የጃዋር 34 በመቶ፣ የዶ/ር ዐቢይ 20 በመቶ የቲውተር ተከታዮች ፌክ ሆነው ተገኙ

የጃዋር 34 በመቶ፣ የዶ/ር ዐቢይ 20 በመቶ የቲውተር ተከታዮች ፌክ ሆነው ተገኙ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የመብቶችና ዴሞክራሲ ብልጽግና ማእከል (ካርድ) ከትዊተር ኦዲት አገኘሁት ባለው ጥናት መሰረት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የግል የትዊተር አካውንትን ከሚከተሉ ከ100 ሺሕ ተከታዮች መካከል 80 በመቶው ትክክለኛ ተከታዮች ሲሆኑ፤ 20 በመቶው ግን ትዊተር ቦት ወይም በማሽን የሚፈበረኩ ሐሰተኛ አካውንቶች መሆናቸውን ይፋ አደረገ።

የኦፌኮ አባል የሆኑት ጃዋር መሐመድ ካሏቸው 95 ሺሕ በላይ ተከታዮች ውስጥ 66 በመቶው ትክክለኛ የትዊተር አካውንቶች ሲሆኑ ቀሪ 34 በመቶ የሚሆኑት ግን እነዚህ ሐሰተኛ አካውንት ወይም ቦቶች መሆናቸውን ካርድ የተሰኘው ኢንተርናሽናል ተቋም አረጋግጫለሁ ብሏል።

በታኅሳስ ወር የተሠራው ይህ ጥናት አምስት ሺኅ የተከታይ ናሙናን በመውስድ የተሠራ ነው:: እነዚህ በገንዘብ የሚገዙት የሐሰት አካውንቶች የሚከተሉትን ግለሰብ ትዊቶች በመጋራት እና በማደናነቅ በእውነተኛ ተከታዮች ላይ ጫና እንደሚያሳድሩም የኒው ዮርክ ታይምስ የምርመራ ሪፖርት ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

መንግሥት መረጃን በጊዜ ባለመስጠቱ ሐሰተኛ መረጃ ለሚያሰራጩ አካላት በር እየከፈተ ነው። ካርድ ለስድሰት ወራት ባካሄደው ጥናትም የተዛቡ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች በተለይም ከማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም መዛባት ጋር ተያይዞ እያመጣው ያለው ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንም ሪፖርቱ ጠቁሟል።

እነዚህን የተዛቡ መረጃዎች የሚያሰራጩ አካላት ምንም እንኳን አንዱ ምክንያታቸው በተመልካች ብዛት የሚገኝ ገቢ ቢሆንም፣ በዋነኛነት ግን ለፖለቲካዊ ዓላማ፣ ለተራ ዝና እና ለግላዊ ብሽሽቅ እንዲሁም ባለማወቅም ጭምር መሆኑ በጥናቱ የተገኙ ውጤቶች ያሳያሉ።

የተዛቡ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች ከመደበኛው ጊዜ በበለጠ የሚበራከቱበት ወቅት አለ የሚለው ተቋም፣ በተለይም የተቃውሞ ሰልፍ፣ ግጭቶች፣ ሃይማኖታዊ በዓላት እና ፌስቲቫሎች በሚኖሩባቸው ጊዜያት የሐሰት መረጃው የሚጠናከርበት ጊዜ ነው። በዩኒቨርሲቲዎች ግጭት ሲኖር፣ የፖለቲካ መሪዎች የገቢ ማሰባሰቢያ ሲያደርጉ እና የሕዝብ ውሳኔዎች ሲካሄዱ እንደሆነም የካርድ ዋና ዳይሬክተር በፍቃዱ ኃይሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭት እንዲበዛ እና ዋጋ እንዲኖራቸው ካደረጉት ምክንያቶች መካከል፣ መንግሥት ግልፅ ባለመሆኑ እና መረጃዎች ክፍት አለመደረጋቸው ተጠቃሽ ናቸው። በተያያዘም መረጃ ክፍት የማያደርጉየመንግሥት ባለሥልጣናት ተጠያቂ ባለመሆናቸው፤ የሲቪክ ማኅበራት የሚዲያ ግንዛቤ በመጨመር ዜጎች እራሳቸውን ከተዛቡ መረጃዎች እና ከጥላቻ ንግግሮች እንዲጠብቁ የአቅም ግንባታ ሥራ መሥራት ባለመቻላቸውም ነው ተብሏል።

የሚዲያ ተቋማት እና ጋዜጠኞች በተለያየ መልኩ የተዛቡ መረጃዎችን ስርጭት ለመከላከል በቂ ትኩረት ያለመስጠታቸው እና ሀቅ የማረጋገጥ ሥራ ላይ ደካማ መሆናቸው ለችግሩ እንደ ዋነኛ መንስኤነት የሚጠቀሱ ናቸው። ከዛ በተጨማሪም የማኅበራዊ ሚዲያ ቅኝቶች እና አካሄዶች የዜጎችን በቂ እና ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብት እና ፍላጎት እንዲስተጓጎል ያደርጋል ብለዋል።

ከዚህ ባሻገር ከወዲሁ የተደራጁ ስለመሆናቸው ምልክት የተገኘባቸው ሲሆን፣ ሐሰተኛ የሥም ማጥፋት እና የማጥላላት ዘመቻዎች እየተካሄዱ በመሆናቸው፤ እነዚህ አሳሳቢ አካሄዶች በሁሉም ሓላፊነት በሚሰማቸው አካላት ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራባቸው ይገባል። ካልሆነ ግን በምርጫው ወቅት ዜጎች በተሳሳተ መረጃ መምረጥ ለማይፈልጉት አካል ድምጻቸውን እንዲሰጡ ከማሳሰቱም በላይ በተለያዩ አካላት ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ ሊያደርጉ ይችላሉ መባሉንም ሰምተናል።

LEAVE A REPLY