የኢትዮጵያ ነገ ዜናዎች ጥር 19 || ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ነገ ዜናዎች ጥር 19 || ቀን 2011 ዓ.ም

የአማራ ሕዝብ የታጋቱት ተማሪዎች ድምጽ ሆኖ አደባባይ ወጣ

ለሁለት ወር ያህል የሚጠቃ ጊዜ (እስካሁን ድረስ) የደረሱበት ያልታወቀ የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ደህንነት ያሳሰባቸው በተለያዩ የአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ድርጊቱን በማውገዝ ሰላማዊ ሰልፎች አካሂደዋል።

በዩኒቨርስቲው ያጋጠመን አለመረጋጋት ሸሽተው ወደ መጡበት ሲመለሱ ባልታወቁ ወገኖች ተይዘው ደብዛቸው የጠፋው ተማሪዎች ጉዳይ  በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ መነጋገሪያ አጀንዳ በመሆኑ የዛሬው ሰልፍ በተለያዮ የአማራ ክልል ከተሞች እንዲካሄድ ምክንያት ሆኗል እየተባለ ነው።

በአማራ ክልል ርዕሰ ከተማ ባህርዳር በተካሄደው የተማሪዎቹን መታገት በሚያወግዘው ሰልፍ ላይ በርካታ ቁጥር ያለው የከተማው ነዋሪ ተሳታፊ ሆኗል። በዚህም ምክንያት የተለያዩ የመንግሥትትና የግል ተቋማት ተዘግተው ውለዋል:: ትምህርት ቤቶችም በተመሳሳይ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ዝግ ሆነው መዋላቸው ተረጋግጧል።

በተቃውሞ ሰልፎቹ የተሳተፉ ሰዎች መንግሥት የታገቱትን ተማሪዎች ጉዳይ ችላ ማለቱንና ተገቢውን መረጃ ባለመስጠቱ ወቀሳ ከማቅረባቸው በተጨማሪ፤ ታጋቾቹ ተለቀዋል ተብሎ የተሰጠው መግለጫን “ሐሰተኛ” በማለት ከመወንጀላቸው ባሻገር ሕዝብን ስላሳሳተው መረጃ በአስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥበት አሳስበዋል።

ድርጊቱን ለማውገዝ በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ አድራጊዎች መንግሥት ስለታገቱት ተማሪዎች ተገቢውን መረጃ እንዲሰጥ፣ ተማሪዎቹ እንዲለቀቁ፣ መንግሥት በአጋቾች ላይ እርምጃ እንዲወሰድና በጉዳዩ ውስጥ እጃቸው አለበት የሚባሉ አካላትም በሕግ እንዲጠየቁ ጥሪ አቅርቧል::

በተለያዮ ቦታዎች በተካሄዱት ሰላማዊ ሰልፎች ላይ፤በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ሲማሩ የነበሩና ለወራት የደረሱበት ያልታወቁት ተማሪዎች ያሉበት ሁኔታ እንዲገለጽ፣ እንዲሁም በቶሎ ተለቀው ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ እንዲደረግ በአጽንኦት መጠየቁን መታዘብ ችለናል።

ታግተዋል የተባሉት ተማሪዎች ቁጥር 17 እንደሆነ የተነገረ ሲሆን ከመካከላቸው 13ቱ ሴቶች መሆናቸው ተጠቅሷል። በዚህም መሰረት ባለፉት ሳምንታት በማሕበራዊ የመገናኛ መድረኮች ላይ “እህቶቻችንን መልሱ” በሚል ርዕስ ዘመቻዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል።

ዛሬ በባሕር ዳር፣ በወልዲያ፣ በደብረ ማርቆስ፣ በደብረ ብርሃን በዱርቤቴ፣ ፍኖተሰላም፣ በራያ ቆቦ፣ በሸዋ ሮቢት፣ በዳንግላና በሌሎች ቦታዎች የተካሄዱት የታገቱ ተማሪዎችን ለማስፈታት የተካሄደው ሰልፍ በሰላም ተጠናቋል ።”የታገቱት ተማሪዎች የት አሉ?”፣ “ደብተርና ስክርቢቶ የያዙ ተማሪዎችን ማገት ጀግንነት አይደለም”፣ “ለታገቱ ተማሪዎች መጮህ ፖለቲካ ሳይሆን ሰብዓዊነት ነው”፣ “መንግሥት ተለቀቁ ያላቸው ተማሪዎች የት አሉ?” የሚሉ ጥያቄዎችና መልዕክቶች በሰላማዊ ሰልፎቹ ላይ በብዛት ተስተውለዋል።


