ሐዘን ጥሩ ነው ምክንያቱም ያሳዝናል። ሐዘን ሰው ሲያዝን ከሰው አይለይም፤ ሁሌም አብሮ ነው። ስለዚህ ሁልጊዜም ከሐዘን ጋር እናዝናለን። ሐዘን አብሮን በመሆኑ ደስ ይለናል። በደስታችንም እናዝናለን። ሰው በመሆናችን እናዝናለን። ሌላውም ሰው ያሳዝነናል። እኛም ሌላውን በማሳዘናችን እናዝናለን። ሕይወት ያሳዝነናል። ስለምንወደነው ነገር ሁሉ እናዝናለን። ሐገራችንን በጣም ስለምንወዳት ስለ ሐገራችን እናዝናለን። የፍቅርና የትዳር ጓደኞች ከመዋደዳቸው ብዛት ሁልጊዜም አንዳቸው አንዳቸውን እንዳሳዛኑ ነው። ሐዘን ምርጫችን ነው። የመረጥናቸው ፖለቲከኞች ያሳዝኑናል። ጣፍጦንና ወደን የበላነው ምግብ እንኳ በሽታ ሆኖ ያሳዝነናል። በፍቅር የበላነው እንጀራ ሆድ እየነፋ ይሳዝነናል። ሙዚቃ እንወዳለን። ከሙዚቃ ሁሉ ግን ትዝታ ልባችንን ያጠፋዋል። የፈጠነው እና እስክስታ የምንወርድበት ዘፈን እንኳ ግጥሙ የሐዘን ሊሆን ይችላል። “ያሳለፍነው ዘመን ደስታን ያየንበት ተመልሶ ቢገኝ አሁን ምን አለበት” በሚለው የጥላሁን ገሠሠ ዘፈን ሰዎች ይደነሱበታል። “ደህና ሁኚ ልበልሽ በእንባ እየታጠብኩኝ” የሚለው ፈጣን ዜማም ያስደንሰናል። ብዙ ሰዎች የተጨፈጨፉ ሰሞን ይሁኔ በላይ ..ሰከን በል.. ሞት ለገዳይ የሚል የሐዘን መጨፈሪያ ዘፈን አውጥቶልን ሠርግ ማድመቂያ እስከመሆን ደርሷል። የሙዚቃችን ከፊል ሙሾ ነው።
መጽሐፍ ቅዱሳችን ከሠርግ ቤት ይልቅ እልቅሶ ቤት ሂዱ ይለናል። አልቅሱ እንጂ ጨፍሩ አላለንም። በእኔ ደስ ይበላችሁ ትንሳኤም ይሁንላችሁ የሚለው የእየሱስ ክርስቶስ አሳዛኝ ታሪክ ደጋግመን ብንሰማው ይጣፍጠናል። አንዳንድ ቤተ ክርስቲያን ለጌታ እየተለቀሰ ይደነሳል። ቀብር እየተደነሰ እሚኬድባቸው አገሮችንም እናውቃለን። ባንዲራ እያስሸከመ በየጎዳናው እሚያስሮጠን ለመጣው ለወጣው…” ጎረቤት ወዳድ ነን እንግዳ ተቀባይ…”ን እሚያስዘምረን፣ መልሶ ደግሞ ጎረቤት ለጎረቤት እሚያገዳድለን….ሐዘን ይሆን?! ባይሆንማ ምን እሚያስደስት ነገር ኖሮ ነው? በዚህም እናዝናለን።
ከአገር ወጥተን የተሰደድን ሰዎች በመሰደዳችን እናዝናለን። ከአገር ከቀረንም ውስጥ መውጣት ባላመቻላችን ብዙዎች እናዝናለን። ከአገራችን መውጣት አንፈልግም የምንል ሰዎች አገራቸውን እየተው በሚሰደዱ ሰዎች ብቻ ሳይሆን አገር ውስጥ ቀርተውም አገራቸውን በሚበድሉ ሰዎች እናዝናለን። እንዲያውም አንዳንዶቹ አገራቸውንና አገራችንን ጥለው ቢሄዱልን ደስ ይለናል። ግን አልሄድ ብለው ይኸው በመከራ ያስተዳድሩናል። ዳሩ እንኳን እነሱ ሊሄዱ የወጡትም እየመጡ ይጨመራሉ። በዚህም ደግሞ እናዝናለን። አገራቸውን የሚያስተዳደሩት መሪዎችም ህዝባቸው አገራቸውን ትቶ መሄድ ባለመቻሉ ያዝናሉ። ሁሉም እየተሰደደ ቢያልቅላቸው ሰላም