀገራችን ትኖር ነበርን? እስቲ የመቀመጫችንን ቀበቶ ጠበቅ አድርገን እንነጋገር።
ሰሞኑን ከዶ/ር አብይ የፖለቲካ መስመር በተቃራኒው የቆመ፡ በአንድ ብሄር ውክልና ራሱን ገልጾ ትግል ውስጥ የገባ፡ በጥቂት ጊዜያትም በርካታ ደጋፊዎችን ያፈራ የአንድ ድርጅት አመራሮችን በግል ያነጋገሩ ወዳጆቼ ያጫወቱኝ ነገር ሰለኢትዮጵያ ጥልፍልፍና ውስብስብ የፖለቲካ ሁኔታ ግልጽ የሆነ መስመር አሳይቶኛል። እነዚህ የብሄር ፓለቲካ አቀንቃኞች በአደባባይ የሚያደርጉትን ሳይሆን በውስጣቸው የሚያምኑበትንና በጀርባ እያደረጉ ያሉትን ለወዳጆቼ ሲነግሯቸው ”ኢትዮጵያን ለማዳን የማያንቀላፋው አምላክ አሁንም አለ” የሚለው መንፈሳዊ እምነት ውስጤ ሲሯሯጥ ተሰማኝ። ”ዶ/ር አብይ መቆየት አለበት። እሱ በመኖሩ ከጽንፈኛ የፖለቲካ ድርጅቶችና ‘ምሁራን’ ኢትዮጵያ ተርፋለች። ካልደገፍነውና ከጎኑ ካልቆምን ሀገሪቱን የሚቀራመቷት ሃይሎች እጅ ላይ ትወድቃለች” ይህ እንግዲህ ከዶ/ር አብይ የብሄርም ሆነ የፖለቲካ መንደር በተቃራኒው ቆመናል ከሚል የፖለቲካ ድርጅት አመራሮች አንደበት ሰማን ብለው የነገሩኝ ወዳጆቼ ያገኘሁት ተስፋ ፈንጣቂ መልዕክት ነው። እውነት ነው። ጭንቀቱ የዶ/ር አብይ ስልጣን አይደለም። የኢትዮጵያ ህልውና እንጂ!
መንግስት ሆይ ዝምታህን ስበር። እህቶቻችንን የት ነው ያሉት? ወንድሞቻችንን ከየት ነው የሚገኙት? ለወላጆቻቸው የሆነው ሁሉ ይነገራቸው። ለኢትዮጵያ ህዝብም እውነቱ ይገለጽለት። ይህን በማድረግ በቅርበት ያደፈጠውን የተአማኒነት ቀውስ ማጥፋት ይቻላል። ይህን በማድረግም የህወህትን የማያባራ ሩጫ ማስቆም ይቻላል። ይህን በማድረግም የቀውስ ጠማቂዎችን ህልም መቅጭት ይቻላል። ስለታገቱት መልስ እንፈልጋለን። ዛሬ ሳይሆን አሁኑኑ!
ኢትዮጵያን ፈጣሪ ይጠብቃት!
መልካም ቅዳሜ!