ከቻይና ዉሃን ግዛት የመጡ 4 ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው ኤርፖርት ላይ ተገኙ

አራት ኢትዮጵያውያን በኮሮና ቫይረስ በመያዝ ተጠርጥረው በለይቶ ማቆያ ማእከል ክትትል እየተደረገላቸው ነው

በአዲስ አበባ ኤርፖርት አራት ኢትዮጵያውያን በኮሮና ቫይረስ በመያዝ ተጠርጥረው በለይቶ ማቆያ ማእከል ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን መንግስት ይፋ አደረገ።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዛሬ በሰጡት የጋራ መግለጫ ፤ ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ የነበሩ አራት ኢትዮጵያውያን ፣ የሰውነታቸው የሙቀት መጠን ከፍ በማለቱ በጥርጣሬ በቡሌ ጣፋ ኳረንቲን ተለይተው ህክምናቸውን እየተከታተሉ እንዲቀመጡ መደረጉን ገልጸዋል።

እስካሁን በበሽታው የተያዘ ሰው አለመኖሩን የተናገሩትተቋማቱ ነገር ግን ከቻይና ውሃን (Wuhan) ግዛት ካለው ዩኒቨርሲቲ የመጡ 4 ተማሪዎች መካከል አንዱ የጉንፋን መሰል ምልክቶች የታዩበት በመሆኑ፤ ሌሎቹንም ሦሰት ተማሪዎች አብረው የመጡ በመሆናቸው በለይቶ ማቆያ ማእከል ክትትል እየተደረገላቸው ብለዋል።

ለተጠርጣሪዎች የላቦራቶሪ ናሙና ተሰርቶ ለጉንፋን መሰል በሽታ ነጋቲቭ መሆናቸው የተረጋገጠ ቢሆንም ለከፍተኛ ምርመራ የደም ናሙናቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኳልም። አራተኛው ተጠርጣሪ የጉንፋን መሰል ምልክት ያሳየ ቢሆንም፣ በአሁኑ ሰአት የሁሉም ተጠርጣሪዎች የጤና ሁኔታ ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም  ተነግሯል።

በሌላ በኩል ከቻይና ጓንዡ ግዛት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሁለት ቻይናውያን መኖራቸውን የቻይና ኤምባሲ ባደረገው ጥቆማ መሰረት፤ ተጓዦቹ በአውሮፕላን ማረፊያ በሚገኘው የምርመራ ቦታ ለሁለት ሰዓታት አስፍላጊው ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ ቫይረሱ ካለበት አካባቢ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውና በሙቀት ልየታ መሣሪያውም የተገኘ ምልክት ስለሌለ ወደ አገራቸው በሰላም የተመለሱ መሆናቸውም እየተነገረ ነው።

ቦቦሌ አውሮፕላን ማረፍያ ያለውን የምርመራ ሥራ በተመለከተ የተጓዦች የጉዞ መረጃና ከማን ጋር እንደተገናኙ የሚያሳይ መረጃ በመሰብሰብ የምርመራ ሥራው እየተካሄደ እንደሆነና ለዚህ ሥራ በሦስት ፈረቃ ተጨማሪ ባለሙያዎች ተመድበው እየተከታተሉት እንደሚገኙም ሰምተናል::


1600 በሽብርና በወንጀል የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎችን ማግኘት እንዳልተቻለ ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ ተናገሩ

በተለያዩ ወንጀሎች ለምርመራና ለክስ ከሚፈለጉ 3 ሺህ ተጠርጣሪዎች 1 ሺህ 600 ገደማ የሚሆኑትን ለህግ ማቅረብ እንዳልተቻለ የኢፌዴሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባ በዛሬው እለት አካሂዷል። ምክር ቤቱ በዛሬው በስብሰባውም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የ2012 በጀት ዓመት የ6 ወር የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አድምጧል።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ባቀረቡት ሪፖርት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባለፉት ስድስት ወራት በፍትህ ጉዳዮች ላይ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ከናውኗል ነውያሉት። የተገልጋይ አመለካከትና አመኔታ ልኬት የተደረገ ሲሆን በዚህም በተቋሙ ላይ የተገልጋይ አመለካከትና አመኔታ 71 በመቶ እንደሆነም ተናግረዋል።

የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የወንጀል ህጉን ለማስጠበቅና ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል ያሉት ጠቅላይ አቃቤ  ህጉ የወንጀል መከላከል ስራን ውጤታማ ለማድረግ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል። የሁሉም የወንጀል አይነቶችን የማጥራት ምጣኔ 100 በመቶ ለማድረግ ታቅዶ፤ የምርመራ ሂደታቸው የተጠናቀቁ 27 ሺህ 959 የክስ መዝገቦች ቀርበው 27 ሺህ 684 መዛግብት ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል፤ 175 መዛግብት ደግሞ በሂደት ላይ ይገኛሉ፤ በዚህም የማጥራት ምጣኔው 99 ነጥብ 01 በመቶ ደርሷል ይላል የብርሃኑ ጸጋዬ ሪፖርት።

ውሳኔ ካገኙት ውስጥ ደግሞ 19 ሺህ 238 መዛግብት ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን ፤ 8 ሺህ 446 በተለያዩ ህጋዊ ምክንያቶች የተዘጉ መሆናቸውም ተሰምቷል። የማስቀጣት ምጣኔን በአማካይ 96 ነጥብ 1 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ 94 ነጥብ 02 ተፈፅሟል ያሉት አቶ ብርሃኑ  በዚህም 32 ሺህ 949 መዛግብት በክርክር ሂደት የነበሩ ሲሆን፣ 7 ሺህ 335 መዛግብት ውሳኔ ሲያገኙ፤ ከእነዚህ ውስጥ 6 ሺህ 897 መዛግብት የጥፋተኝነት፣ 438 መዛግብት ደግሞ የነፃ ውሳኔ ያገኙ ናቸው ይፋ አድርገዋል።

ልዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን አፈፃፀም ለማሻሻል ባለፈው በጀት ዓመት የተጀመሩ እና በበጀት ዓመቱ አዲስ የተከፈቱ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና የሙስና ወንጀሎች ትኩረት በመስጠት ሢሠራ መቆየቱን ያስታወሱት ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ በተለያዩ ወንጀሎች ለምርመራ እና ለክስ ከሚፈለጉ 3 ሺህ ተጠርጣሪዎች ውስጥ ለህግ ማቅረብ የተቻለው 1 ሺህ 404 የሚሆኑትን ነው ብለዋል።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል 1 ሺህ 600 ገደማ የሚሆኑትን ለህግ ማቅረብ አልተቻልም ያሉት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፥ እነዚህም ተጠርጣሪዎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 827፣ በደቡብ ክልል 655፣ በኦሮሚያ 50፣ በአማራ 18፣ በትግራይ 4፣ በሶማሌ 33፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ 9 ተጠርጣዎች ክስ ተመስርቶባቸው እንዳልቀረቡ በሪፖርቱ ላይ ተጠቁሟል።

ተጠርጣሪዎቹን ለህግ ማቅረብ ያልተቻለው ክልሎችና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ባለመቻላቸው ነውም ተብሏል። ከሙስና ጋር በተያያዘም ከስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የተቀበሏቸው 360 መዛግብት ላይ ውሳኔ ለማሰጠት መሟላት ያለባቸው ጉዳዮች እየተሟሉ ነው ያለው ሪፖርት ፤ በሙስና ከገንዘብ ቅጣት 10 ሚሊየን 476 ሺህ እንዲሁም ክስ ከተመሰረተባቸው ከ500 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መደረጉን ገልፀዋል።


አምንስቲ ጫልቱ ታከለን ጨምሮ የታሰሩት 75 የኦነግ ደጋፊዎች እንዲፈቱ አሳሰበ

ዓለም ዐቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ትናንት ባወጣው መግለጫ፤ በተለይ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ደጋፊ የሆኑ 75 ሰዎች በሳምንቱ መጨረሻ በጅምላ  መታሰራቸውን ጠቁሞ እስረኞቹ በአስቸኳይ ይፈቱ ሲል ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