ስለሚያገኙ ደስታቸው ነበር። ግን አልተደሰቱም። በዚህም ያዝናሉ። ስላዘኑም ከአገር የቀረውን ህዝብ ይበድሉታል። የተበደለውም ህዝብ ያዝናል። ከውጭ በስደት ሆነው ይህን በደል የሚመለከቱም ስለተበደለው ወገናቸው ያዝናሉ። በአጭበርባሪዎችና ደናቁርት ዝነኞች፣ ወስላቶችና ቀባጣሪዎች… ህዝብ በመንጋነት ሲራኮትና ሲፈነካከት ያሳዝናል። በቃ ሰው በአገር ጠፋ? ያስብላል። አገርም በሰው ጠፍታ ያስገርማል።
ከውጭ አንዳንድ ሰዎች ወደ አገራቸው ወደ ኢትዮጵያ ይመላለሳሉ። እዚያ የሆነውን ሁሉ ይመለከታሉ- በሆነውም ነገር ያዝናሉ። ያደጉበት ሠፈራቸው ተደምስሶ ፎቅ ስለተሰራበት፣ ኳስ የተጫወቱበት ኮረኮንች መንገድ የተንጣለለ አስፋልት ስለተሰራበት የተንቦጫረቁባት ኩሬ ድልድይ ስለወጣባት ያዝናሉ። ሠፈራቸው በመለወጧ ያዝናሉ። በቃ አሁን እኮ ተመልሰህ ብትሄድ እንዴት ያሳዝንሃል መሰል ብዙ ነገር እንዳልነበር ሁኗል። አንዱንም አታውቀውም እያሉ ሐዘንን ይጨዋወታሉ። ሌሎችም ደግሞ እንዲሁ ወደ ሠፈራቸው ይሄዳሉ። ያቺ ያደጉባት መንደራቸው አሁንም እንደዚያቹ ናት። እንደ አደራ እቃ የተለወጠ ነገር የለም። ሁሉም ነገር ያው ነው። ምንም ነገር አልተሰራም። እነዚህም በዚህ ያዝናሉ። ለውጥ መኖሩ ያሳዝናል ለውጥ አለመኖሩም ያሳዝናል። ጉዳያችን ከለውጡ ሳይሆን ከሐዘኑ ይሆን?
ብዙ ሰው ለውጥ የሚያመጣ አብዮት ይፈልጋል። ምክንያቱም አብዮት ልጆቿን ትበላለች። አብዮት ልጆቿን ስትበላ ታሪኩ እንደስኒማ ወለል ተብሎ ይታያል። አብዮት የግደል ተጋደል – ገድል (አድቬንቸር) ሲኒማ ነው። አብዮት እሚናፈቅ እልቂት ነው። ከአብዮት ብዙ ሐዘኖች ይመነጫሉ። ሐዘኖቹ ሲዘመርላቸው ልብ ያሞቃሉ። በዚያ አብዮት ውስጥ ያለፉት ሰዎች ሁሌም ደስ የሚል ሐዘን ይሰማቸዋል። ከሐዘንም እኮ የሚያኮራ ሐዘን አለ ብለው እሚኮሩበትም አሉ። አንዳንዶችም ድልና ሐዘን የተቀላቀለበት ሐውልት ያቆማሉ። የገደሉትም የሞቱትም ታሪካቸውን በኩራት ይጽፋሉ። ብዙ እሚያሳዝኑ መጽሐፍት ወጥተዋል። በሚያሳዝኑ መጻሕፍት ያዘኑ ሰዎች አሉ። አንዱ የኮራበትን ሌላው ያፍርበታል። አሁን ይህን የመሰለ ታሪክ ምኑ ያሳፍራል ብሎ የኮራው ባፈረው ያዝናል። በዚህ የተነሳ ስድብም ከወዲያ ወዲህ ይሆናል። ነገር ሁሉ ስድብ ብቻ እየሆነ እዚህም እዚያም በፈላው የስድብ አሸን ደግሞ ዳር ሆኖ ተመልካቹ ህዝብ ያዝናል። አዛኝ እና አሳዛኝ ቦታ እየተለዋወጡ ሐዘንን ይቀባበላሉ። ይህ ሲሆን ኢትዮጵያም ወይ ይታዘንላታል ወይ ይታዘንባታል። ስለ ሐዘኗ ግን ሁሌም በስሟ ይዘፈናል። ለእኔ እህህ ማለት ለአንተ ሙዚቃ ነው ብላለች አስቴር አወቀ። እውነት ነው የአንዱ እህህ ማለት ለአንዱ ሙዚቃው ነው። ሐዘን ሙዚቃ ነው። ሙዚቃስ ደግሞ ሐዘን እንደሁ ማን ያውቃል?!
ከሀዘን ሁሉ ደግሞ ጎሰኞች ያሳዝኑናል። ጎሰኞች የሆኑት ፀረ ጎሰኞችም ያሳዝኑናል። ጎሰኞች ተሸናንፈው አያበቁም፣ ጨዋታቸውም አያልቅም። አማሮች ትግሮች ኦሮሞዎች ጎሰኝነትን እንደ ዓለም ዋንጫ ተጫውተውና ተሸናንፈው ነገር እስኪሰክን የአገር ቆሽት ይበግናል። አገርም እነሱ፣ እነሱም አገር ናቸውና አርፎና ተጠርንፎ በተስፋ ከመጠባበቅ ሌላ አማራጭ የለም። ይህም ያሳዝናል። በቃ የደከምነው፣ የገደልነው፣ የሞትነው ለዚህቹ ነው? ያ ሁሉ አቅማችን አቅማ አልባ ለመሆን ነው? እንዲህ ወርደን ሰግደን የቀረነው በምንወዳት አገራችን እሚጠሏትን ሰዎች ለማንገሥ ነው? ወይስ ነግሠው አገር ያነገሡትን ሰዎች ለማርከስ ነው? ሐዘን ያጣን ይመስል፣ ከሱም ብሶ ደግሞ በላዩ ላይ ሰው መግደል መገዳደል የበለጠ ያሳዝናል። ከዚያም ሐዘን እሚያተርፍ መኖሩም የበለጠ ያሳዝናል። ከሁሉ በላይ መንግሥት ያተርፋል፣ ይፈረጥማል፣ ይፋፋል። ድል ለዴሞክራሲ ማለት ቀርቶ ሞት ለዴሞክራሲ ማለት ይመጣል። “ነጻነት እንዲህ ከሆነ ይቅርብን!” ማለት ከተጀመረ ነገር አበቃ ማለት ነው። ያን ጊዜ በሽታው ብቻ ሳይሆን መድሃኒቱም አብሮ ይሞታል። ትንሽ ሁከትና ጩኸት ለማስታገስ ትልቁን ሁከትና ዋይታ መደገስ እሚቀጥል ይሆናል። ሞኝ የእለቱን ብልህ ያመቱን እንዲሉ አገር ጅምላ መሆኗ ቀርቶ ችርቻሮ እንደሆነች፣ ነፍስን እንደ ዘር ዘርዝራ፣ ህይወትን በትና ቆንጥራ፣ ስትሸጥ ስትለውጥ ትውላለች። ትርፏም ንግዷም ግን ብላሽ ነው። ብላሽ እንዲሁ በሜዳ ባዶ መቅረት እንጂ ነጻነትን በነጻ ማግኘት አይደለም። ነጻነት በዝቶ ነገር ተበላሸ ማለት የቂል ነው።
ደግሞ ነጻነት ማጣት እንጂ ነጻነት ማግኘት ሰው አይገድልም። ልቅነትኮ ነጻነት አይደለም። መረን የጎሰኝነት መገለጫው ነው። ምንም ይሁን ምን ጎሰኝነት ድንቁርና እሚወልደው ስሜት ነው። ድንቁርና ደግሞ ነጻነት አይደለም። በተማረውም ባልተማረውም በሰለጠነውም ባልሰለጠነውም ላይ ሁሉ ውሎ አድሮ እሚታይ ክፉና ረቂቅ ደዌ ነው። ጎሰኝነት ካልተጠነቀቁት ሲያራምዱት ቀርቶ ሲቃወሙት እንኳ ጎሰኛ እሚያደርግ ተላላፊ በሽታ ነው። እንኳን ከሰው ወደ ሰው፣ ከሥርዓት ወደ ሥርዓት ይተላለፋል። እና ወዳጄ ሆይ አሳሩ ገና ሐዘኑም ታሪካዊ ነው። ታሪካችን የሐዘን እንደሆነ ሁሉ ሐዘናችም ታሪክ መሆኑ ያሳዝናል። እንዲህ እያስባለ ሐዘን በሐዘን እየተቀጣጠለ…ሰንሰለቱ ረዝሞ ስሜት ያደክማል። ደግነቱ በደልን የሰጠ አምላክ ሐዘንን አይነሳም። ሐዘንህም እንደ ወንዝ ይዞህ ወራጅ፣ እንደ ጣፋጭ ሙዚቃ አስቆዝሞ ወሳጅ መሆኑም ለዚህ ነው። መልካም ሐዘን!