ደጋፊዎቹ የታሰሩት በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች እንደሆነና በተለይም በምዕራብ ጉጂ ዞን ፊንጫ ከተማ እንዲሁም በሻምቡ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች መሆኑን መግለጫው ያሳያል።

ተቀዛቅዞ የነበረው የመብት ተቆርቋሪዎች፣ የተቃዋሚዎችና የፓርቲ ደጋፊዎች የጅምላ እስር እየተመለሰ እንደሆነ ምልክቶችን እያየን ነው፤ ይህ ደግሞ ያሳስበናል ብሏል አምንስቲ። “ይህ ድንገቴ የጀምላ እስር የዲሞክራሲ መብቶችን ሚሸረሽር ነው፤ በተለይም ነጻና ገለልተኛ እንዲሆን በሚጠበቀው የመጪው ምርጫ ላይ ጥላውን ያጠላል” ሲሉ ተናግረዋል የአምነስቲ ኢንርናሽናል የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ዲፕሮሴ ሙቼና።

ከታሳሪዎቹ መካከልም በህወሓት መራሹ መንግሥት በጠቅላላው ለዐስር ዓመታት በመታሰር ከባድ የሰብኣዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባት ጫልቱ ታከለ ትገኝበታለች። ፖሊስ የጫልቱ ቤተሰቦች ይኖሩበታል ተብሎ በሚገመተውና ሻምቡ በሚገኘው መኖርያ ቤት እሁድ ጥር 17 ሌሊት 11 ሰዐት ሰብሮ በመግባት በቁጥጥር ሥር አውሏታል ያለው የአምንስቲ መግለጫ ወጣቷ የኦነግ የሻምቡ ቅርንጫፍ ሓላፊ አሁን በሻምቡ ፖሊስ ጣቢያ እንደምትገኝም አረጋግጧል።

ጫልቱ በፈረንጆቹ 2008 ጀምሮ ‘የአሸባሪው’ የኦነግ አባል ናት በሚል ለስምንት ዓመታት በእስር ማሳለፏን የጠቀሰው መግለጫው፤ ኦነግ ከአሸባሪ ድርጅትነት በመሰረዙ ለውጦች ታይተው ነበር ብሏል። ሆኖም ጫልቱ በድጋሚ 2017 ለአጭር ጊዜ መታሰሯን ፣ በኋላም በ2019 እርጉዝ ሳለች በድጋሚ መታሰሯን አስታውሰዋል።

ባለፉት የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት የተካሄዱት የጅምላ እስሮች ያሳሰቡት አምነስቲ ፖሊስና መከላከያ የመልሶ ማቋቋሚያ ስልጠና በሚል ከባለፈው ዓመት የካቲት ወር ጀምሮ እስር ሲያካሄድ ነበር በማለት የሚከሰው አምንስቲ ፤ ሆኖም ብዙዎች በተለያዩ የመከላከያና የፖሊስ ማጎሪያዎች ጊዜያቸውን ካሳለፉ በኋላ በመስከረምና ጥቅምት ወር ላይ መፈታታቸውን ጠቁሟል::


የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከፍተኛ አፈጻጸም አስመዝግቧል ተባለ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ከፍተኛ አፈጻጸም ማስመዝገቡን የአለም ዐቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ገለጸ።ለአንድ ሳምንት በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የተለያዩ የሥራ ክፍሎችን ሲገመግም የቆየው የአለም ዐቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የልኡካን ቡድን በዛሬው እለት የቅድመ ምዘና ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።

በዚህም የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በፈረንጆቹ 2019 እጅግ ከፍተኛ አፈጻጸም ማስመዝገቡን  ጠቁሟል።የልኡካን ቡድኑ መሪ  ኡስማን ኬሞ ማጃንግ፤በፈረንጆቹ  2019 በጀት አመት የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ቅድመ ምርመራ የሥራ አፈፃፀም  በፊት ከነበረበት 73  ነጥብ 2 ደረጃ በበጀት ዓመቱ ወደ 91 ነጥብ 78 ማሳደግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በፕሮግራሙ  የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሥራ ሓላፊዎች፣ የግል ኦፕሬተሮች እና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርና የስራ ክፍል ሓላፊዎች ተሳታፊ ነበሩ::

LEAVE A REPLY